አዋጅ ቁጥር ፪፻፲፯/፲፱፻፺፪ ዓ.ም. የትምህርት ቤቶችን አመራር አስተዳደር ለማጠናከር የወጣ (ማሻሻያ) አዋጅ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

አዋጅ ቁጥር ፪፻፲፯/፲፱፻፺፪ ዓ.ም. የትምህርት ቤቶችን አመራር አስተዳደር ለማጠናከር የወጣ (ማሻሻያ) አዋጅ

አዋጅ ቁጥር ፪፻፲፯/፲፱፻፺፪ ዓ.ም.
የትምህርት ቤቶን አመራርና አስተዳደር ለማጠናከር የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የወጣ አዋጅ

የግል ትምህርት ቤቶችን የሕዝብ ሀብት ለማድግ በወጣው አዋጅ መሠረት የሕዝብ ሀብት የተደረጉትን ትምህርት ቤቶች አመራርና አስተዳደር አግባብ ካላቸው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት አካላት አወቃቀር ጋር እንዲጣጣም ማድረግ በማስፈለጉ፤
የሕዝብ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አሰጣጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊኖር የሚገባውን የትምህርት ደረጃ የጠበቀና ትምህርት ቤቶቹ በሚገኙበት ብሔራዊ ክልል ወይም የከተማ መስተደድር የተዘረጋውን የትምህርት ሥርዓት የተከተለ እንዲሆን በማስፈለጉ፤
በሕዝብ ትምህርትቤቶች የሚሰጠውን የትምህርት ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችል፣ የትምህርት ቤቶቹን መምህራን መብትና ጥቅም የሚያስከብር እንዲሁም ተጠቃሚ የሆነው ኅብረተሰብ የተሻለ  አገልግሎት የሚያገኝበት አደረጃጀት እንዲኖር ማድረግ በማስፈለጉ፤
የትምህርት ቤቶችን አመራርና አስተዳደር ለማጠናከር የወጣውን አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፶፭ (፩) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

፩. አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ “የትምህርት ቤቶችን አመራር አስተዳደር ለማጠናከር የወጣ (ማሻሻያ) አዋጅ ፪፻፲፯/፲፱፻፺፪” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ማሻሻያ
፩. የትምህርት ቤቶችን አመራርና አስተዳደር ለማጠናከር በወጣው አዋጅ ቁጥር ፪፻፷/፲፱፻፸፮፤
ሀ/ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች አመራርና አስተዳደርን በተመለከተ ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሚኒስትሩ የተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ተሽሮ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፫ ሥራ ለተገለጹት የመስተዳድር አካላት ተላልፎአል፡፡
ለ/ ከአንቀጽ ፲፬-፳፭፣ አንቀጽ ፳፰፣ ፳፱፣ እና ፴ በዚህ አዋጅ ተሽረዋል፡፡
፪. የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን አመራርና አስተዳደር ለማጠናከር በወጣው አዋጅ ቁጥር ፪፻፷/፲፱፻፸፮ መሠረት የወጣው የሕዝብ ትምህርት ቤቶች የሠራተኛ ጉዳይ ደንብ (የሕግ ክፍል ማስታወቂያ ቁጥር ፹፭/፲፱፻፸፮) ተሽሯል፡፡

፫. ደንብ የማውጣት ሥልጣን
የሕዝብ ት/ቤቶች የሚኙባቸው የብሔራዋ ክልላዊ መንግሥታት ምክር ቤቶች፣ እና ተጠሪነታቸው ለፌዴራሉ መንግሥት የሆኑ የከተማ መስተዳድር ምክር ቤቶች በየክልላቸው የሚገኙ የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን አመራርና አስተዳደር፣ የትምህርት አሰጣጥ፣ የመምህራንን አቀጣጠርና አስተዳደር የሚመለከቱ ደንቦችን ያወጣሉ፣ ደንቦቹ በሥራ ላይ መዋላቸውንም በበላይነት ይቆጣጠራሉ፡፡

፬.  መመሪያ የማውጣት ሥልጣን
የብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት እንዲሁም የከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች የየክልሎቻቸው ምክር ቤቶች የሚያወጧቸውን ደንቦች ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆነ መመሪያዎችን ማውጣት ይችላሉ፡፡

፭.  ተጠሪነት
በማንኛውም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ክልል ውስጥ የሚገኙ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ተጠሪነት ት/ቤቶቹ በሚገኙበት ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ ወይም የከተማ መስተዳድር ለሚገኘው አግባብነት ላለው የትምህርት ቢሮ አካል ይሆናል፡፡

፮.  መብትና ግዴታ ስለማስተላለፍ
በአዋጅ ቁጥር ፪፻፷/፲፱፻፸፮ መሠረት ተቋቁመው የነበሩት የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ኮሚቴዎች መብትና ግዴታ በዚህ አዋጅ መሠረት በሚወጡት ደንቦች የሕዝብ ትምህርት ቤቶቹን ለማስተዳደር ለሟቋቋሙት አካላት ተላልፏል፡፡

፯.  የመሸጋገሪያ ድንጋጌ
በአዋጅ ቁጥር ፪፻፷/፲፱፻፸፮ መሠረት የተቋቁሙት የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ኮሚቴዎች በዚህ አዋጅ  አንቀጽ ፫ ውስጥ በተደነገገው መሠረት የሕዝብ ት/ቤቶቹ አስተዳደር ኃላፊነት የሚሰጣቸው አካላት እስኪቋቋሙ ድረስ ሥራውን በነበረው አሠራር መሠረት የሚካሔድ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

፰.  ተፈጻሚነት የሌላቸው ሕጎች
ማናቸውም ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ ሕጎች እና አሠራሮች በዚህ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡

፱. አዋጁ የሚጸናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ ከሰኔ ፳፱ ቀን ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡
አዲስ አበባ ሰኔ ፳፱ ቀን ፲፱፻፺፪ ዓ.ም.
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት
የኢትየጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ
ስድስተኛ ዓመት ቁጥር ፵፰ አዲስ አበባ ሰኔ ፳፱ ቀን ፲፱፻፺፪
በኢትየጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠባቂነት የወጣ