አዋጅ ቁጥር ፫፻፺፭/፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

አዋጅ ቁጥር ፫፻፺፭/፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ

አዋጅ ቁጥር ፫፻፺፭/፲፱፻፺፮
ይቅርታ የሚፈጸምበትን ሥነ ሥርዓት ለመደንገግ የወጣ አዋጅ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፸፩/፯/ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት በሕግ መሠረት ይቅርት እንደሚያደርግ የተደነገገ በመሆኑ፤
ይቅርታን በተመለከተ በወንጀል ሕግና በሌሎች ሕጎች የተደነገጉትን ከሕግ መንግሥቱ ጋር በማጣጣም ይቅርታ የሚሰጥበትን ሥነ ሥርዓት በሕግ መደንገግ በማስፈለጉ፤ እና አንቀጽ ፶፭/፩/
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፸፩/፯/ እና አንቀጽ ፶፭/፩/ መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ
ጠቅላላ
፩. አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ “የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ፫፻፺፭/፲፱፻፺፮”+ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ትርጓሜ
በዚህ አዋጅ ውስጥ፣
፩. “ምክር ቤት” ማለት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፤
፪. “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፡፡
፫. “ፍርድ” ማለት በወንጀል ጉዳይ በፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሣኔ የተወሰነ ዋና ቅጣት፣ ተጨማሪ ቅጣት ወይም የጥንቃቄና ጥበቃ ውሣኔ ነው፤
፬. “የይቅርታ ጥያቄ” ማለት አንድ ፍርድ በሙሉ ወይም በከፊል ቀሪ እንዲሆን ወይም የቅጣቱ አፈጻጸምና ዓይነት በቀላል ሁኔታ እንዲፈጸም የሚቀርብ ጥያቄ ነው፤
፭. “ፍርድ ቤት” ማለት ማለት በሕግ የተቋቋመ የፌዴራል ፍርድ ቤት ሲሆን በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 78/2/ መሠረት የፌዴራል ጉዳዮችን የሚያስተናግድ የክልል ፍርድ ቤትን እና የሞት ቅጣት ውሣኔ የሰጠ የክልል ፍ/ቤትን ይጨምራል፡፡
፮. “ፕሬዚዳንት” ማለት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ነው፤
፯. “ይቅርታ ጠያቂ” ማለት ይቅርታ የተጠየቀበት ፍርድ የሚመለከተው ሲሆን ወንጀሉ ግብረ አበር ወይም ወይም አባሪ ያለበት ከሆነ ግበረ አበሩን ወይም አባሪውን ይጨምራል፡፡

ክፍል ሁለት
ስለይቅርታ አስፈጻሚ አካላት
፫. የቦርድ መቋቋም
፩. የይቅርታ ጉዳዮችን የሚመረምርና ለፕሬዚዳንቱ የውሣኔ ሃሣብ የሚያቀርብ የይቅርታ ቦርድ /ከዚህ በኋላ “ቦርድ” እየባለ የሚጠራ/ ተቋቁሟል፡፡
፪. የቦርዱ ተጠሪነት ለፕሬዚዳንቱ ይሆናል፡፡

፬. የቦርዱ ሥልጣንና ተግባር
ቦርዱ የሚከተሉት ስልጣን እና ተግባር ይኖሩታል፡፡
፩. በሕግ አግባብ የሚቀርቡለትን የይቅርታ ጥያቄዎች በመመርመር ቅጣቱ በቅድሙ ሁኔታ ወይም ያለቅድመ ሁኔታ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲሻር ወይም የቅጣቱ አፈጻጸምና ዓይነት በቀላል ሁኔታ እንዲፈጸም ወይም ይቅርታ የማያሰጥ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ቅጣቱ እንዲፀና ለፕሬዚዳንቱ የውሣኔ ሃሣብ ያቀርባል፤
፪. እንደአስፈላጊነቱ ክሱን የተከታተለውን ዐቃቤ ሕግ እና ሌላ ማንኛውም ባለሥልጣን ወይም ግለሰብ እንዲቀርብ ወይም በጽሑፍ ሃሣብ እንዲያቀርብ ያደርጋል፤
፫. በፕሬዚዳንቱ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ይቅርታ የሚሰጣቸው ሰዎች ቅድመ ሁኔታውን አላሟሉም ወይም ጥሰዋል የሚል ክስ ሲቀርብባቸው ጉደዩን መርምሮ ለፕሮዚዳንቱ የውሣኔ ሃሣብ ያቀርባል፤
፬. የይቅርታ ጥያቆዎች አፋጣኝ መልስ የሚያኙበትን መንገድ በማስጠናት ተግባራዊ ያደረጋል፤
፭. ሌሎች በሕግ የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፡፡

