አዋጅ ቁጥር ፭፻፶፮/፪ሺህ ዓ.ም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

አዋጅ ቁጥር ፭፻፶፮/፪ሺህ ዓ.ም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ

አዋጅ ቁጥር ፭፻፶፮/፪ሺህ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤትን
ለማቋቋም የወጣ አዋጅ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራሉ መንግሥት አባል ክልሎች፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መርጠው በሚልኳቸው አባላት የተመሠረተ በመሆኑ፣
ምክር ቤቱ በሕገመንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር በአግባቡ እንዲያከናውንና ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንዲሁም አፈ-ጉባኤው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፷፮/፪/ የምክር ቤቱን የአስተዳደር ሥራዎች አቀናጅቶ ለመምራት እንዲችል የምክር ቤቱን ጽሕፈት ቤት ማቋቋም በማስፈለጉ፣
የሚቋቋመው ጽሕፈት ቤት ምክር ቤቱንና የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤውን በጋራ እንዲያገለግል አድርጐ ማቋቋምና ሁለቱም አካላት ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ የሚያስችል የራሱ አደረጃጀት፣ አሠራርና በቂ የሰው ኃይል ሊኖረው የሚገባ መሆኑን በማመን፣
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፶፭/፩/ መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ
ጠቅላላ
፩. አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ ‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር ፭፻፶፮/፪ሺህ›› ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ትርጓሜ
የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር
፩/ ‹‹ምክር ቤት›› ማለት በሕገመንግሥቱ አንቀጽ ፶፫ መሠረት የተቋቋመው የፌዴራሉ መንግሥት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡
፪/ ‹‹አፈ-ጉባዔ›› እና ‹‹ምክትል አፈ-ጉባዔ›› ማለት በሕገመንግሥቱ አንቀጽ ፷፪ /፲፩/ መሠረት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚመረጡ አፈ-ጉባዔና ምክትል አፈ-ጉባዔ ናቸው፡፡
፫/ ‹‹አጣሪ ጉባዔ›› ማለት በሕገመንግሥቱ አንቀጽ ፹፪ መሠረት የተቋቋመ የፌዴራሉ መንግሥት የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ማለት ነው፡፡
፬/ ‹‹ኮሚቴዎች›› ማለት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፷፪ /፲/ መሠረት በምክር ቤቱ የሚቋቋሙ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ናቸው፡፡
፭/ ‹‹አስተባባሪ ኮሚቴ›› ማለት አፈ-ጉባዔው፣ ምክትል አፈ-ጉባዔው፣ የቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች፣ ምክትል ሰብሳቢዎችና የንዑስ ቋሚ ኮሚቴዎች ተወካዮች ያሉበት በምክር ቤቱ የተቋቋመ ኮሚቴ ነው፡፡
፫. መቋቋም
፩/ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት /ከዚህ በኋላ ‹‹ጽሕፈት ቤቱ›› ተብሎ የሚጠራ/ ራሱን የቻለ ሕጋዊ ሰውነት ያለው አካል በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡
፪/ ጽሕፈት ቤቱ ተጠሪነቱ ለአፈ-ጉባዔው ይሆናል፡፡

ክፍል ሁለት
ስለምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት
፬. የጽሕፈት ቤቱ ሥልጣንና ተግባር
ጽሕፈት ቤቱ አፈ-ጉባዔው በሚሰጠው አመራር መሠረት፡-
፩/ ለምክር ቤቱና ምክር ቤቱ ለሚያቋቁማቸው ኮሚቴዎች፣ ለአፈ-ጉባዔዎች፣ ለምክር ቤቱና ለአጣሪ ጉባኤ አባላት ወጠቃላይ አስተዳደራዊ፣ የጽሕፈት፣ የመስተንግዶና የመረጃ አልግሎት ይሰጣል፣
፪/ በአፈ-ጉባዔው ወይም በምክትል አፈ-ጉባዔው ወይም በአጣሪ ጉባኤው ሰብሳቢ ውሳኔ መሠረት በወቅቱ ለአባላት የስብሰባ ጥሪ ያስተላልፋል፣ አጀንዳዎችንና ተፈላጊ ሰነዶችንም ያሰራጫል፤
፫/ የምክር ቤቱና የአፈ-ጉባዔዎች እንግዶች አስፈላጊውን የመስተንግዶ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል፤
፬/ የምክር ቤቱ፣ የአጣሪ ጉባኤውና የጽሕፈት ቤቱ፡-
ሀ/ ቃለ-ጉባኤዎች፣ ውሳኔዎች፣ አቋሞች፣ ሰነዶችና መዛግብቶች፣ እና
ለ/ አስፈላጊ የሆኑ መጽሐፍት ጥራዞች ጥናታዊ ጽሑፎችና መረጃዎች በአግባቡ ተሰብስበው ተመዝግበውና ተደራጅተው አገልግሎት እንዲሰጡና እንዲጠበቁ ያደርጋል፡፡
፭/ የምክር ቤቱን የአጣሪ ጉባኤውና የጽሕፈት ቤቱን አቋም አሰራርና ተልእኮ የሚመለከቱ ጉዳዮችን የያዙ መጽሔቶች ጋዜጦችና በራሪ ጽሑፎች አዘጋጅቶ እንዲታተሙና እንዲሰራጩ ያደርጋል፤
፮/ በምክር ቤቱና በአጣሪ ጉባኤው ሥልጣነና ተግባር አሠራር አደረጃጀትና አግባብነት ባላቸው ሕጎች ዙሪያ ጥናትና ምርምር እንዲያደርግ ሲታዘዝ ጥናት ያካሂዳል፡፡ ውጤቱንም ከሙያዊ አስተያየት ጋር ያቀርባል፤
፯/ የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡና የተሰበሰቡ ገቢዎች በሁለት መካከል የሚከፋፈሉበትን እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥበትን በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ቀመር የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት አዘጋጅቶ ለኮሚቴው ያቀርባል፤
፰/ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም በሚሰጠው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ምክር ቤቱ ተጨሪማ የባለሙያ አስተያየት ሲጠይቅ ወይም የሕገመንግሥት ትርጉም አያስፈልግም በማለት በሰጠው ውሳኔ ላይ ይግባኝ ሲቀርብ ቋሚ ኮሚቴው በሚያዘው መሠረት ጥናት አድርጎ ሙያዊ አስተያየት ያቀርባል፤
፱/ ሕዝቡ ስለ ሕገ መንግሥቱና ስለምክር ቤቱ ሥልጣንና ተግባራት እንዲያውቅ ከሚመለከተው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ጋር በመሆን በተለያዩ መንገዶችና ዘዴዎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እንዲሰራ ያደርጋል፤
፲/ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያግዙና ሕግ ሊወጣላቸው የሚገቡ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ቋሚ ኮሚቴው በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት ያጠናል፣ ይለያል፣ ለኮሚቴ ያቀርባል፣
፲፩/ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የማንነት ጥናት ያካሂዳል፡፡ የጥናቱንም ውጤት ለሚመለከተው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ያቀርባል፣
፲፪/ በክልሎችና በሕዝቦች መካከል ያሉ አለመግባባቶች እንዲጠኑ ሲታዘዝ የዳሰሳ፣ የትንተናና የመከላከያ ስትራቴጂ በማጥናት የጥናቱን ውጤት ለኮሚቴው ያቀርባል፤
፲፫/ የምክር ቤቱ የአገር ውስጥና የውጪ ግንኙነት የተሳካና የተቃና እንዲሆን አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል፤
፲፬/ በክልሎች መካከል በተከሰተ አለመግባባት፣ በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመብት ጥያቄ መነሻነት ለምክር ቤቱ የቀረቡ አቤቱታዎች ሲመሩለት እና በሚሰጠው መመሪያ መሠረት መርምሮና አጣርቶ ለሚመለከተው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አስተያየት ያቀርባል፣
፲፭/ ምክር ቤቱ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አፈፃፀምና ያስገኙት ውጤት በተመለከተ በአፈ-ጉባዔው ሲታዘዝ ክትትልና ግምገማ በማድረግ ሙያዊ አስተያየት ያቀርባል፤
፲፮/ የንብረት ባለቤት ይሆናል፣ ውል ይዋዋላል፣ በስሙ ይከሳል፣ ይከሰሳል፣
፲፯/ በምክር ቤቱና በአፈ-ጉባዔው የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል፡፡

፭. የጽሕፈት ቤቱ አቋም
የጽሕፈት ቤቱ፡-
፩/ የምክር ቤት አባል ያልሆነና ባለሙያ በአፈጉባኤው አቅራቢነት በምክር ቤቱ አስተባባሪ ኮሚቴ የሚሾም፤
፪/ ብዛታቸው እንደሥራው አስፈላጊነት የሚወሰንና በአፈ-ጉባዔው የሚመደቡ የመምሪያ ኃላፊዎች፤
፫/ አስፈላጊው ሠራተኞች፤
፬/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፪/ የተጠቀሱት የጽሕፈት ቤቱ የመምሪያ ኃላፊዎች በፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ አይካተቱም፡፡

የጽሕፈት ቤቱ የሠራተኞች አስተዳደር ደንብ
ድርጅታዊ መዋቅርና የደመወዝ ስኬል
፩/ የጽሕፈት ቤቱ የሠራተኞች አስተዳደር ደንብ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ሕግን መሠረታዊ መርሆዎች በመከተል ተዘጋጅቶ በምክር ቤቱ ሲፀድቅ ሥራ ላይ ይውላል፡፡
፪/ የጽሕፈት ቤቱ ድርጅታዊ መዋቅርና የደመወዝ ስኬል የመንግሥትን የኢኮኖሚ አቅም ባገናዘበ መልኩ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ቀርቦ ከታየ በኋላ ይፀድቃል፡፡
፫/ ጽሕፈት ቤቱ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፪/ መሠረት መዋቅሩና የደመወዝ ስኬሉ ሲፀድቅና ሲፈቀድ ሥራ ላይ ያውላል፡፡

፯. የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ሥልጣንና ተግባር
፩/ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ከአፈ-ጉባኤው በሚሰጠው አመራርና የጽሕፈት ቤቱን የአስተዳደር ደንብ በመከተል የጽሕፈት ቤቱን ሥራዎች ይመራል፣ ያስተዳድራል፡፡
፪/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፩/ አጠቃላይ ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ፡-
ሀ/ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፬ የተመለከተቱትን የጽሕፈት ቤቱን ሥልጣንና ተግባራት ሥራ ላይ ያውላል፣
ለ/ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር ፪፻፶፩/፲፱፻፺፫ አንቀጽ ፵፭ እንደተመለከተው የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ሕግ አጠቃላይ መርሆዎችን መሠረት በማድረግና በጽሕፈት ቤቱ የአስተዳደር ደንብ መሠረት የጽሕፈት ቤቱን ሠራተኞች ይቀጥራል፣ ያስተዳድራል፣
ሐ/ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፮ /፪/ የተመለከተውን የጽሕፈት ቤቱን ድርጅታዊ መዋቅርና የደመወዝ ስኬል ለአስተባባሪ ኮሚቴ ያቀርባል፡፡ በአስተባባሪ ኮሚቴው ታይቶ ሲፀድቅና ሲፈቀድም በሥራ ላይ ያውላል፣
መ/ የጽሕፈት ቤቱን ዓመታዊ የሥራ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ለአፈ-ጉባኤው ያቀርባል ሲፈቀድም በሥራ ላይ ያውላል፣
ሠ/ ለጽሕፈት ቤቱ በተፈቀደለት በጀትና ባዘጋጀው የሥራ ፕሮግራም መሠረት የፋይናንስ ሕግን ተከትሎ ገንዘብ ወጪ ያደርጋል፣
ረ/ ጽሕፈት ቤቱ ከሦስተኛ ወገኖች ጋር በሚያደርጋቸው ግንኙነቶች ጽሕፈት ቤቱን ይወክላል፣
ሰ/ የጽሕፈት ቤቱን የሥራ እንቅስቃሴ አፈፃፀምና የሂሣብ ሪፖርት አዘጋጅቶ ለአፈጉባኤ ያቀርባል፣
ሸ/ ከአፈ-ጉባኤውና ከምክትል አፈጉባኤው የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል፡፡
፫/ ኃላፊው ለጽሕፈት ቤቱ የሥራ ቅልጥፍና ባስፈለገ መጠን ከሥልጣኑና ተግባሩ በከፊል ለጽሕፈት ቤቱ የበታች ኃላፊዎችና ሌሎች ሠራተኞች በውክልና ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ ሆኖም እርሱ በማይኖርበት ጊዜ ተክቶ እንዲሰራ የሚወክለው ኃላፊ ከሰላሳ ቀናት በላይ የሚሠራ ከሆነ ውክልናው በቅድሚያ ለአፈ-ጉባዔው ቀርቦ መጽደቅ ይኖርበታል፡፡

፰. በጀት
ጽሕፈት ቤቱ ለምክር ቤቱ የተመደበውን ዓመታዊ በጀት ያስተዳድራል በአግባቡም ሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፡፡

፱. የሂሣብ መዛግብት
፩/ ጽሕፈት ቤቱ የተሟሉና ትክክለኛ የሂሣብ መዛግብት ይኖሩታል፡፡
፪/ የጽሕፈት ቤቱ የሂሣብ መዛግብትና ገንዘብ ነክ ሰነዶች በዋናው ኦዲተር በየዓመቱ ይመረመራሉ፡፡ ሆኖም አፈ-ጉባዔው በማናቸውም አስፈላጊ ጊዜና ሰዓት የሂሣብ መዛግብት ሰነዶች በከፊልም ሆነ በሙሉ በዋናው ኦዲተር እንዲመረመሩ ሊያዝ ይችላል፡፡

ክፍል ሦስት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
፲. መመሪያ የማውጣት ሥልጣን
አስተባባሪ ኮሚቴው ይህንን አዋጅና ምክር ቤቱ የሚያወጣውን ደንብ ለማስፈፀም የተለያዩ መመሪያዎችን ሊያወጣ ይችላል፡፡

፲፩. የተሻሩና ተፈፃሚነት የማይኖራቸው ሕጎች
፩/ ይህን አዋጅ የሚቃረኑ ማናቸውም ሕጐች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና የአሠራር ልምዶች በዚህ አዋጅ ውስጥ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት አይኖራቸውም፡፡
፪/ የአዋጅ ቁጥር ፪፻፶/፲፱፻፺፫ አንቀጽ ፭፣ ፲፬፣ ፲፭፣ እና ፲፮ እንዲሁም የአዋጅ ቁጥር ፪፻፶፩/፲፱፻፺፫ አንቀጽ ፵ እና ፵፬ ድንጋጌዎች በዚህ አዋጅ ተሽረዋል፡፡

፲፪. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ታህሣሥ ፳፪ ቀን ፪ሺ ዓ.ም
ግርማ ወልደጊዮርጊስ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ
ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት