አዋጅ ቁጥር ፺፯/፲፱፻፺ ዓ.ም. በባንክ በመያዣ ስለተያዘ ንብረት የወጣ አዋጅ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

አዋጅ ቁጥር ፺፯/፲፱፻፺ ዓ.ም. በባንክ በመያዣ ስለተያዘ ንብረት የወጣ አዋጅ

አዋጅ ቁጥር ፺፯/፲፱፻፺
በባንክ በመያዣ ስለተያዙ የማይንቀሳቀሱና
የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች የወጣ አዋጅ

በባንኮች በዋስትና የተያዙ የማይንቀሳቀሱና የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች እንዲሸጡ ለፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ ለማስወሰንና ውሳኔውንም ለማስፈጸም የሚወስደው ጊዜ በጣም ረጅም በመሆኑ፤
በቁጠባ ሂሣብ መልክ ከሕዝብ የሰበሰቡትንና ከተለያዩ ምንጮች ያገኙትን ገንዘብ በማበደር በሚገኘው የወለድ ገቢ የሚተዳደሩ ባንኮች ሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ በማሳደሩ፤
ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴው አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ባንኮች በተለያዩ የነግድና የልማት እንቅስቃሴ የሚሰጧቸው ብድሮችን በተቀላጠፈ መንገድ ለመሰብሰብ እንዲችሉና ለወደፊቱ ጥሩ የነግድ አሰራር ባህል እንዲዳብር ለማድረግ ለባንክ ብድር በመያዣ የተሰጡ የማይንቀሳቀሱና የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችን ሽያጭ በሚመለከት በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎች ማሻሻልና አዲስ ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግሥት አንቀጽ ፶፭(፩) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡
፩. አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ “በባንክ በመያዣ ስለተያዘ ንብረት የወጣ አዋጅ ቁጥር ፺፯/፲፱፻፺” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ትርጓሜ
በዚህ አዋጅ ውስጥ “ሬጅስትራር” ማለት በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያለ መበትን በተመለከተ የማይንቀሳቀስ ንብረት የመመዝገብ ኃላፊነትተ ያለው የክልል ወይም የከተማ አካል ወይም በሚንቀሳቀስ ንብረት ላይ ለየ መበትን በተመለከተ የስምምነቱን መፈረም የሚያረጋግጠውና ስምመነቱን የሚያስቀምጠው የክልል ወይም የከተማ አካል ነው፡፡

፫. የማይንቀሳቀስ ወይም የሚንቀሳቀስ ንብረት መያዣ ስምምነት
የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ ፪ሺ፰፻፶፩ እና አንቀጽ ፫ሺ፷ ድንጋጌ ቢኖርም የማይንቀሳቀስ ወይም የሚንቀሰቀስ ንብረት በዋስትና የያዘ ባለገንዘብ ባንክ የሚፈልገው እደው ንብረት በዋስትና የያዘ ባለገንዘብ ባንክ የሚፈልገው እዳው እንዲከፈል በተወሰነ ጊዜ ሳይከፈለው ቢቀር ከሠላሳ ቀናት ያላነሰ ማስጠንቀቂያ ለባለዕዳው በመስጠት በመያዣ የያዘውን የማይንቀሳቀስ ወይመ የሚንቀሳቀስ ንብረት በሐራጅ ለመሸጥ የባለቤትነት መበቱንም ለገዢው ለማዛወር ወይም ለሁለተኛ ጊዜ በወጣ የሐራጅ ማስታወቂያ መሠረት ገዥ ካልቀረበ ንብረቱን በብድር ውሉ ውስጥ በሰፈረው የዋጋ ግምት መሠረት ለመውሰድና የባለቤትነት መብቱ በስሙ እንዲዛወርለት ለማድረግ ከባለዕዳው ጋር የሚያደርገው ስምምነት ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

፬. በማይንቀሳቀስ ወይም በሚንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያለ የማያዣ መብት
ይህ አዋጅ ከመጽቱ በፊት የማይንቀሳቀስ ወይም የሚንቀሳቀስ ንብረት በመያዣ የያዘና ዕዳው እንዲከፈል በተወሰነው ጊዜ ያልተከፈለው ባለገንዘብ ባንክ ለባለዕዳው ከሠላሳ ቀናት ያላነሰ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በመያዣ የያዘውን የማይንቀሳቀስ ወይም የሚንቀሳቀስ ንብረት በሐራጅ ለመሸጥና የባለቤትነቱንም መበት ለገዢው ለማዛወር ወይመ ለሁለተኛ ጊዜ የወጣ የሐራጅ ማሰታወቂያ መሠረት ገዢ ካልቀረበ ንብረቱን በብድር ውሉ ውስጥ በሰፈረው የዋጋ ግምት መሠረት ለመውጸድና የባለቤትነት መብቱ በስሙ እንዲዛወርለት ለማድረግ ይችላል፡፡

፭. በባንክና በባለዕዳው መካከል ስለሚኖር ግንኙነት
በዚህ አዋጅ ፫ እግ ፬ መሠረት በባንክ የተደረገ ሽያጭ ባለዕዳውን በመወከል እንደተፈጸመ ይቆጠራል፡፡

፮. በሐራጅ ሽያጭ ላይ የፍትሐበሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ተፈጻሚነት
ባንክ በመያዣ የያዘውን የማይንቀሳቀስ ወይም የሚንቀሳቀስ ንብረት በሐራጅ የመሸጥ ሥልጣን በሥራ ላይ በሚያውልበት ጊዜ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ከቁጥር ፫፻፵፱-፬፻፵፱ የተመለከቱት ድንጋጌዎች እንደአግባብነታቸው ተፈጻማነት ይኖራቸዋል፡፡

፯. ስለባንክ ተጠያቂነት
ባንክ አዋጅ አንቀጽ ፮ የተጠቀሱትን አግባብ ያላቸውን ድንጋጌዎች በመተላለፍ ሽያጩን በመፈጸሙ በባለዕዳው ላይ ለሚደርሰው ጉዳት በኃላፊነት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

፰. የማይንቀሳቀስ ወይም የሚንቀሳቀስ ንብረት መያዣ መዝጋቢ ሥልጣንና ኃላፊነት
፩. ሬጅትራሩ ለማይንቀሳቀስ ወይም ለሚንቀሳቀስ ንብረት የሐራጅ ሽያጭ አፈጻጸም የሚረድ አስፈላጊ እርምጃዎችን የመውሰድ ሥልጣንና ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡
፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ሬጅስትራሩ ለሚወስደው እርምጃ የፖሊስ ኃይል መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ፖሊስን ማዘዝ ይችላል፡፡

፱. በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ስላሉ ጉዳዮች
የማይንቀሳቀስ ወይም የሚንቀሳቀስ ንብረት በዋስትና በያዘ ባለገንዘብ ባንክ አመልካችነት ይህ አዋጅ ከመጽናቱ በፊት በፈርድ ቤት በመታየት ላይ ያለ ክስ ወይም አፈጻጸም ተቋርጦ በዚህ አዋጅ መሠረት ባንክ ንብረቱን በሐራጅ ለመሸጥና የባለቤትነቱንም መብት ለገዢ ለማስተላለፍ ይችላል፡፡

፲. የተሻረ ሕግ
የፍትሐብሔር ሕግ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር ፷፭/፲፱፻፹፱ በዚህ አዋጅ ተሽሯል፡፡

፲፩. መሸጋገሪያ ድንጋጌ
ይህ አዋጅ ከመጽናቱ በፊት የፍትሐብሔር ሕግ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር ፷፭/፲፱፻፹፱ መሠረት በአፈጻጸም ላይ ያሉ ጉዳዮች በዚህ አዋጅ መሠረት ይመራሉ፡፡

፲፪. ተፈጻሚነት የማይኖራቸው ሕጎች
ይህንን አዋጅ የሚቃረን ማናቸውም ሕግ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡

፲፫. አዋጁ የሚጸናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ ከየካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም. ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ የካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም.
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ፕሬዚዳንት