፭. የቦርዱ አባላት
ቦርዱ የሚከተሉት አባላት ይኖሩታል፡፡
፩. የፍትሕ ሚኒስትር . . . . ሰብሳቢ
፪. በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚመደብ ከፍተኛ ሐኪም . . . . አባል
፫. በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመደብ ከፍተኛ የማሕበራዊ ጉሮ ጠቢብ . አባል
፬. የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተወካይ . . . . . . . . . አባል
፭. የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ተወካይ . . . . . . አባል
፮. እንደአስፈላጊነቱ በቦርዱ አቅራቢነት በፕሮዚደንቱ የሚመረጡ ኅብረተሰቡን የሚወክሉ ከሁለት የማይበለጡ ሰዎች . . . . . . . . . . . . . . አባል

፮. የቦርዱ ሰብሳቢ ሥልጣንና ተግባር
የቦርዱ ሰብሳቢ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባር ይኖሩታል፤
፩. የቦርዱን ስብሰባ በሊቀመንበርነት ይመራል፤
፪. ይቅርታ የተደረገላቸው ወይም የተከለከሉ ሰዎችን በተመለከተ የፕሬዚዳንቱን ውሣኔ በቦርዱ ጽሕፈት ቤት በኩል ለሚመለከታቸው አካላት እንዲተላለፍ ያደርጋል፤
፫. ስለቦርዱ የሥራ አካሄድ በየ፮ ወሩ ለፕሬዚዳንቱ ሪፖርት ያቀርባል፤
፬. በፕሬዚዳንቱ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል፡፡

፯. የቦርዱ የስብሰባ ሥነ ሥርዓት
፩. ከቦርዱ አባላት መካከል ሁለት ሦስተሀኛው ከተገኙ ምልዕተ ጉባኤ ይኖራል፤
፪. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ቢኖርም፣ የይቅርታ ጥያቄ የቀረበበት ጉዳይ አጣዳፊ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ከአባላቱ ከግማሽ በላይ ከተገኙ ስብሰባው ሊካሄድ ይችላል፤
፫. ቦርድ ውሣኔውን በአብላጫ ድምጽ ያሳልፋል፤ ድምጽ እኩል ለእኩል በተከፈለ ጊዜ የቦርዱ ሰብሳቢ የተቀበለው ሃሣብ የቦርድ የውሣኔ ሃሣብ ይሆናል፡፡ የአነስተኛው ድምጽ ሃሣብም በሪፖርት መልክ ይቀርባል፤
፬. አስቸኳይ ስበሰባ መጥራት ሲያስፈልግ የቦርዱ ሰብሳቢ ጥሪ ሊያደርግ ይችላል፤
፭. የቦርዱ የራሱ የስብሰባ ሥነ ሥርዓት ደንብ ይኖረዋል፡፡

፰. የቦርዱ ጽሕፈት ቤት
፩. የፍትሕ ሚኒስቴር አካል የሆነ የይቅርታ ቦርድ ጽሕፈት ቤት /ከዚህ በኋላ ጽሕፈት ቤት እየተባለ የሚጠራ/ ይኖራል፤
፪. ጽሕፈት ቤቱ የሚከተሉት ተግባርና ኃላፊነት ይኖሩታል፤
ሀ) የይቅርታ ማመልከቻዎችን ይቀበላል፣ አስፈላጊ የሆኑ መዛግብቶችንና ሰነዶችን ያሰብስባል፤
ለ) የብርዱን መዛግብትና ሠነዶች በአግባቡ ይይዛል፣ ይጠብቃል፤
ሐ) በቦርዱ የውሣኔ ሃሣብ የተሰጠባቸውና በፕሬዚዳንቱ የጸደቁትን ወይም ሳይፀደቁ የቀሩትን የውሣኔ ሃሣቦች በአግባቡ ይይዛል፣ ይጠብቃል፣ ስትትስቲክስ ያዘጋጃል፤
መ) ሞዴል የይቅርታ የምስክረ ወረቀት አዘጋጅቶ እንዲፀድቅ ለቦርዱ ያቀርባል፣ ይቅርታ ለተደረገላቸው ሰዎች በፀደቀው የይቅርታ ሠርተፊኬት አስፈላጊውን መረጃ እየሞላ ለቦርዱ ሰብሳቢ ያቀርባል፤
ሠ) ይቅርታ የተሰጠበትን ወም የተከለከለበትን ውሣኔ በመዝገብ ያሰፍራል፣ መዝገቡንም ይጠብቃል፣ ቦርዱ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት መዝገቡን ለሕዝብ ክፍት ያደርጋል፤
ረ) ሌሎች ከይቅርታ ጉዳዮች ጋር ተዛማጅነትያላቸውን ሥራዎች ያከናውናል፡፡

፱. የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተግባርና ኃላፊነት
የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሚከተሉት ተግባርና ኃላፊነት ይኖሩታል፤
፩. ጽሕፈት ቤቱን ይመራል፣ ይቆጣጠራል፤
፪. ለቦርዱ አባላት የስብሰባ ጥሪ ያስተላልፋል፣ ለቦርዱ ስብሰባ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች መድረሳቸውን ያረጋግጣል፤
፫. በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፲፮/፬/ መሠረት የተሰጠውን ውሣኔ መሠረት በማድረግ ለሚመለከተው አካል ትዕዛዝ ያስተላልፋል፤
፬. የቦርዱ ፀሐፊ ሆኖ ያገላግላል፤
፭. ከቦርዱ ሰብሳቢ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባሮች ያከናውናል፡፡

፲. የፕሬዚዳንቱ ሥልጣንና ተግባር
ፕሬዚዳንቱ፣
፩. በቦርዱ የውሣኔ ሃሣብ መሠረት ወይም በራሱ ምክንያት ይቅርታ ለመሰጠት ወይም ለመከልከል ይችላል፤
፪. በቅድመ ሁኔታ ይቅርታ ተደርጎላቸው ቅድመ ሁኔታውን ያላሟሉትን ወይም የጣሱትን በተመለከተ ከኮርድ የሚቀርብለትን የውሣኔ ሃሣብ መሠረት በማድረግ ይቅርታውን ለመሠረዝ ይችላል፡፡

ክፍል ሦስት
ስለይቅርታ ጥያቄ አቀራረብ፣ ስለ ይቅርታ መሠረዝና ማስረዳት
ንዑስ ክፍል አንድ
ስለ ይቅርታ ጥያቄ አቀራረብ
፲፩. የይቅርታ ዓላማ
የይቅርታ ዓላማ የሕዝብን ደኅንነትና ጥቅም የማስከበር ነው፡፡

፲፪. ስለይቅርታ ጥያቄ አቀራረብ
፩. በወንጀል ጉዳይ በፍርድ ቤት ተከሶ የመጨረሻ ፍርድ የተፈረደበት ማንኛውም ሰው የተወሰነው ፍርድ በሕግ ይቅርታ የሚያስከለክል ካልሆነ በቀር የይቅርታ ጥያቄውን ራሱ ወይም በባለቤቱ፣ በቅርበ ዘመዶቹ፣ በወኪሉ ወይም በጠበቃው አማካይነት ማቅረብ ይችላል፡፡
፪. ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ይቅርታ ሊደረግላቸው የሚገባቸውን ሰዎች በመምረጥ በበኩላቸው የይቅርታ ጥያቅ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ መሥሪያ ቤቶቹ የይቅርታ ጥያቄ ለማቅረብ የወሰኑ እንደሆነ የይቅርታ መጠየቂያውን ደብዳቤ ቅጂ ይቅርታ ለተጠየቀለት ሰው እንዲደርሰው ማድረግ ይኖርባቸዋል፤
፫. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፪ በተደነገገው አኳኋን ይቅርታ እንዲደረግለት የተጠየቀለት ሰው ይቅርታውን ለመቀበል የማይፈለግ የሆነ እንደሆነ የይቅርታ መጠየቂያው ደብዳቤ ቅጂ በደረሰው በአሥራ አምስት ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ በጽሑፍ ለቦርዱ ማስታወቅ አለበት፤
፬. ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በቀር፣ ከላይ በንዑስ አንቀጽ ፫ በተደነገገው የጊዜ ገደብ ውስጥ ይቅርታ እንዲደረግለት የቀረበለትን ጥያቄ አለመቀበሉን ካላስታወቀ ይቅርትውን እንደተቀበለው ይቆጠራል፤ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት አጋጥሞት ለማስታወቅ ያልቻለ ሰው ያጋጠመውን ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ገልጾ ችግሩ ከተወገደለት ዕለት አንስቶ ባሉት አሥራ አምስት ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ ማስታወቅ አለበት፤
፭. ይቅርታ የተጠየቀበት ፍርድ በሕግ ይቅርታ የማያሰጥ የሆነ እንደሆነ፣ ፍርድ በሕግ ይቅርታ የማያሰጥ መሆኑን ይቅርታ ጠያቂው አንዲያውቀው ይደረጋል፤
፮. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፩/ እና /፪/ መሠረት የይቅርታ ጥያቄ የቀረበበት ፍርድ ግብረ አበር ወይም አባሪ ያለበት የሆነ እንደሆነ የይቅርታ ጥያቄው እነርሱን የሚመለከት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

፲፫. የይቅርታ ጥያቄው ማመልከቻ መያዝ ያለበት ዝርዝር ነገሮች
የይቅርታ ጥያቄ ማመልከቻ ይቅርታ ጠያቂውን በተመለከተ በተለይ የሚከተሉት መረጃዎች መያዝ ይኖርበታል፤
፩. ሙሉ ስም /እስከነአያት/፣ ዕድሜ፣ የእናት ሙሉ ስም እና አድራሻ፤
፪. የመንግሥት ሠራተኛ የነበረ ከሆነ የኃላፊነቱን ደረጃ፤
፫. ወንጀሉን ከመፈጸሙ በፊት ለአምስት ዓመታት ይኖርበት የነበረው ቦታ ሙሉ አድራሻ፤
፬. የተከሰሰበት የወንጀል ድርጊት፣ ተጠያቂ የሆነበት ወንጀልና የተፈረደበት ፍርድ፣ የፈረደውን ፍርድ ቤት፣ የፍርዱ አፈፃፀም የሚገኝበት ደረጃ እና የክሱ መዝገብ ቁጥር፤
፭. የደንብ መተላለፍን ሳይጨምር ቀድሞ ተከሶ የተፈረደበት የወንጀል ድርጊት ካለ የወንጀሉን ዓይነት፣ የተወሰነውን ቅጣትና የፍርዱን አፈጻጸም፤
፮. በማረሚያ ቤት፣ በፀባይ ማረሚያ፣ በግዞት ወይም በጽኑ ግዞት ስፍራ የሚገኝ ከሆነ የሚገኝበትን ተቋም ወይም ሥፍራ፤
፯. ይቅርታ ሊደረግለት የሚገባበትን ምክንያት፤
፰. የይቅርታ ጥያቄውን የሚደግፉ በአባሪነት የተያያዙ መረጃዎች ካሉ ዝርዝራቸውን፣
፱. ከይቅርታ ጥያቄው ማመልከቻ ጋር ያልተያያዙት መረጃዎች ካሉ መረጃዎቹ የማገኙበትን ሥፍራ፤
፲. የይቅርታ ጥያቄውን የሚደግፉ በሥጋ ወይመ በጋብቻ ከጠያቂው ጋር ዝምድና የሌላቸው ከሦስት ያልበለጡ ግለሰቦች እንዲሁም ድርጅቶችና ማኅበራት ሙሉ ስም እና አድራሻ እና ይቅርታውን የሚደግፉበት ምክንያት፣
፲፩. ከመንግሥት የሚፈልግ ዕዳ መኖር አለመኖሩን፣
፲፪. ቀደም ሲል ይቅርታ ተደርጎ እንደሆነ ወይም የይቅርታ ጥያቄ ቀርቦ ውደቅ ሆኖ እንደሆነ ውሳኔው የተሰጠበት ቀን፣
፲፫. ይቅርታ ጠያቂው በሌላ ሰው ስም የሚያመለክት ከሆነ ይህንኑ ለመፈጸም መብት የሚሰጠውን ሕጋዊ ምክንያት፡፡
፲፬. የይቅርታ ጥያቄ የማቅረቢያ ጊዜ
በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፲፪ መሠረት የይቅርታ ጥያቄ የሚያቀርብ ሰው የይቅርታ ጥያቄውን፤
፩. ፍርዱ ከተሰጠ በኋላ በማናቸውም ጊዜ፤
፪. የይቅርታ ጥያቄ አቅርቦ ጥያቄው ወድቅ ከተደረገ ከስድስት ወር በኋላ፤
፫. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፪ የተደነገገው ቢሃርም፣ በአፋጣኝ ታይቶ ምላሽ ማግኘት ያለበት የይቅርታ ጥቄ ከሆነና ከቦርዱ አባላት በሶስት አራተኛ ድምጽ ከተደገፈ ስድስት ወር ሳይጠበቅ በማናቸውም ጊዜ ማቅረብ ይችላል፡፡

፲፭. የይቅርታ ጥያቄን ማመልከቻ ስለመመርመር
የቦርዱ የይቅርታ ጥያቄ ሲቀርብለት ከዓቃቤ ሕግ መዝገብ ወይም ከፍርድ መዝገብ በተጨማሪነት በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፲፫ የተመለከቱትን መረጃዎች እንዲሁም ከማናቸውም ሰው የሚቀርቡለትን ማስረጃዎችንና ጥቆማዎችን እንዲሁም በራሱ የሚያገኛቸውን ማናቸውንም የይቅርታ ጥያቄውን የሚደግፉ ወይም የሚቃወሙ ማስረጃዎች መመርመር ይኖርበታል፡፡

ንዑስ ክፍል ሁለት
ይቅርታን ስለመሰረዝና ስለማስረዳት
፲፮. ይቅርታን ስለመሰረዝ
፩. የይቅርታ ውሳኔ ለይቅር ተባዩ ከመድረሱና ተቀባይነት ከማግኘቱ በፊት የይቅርታውን ውሳኔ ለማሰረዝ የሚያስችሉ ምክንያቶች ካሉ የይቅርታው ውሳኔ ሊሰረዝ ይችላል፤
፪. የይቅርታ ውሳኔ ለይቅር ተባዩ ከደረሰና ተቀባይነት ካገኘ በኋላ የይቅርታ ውሳኔ በማጭበርበር ወይም በማታለል የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ የይቅርታ ውሣኔው ዋጋ አይኖረውም፤
፫. በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ይቅርታ ቅድመ ሁኔታው መጣሱ ከተረጋገጠ የይቅርታ ውሳኔው ዋጋ አይኖረውም፤
፬. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) እና (፫) መሠረት ውሳኔው ከተሰረዘ ይቅር ተባዩ የይቅርታ ውሣኔ ከመስጠቱ በፊት ወደነበረው ቦት እንዲመለስ ቦርዱ ይወስናል፡፡

፲፯. ይቅርታን ሲሰረዝ መሟላት ያለበት ሥነ ሥርዓት
፩. ይቅርታ ለማሰረዝ የሚያበቃ ምክንያት ከተገኘ፣ ምክንያቱ በግልጽና ይቅርታ የተደረገለት ሰው በሚገባው ቋንቋ በጽሑፍ ተዘጋጅቶ ለይቅር ተባዩ እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡
፪. ይቅር ተባዩም ጽሑፉ በደረሰው ቢበዛ በሃያ ቀናት ውስጥ መልሱን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

፲፰. ይቅርታን ስለማስረዳት
፩. ማንኛውም ይቅር ተባይ ይቅርታ የደረገለት መሆኑን የሚያረጋግጠው በዋናው የየቅርታ የምስክር ወረቀት ነው፤
፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተደነገገው ቢኖር/፣ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ዋናው የይቅርታ ምስክር ወረቀት ለመጥፋቱ አሳማኝ ማስረጃ ያለው ይቅር ተባይ ይቅርታ የተደረገለት መሆኑን ትክክለኛነቱ በተረጋገጠ የይቅርታ ምስክር ወረቀት ቅጂ ማረጋገጥ ይችላል፡፡

ክፍል አራት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
፲፱. ተፈጻሚነት ስለማይኖራቸው ሕጎች
ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረን ማናቸውም ሕግ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡

፳. የመተባበር ግዴታ
ማንኛውም ሰው ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡

፳፩. አዋጁ የሚጸናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ በፌዴራል በነጋሪት ጋዜጣ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ሚያዝያ ፱ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓ.ም.
ግርማ ወልደጊዮርጊስ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት

የኢትየጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ
አሥረኛ ዓመት ቁጥር ፴፮ አዲስ አበባ መጋቢት ፲፮ ቀን ፲፱፻፺፮