አዋጅ ቁጥር ፬፻፵፪/፲፱፻፺፯ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ክንውን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

አዋጅ ቁጥር ፬፻፵፪/፲፱፻፺፯ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ክንውን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ

አዋጅ ቁጥር ፬፻፵፪/፲፱፻፺፯
የማዕከላዊ ስታስቲክስ ክንውን ለማቋቋም
የወጣ አዋጅ

የአገሪቱን የስታቲስቲክስ ክንውን በተቀላጠፈና በተቀናጀ መንገድ በማደራጀት ወቅታዊና አስተማማኝ ስታቲስቲካዊ መረጃዎችን ለኢኮኖሚያዊና ለማኀበራዊ ልማት ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል፤ ለምርምርና ቁጥጥር፤ ለፖሊሲ ቅየሳና ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች በሚያገለግሉበት ሁኔታ አሰባስቦ አቀነባብሮና ተንትኖ ለተጠቃሚዎች ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
ከአገሪቱ የስታስቲክስ የዕድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣም የስታቲስቲክስ መረጃ ሰጪዎችን፣ የመረጃ አመንጪዎችና ተጠቃሚዎችን እንደዚሁም የባለሥልጣኑንና የሠራተኞቹን ኃላፊነትና ግዴታ የሚወስን ሕገ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ ፶፭/፩/ መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡
፩. አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ “የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር     ፬፻፵፪/፲፱፻፺፯” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ትርጓሜ
የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም ካልሰጠው በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፣
፩. “ሚኒስቴር” ወይም “ሚኒስትር” ማለት እንደቅደም ተከተሉ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ወይም ሚኒስትር ነው፡፡
፪. “ባለሥልጣን” ማለት የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለሥልጣን ነው፤
፫. “ስታስቲክስ” የሚለው በነጠላ ትርጉም እውነታዎችን የመሰብሰብና የመተንተን ሳይንሳዊ የአጠናን ስልትን ሲመለከት በብዙ ትርጉሙ ደግሞ ዕውነታዎችን የሚገልፁ አሃዛዊ መረጃዎችን የሚያመለክት ነው፤
፬. “ውህብን” ማለት በቆጠራ ወይም በመለካት የተሰበሰበ አሃዛዊ የመረጃ ክምችት ነው፤
፭. “ቆጠራ” ማለት ወሰኑ በውል በታወቀና በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ በኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊና ዲሞግራፊያዊ ዘርፎች ላይ የሚደረግ አጠቃላይ ወይም ሙሉውን የሚሸፍን ቆጠራን በማካሄድ መሠረታዊ መረጃዎችን የመሰብሰብዘ የማጠናቀር፣ የመገምገምና ውጤቱንም ለተጠቃሚዎች የማሠራጨት ተግባር ነው፤
፮. “የናሙና ጥናት” ማለት መረጃ ከሚፈልግበት ከጠቅላላው ውስጥ በከፊል ወይም የሚያስፈልገውን ያህል በመምረጥ በየትኛውም የኢኮኖሚያዊ፣ የማኀበራዊና የዲሞግራፊያዊ ዘርፎች ወካይ የሆኑ መረጃዎች የመሰብሰብና በዚሁም መሠረት የማጠናቀር፣ የመገምገምና ውጤቱንም ለተጠቃሚዎች የማሰራጨት ተግባር ነው፤
፯. “የማያቋርጥ ምዝገባ” ማለት የአስተዳደር ክፍፍልን ተከትሎ በሀገር አቀፍ፤ በክልል ወይም በአነስተኛ የአስተዳደር እርከን ደረጃ በሕጋዊ የማያቋርጥ ምዝገባ ሥርዓት የወሳኝ ኩነቶችን ወይም የኢኮኖሚና የማህበራዊ ድርጅቶችን ተከታታይነት ባለው ሁኔታ የመመዝገብ ተግባር ነው፤
፰. “አስተዳደራዊ መዛግብት” ማለት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወይም ተቋሞች ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከዕለት ተዕለት ሥራቸው የሚመነጩ መረጃዎችን በማጠናቀርና በማቀናበር የሚያዘጇጋቸው ሰነዶች ናቸው፣
፱. “ሀገራዊ የስታቲስቲክስ ፕሮግራም” ማለት የባለሥልጣኑ የሥራ መመሪያ ሰነድ ሆኖ እንዲያገለግል በየተወሰነ ጊዜ የሚዘጋጅ ሕጋዊ የስታስቲክስ ዕቅድና መርሃ ግብር ነው፤
፲. “ሀገር አቀፍ ባህርይ ያለው ስታቲስቲክስ” ማለት ወካይ በሆነ መልኩ ከመስክ ተሰብስቦ ሲጠቃለል በአገሪቱ ከተሞች ወይመ ገጠር ወይም በአገር ደረጃ ውጤት የሚያስገኝ መረጃ ማለት ነው፡፡
፲፩. “መደበኛ ስታቲስቲክስ” ማለት በባለሥልጣኑ መደበኛ ስታቲስቲክስ ተብሎ የተወሰነ ነው፡፡
፲፪. “ክልል” ማለት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፵፯ የተጠቀሰው ክልል ሲሆን ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም ሲባል የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደሮችንም ይጨመራል፤
፲፫. “የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም ተቋም” ማለት የፌዴራል ወይም የክልል መንግሥት አካል ሲሆን የፌዴራል ወይም የክልል መንግሥት የልማት ድርጅትን ይጨምራል፤
፲፬. “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፡፡

