አዋጅ ቁጥር ፹፰/፲፱፻፹፱ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመራጮቻቸው አመኔታ በሚያጡበት ጊዜ ስለሚወሰድ እርምጃ የወጣ አዋጅ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

አዋጅ ቁጥር ፹፰/፲፱፻፹፱ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመራጮቻቸው አመኔታ በሚያጡበት ጊዜ ስለሚወሰድ እርምጃ የወጣ አዋጅ

አዋጅ ቁጥር ፹፰/፲፱፻፹፱ ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመራጮቻቸው
አመኔታ በሚያጡበት ጊዜ ስለሚወሰድ እርምጃ
የወጣ አዋጅ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፶፬ ንዑስ አንቀጽ (፯) ማናቸውም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ባጣ ጊዜ በሕግ መሠረት ከምክር ቤት አባልነቱ እንደሚወገድ ስለሚደነግግ፤
ይህ መሠረታዊ ዲሞክራሲያዊ መርሆ በሥራ ላይ መዋሉ አስፈላጊ በመሆኑ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፶፭ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ
ጠቅላላ
፩. አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመራጮቻቸው አመኔታ በሚያጡበት ጊዜ ስለሚወሰድ እርምጃ የወጣ አዋጅ ቁጥር ፹፰/፲፱፻፹፱›› ተብሎ ሊጠቀስ ይቻላል፡፡

፪. ትርጓሜ
፩. በዚህ አዋጅ ውስጥ፣ ‹‹ተመራጭ›› ማለት በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚነት በተካሄደ ምርጫ አንድን የምርጫ ክልል ለመወከል የተመረጠና በምርጫ ቦርድ የምስክር ወረቀት የተሰጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነው፤
፪. ‹‹የምርጫ ክልል›› ማለት በምርጫው ሕግ መሠረት ፩፻ ሺህ ሕዝብ እና በልዩ ምርጫ ክልል የተወከሉትንም ያካተተ ወረዳ ወይም ወረዳዎች ማለት ነው፤
፫. ‹‹መራጭ›› ማለት በሕጉ መሠረት አሥራ ስምንት ዓመት የሞለውና በምርጫ ክልሉ ለሁለት ዓመት ወይም በላይ የኖረ ግለሰብ ነው፤
፬. ‹‹ወረዳ›› ማለት የክልሉ ምክር ቤት በሚወስነው መሠረት የተከለለ የአስተዳደር እርከን ነው፡፡

ክፍል ሁለት
መብቶችና ግዴታዎች
፫. መሠረታዊ መብቶች
፩. ማንኛውም ዜጋ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካዩን የመምረጥ መብት አለው፡፡
፪. ማንኛውም ዜጋ ከሌሎች መራጮች ጋር በመሆን የወከለውን ተመራጭ በየጊዜው መመርመር፣ መገምገምና መመዘን ይችላል፡፡
፫. ማንኛውም ዜጋ ለወከለው ተመራጭ ሲሰጥ የነበረውን ድጋፍ የማቋረጥ ወይም የመቀጠል መብት አለው፡፡
፬. ማንኛውም ተመራጭ በመራጮች የሚቀርብለትን ምስጋና፣ ተግሳጽ፣ ግምገማ ወይም ሂስ በግልጽና በአደባባይ የማስተጋባት፣ የመቃወምና ሂስ የማድረግ መብት አለው፡፡

፬. የመራጮች አመኔታ የሚለካበት ዘዴ
አንድ ተመራጭ የመራጮች አመኔታ የለውም ሊባል የሚችለው፤
፩. በተወከለበት የምርጫ ክልል ከሚገኙ መራጮች ከ፲፭ሺህ በላይ የምርጫ ቦርድ በሚያወጣው ደንብ መሠረት የይውረድልን ጥያቄ ለምርጫ ቦርድ ሲያቀርቡ፤
፪. በተወከለበት የምርጫ ክልል በሚገኙ ፲ ሺህ መራጮች አሳሳቢነት የምርጫ ቦርድ በሚያወጣው ደንብ መሠረት የወረዳ ምክር ቤቶች በአብላጫ ድምጽ ተወካዩ ተመልሶ እንዲጠራ ውሳኔ ያሳለፉ እንደሆነ፤
፫. የልዩ ምርጫ ክልል ተወካይን በተመለከተ የምርጫ ቦርድ በሚያወጣው ደንብ መሠረት የመራጮች አመኔታ ማጣቱ ሲረጋገጥ፤
፬. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጮች በሚያሳየው ሥነ ምግባር የወከለውን ሕዝብ በብቃት ሊወክል አልቻለም ብሎ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ሲወስን ይሆናል፡፡

፭. የሥነ ምግባር መለኪያዎች
፩. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ተገዥነቱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፶፬(፬) (ሐ) ለሕሊናውም ጭምር በመሆኑ በማናቸውም ረገድ የጸዳና የጠራ መሆን አለበት፡፡
፪. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሕዝብን ጉዳይ በሚወያይበት ጊዜ ሀቀኛና ግልጽ የመሆን ኃላፊነት አለበት፡፡
፫. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሀሰት ማስረጃዎች መፍጠር፣ መቅጠፍ፣ ያልተጣሩ ጉዳዮች ወደ ምክር ቤቱ መድረክ ማቅረብና መዋሸት ዋነኞቹ የሥነ ምግባር ብልሹነት መግለጫዎች ናቸው፡፡

፮. በሥነ ምግባር ብልሹነት ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች
፩. ምክር ቤቱ በሚያቋቁመው ኮሚቴ አማካይነት በሥነ ምግባር ብልሹነት የተከሰሰ ተመራጭ ጉዳይ ይጣራል፡፡
፪. አጣሪ ኮሚቴው በሚሰጠው የውሳኔ ሃሳብ ምክር ቤቱ ተወያይቶ ይወስናል፡፡
፫. ምክር ቤቱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ይችላል፤
ሀ) የሥነ ምግባር ብልሹነት ለተገኘበት ተመራጭ ለሕዝብ ይፋ በሆነ መልኩ የማስጠንቀቂያ ተግሳጽ ሊሰጠው ይችላል፤
ለ) የሥነ ምግባር ብልሹነት የተገኘበት ተመራጭ ለተወሰነ ጊዜ ከምክር ቤቱ እንዲታገድ ማድረግ ይችላል፤
ሐ) የሥነ ምግባር ብልሹነት የተገኘበት ተመራጭ በዚህ ንዑስ አንቀጽ (ሀ) እና (ለ) የተደነገጉትን ቅጣቶች ከተቀበለ በኋላ የሥነ ምግባር ብልሹነቱ የቀጠለ እንደሆነ ምክር ቤቱ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ከምክር ቤት አባልነቱ ሊሰርዘው ይችላል፡፡
፬. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፫) የተመለከቱት ተከታታይ የዲስፕሊን እርምጃዎች እንደጥፋቱ ክብደት ቅደም ተከተላቸው ሳይጠበቅ ተፈጻሚ ሊደረጉ ይችላሉ፡፡

፯. ከምክር ቤቱ መወገድ የሚኖረው ውጤት
፩. አንድ ተመራጭ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፬ እና ፮ መሠረት መቀመጫውን ሲያጣ በምርጫ ቦርድ የተሰጠው የተወካይነት መታወቂያ ሕጋዊነቱ ያከትማል፡፡
፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የምክር ቤት መቀመጫውን ያጣ የቀድሞ ተመራጭ በምርጫ ክልሉ መቀመጫውን ለመሙላት በሚደረገው ምርጫ ተወዳዳሪ ለመሆን ይችላል፡፡
፫. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) የተጠቀሰው ምርጫ የሚከናወነው የቀድሞው ተመራጭ የምክር ቤት መቀመጫውን ካጣበት ቀን ጀምሮ ከ፫ ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይሆናል፡፡

፰. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ ከሰኔ ፴ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ.ም. ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ሰኔ ፴ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ.ም.

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ
ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት