የመክሰስና የምርመራ ሥነ ሥርዐት | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

የመክሰስና የምርመራ ሥነ ሥርዐት

ሁለተኛ መጽሐፍ፡፡
የመክሰስና የምርመራ ሥነ ሥርዐት
አንቀጽ ፩
የመክሰስና የምርመራ ሥራ አጀማመር
ምዕራፍ ፩
የሥነ ሥርዐቱ አጀማመር፡፡
ክፍል ፩
ክስና አቤቱታ ስለ ማቅረብ፡፡

 

ቍ ፲፩፡፡ ስለ ወንጀል ክስ በጠቅላላው፡፡
(፩) ማንም ሰው ማንኛውንም ወንጀል ሲሠራ ያየ ወይም ያላየም ቢሆን የወንጀል ክስ እንዲቀርብ ወንጀሉን ለማስታወቅ መብት አለው፡፡
(፪) ማንም ሰው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ውስጥ በቍጥር ፪፻፷፯፤ ፫፻፵፬ እና ፬፻፴፰ በተመለከተው መሠረት የተሠራውን ወንጀል የማስታወቅ ግዴታ አለበት፡፡

ቍ ፲፪፡፡ ጠቋሚው ሳይታወቅ የሚቀርብ የወንጀል ክስ፡፡
ካልታወቀ ጠቋሚ የቀረበ የወንጀል ማስታወቅ ከፍ ያለ የሕግ መጣስን የሚገልጽ ሆኖ ወንጀሉ ለመሠራቱ በአካባቢ ሁኔታ የተደገፈና የሚታመን መስሎ የተገኘ እንደ ሆነ በቍጥር ፳፪ እና በተከታዩ በተመለከተው መሠረት እውነትን ለማግኘት ያለዚያም የቀረበውን ክስ ለማረጋገጥ ሥልጣን ባለው ፖሊስ ይመረመራል፡፡
ቍ ፲፫፡፡ በክስ አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ የሚያስቀጣ ወንጀል፡፡
በተበዳዩ ወይም ስለተበዳዩ ባለመብት በሆኑ ሰዎች ክስ አቅራቢነት ብቻ በሕጉ መሠረት የሚያስከስሱና የሚያስቀጡ ወንጀሎች ከሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ውስጥ በቍጥር ፪፻፲፯  እስከ ፪፻፳፪ እና ፯፻፳፩ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈጻሚዎች ይሆናሉ፡፡

ቍ ፲፬፡፡ የወንጀል ክስ ወይም የክስ አቤቱታ የማቅረብ ሥነ ሥርዐት፡፡
(፩) ማናቸውም የወንጀል ክስ (ቍጥር ፲፩) ወይም የክስ አቤቱታ (ቍጥር ፲፫) የቀረበለት ሰው በጽሑፍ ከተቀበለ በኋላ የክሱን አቤቱታ ላቀረበው ሰው ተነቦለት ቀኑን ጽፎ ይፈርምበታል፡፡
(፪) በወንጀለኛ መቅጫ በቁጥር ፪፻፲፱ እንደተመለከተው የወንጀል ክስ ወይም የክስ አቤቱታ አቅራቢዎች ብዙ ሰዎች የሆኑ እንደሆነ ሁሉም በወንጀሉ ክስ ወይም በክስ አቤቱታው ላይ መፈረም አለባቸው፡፡

ቍ ፲፭፡፡ ባልታወቀ ሰው ላይ የሚቀርብ የወንጀል ክስ ወይም የክስ አቤቱታ፡፡
የወንጀል ክስ ወይም የክስ አቤቱታ ያቀረበው ሰው ወንጀለኛውን ለይቶ ለማወቅ ያልተቻለው እንደሆነ፤ ወንጀለኛውን ለይተው የሚያሳውቁትን ልዩ ልዩ ምልክቶች ሁሉ በዝርዝር መስጠት አለበት፡፡

ቍ ፲፮፡፡ ክስን ወይም የክሱን አቤቱታን ለመቀበል መብት ያለው ባለሥልጣን፡፡
(፩) ማናቸውንም የወንጀል ክስ (ቍጥር ፲፩) ወይም ማናቸውንም የክስ አቤቱታ (ቍ ፲፫) ለፖሊስ ወይም ለዐቃቤ ሕግ ማቅረብ ይቻላል፡፡ አካለመጠን ባልደረሰ ወጣት ላይ የሚቀርብ ክስ ወይም የክስ አቤቱታ በቍጥር ፩፸፪ መሠረት መቅረብ አለበት፡፡
(፪) የወንጀሉ ክስ ወይም የክሱ አቤቱታ ለዐቃቤ ሕጉ ሲቀርብለት በቍጥር ፳፪ እና በተከታዮቹ ቁጥሮች መሠረት የተባለው ወንጀል እንዲመረመር ዐቃቤ ሕጉ ሥልጣን ላለው ፖሊስ ማስተላለፍ አለበት፡፡

ቍ ፲፯፡፡ የወንጀል ክስ ወይም የክስ አቤቱታ መብት ለሌለው ባለሥልጣን ስለ ማቅረብ፡፡
የወንጀሉ ክስ ወይም የክሱ አቤቱታ ለፖሊስ ወይም ለዐቃቤ ሕግ መቅረቡ ቀርቶ ለአንድ ሰው ወይም ለሌላ ባለሥልጣን ወይም ይህንኑ ጉዳይ ለመቀበል መብት ለሌለው ለፖሊሲ ባለሥልጣን ወይም ለዐቃቤ ሕግ የቀረበ እንደሆነ ይኸው ሰው ባለሥልጣን ወይም ዐቃቤ ሕጉ ሳይዘገይ በቶሎ ጉዳዩ ለሚመለከተው ሥልጣን ላለው ፖሊስ ወይም ዐቃቤ ሕግ ይህንኑ ክስ ወይም የክስ አቤቱታ መላክ አለበት፡፡

ቍ ፲፰፡፡ ሐሰተኛ ክስ ወይም ሐሰተኛ የክስ አቤቱታ፡፡
ሐሰተኛ ክስ ወይም ሐሰተኛ የክስ አቤቱታ ያቀረበ ማናቸውም ሰው በወንጀለኛው መቅጫ ሕግ ቍጥር ፬፻፵፩ እና ፭፻፹ በተመለከተው መሠረት ይቀጣል፡፡
ክፍል ፪
የእጅ ተፍንጅ ወንጀል ክስ አጀማመር፡፡

ቍ ፲፱፡፡ እጅ ተፍንጅ የሚባሉ ወንጀሎች፡፡

(፩) አንድ ወንጀል እጅ ተፍንጅ ነው የሚባለው ወንጀል አድራጊው ወንጀሉን ሲሠራ የተያዘ ሲሆን ወይም ለመሥራት ሲሞክር ወይም የወንጀሉን ሥራ እንደ ፈጸመ ወዲያውኑ የተያዘ ሲሆን ነው፡፡
(፪) ወንጀል አድራጊው የወንጀሉን ሥራ ከፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ ሲሸሽ ምስክሮቹ ወይም ሕዝቡ የተከታተሉት ወይም የሕዝቡ ጩኸትና እሪታ የተሰማ እንደሆነ፤ ወንጀሉ የእጅ ተፍንጅ መሰል እንደሆነ ይቆጠራል፡፡
ቍ ፳፡፡ ተመሳሳይ ሁኔታዎች፡፡
አንድ ወንጀል የእጅ ተፍንጅ ነው ተብሎ በቁ ፲፱ ሊጠቀስ የሚቻለው፤
(ሀ) ወንጀሉ በተሠራበት ቦታ ወዲያውኑ ፖሊስ የተጠራ እንደሆነ ወይም
(ለ) ወንጀሉ ሲሠራ ወይም እንደተፈጸመ ወንጀሉ ከተሠራበት ቦታ ላይ የይድረሱልኝ እሪታ የተሰማ እንደሆነ ነው፡፡

ቍ ፳፩፡፡ የክስንና የመያዝን ሥነ ሥርዐት አጀማመር ስለሚመለከቱ ውጤቶች፡
(፩) በቍጥር ፲፱ እና ፳ በተዘረዘሩት ወንጀሎች መሠረት ወንጀሉ የክስ አቤቱታ ሳይቀርብ ክስ ሊቀርብበት የማይችል ካልሆነ በቀር ክስ ወይም የክስ አቤቱታ እንዲቀርብበት አስፈላጊ ሳይሆን ክስ ለማቅረብ ይቻላል፡፡
(፪) እንደዚህ ያለው ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ፍርድ ቤት የሚሰጠው የመያዝ ትእዛዝ ሳይኖር በቍጥር ፵፱ እና በተከታታዮቹ ቁጥሮች መሠረት ወንጀለኛውን ለመያዝ ይቻላል፡፡