የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፩፻፷፱/፪ሺ፩ የጀነቲክ ሀብትና የማህበረሰብ ዕውቀት አርክቦትና የማህበረሰብ መብቶች የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፩፻፷፱/፪ሺ፩ የጀነቲክ ሀብትና የማህበረሰብ ዕውቀት አርክቦትና የማህበረሰብ መብቶች የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፩፻፷፱/፪ሺ፩
የጀነቲክ ሀብትና የማህበረሰብ ዕውቀት አርክቦትና
የማህበረሰብ መብቶች የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር ፬፻፸፩/፲፱፻፺፰ አንቀጽ ፭ እና የጀነቲክ ሀብትና የማህበረሰብ ዕውቀት አርክቦትና የማህበረሰብ መብቶችን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር ፬፻፹፪/፲፱፻፺፰ አንቀጽ ፴፯ መሠረት ይህንን ደንብ አውጥቷል፡፡
ክፍል አንድ
ጠቅላላ ድንጋጌዎች
፩. አጭር ርዕስ
ይህ ደንብ ‹‹የጀነቲክ ሀብትና የማህበረሰብ ዕውቀት አርክቦት እና የማህበረሰብ መብቶች የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፩፻፷፱/፪ሺ፩›› ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ትርጓሜ
የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ ደንብ ውስጥ፡-
፩/ ‹‹የአርክቦት ውል›› ማለት የጀነቲክ ሀብት እና/ወይም የማህበረሰብ ዕውቀት ለማርከብና ከዚያም የሚገኘውን ጥቅም ለመጋራት በአዋጁ አንቀጽ ፲፬ (፪) መሠረት የሚፈረም ስምምነት ነው፤
፪/ ‹‹የአርክቦት አመልካች›› ማለት በአዋጁ አንቀጽ ፲፬ (፩) መሠረት የአርክቦት ማመልከቻ ለኢንስቲትዩቱ ያቀረበ ሰው ነው፤
፫/ ‹‹የአርክቦት ማመልከቻ›› ማለት የጀነቲክ ሀብት እና/ወይም የማህበረሰብ ዕውቀት ለማርከብ በአዋጁ አንቀጽ ፲፬(፩) መሠረት ለኢንስቲትዩቱ በጽሑፍ የቀረበ ጥያቄ ነው፤
፬/ ‹‹የአርክቦት ገንዘብ›› ማለት በአርክቦት ውል መሠረት የጀነቲክ ሀብት እና/ወይም የማህበረሰብ ዕውቀት ጥቅም ላይ በመዋሉ ከተገኘው ገቢ በጥቅም ተጋሪነት የሚገኝ ገንዘብ ነው፤
፭/ ‹‹ሥልጣን ያለው አካል›› ማለት በአርክቦት አመልካቹ ሀገር ውስጥ የአርክቦት ውልን ለማስፈጸም ሥልጣን የተሰጠው የመንግሥት አካል ነው፤
፮/ ‹‹የማህበረሰብ እሺታ›› ማለት የማህበረሰብ ዕውቀት አርክቦትን ለመፍቀድ የአካባቢ ማህበረሰቦች በአዋጁ አንቀጽ ፯ (፩) (ሀ) መሠረት የሚሰጡት አስቀድሞ ተገንዝቦ የሚሰጥ ፈቃድ ነው፤
፯/ ‹‹ኢንስቲትዩት›› ማለት በአዋጅ ቁጥር ፩፻፳/፲፱፻፺ (እንደተሻሻለ) የተቋቋመው የብዝሀ ህይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩት ነው፤
፰/ ‹‹ዓለም አቀፍ ስምምነት›› ማለት በተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት ሰላሳ አንደኛ ጉባኤ እ.ኤ.አ. በኖቬምበር ፫ ቀን ፪ሺ፩ የፀደቀው እና በአዋጅ ቁጥር ፫፻፴/፲፱፻፺፭ ኢትዮጵያ ያፀደቀችው የምግብና ግብርና ዕፀዋት ጀኒቲክ ሀብት ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው፤
፱/ ‹‹የባለብዙ ወገን አርክቦት ሥርዓት›› ማለት በዓለም አቀፍ ስምምነቱ አንቀጽ ፲ መሠረት የምግብና ግብርና ዕፀዋት ጀነቲክ ሀብቶችን አርክቦት እና ከዚያም የሚገኘውን ጥቅም ፍትሐዊና ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ መጋራትን ለማቀላጠፍ የተመሠረተው ሥርዓት ነው፤
፲/ ‹‹አዋጅ›› ማለት የጀነቲክ ሀብትና የማህበረሰብ ዕውቀት አርክቦት እና የማህበረሰብ መብቶች አዋጅ ቁጥር ፬፻፹፪/፲፱፻፺፰ ነው፤
፲፩/ ‹‹አግባብነት ያለው የክልል አካል›› ማለት የጀነቲክ ሀብት እና/ወይም የማህበረሰብ ዕውቀትን እንዲያስተዳድር ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው የክልል መንግሥት መሥሪያ ቤት ነው፤
፲፪/ ‹‹የጀነቲክ ቁስ ማስተላለፊያ መደበኛ ውል›› ማለት  በዓለም አቀፍ ስምምነቱ አንቀጽ ፲፪ መሠረት የፀደቀው የምግብና ግብርና ዕፅዋት ጀነቲክ ሀብት ቁስ ማስተላለፊያ ስምምነት ነው፤
፲፫/ ‹‹አርክቦት››፣ ‹‹የጀነቲክ ሀብት››፣ ‹‹የማህበረሰብ ዕውቀት››፣ ‹‹የአካባቢ ማህበረሰብ››፣ ‹‹ሰው››፣ ‹‹አግባብነት ያለው ተቋም›› እና ‹‹መንግሥት›› የሚሉት ቃላት በአዋጁ የተሰጣቸው ትርጉም ይኖራቸዋል፤
፲፬/ ማንኛውም በወንድ ጾታ የተገለጸው አነጋገር ሴትንም ይጨምራል፡፡

ክፍል ሁለት
የአርክቦት ሥነ-ሥርዓት
ንዑስ ክፍል አንድ
ለንግድ ዓላማ የሆነ አርክቦት ስነ-ሥርዓት
፫. የአርክቦት ማመልከቻ አቀራረብ
የጀነቲክ ሀብት እና/ወይም የማህበረሰብ ዕውቀትን ለማርከብ በአዋጁ አንቀጽ ፲፬(፩) መሠረት የሚቀርበውን የአርክቦት ማመልከቻ በዚህ ደንብ አባሪ-፩ ላይ በተገለጸው መሠረት መቅረብ ይኖርበታል፡፡

፬. የአርክቦት ማመልከቻን ስለመቀበል
ኢንስቲትዩቱ የአርክቦት ማመልከቻ ሲቀርብለት፡-
፩/ የአርክቦት ማመልከቻው በዚህ ደንብ አባሪ -፩ ውስጥ የተገለጹትን መረጃዎች አሟልቶ የቀረበ መሆኑን ካረጋገጠ ማመልከቻውን በመቀበል በአርክቦት መዝገብ ላይ ይመዘግባል፤ ወይም
፪/ የአርክቦት ማመልከቻው በዚህ ደንብ አባሪ-፩ ላይ የተገለፁትን መረጃዎች አሟልቶ የቀረበ አለመሆኑን ካረጋገጠ የሚጎድለውን መረጃ በመግለጽ ተሟልቶ እንዲቀርብ ለአመልካቹ ይመልስለታል፡፡

፭. የአርክቦት ማመልከቻን ስለመመርመር
፩/ ኢንስቲትዩቱ በዚህ ደንብ አንቀጽ ፬ መሠረት ተቀብሎ የመዘገበውን የአርክቦት ማመልከቻ፣ ከአዋጁ ድንጋጌ እና ቀደም ሲል ከተፈረሙ የአርክቦት ውሎች አንፃር በመመርመር የተጠየቀው አርክቦት ሊፈቀድ የሚችል ወይም መከልከል ያለበት መሆኑን ይወስናል፡፡
፪/ ኢንስቲትዩቱ የአርክቦት ማመልከቻውን ከመረመረ በኋላ፡-
ሀ) የተጠየቀውን አርክቦት ለመፍቀድ የሚከለክል በቂ ምክንያት መኖሩን ካረጋገጠ፣ አርክቦቱን በመከልከል የከለከለበትን ምክንያት በመግለጽ ለአመልካቹ በጽሑፍ ያሳውቃል፤ ወይም
ለ) የተጠየቀውን አርክቦት መፍቀድ የሚከለክል ምክንያት አለመኖሩን ካረጋገጠ ማመልከቻው ለሕዝብ እንዲገለጽ ያደርጋል፡፡

፮. የአርክቦት ማመልከቻን ለሕዝብ ስለመግለጽ
፩/ ኢንስቲትዩቱ የአርክቦት ማመልከቻውን በአመልካቹ ወጪ ሰፊ ስርጭት ባለው ብሔራዊ ጋዜጣ እና እንደ ሁኔታው አርክቦቱ ሊፈፀም በታቀደበት አካባቢ በሚታተም የአካባቢ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ለሕዝብ እንዲገለጽ ያደርጋል፡፡
፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተጠቀሰው የህዝብ ማስታወቂያ፡-
ሀ) የአመልካቹን ማንነትና ሌሎች አስፈላጊ ዝርዝሮችን፣
ለ) ማርከብ የተፈለገውን የጀነቲክ ሀብት እና/ወይም የማህበረሰብ ዕውቀት መግለጫ፣ እና
ሐ) የጀነቲክ ሀብቱ እና/ወይም የማህበረሰብ ዕውቀቱ ሊውል የታሰበበትን አገልግሎት የሚገልጹ ዝርዝሮችን፣ መያዝ አለበት፡፡
፫/ ማናቸውም ሰው የሕዝብ ማስታወቂያው ለህዝብ ከተገለፀበት ዕለት አንስቶ በ፴ ቀናት ውስጥ በአርክቦት ማመልከቻው ላይ ተቃውሞ ለማቅረብ ወይም አስተያየት ለመስጠት ይችላል፡፡
፬/ ኢንስቲትዩቱ እንደ አስፈላጊነቱ አግባብነት ያላቸው ተቋማት በአርክቦት ማመልከቻው ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለማድረግ ይችላል፡፡

፯. የአርክቦት መረጃ ለሕዝብ ግልጽ ስለማድረግ
የአርክቦት ማመልከቻ በማቅረብ ወይም አርክቦትን በመቆጣጠር ሂደት ለኢንስቲትዩቱ የሚቀርብ የአርክቦት መረጃ ለሕዝብ ግልጽ ይደረጋል፤ መረጃውን መመልከት የፈለገም ማንኛውም ሰው ሊመለከተው ይችላል፡፡

፰. በሚስጥር የሚያዝ መረጃ
፩/ የዚህ ደንብ አንቀጽ ፯ ድንጋጌ ቢኖርም አሳማኝ ምክንያት በቀረበ ጊዜ ኢንስቲትዩቱ የአርክቦት ማመልከቻ በሚቀርብበት ወይም የአርክቦት ቁጥጥር በሚደረግበት ሂደት ለኢንስቲትዩቱ የሚቀርብ፣ በይፋ ያልተገለፀና በሦስተኛ ወገኖች ቅን ላልሆነ የንግድ ዓላማ ላልበለጠ ጊዜ በሚስጥር እንዲያዝ ለመፍቀድ ይችላል፡፡
፪/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) ድንጋጌ ቢኖርም የአርክቦት አመልካቹን ማንነት፣ ለማርከብ የተፈለገውን የጀነቲክ ሀብት ዓይነት፣ የጀነቲክ ሀብቱ የሚገኝበትን አካባቢ፣ የጀነቲክ ሀብቱን የሚያቀርበው ሰው ማንነት ወይም የጀነቲክ ሀብቱ በሚሰበሰብበት ወቅት አብሮ የሚገኘውንና አርክቦቱን የሚቆጣጠረውን ተቋም ማንነት የሚመለከት መረጃ በሚስጥር እንዲያዝ አይፈቀድም፡፡
፫/ የአርክቦት መረጃ በሚስጥር እንዲያዝለት የሚፈልግ የአርክቦት አመልካች፤ መረጃው በሚስጥር እንዲያዝ የሚያስፈልግበትን ምክንያትና በሚስጥር እንዲያዝ የተፈለገውን መረጃ በመግለጽ ጥያቄውን በጽሑፍ ለኢንስቲትዩቱ ማቅረብ አለበት፡፡
፬/ ኢንስቲትዩቱ የአርክቦት መረጃ በሚስጥር እንዲያዝ ሲፈቅድ፣ በሚስጥር የሚያዘውን መረጃና በሚስጥር የሚቆይበትን ጊዜ ማመልከት ይኖርበታል፡፡
፭/ ኢንስቲትዩቱ በሚስጥር እንዲያዝ የፈቀደውን መረጃ በተለየ ፋይል በማድረግ በሚስጥር ይይዛል፡፡

፱. በሚስጥር የተያዘ መረጃን ስለመግለጽ
፩/ በሚስጥር እንዲያዝ የተፈቀደ መረጃ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ፣ በሚስጥር እንዲያዝ የተፈቀደበት ጊዜ ሲያበቃ ወይም በተዋዋይ ወገኖች የጋራ ስምምነት መሠረት ካልሆነ በስተቀር ለሦስተኛ ወገን አይገለጽም፡፡
፪/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) ድንጋጌ ቢኖርም፣ ኢንስቲትዩቱ በሚስጥር እንዲያዝ የተፈቀደ መረጃን ሠራተኞቹ ወይም አማካሪዎቹ እንዲገመግሙት ሊገልጽላቸው ይችላል፤ ሆኖም ይህ በሚፈፀምበት ወቅት ኢንስቲትዩቱ መረጃው በሚስጥር የተያዘ መሆኑን ሠራተኞቹንና አማካሪዎቹን ማስገንዘብ አለበት፡፡

፲. የአርክቦት ውሳኔ አሰጣጥ
፩/ በአርክቦት ማመልከቻው ላይ ተቃውሞ ለማቅረብ ወይም አስተያየት ለመስጠት የተቀመጠው የጊዜ ገደብ እንዳበቃ፣ ኢንስቲትዩቱ የቀረቡለትን ተቃውሞዎችና አስተያየቶች በመመርመር፡-
ሀ) የአርክቦት ማመልከቻው ሊከለከል የሚችልበት ምክንያት መኖሩን ካረጋገጠ፣ የአርክቦት ማመልከቻውን ውድቅ በማድረግ ይህንኑ ለአመልካቹ ያሳውቃል፤ ወይም
ለ) የአርክቦት ማመልከቻውን የሚያስከለክል ምክንያት አለመኖሩን ካረጋገጠ፣ አርክቦቱ ሊፈቀድ እንደሚችል በመወሰን የአርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት ድርድር እንዲደረግ ለአርክቦት አመልካቹ ያሳውቃል፡፡
፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) (ለ) መሠረት ሊፈቀድ እንደሚችል የተወሰነ የአርክቦት ማመልከቻ የማህበረሰብ ዕውቀት ማርከብን የሚጨምር በሆነ ጊዜ፣ ኢንስቲትዩቱ በዚህ ደንብ ክፍል ሦስት በተገለጸው መሠረት የማህበረሰብ እሺታ እንዲሰጥበት ይደረጋል፡፡

ንዑስ ክፍል ሁለት
ለንግድ ዓላማ ያልሆነ አርክቦት ሥነ-ሥርዓት
፲፩. የማመልከቻ አቀራረብ
በአዋጁ አንቀጽ ፲፭ መሠረት ለሚያከናውኑት የትምህርት ወይም የምርምር ተግባራት ለማዋል የጀነቲክ ሀብት እና/ወይም የማህበረሰብ ዕውቀት ማርከብ የሚፈልጉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የምርምር ተቋማት እንዲሁም ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆነ የበይነ-መንግሥታት ተቋማት ለኢንስቲትዩቱ የሚያቀርቡት የአርክቦት ማመልከቻ በዚህ ደንብ አባሪ-፪ መሠረት መቅረብ ይኖርበታል፡፡

፲፪. የፈቃድ አሰጣጥ
የኢንስቲትዩቱ በዚህ ደንብ አንቀጽ ፲፩ መሠረት በኢትዮጵያ የትምህርት ወይም የምርምር ተቋም ወይም ተቀማጭነቱ በኢትዮጵያ በሆነ የበይነ-መንግሥታት ተቋም የአርክቦት ማመልከቻ ሲቀርብለት፤ አመልካቹ አርክቦቱን ሲያካሂድ የሚኖሩበትን ግዴታዎች በመወሰንና ለዚህም የአርክቦት ውል በማስፈረም የአርክቦት ፈቃድ ይሰጣል፡፡

፲፫. የጀነቲክ ሀብትን ከሀገር ስለማስወጣት
፩/ በዚህ ደንብ አንቀጽ ፲፪ መሠረት የአርክቦት ፈቃድ የሚሰጣቸው የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የምርምር ተቋማት እንዲሁም ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሆነ የበይነ-መንግሥታት ተቋማት የጀነቲክ ሀብትን ወደ ውጭ እንዲልኩ ፈቃድ ካልተሰጣቸው በስተቀር የአረከቡትን የጀነቲክ ሀብት ከኢትዮጵያ ማስወጣት አይችሉም፡፡
፪/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) ድንጋጌ ቢኖርም፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወይም የምርምር ተቋም ወይም ተቀማጭነቱ በኢትዮጵያ የሆነ የበይነ-መንግሥታት ተቋም ምርምሩን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማካሄድ የማይችል መሆኑን ኢንስቲትዩቱ ካረጋገጠ፣ የጀነቲክ ሀብትን ወደውጪ መላክ የሚችል መሆኑን በሚሰጠው የአርክቦት ፈቃድ ውስጥ ማመልከት ይችላል፡፡
፫/ ኢንስቲትዩቱ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) መሠረት የጀነቲክ ሀብትን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት ፈቃድ ሲሰጥ፣ ሀገሪቱ በጀነቲክ ሀብቱ ላይ ያላትን መብት ሊያስጠብቅ የሚችልና የጀነቲክ ሀብቱ የሚወሰድበትን የውጭ ሀገር ተቋም ያካተተ የአርክቦት ውል ማስፈረምና የስምምነቱን አፈጻጸም መከታተል ይኖርበታል፡፡

ንዑስ ክፍል ሦስት
የባለብዙ ወገን አርክቦት ሥነ ሥርዓት
፲፬. የባለብዙ ወገን አርክቦት ቅድመ ሁኔታዎች
በባለብዙ ወገን አርክቦት ሥርዓት መሠረት የጀነቲክ ሀብት አርክቦት የሚፈቀደው፡-
፩/ የተጠየቀውን የጀነቲክ ሀብት ዓይነት በዓለም አቀፍ ስምምነቱ አባሪ-፩ ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኝ ከሆነ እና የጀነቲክ ሀብቱ ለምግብና ግብርና ምርምር፣ ማዳቀልና ሥልጠና አገልግሎት ለመጠቀምና ለማንበር ብቻ የሚውል እና ይህም አገልግሎት ለኬሚካል፣ ለመድሀኒት እና/ወይም ለሌላ ለምግብ ወይም ለመኖ ያልሆነ ኢንዱስትሪያዊ አገልግሎት ማዋልን የማይጨምር ከሆነ፤
፪/ የአርክቦት አመልካቹ የዓለም አቀፍ ስምምነቱ ፈራሚ የሆነ ሀገር ዜጋ ወይም ነዋሪ ከሆነ፣ እና
፫/ የጀነቲክ ሀብቱ ለሕዝብ ጥቅም አገልግሎት እንዲውል በኢትየጵያ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የዘቦታ ወይም የኢዘቦታ ጥበቃና አስተዳደር ስር የሚገኝ ከሆነ ወይም የጀነቲክ ሀብቱ ባለይዞታ የሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ሰው የጀነቲክ ሀብቱ በባለብዙ ወገን አርክቦት ሥርዓቱ ውስጥ አንዲካተት የፈቀደ በሆነ ጊዜ ብቻ፣ ነው፡፡

፲፭. የአርክቦት ማመልከቻ
በባለብዙ ወገን አርክቦት ሥርዓት መሠረት የጀነቲክ ሀብት ለማርከብ የሚፈልግ ሰው በዚህ ደንብ አባሪ-፫ በተገለጸው መሠረት የተዘጋጀ የአርክቦት ማመልከቻ ለኢንስቲትዩቱ ማቅረብ አለበት፡፡

፲፮. የባለብዙ ወገን አርክቦት ውሳኔ አሰጣጥ
ኢንስቲትዩቱ የቀረበለትን የባለብዙ ወገን አርክቦት ማመልከቻ ከመረመረ በኋላ፡-
፩/ የአርክቦት ማመልከቻው በዚህ ደንብ አንቀጽ ፲፬ የተጠቀሱትን የባለብዙ ወገን አርክቦት ቅድመ ሁኔታዎች ያሟላ መሆኑን ካረጋገጠ፣ የባለብዙ ወገን አርክቦት ፈቃድ ለአመልካቹ ይሰጣል፤ ወይም
፪/ የአርክቦት ማመልከቻው በዚህ ደንብ አንቀጽ ፲፬ የተጠቀሱትን የባለብዙ ወገን አርክቦት ሥርዓት ቅድመ ሁኔታዎች የማያሟላ መሆኑን ካረጋገጠ፣ አርክቦቱን በመከልከል ይህንኑ ለአመልካቹ ያሳውቃል፡፡

፲፯. የአርክቦት ክፍያ
፩/ የባለብዙ ወገን አርክቦት የተፈቀደለት አመልካች የጀነቲክ ሀብቱን ለማቆየትና ለእርሱ ለማቅረብ የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን ይገባዋል፡፡ ይህም የጀነቲክ ሀብቱን ለመጠበቅ የወጣውን ወጪ፣ ናሙናው ሊሰጠው የሚችለው ተባዝቶ ወይም ተሰብስቦ ከሆነ ለማባዛት ወይም ለመሰብሰብ የሚያስፈልገውን ወጪ፣ እንዲሁም ናሙናው ከበሽታ ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ ለማሸግና በፖስታ ለመላክ የሚያስፈልጉ እና የመሳሰሉ ወጪዎችን ይጨምራል፡፡
፪/ ኢንስቲትዩቱ የባለብዙ ወገን ጀነቲክ ሀብት አርክቦት ፈቃድ ሲሰጥ አመልካቹ መክፈል የሚገባውን የአርክቦት ክፍያ ይወስናል፡፡

፲፰. የተቀላጠፈ አርክቦት ስለመስጠት
ኢንስቲትዩቱ የባለብዙ ወገን የአርክቦት ፈቃድ ሲሰጥ፣ ሌላ ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታ ሳይጠይቅ የጀነቲክ ሀብት ቁስ ማስተላለፊያ መደበኛ ውል በማስፈረምና የአርክቦት ክፍያ በማስከፈል የጀነቲክ ሀብቱን ካለው የፓስፖርት መረጃና ሚስጥር ያልሆኑ ተያያዥ ገላጭ መረጃዎች ጭምር ለአመልካቹ ይሰጣል፡፡

፲፱. ክትትልና ቁጥጥር
ኢንስቲትዩቱ በባለብዙ ወገን አርክቦት ሥርዓት መሠረት የሰጠው የጀነቲክ ሀብት በተፈረመው የጀነቲክ ቁስ ማስተላለፊያ መደበኛ ውል መሠረት ጥቅም ላይ መዋሉን በመከታተልና በመቆጣጠር አግባብነት ባለው ህግ መሠረት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡

፳. ክስ ስለማቅረብ
የጀነቲክ ቁስ ማስተላለፊያ መደበኛ ውል አፈጻጸምን አስመልክቶ የሚነሳ ክርክር ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ይችላል፡፡

ክፍል ሦስት
የማህበረሰብ እሺታ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት
፳፩. እሺታ የሚሰጠውን ማህበረሰብ ስለመለየት
፩/ የማህበረሰብ ዕውቀትን ለማርከብ ለሚቀርብ የአርክቦት ማመልከቻ እሺታ የሚሰጠው የዕውቀቱ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ ነው፡፡
፪/ የማህበረሰብ ዕውቀትን ለማርከብ ማመልከቻ ሲቀርብለት፣ ኢንስቲትዩቱ ቀደም ሲል ባካሄደው የጀነቲክ ሀብት እና/ወይም የማህበረሰብ ዕውቀት ስርጭት አሰሳ ላይ በመመስረትና አግባብነት ካላቸው የክልል አካላት ጋር በመመካከር የማህበረሰብ ዕውቀቱ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ እንዲለይና የማህበረሰብ እሺታ እንዲሰጥበት ያደርጋል፡፡

፳፪. የማህበረሰብ እሺታ አሰጣጥ
የማህበረሰብ እሺታ የሚሰጠው፤ የማህበረሰብ ዕውቀቱ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ የሚገኘው፡-
፩/ በአንድ ወረዳ ውስጥ ብቻ ከሆነ፣ በወረዳው ምክር ቤት፣
፪/ በአንድ ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ወይም ዞኖች ውስጥ ከሆነ፣ ከእነዚህ ወረዳዎች ወይም ዞኖች የተወከሉ የክልል ምክር ቤት አባላትን በማካተት በሚቋቋም የክልል ምክር ቤት ጊዜያዊ ኮሚቴ፣ ወይም
፫/ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ከሆነ፣ ማህበረሰቡ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች የተወከሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን በማካተት በሚቋቋም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጊዜያዊ ኮሚቴ፣ አማካይነት ይሆናል፡፡

፳፫. የአርክቦት ማመልከቻን ለእሺታ ስለማቅረብ
ለማህበረሰብ ዕውቀት አርክቦት ማመልከቻው እሺታ የሚሰጠው ማህበረሰብ በዚህ ደንብ አንቀጽ ፳፩(፪) መሠረት ተለይቶ እንደታወቀ ኢንስቲትዩቱ፡-
፩/ የማህበረሰብ እሺታ የሚሰጠው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚቋቋም ጊዜያዊ ኮሚቴ ከሆነ፣ የአርክቦት ማመልከቻውን ከውሳኔ ሀሳብ ጋር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፤
፪/ የማህበረሰብ እሺታ የሚሰጠው በወረዳ ምክር ቤት ወይም በክልል ምክር ቤት በሚቋቋም ጊዜያዊ ኮሚቴ ከሆነ፣ የአርክቦት ማመልከቻውን ከውሳኔ ሀሳብ ጋር እሺታውን ለሚሰጠው የወረዳ ምክር ቤት ወይም የክልል ምክር ቤት እንዲያቀርብ አግባብነት ላለው የክልል አካል ያስተላልፋል፡፡

፳፬. የእሺታ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት
፩/ የወረዳ ምክር ቤቶች፣ የክልል ምክር ቤት ጊዜያዊ ኮሚቴዎች እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጊዜያዊ ኮሚቴዎች የማህበረሰብ እሺታ የሚሰጡት የምክር ቤቶቻቸውን የስብሰባና የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት በመከተል ይሆናል፡፡
፪/ የወረዳ ምክር ቤቶች፣ የክልል ምክር ቤት ጊዜያዊ ኮሚቴዎች እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጊዜያዊ ኮሚቴዎች የሚሰጡት ውሳኔ ቅጂ ለኢንስቲትዩቱ ቀርቦ ከአርክቦት መዝገቡ ጋር ይያያዛል፡፡

፳፭. ወጪን ስለመሸፈን
የማህበረሰብ እሺታ ለማሰጠት የሚያስፈልገውን ወጪ የአርክቦት አመልካቹ ይሸፍናል፡፡

ክፍል አራት
የአርክቦት ገንዘብ አስተዳደርና አጠቃቀም
፳፮. የአርክቦት ገንዘብ አስተዳደር
፩/ ከጀነቲክ ሀብት እና/ወይም የማህበረሰብ ዕውቀት አርክቦት የሚገኘው ገንዘብ ሁሉ ጥቅም ላይ እስከሚውል ድረስ ‹‹የአርክቦት ፈንድ›› በሚሰጠኝ ልዩ ሂሳብ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡
፪/ ከእያንዳንዱ የአርክቦት ውል የሚገኝ ገንዘብ በተለየ የባንክ ሂሳብ ሆኖ በአርክቦት ፈንዱ ውስጥ ተለይቶ ይቀመጣል፡፡
፫/ ኢንስቲትዩቱ የእያንዳንዱ የአርክቦት ውል ዘመን ሲያበቃ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ከዚያም በፊት በማናቸውም ጊዜ የአርክቦት ገንዘቡ በዚህ ደንብ አንቀጽ ፳፯ እና ፳፰ በተደነገገው መሠረት ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋል፡፡

፳፯. የአርክቦት ገንዘብን ለብዝሀ ህይወት ጥበቃ ስለማዋል
፩/ በአዋጁ አንቀጽ ፲፰(፩) መሰረት ለብዝሀ ህይወትና ለማህበረሰብ ዕውቀት ጥበቃ እንዲውል የተመደበው የአርክቦት ገንዘብ፣ ገንዘቡን ያስገኘውን የጀነቲክ ሀብት ለመጠበቅ፣ ወይም ገንዘቡን ያስገኘው የጀነቲክ ሀብት የመመናመን አደጋ ከሌለበት ሌሎች የጀነቲክ ሀብቶችን ለመጠበቅና በዘላቂነት ለመጠቀም እንዲሁም ተያያዥ የማህበረሰብ ዕውቀቶችን ለመጠበቅ ለሚነደፉ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ይውላል፡፡
፪/ የአርክቦት ገንዘቡ ጥቅም ላይ የሚውልባቸው የብዘሃ ሕይወት ጥበቃ ፕሮጀክቶች የሚመረጡት ኢንስቲትዩቱ አግባብነት ላላቸው የክልልና የፌዴራል አካላት በሚያደርገው ግብዣ መሠረት ከሚቀርቡት የፕሮጀክት ሀሳቦች መሀከል ይሆናል፡፡
፫/ ኢንስቲትዩቱ የእያንዳንዱ የአርክቦት ውል ዘመን ሲያበቃ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ከዚያም በፊት በማናቸውም ጊዜ ኢንስቲትዩቱ የፕሮጀክት ሀሳቦች የሚቀርቡበትንና የሚመረጡበትን መመዘኛዎች በመወሰን የፕሮጀክት ሀሳቦች እንዲቀርቡ አግባብነት ላላቸው የክልልና የፌዴራል አካላት ጥሪ ያደርጋል፡፡
፬/ አሸናፊው ፕሮጀክት እንደተመረጠ፣ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ ከአርክቦት ገንዘብ ሂሳቡ ወጪ ሆኖ ፕሮጀክቱን ለሚያስፈጽመው አካል ይከፈላል፡፡

፳፰. የአርክቦት ገንዘብን ለማህበረሰቦች ጥቅም ስለማዋል
በአዋጁ አንቀጽ ፱ (፩) እና (፪) መሠረት ለማህበረሰቦች ጥቅም እንዲውል የተወሰነው የአርክቦት ገንዘብ የዚያ የጀነቲክ ሀብትና የማህበረሰብ ዕውቀት ባለቤት ለሆነው ማህበረሰብ ጠቀሜታ ለሚነደፉ የልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ይውላል፡፡

፳፱. ተጠቃሚውን ማህበረሰብ ስለመለየት
፩/ ኢንስቲትዩቱ ባካሄደው የጀነቲክ ሀብትና የማህበረሰብ ዕውቀት ስርጭት ቅኝት ላይ በመመስረት አግባብነት ካላቸው የክልል አካላት ጋር በመመካከር ከእያንዳንዱ የአርክቦት ውል የሚገኘው ገንዘብ ተጠቃሚ መሆን የሚገባው ማህበረሰብ እንዲለይ ያደርጋል፡፡
፪/ የአርክቦት ገንዘቡ ተጠቃሚ የሆነው ማህበረሰብ የሚገኘው በተለያዩ ወረዳዎች፣ ዞኖች ወይም ክልሎች ውስጥ በሆነ ጊዜ፣ በነዚህ ወረዳዎች፣ ዞኖች እና ክልሎች ውስጥ የሚገኙት ማህበረሰቦች የተጠቃሚነት ድርሻ መጠን የጀነቲክ ሀብቱን እና/ወይም የማህበረሰብ ዕውቀቱን ለመጠበቅ ካደረጉት አስተዋጽኦ አንፃር እየታየ የሚወሰን ይሆናል፡፡

፴. የአርክቦት ገንዘብ አጠቃቀምን ስለመወሰን
ለማህበረሰቦች ጥቅም የሚነደፉት የልማት ፕሮጀክቶች የሚወሰኑት፣ ተጠቃሚው ማህበረሰብ የሚገኘው፡-
፩/ በአንድ ወረዳ ውስጥ ብቻ ከሆነ፣ በወረዳው ምክር ቤት፣
፪/ በአንድ ክልል በተለያዩ ወረዳዎች ወይም ዞኖች ውስጥ ከሆነ፣ ከእነዚህ ወረዳዎች ወይም ዞኖች የተወከሉ የክልል ምክር ቤት አባላትን በማካተት በሚቋቋም የክልል ምክር ቤት ጊዜያዊ ኮሚቴ፣ ወይም
፫/ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ከሆነ፣ ማህበረሰቡ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች የተወከሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን በማካተት በሚቋቋም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጊዜያዊ ኮሚቴ፡- አማካይነት ይሆናል፡፡

፴፩. የፕሮጀክት ሀሳቦችን ስለማቅረብ
የእያንዳንዱ የአርክቦት ውል ዘመን ሲያበቃ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ከዚያም በፊት በማናቸውም ጊዜ ኢንስቲትዩቱ፡-
፩/ ተጠቃሚው ማህበረሰብ የሚገኘው በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ከሆነ፣ ለማህበረሰቡ ጥቅም የሚውሉ የልማት ፕሮጀክት ሀሳቦችን በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውሳኔ ያቀርባል፤
፪/ ተጠቃሚው ማህበረሰብ የሚገኘው በአንድ ክልል ውስጥ ከሆነ፣ ለማህበረሰቡ ጥቅም የሚውሉ የልማት ፕሮጀክት ሀሳቦች በማዘጋጀት የገንዘቡን አጠቃቀም ለሚወስነው የወረዳ ምክር ቤት ወይም የክልል ምክር ቤት ለውሳኔ እንዲያቀርብ የአርክቦት ገንዘቡን መጠን አግባብነት ላለው የክልል አካል ያሳውቃል፡፡

፴፪. የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት
የወረዳ ምክር ቤቶች፣ የክልል ምክር ቤት ጊዜያዊ ኮሚቴዎች እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጊዜያዊ ኮሚቴዎች የአርክቦት ገንዘብ ጥቅም ላይ የሚውልበትን የልማት ፕሮጀክት የሚወስኑት የምክር ቤቶቻቸውን የስብሰባና የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት በመከተል ይሆናል፡፡

፴፫. ወጪን ስለመሸፈን
ለማህበረሰብ ጥቅም የሚነደፉ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስወሰን ወጪ የሚጠይቅ ከሆነ ወጪው ከማህበረሰቡ የአርክቦት ገንዘብ ድርሻ ላይ የሚሸፈን ይሆናል፡፡

ክፍል አምስት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
፴፬. የአርክቦት መዝገብ
፩/ ኢንስቲትዩቱ ለሕዝብ ክፍት የሆነ የአርክቦት መዝገብ ይይዛል፡፡
፪/ የአርክቦት መዝገቡ የሚከተሉትን ሰነዶች ያካትታል፡፡
ሀ) የአርክቦት ማመልከቻዎችን፤
ለ) የአርክቦት ማመልከቻዎች ውድቅ የተደረገባቸውን ውሳኔዎች፤
ሐ) የአርክቦት ማመልከቻዎች ለሕዝብ የተገለፁባቸውን ማስታወቂያዎች፤
መ) በአርክቦት ማመልከቻዎች ላይ የቀረቡ መቃወሚያዎችንና አስተያየቶችን፤
ሠ) የአርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት ውሎችን፤
ረ) የተፈረሙ የጀነቲክ ቁስ ማስተላለፊያ መደበኛ ስምምነቶችን፤
ሰ) የአርክቦት ፈቃዶችን፤
ሸ) የአርክቦት ውል ክትትልና ቁጥጥር ሪፖርቶችን፤
ቀ) የአርክቦት ውል ማሻሻያዎችን፣ ዕገዳዎችን ወይም መቋረጦችን፤
በ) የአርክቦት ውሎችን እና የጀነቲክ ቁስ ማስተላለፊያ መደበኛ ስምምነቶችን በሚመለከት የተሰጡ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን፡፡

፴፭. የኢንስቲትዩቱ ሥልጣንና ሃላፊነት
ኢንስቲትዩቱ የሚከተሉት ሥልጣንና ሀላፊነት ይኖሩታል፡-
፩/ ይህንን ደንብ ለማስፈፀም የሚያስፈልግ መመሪያ የማውጣት፤
፪/ አግባብነት ያላቸውን አካላት በማስተባበር ለክልሎች የቴክኒክ ድጋፍ የመስጠት፤
፫/ በባለብዙ ወገን የአርክቦት ሥርዓቱ የሚሸፈን የጀነቲክ ሀብት በእጃቸው የሚገኝ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የጀነቲክ ሀብቱን በባለብዙ ወገን ሥርዓቱ ውስጥ እንዲያካትቱ የማበረታታት፡፡-

፴፮. የክልሎች ሥልጣንና ሃላፊነት
ክልሎች የሚከተሉት ሥልጣንና ሀላፊነቶች ይኖራቸዋል፡-
፩/ ይህንን ደንብ በክልላቸው ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ ደንቦችን ማውጣት፤ እና
፪/ ይህንን ደንብ በክልላቸው የሚያስፈፅም አካል የመሰየምና የማጠናከር፡፡

፴፯. ተፈፃሚነት የሌላቸው ሕጎች
ማናቸውም ደንቦች፣ መመሪያዎች ወይም አሠራሮች ይህንን ደንብ እስከተቃረኑ ድረስ በዚህ ደንብ ውስጥ በተደነገጉ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡

፴፰. ደንቡ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ ደንብ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ
ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ጥቅምት ፴ ቀን ፪ሺ፪ ዓ.ም
መለስ ዜናዊ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ጠቅላይ ሚኒስትር