ክሱ በፍርድ ቤት ስለ መሰማት | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

ክሱ በፍርድ ቤት ስለ መሰማት

አራተኛ መጽሐፍ፡፡
ክሱ በፍርድ ቤት ስለ መሰማት፡፡
ምዕራፍ ፩
ጠቅላላ ድንጋጌዎች
 

ቍ ፺፬፡፡ የቀጠሮ ቀን የሚሰጡበት ምክንያቶች፡፡

(፩) ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ ሲያመለክት ወይም ፍርድ ቤቱ በራሱ አስተያየት ትክክለኛፍርድ ለመስጠት የሚረዳ ከሆነ ክሱ በሚሰማበት በማንኛውም ጊዜ ቀጠሮ ለማድረግ ይችላል፡፡
(፪) በተለይም ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ምክንያቶች ካልሆነ በቀር ቀጠሮ ሊሰጥ አይቻልም፡፡

(ሀ) ዐቃቤ ሕጉ የግል ከሳሹ ወይም ተከሳሹ በበቂ ምክንያት ሳይቀርቡ የቀሩ እንደ ሆነ ወይም
(ለ) የዐቃቤ ሕጉ ወይም የተከሳሹ ምስክሮች ሳይቀርቡ የቀሩ እንደ ሆነ፤ ወይም
(ሐ) በከፍተኛው ፍርድ ቤት በሚፈረድ ነገር ቀዳሚ ምርመራ ያልተደረገበት ሆኖ ዐቃቤ  ሕጉ ለምርመራ ጊዜ የሚያስፈልገው ሲሆን፤ ወይም፡፡
(መ) ተጨማሪ መረጃ ማቅረብ አስፈላጊ ሲሆን፤ ወይም
(ሠ) ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ እንደሚቀርብ ቀደም ብሎ ሊገምት የማይችለው ወይም እንደሚቀርብ ያላሰበው አዲስ ማስረጃ በድንገት የቀረበ እንደ ሆነ፤
(ረ) የክሱ ማመልከቻ በተለወጠ ወይም በጨመረ ጊዜ ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ ክሱን ወይም መከላከያውን እንደ ገና ለማመዛዘን ጊዜ የሚያስፈልገው ሲሆን ወይም
(ሰ) ተከሳሹ የክሱ ወይም የቀዳሚው ምርመራ መዝገብ ግልባጭ ያልደረሰው ወይም የደረሰው ክሱ የሚሰማበት ቀን አቅራቢያ በመሆኑ የሚገባውን መከላከለያ ለማቅረብ ጊዜ
ያጠረው ሲሆን፤ ወይም
(ሸ) የነገሩ መሰማት ከመጀመሩ በፊት ዐቃቤ ሕጉ ክሱን እንዲጀምር ፈቃድ የሚያስፈልገው ሲሆን፤ ወይም
(ቀ) በሌላው ፍርድ ቤት የቀረቡ ክሶች በመጀመሪያ ውሳኔ ካላገኙ በቀር በተሰማው ነገር ውሳኔ የማይሰጥ ሲሆን ወይም
(በ) የተከሳሽን አእምሮ ትክክለኛነት በልዩ ዐዋቂ መወሰን የሚያስፈልገው ሲሆን ወይም
(ተ) ተከሳሹ አካለመጠን ያላደረሰ በሆነ ጊዜ ፍርድ ቤቱ በጥበቃ ሥር እንዲቆይ የሚስፈልግ ሆኖ ሲያገኘው ወይም
(ቸ) የነገሩ መሰማት በአንድ ቀን ለመፈጸም የማይቻል በመሆኑ ለሚቀጥለው ቀን የሚቀጠር ሲሆን ነው፡፡
(፫) በ (ሀ) እና ከ (ረ) እስከ (ሸ) ድረስ ባሉት ምክንያቶች ከአንድ ሳምንት የበለጠ ቀጠሮ አይሰጥም፡፡

ቍ ፺፭፡፡ አዲስ ቀጠሮና መጥሪያዎች፡፡

(፩) በቍ ፺፬ ንኡስ ቍ ፫ የተመለከተው እንደ ተጠበቀ ሆኖ የነገሩ መስማት የሚቀጠረው ለቀጠሮ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለመፈጸም በቂ እስከሚሆንበት ጊዜ ብቻ ነው፡፡
(፪) በዐቃቤ ሕጉ ወይም በተከሳሹ ጥፋት ሳይሆን ቀጠሮ የተሰጠበት ምክንያት ሳይፈጸም የቀረ እንደሆን ያንኑ ያህል ወይም አጭር ቀጠሮ ይሰጣል፡፡
(፫) በቍ ፺፬ ንኡስ ቍ ፪ (ሐ) እና ከ (ቀ) እስከ (ተ) በተጻፈው መሠረት የነገሩ መሰማት ከተቀጠረ በኋላ ቀጠሮ የተሰጠበት ምክንያት ሲፈጸም ባለጉዳዮቹና ምስክሮቹ እንዲቀርቡ
አዲስ መጥሪያ ፍርድ ቤቱ ይሰጣል፡፡

ቍ ፺፮፡፡ የቀጠሮ ውጤት፡፡

(፩) ቀጠሮ በተሰጠ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ የተሰጠበት ምክንያት እንዲፈጸም አስፈላጊውን ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ ይኸውም በቍ ፴፫ ፶፫ እና ፻፳፭ በተመለከቱት  ሁኔታዎች መሠረት
ከሚሰጠው የመያዝ ትእዛዝ ጭምር ነው፡፡
(፪) በቍጥር ፺፬ ንኡስ ቍ ፪ (በ) ወይም (ተ) መሠረት ቀጠሮ ሲሰጥ ተከሳሹ አእምሮውን ልዩ ዐዋቂ ሊመረምረው በሚቻልበት ስፍራ ተይዞ እንዲቆይ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ይሰጣል፡፡

ቍ ፺፯፡፡ መረጃዎች (ኢግዚቢቶች)፡፡

መረጃዎች (ኢግዚቢቶች) ሁሉ ላይና በቍ ፴ መሠረት ምስክር በሰጠው ቃልና በቍጥር ፳፯ መሠረት ተከሳሹ የሰጠው ቃል ጭምር ላይ የፍርድ ቤት መዝገብ ሹም ቍጥርና ምልክት ያደርግባቸዋል፡፡ እነዚህን መረጃዎች የፍርድ ቤት መዝገብ ቤት ሹም በተጠበቀ ስፍራ ያስቀምጣቸዋል፤ ያለ ፍርድ ቤትም ትእዛዝ አይወጡም፡፡

ቍ ፺፰፡፡ በመዝገቡ ውስጥ መኖር ስለሚገባው  ነገር፡፡

(፩) በፍርድ ቤት ነገሩ የሚመረመርበትን መዝገብ ዳኞች ይፈርሙበታል፡፡ በመዝገቡም ላይ ቀጥሎ የተመለከቱት ሊኖሩበት ያስፈልጋል፡፡

(ሀ) የክሱ ወይም የአቤቱታው ግልባጭ፤
(ለ) የቀዳማዊ ምርመራ ፍርድ ቤት መዝገብ፤ ያለ እንደ ሆነ፤
(ሐ) የመያዝ ትእዛዝ የተሰጠበት ቀን (ያለ እንደ ሆነ)፤ ወይም ተከሳሹ መጀመሪያ የተያዘበት ቀን፤
(መ) ለመጀመሪያ ጊዜ ተከሳሹ ፍርድ ቤት የቀረበበት ቀን፤
(ሠ) ዐቃቤ ሕጉ ወይም የግል ከሳሹ ያቀረበው የክስ ማመልከቻና በክሱ ማመልከቻ የተለወጠው ወይም የተጨመረው ነገር እንዲሁም የግል ከሳሽ ያቀረበው ክስ በሆነ ጊዜ ዐቃቤ ሕግ የፈቀደበት የምስክር ወረቀት አብሮ ይያያዛል፤
(ረ) ዐቃቤ ሕጉ ወይም የግል ከሳሹ የሰጠው የክስ መክፈቻ ንግግር ግልባጭ፤
(ሰ) የተከሳሹ እምነት ክደት፤
(ሸ) ምስክሮች የሰጡት ቃል በሙሉ፤ መስቀልያና ዳግመኛ ጥያቄ ጭምር፤
(ቀ) ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ የተቃወመው ማንኛውም ነገር እና ለተቃወመው ጉዳይ የተሰጠው ውሳኔ፤ ወዲያውኑ በመዝገብ ይጻፋል፡፡ ምስክር ቃሉን በሚሰጥበት ጊዜሲሆን የምስክሩን ቃል መስጠት አቁሞ እዚሁ ቦታ መቃወሚያው መጻፍ አለበት፡፡
(በ) የቀረበው መረጃ የተሰጠው ቍጥርና ያቀረበው ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ መሆኑ ተለይቶ ይጻፋል፤
(ተ) ስለ ሕግ የቀረበ ክርክር እና የተሰጠው ውሳኔ ይኸውም በመዝገቡ የሚጻፈው ክርክሩ በተነሳበት ጊዜ ነው፤
(ቸ) የተሰጠውን ቀጠሮ ሁሉና የክሱ መሰማት እንዲቀጠር የተደረገበት ቀንና ለቀጠሮው ምክንያት የሆነው ጉዳይ ጭምር፤
(ነ) ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ ይግባኝ ለማለት መብት ያላቸው ለመሆኑ መነገራቸውን ነው፡፡

(፪) ነገሩ በሚሰማበት በማንኛውም ቀን መዝገቡ ከዚህ በታች በተመለከተው ዐይነት ይጀመራል፤

(ሀ) የነገሩ ስምና ቁጥር፤
(ለ) ቀኑና ሰዓቱ ፤
(ሐ) የዐቃቤ ሕጉና የተከሳሹ ጠበቃ ስም፤
(መ) የዳኞቹ ስም፤

(፫) ነገሩ በሚሰማበት ጊዜ ሁሉ ነገሩ ምን ሰዓት እንደ ተቋረጠና የተቀጠረበት ቀንና ሰዓት መጻፍ አለበት፡፡