፫. የተፈጻሚነት ወሰን
፩. ይህ አዋጅ ኢኮኖሚያዋ፣ ማኀበራዊና ዲሞግራፊያዊ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማጠናቀርና በማሰራጨት ተግባር ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል፤
፪. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) ቢኖርም ይህ አዋጅ የአገር መከላከያና የድኀንነት ጉዳዮችን በተመለከተ በሚያዙ ሚስጢራዊ መረጃዎች ላይ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡

፬. መቋቋም
፩. የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባለሥልጣን (ከዚህ በኋላ “ባለሥልጣን” እየተባለ የሚጠራ) በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው ራሱን የቻለ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሆኖ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፤
፪. ባለሥልጣኑ ተጠሪነቱ ለሚኒስቴሩ ይሆናል፡፡

፭. ዋና መሥሪያ ቤት
የባለሥልጣኑ ዋና መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ሆኖ እንደአስፈላጊነቱ በማናቸውም ሥፍራ ቅርንጫፍ ሊኖረው ይችላል፡፡

፮. የባለሥልጣኑ ዓላማ
የባለሥልጣኑ ዓላማ፤
፩. በቆጠራ፣ በናሙና ጥናት፣ በማያቋርጥ ምዝገባና ከአስተዳደር መዛግብት የተሰበሰቡ የኢኮኖሚያዊ፣ የማኀበራዊና የዲሞግራፊያዊ የስታቲስቲክስ መረጃዎችን በተቀናጀ አሠራር ሰብስቦ፣ አቀነባብሮና ተንትኖ ለተጠቃሚዎች የማሠራጨት፣ እና
፪. የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ሌሎች አካላት የስታቲስቲክስ መዝገብ አያያዝ፣ የሚያቋርጥ የምዝገባ አሠራርና የራፖርት ሥርዓት እንዲዘረጉ የቴክኒክ ምክርና ድጋፍ የማድረግ፣ እንዲሁም ስለማያቋርጥ ምዝገባ፣ የአስተዳደራዊ መዛግብት መረጃ ክምችቶች በመፍጠርና የአያያዝ ሥርዓት በማደራጀት ምክርና ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል አቅም የመገንባት፣ ይሆናል፡፡

፯. የባለሥልጣኑ ሥልጣንና ተግባር
ባለሥልጣኑ የአገሪቱ የስታቲስቲክስ ማዕከል ሆኖ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባሮች ይኖሩታል፤
፩. የስታቲስቲክስ መረጃዎችን በቆጠራ፣ በናሙና ጥናቶች፣ በማያቋርጥ መዝገባና ከአስተዳደር መዛግብት ይሰበስባል፤ እንዲሰበሰቡም ያደርጋል፤ የተሰበሰቡ መረጃዎችን ያደራጃል፤ ያቀነባብራል፤ ይተነትናል፣ በጽሑፍ ያወጣል፣ ያሰራጫል፤
፪. በየወቅቱ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የስታቲስቲክስ ፕሮግራሞችን ያዘጋጃል፤ የበጀት ረቂቅ ያቀርባል፤ ሲፈቀድም በሥራ ላይ ያውላል፤ ሌሎች የመንግሥት መ/ቤቶችና ተቋማትም በሥራ ላይ ማዋላቸውን ያረጋግጣል፤
፫. ከመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ወይም ተቋማት ወይም የግል ድርጅቶች በሚቀርብለት ጥያቄ መሠረት የስታቲስቲክስን ሥራ በተመለከተ የምክር አገልግሎት ይሰጣል፤
፬. የስታቲስቲክስ አሠራር ዘዴዎችን በተመለከተ የጥናትና ምርምር ተግባር ያከናውናል፣ የተገኙ ውጤቶችንም በሥራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል፤

፳፫. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ ከሚያዝያ ፲፪ ቀን ዓ.ም. ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.
ግርማ ወልደጊዮርጊስ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ
ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት