አዋጅ ቁጥር ፺፰/፲፱፻፺ ዓ.ም. ስለንግድ ተቋም የዋስትና መያዣ የወጣ አዋጅ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

አዋጅ ቁጥር ፺፰/፲፱፻፺ ዓ.ም. ስለንግድ ተቋም የዋስትና መያዣ የወጣ አዋጅ

አዋጅ ቁጥር ፺፰/፲፱፻፺
ስለንግድ ተቋም የዋስትና መያዣ የወጣ አዋጅ

የንግድ ተቋሞች በዋሰትና መያዣነት ስለማመዘገቡበት መዝገቦች አያያዝና አፈጻጸም፣ ዋሰትናውን ከመዝገብ ስለመሰረዝና ስለሥርዓቱ በሕግ እንደሚደነገግ በንግድ ሕጉ አንቀጽ ፻፹፮ የተመለከተ በመሆኑ፤
በንግድ ሕጉ አንቀጽ ፻፸፱ በንግድ ተቋም ላይ የሚሠጡ መያዣዎችን ስለማስመዝገብ የተመለከቱት ድንጋጌዎች የሚጸኑት ወደፊት በነጋሪት ጋዜጣ በሚነገረው ቀንና ሁኔታ መሠረት እንደሚሆን በዚሁ የንግድ ሕግ አንቀጽ ፩ሺ፻፸፭(፩) የተደነገገ በመሆኑ፤
ለኢኮኖሚው እንቅስቃሴ አመች ሁኔታ ለመፍጠር የንግድ ተቋሞቻቸውን ለባነክ በዋስትና ካስያዙ ባለዕዳዎች ላይ የሚፈለጉ ዕዳዎችን በተቀላጠፈ መንገድ ማሰባሰብና ለወደፊቱ ጥሩ የንግድ አሠራር ባሕል እንዲዳብር ማድረግ በማሰፈለጉ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግሥት አንቀጽ ፶፭(፩) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ
ጠቅላላ

፩. አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ “ስለንግድ ተቋም የዋስትና መያዣ የወጣ አዋጅ ቁጥር ፺፰/፲፱፻፺ “  ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ትርጓሜ
በዚህ አዋጅ ውስጥ፤
፩. “የንግድ ተቋም” ማለት በ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. በወጣው የንግድ ሕግ የተመለከተው የንግድ መደብር ነው፡፡
፪. “ቢሮ” ማለት የክልል ወይም የከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ወይም በዋስትና የተሰጡ መያዣዎችን እነዲመዘግብ ሥልጣን የተሰጠው የክልል ወይም የከተማ አካል ነው፤
፫. “ከተማ” ማለት አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ ወይም ሌላ ለፌዴራሉ መንግሥት ተጠሪ የሆነ ከተማ ነው፤
፬. “ክልል” ማለት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክርሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመነግሥት አንቀጽ  ውስጥ የተመለከተ ክልል ነው፤
፭. “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፡፡

ክፍል ሁለት
ስለንግድ ተቋም ዋስትና መያዣ ምዝገባ
፫. መዝገብ ስለማቋቋም
፩. በንግድ ተቋም ላይ የሚደረግ የዋሰትና መያዣ መዝገብ በያንዳንዱ ክልለ ወይም ከተማ ይቋቋማል፡፡
፪. የዋስትና መያዣ መዝገብ አደረጃጀትና አቀማመጥ በክልል ወይም በከተማ አስፈጻሚ አካል ይወሰናል፡፡

፬. ስለንግድ ፈቃድ አስፈላጊነት
የንግድ ተቋምን በመያዣነት ለመስጠት በቅድሚያ የንግድ ተቋሙ አግባብ ባለው የፌዴራል ወይም የክልል አካል ተመዝግቦ የንግድ ፈቃድ ያወጣ መሆን አለበት፡፡

፭. ለምዝገባ ስለማመልከት
፩. ማናቸውም የዋስትና መያዣ ጥያቄ ጉዳዩ በሚመለከተው ሰው አመልካችነት ሊቀርብ ይችላል፡፡
፪. የዋስትና መያዣ ለማስመዝገብ ጥያቄ የሚቀርበው በቢሮው የተዘጋጀውን የምዝገባ ማመልከቻ ቅጽ በሁት ኮፒ ሞልቶ በማቅረብ ይሆናል፡፡
፫. አመልካቹ ከቅጹ ጋር ለምዝገባው ጥያቄ መነሻ የሆነውን የውል ሰነድ ወይም ሌላ ማስረጃ አያይዞ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
፬. ቢሮው ቅጹ ተሞልቶ ሲቀርብለት ትክክለኛነቱን ካረጋገጠ በኋላ እንደአመጣጡ ለቅጹ ተከታታይ ቁጥር ይሰጠዋል፡፡

፮. ስለምዝገባ ማመልከቻ ቅጽ ይዘት
፩. ቢሮው ለዋስትና መያዣ ምዝገባ ማመልከቻ ቅጽ አዘጋጅቶ ያወጣል፡፡
፪. የምዝገባ ማመልከቻ ቅጽ የሚከተሉትን ይጨምራል፤
ሀ. የምዝገባ ጥያቄ ያቀረበው ሰው ወይም ወኪል ስምና አድራሻ፣
ለ. የንግድ ተቋሙ አስቀድሞ በመያዣነት የተሰጠ ከሆነ የመዝገቡ ቁጥርና ቀን፣
ሐ. የዋስትና መያዣው ከሕግ ወይም ከውል የመነጨ መሆኑ፣
መ. የምዝገባው ጥያቄ አዲስ ምዝገባ ለማድረግ ወይመ ቀድሞ የተደረገ ምዝገባን ለማሻሻል የቀረበ መሆኑ፣
ሠ. ቅጹ የተሞላበት ቀን ወር እና ዓመተ ምህረት፡፡
፯. የንብረት መለያ ምልክት ስለመስጠት
፩. በንግድ ሕጉ አንቀጽ ፻፸፭(፩) (ሰ) እና አንቀጽ ፻፸፱(፩) (ሠ) መሠረት በዋስትና መያዣነት በተሰጡት የንግድ ተቋም ንብረቶች ላይ የዋስትና መያዣ የተሰጠው ገንዘብ ጠያቂ መለያ ምልክት ሊያደረግባቸው ይችላል፡፡
፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት የተሰጡት መለያ ምልክቶች በመዝገብ ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡

፰. በመዝገብ ስለሚጻፉ መግላዎች
፩. በመዝገብ ውስጥ የሚገቡ አስፈላጊ መግለጫዎች በተለይም
ሀ. የዋስትና መያዣው በመዝገብ የገባበት ቀን ወረና ዓመተ ምህረት
ለ. ማናቸውም የገንዘብ መጠን ወይም ሌላ ድምር በአኃዝና በፊደል፣ በማያሻማ ሁኔታ በግልጽ መጻፍ ይኖርባቸዋል፡፡
፪. በመዝገብ ላይ የሚጻፉ መግለጫዎች በማይጠፋ ቀለም መጻፍ ይኖርባቸዋል፡፡

፱. ስለመመዝገብና ስለምዝገባ ክፍያ
ማንኛውም የዋሰትና መያዣ ምዝገባ ማመልከቻ ቅጽ ከስፈላጊው ሰነዶች ጋር ቀርቦ የተሟላ መሆኑን ቢሮው ካረጋገጠ አመልካቹን የምዝገባ ክፍያ በማስከፈል ይመዘግባል፡፡

፲. በመዝገብ የገቡ መግለጫዎችን ስለማረም
፩. በመዝገቡ ውስጥ የገባ ማንኛውም መግለጫ ያልተሟላ ወይመ ትክክል ያልሆነ ሆኖ ከተገኘ ሊታረም ይችላል፡፡
፪. ቢሮው በመዝገብ የገቡ መግለጫዎች ስለሚታረሙበት ሁኔታ መመሪያ ያወጣል፡፡

፲፩. ቁጥጥር ስለማድረግ
ቢሮው በዋስትና መያዣነት የተመዘገበውን የንግድ ተቋም ስለሚገኝበት ሁኔታ ለማጣራት ወይም ለመመርመር በቦታው ተገኝቶ ለመቆጣጠር ወይም መግለጫ እንዲሰጥበት ለመጠየቅ ይችላል ባለንብረቱም ተገቢውን ትብብር የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡

፲፪. ስለመሰረዝ ሥርዓት
፩. የዋስትና መያዣው ከዝገብ እንዲሰረዝለት የሚጠይቅ ሰው መያዣው እንዲለቀቅለት የተደረገበትን ስምምነት ወይም በፍርድ ቤት የተሰጠውን የመጨረሻ ውሳኔ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
፪. መዝጋቢው የቀረበውን ሰነድ ትክክለኛነት በማረጋገጥ መያዣውን ከመዝገብ ይሰርዛል፡፡

ክፍል ሦስት
በዋስትና የተሰጠን የንግድ ተቋም በሐራጅ ስለመሸጥ
፲፫. የዋስትና መያዣ ስምምነት
የ፲፱፻፺ ዓ.ም. የንግድ ሕግ አንቀጽ ፻፹፱ ቢኖርም፣ የዋስትና መያዣ ያለው ገንዘብ ጠያቂ ባንክ የሚፈልገው ገንዘብ ሳየከፈለው ቢቀር ከሠላሳ ቀናት ያላነሰ ማስጠንቀቂያ ለባለዕዳው በመስጠት ለባነክ ብድር ዋስትና በመያዣ የተሰጠን የንግድ ተቋም በሐራጅ ለመሸጥና የንግድ ተቋሙን የባለቤትነት መብት ለገዢ ለማዛወር ወይመ ለሁለተኛ ጊዜ የወጣ የሐራጅ ማሰታወቂያ መሠረት ገዢ ካልቀረበ ንብረቱን በብድር ውሉ ውሰጥ በሰፈረው የዋጋ ግምት መሠረት ለመውሰድና የባቤትነት መብቱ በስሙ እንዲዛወርለት ለማድረግ ከባለዕዳ ጋር የሚያደርገው ስምምነት ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

፲፬. በንግድ ተቋም ላይ ያለ የዋስትና መብት
ይህ አዋጅ ከመጽናቱ በፊት የንግድ ሕጉ የንግድ ተቋም መያዣ እንዲመዘገብ በማስገደዱ በአንቀጽ ፩ሺ፻፸፭(፪) መሠረት በአውራጃ ፍርድ ቤት የተመዘገበ የዋስትና መያዣ ያለውና ገንዘቡ ያልተከፈለው ገንዘብ ጠያቂ ባንክ ለባለዕዳው ከሠላሳ ቀናት ያላነሰ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የንግድ ተቋሙን በሐራጅ ለመሸጥና ባለቤትነቱንም ለገዢው ለማዛወር ወይም ለሁለተኛ ጊዜ በወጣው የሐራጅ ማሰታወቂያ መሠረት ገዢ ካለቀረበ ንብረቱን በብድር ውሉ ውስጥ በሰፈረው የዋጋ ግምት መሠረት ለመውሰድና የባለቤትነት መብቱ በስሙ እንዲዛወርለት ለማድረግ ይችላል፡፡

፲፭. በባንክና በባለዕዳው መካከል ስሊሚኖር ግንኙነት
በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፲፫ እና ፲፬ መሠረት በባንክ የተደረገ ሽያጭ ባለዕዳውን በመወከል እንደተፈጸመ ይቆጠራል፡፡

፲፮. በሐራጅ ሽያጭ ላይ የፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ተፈጻሚ
ባንክ በዋስትና መያዣ የያዘውን የንግድ ተቋም በሐራጅ የመሸጠ ሥልጣኑን በሥራ ላይ በሚያውልበት ጊዜ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ከቁጥር ፫፻፺፬-፬፻፵፱ የተመለከቱት ድንጋጌዎች እንደአግባብነታቸው ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡

፲፯. ስለባንክ ተጠያቂነት
ባንክ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፲፮ የተጠቀሱትን አግባብ ያላቸውን የፍትሐበሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች በመተላለፍ ሽያጩን በመፈጸሙ ባለዕዳው ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት በኋላፊነት ተጠያቂነት ይሆናል፡፡

፲፰. የቢሮው ሥልጣንና ኃላፊነት
፩. የዋስትና መያዣውን የመዘገበው ቢሮ ለሐራጅ ሽያጭ አፈጻጸም የሚተዱ አስፈላጊ እርምጃዎችን የመውሰድ ሥልጣንና ኃላፊነት አለው፡፡
፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ቢሮው ለሚወስደው እርምጃ የፖሊስ ኃይል መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ፖሊስ ማዘዝ ይችላል፡፡

፲፱. በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ስላሉ ጉዳዮች
የንግድ ተቋምን በዋስትና በያዘ ባለገንዘብ ባንክ አመልካችነት ይህ አዋጅ ከመጽናቱ በፊት በፍርድ ቤት በታየት ላይ ያለ ክስ ወይም አፈጻጸም ተቋርጦ በዚህ አዋጅ መሠረት ባንኩ የንግድ ተቋሙን በሐራጅ ለመሸጥና የባለቤትነቱንም መብት ለገዢ ለማስተላለፍ ይችላል፡፡

ክፍል አራት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
፳. ስለንግድ ሕግ አፈጻጸም
፩. አግባብ ያላቸው የ፲፱፻፶፪ ዓ.ም. የንግድ ሕግ ድንጋጌዎች በንግድ ተቋም የዋሰትና መያዣዎች ላይ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡
፪. ለዚህ አዋጅ አፈጻጸም በንግድ ሕጉ የንግድ ተቋምን በዋስትና መያዣዎች ላይ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡
ሀ. ክልልን የሚመለከት ከሆነ “ጠቅላይ ግዛት” የሚለው “ክልል” እንዲሁም “የንግድ ሚኒስቴር” የሚለው “ቢሮ” ወይም
ለ. ከተማን የሚመለከት ከሆነ “ጠቅላይ ግዛት” የሚለው “ከተማ” እንዲሁም “ንግድ ሚኒስቴር” የሚለው “ቢሮ” ተብሎ ይነበባል፡፡

፳፩. ስለ ክፍያ
በንግድ ሕጉና በዚህ አዋጅ መሠረት ለዋስትና መያዣ ምዝገባና ለተዛመዱ አገልግሎቶች የሚከፈል ክፍያ በክልል ወይም በከተማ ሕግ ይወሰናል፡፡

፳፪. አዋጁ የሚጸናበት ጊዜ
በንግድ ተቋም ላይ ስለሚሰጡ መያዣዎች ምዝገባ የንግድ ሕጉ አንቀጽ ፻፸፱ እና የዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች የሚጸኑት ከየካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም. ጀምሮ ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ የካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም.
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ፕሬዚዳንት