አዋጅ ቁጥር ፻፳፫/፲፱፻፺ ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊት (ማሻሻያ) አዋጅ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

አዋጅ ቁጥር ፻፳፫/፲፱፻፺ ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊት (ማሻሻያ) አዋጅ

አዋጅ ቁጥር ፻፳፫/፲፱፻፺
የመከላከያ ሠራዊት አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ

የመከላከያ ሠራዊት አዋጅን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፶፭(፩) እና (፯) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

፩. አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ “የመከላከያ ሠራዊት (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር ፻፳፫/፲፱፻፺” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ማሻሻያ
የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር ፳፯/፲፱፻፹፰ እንደሚከተለው ተሻሽሏል፤
፩. የአንቀጽ ፱ ንዑስ አንቀጽ (፪) ተሠርዞ፤ የዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፫) እና (፬) እንደቅደም ተከተላቸው ንዑስ አንቀጽ (፪) እና (፫) ሆነዋል፡፡
፪. የአንቀጽ ፲፫ ንዑስ አንቀጽ (፫) ተሠርዞ፤ በሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ (፫) ተተክቷል፤
“፫. በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፱ ንዑስ አንቀጽ (፩) እና (፪) የተመለከቱት የሥራ መሰናበቻ ዕድሜ ጣራዎች ለጡረታ ሕግ አፈጻጸም የጡረታ መገለያ ዕድሜ ሆነው ይቆጠራሉ፡፡”
፫. አንቀጽ ፲፭ ተሠርዞ በሚከተለው አዲስ አንቀጽ ፲፭ ተተክቷል፡፡
“፲፭. ሜዳይ ኒሻንና ሽልማት
ማንኛውም የሠራዊቱ አባል በዚህ አዋጅ ወይም አግባብ ባላቸው ሌሎች ሕጐችና መመሪያዎች መሠረት ለፈጸመው አገልግሎትና ጀግንነት እንዲሁም ለአዲስ ግኝት ወይም የፈጠራ ሥራ ሜዳይ ኒሻን ወይም ሽልማት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡”
፬. አንቀጽ ፳፩ ተሠርዞ በሚከተለው አዲስ አንቀጽ ፳፩ ተተክቷል፡፡
“፳፩. የግዴታ አገልግሎት
አንድ የሠራዊት አባል ልዩ ሥልጠና ወይም ትምህርት እንዲያገኝ ከተደረገ ሥልጠናውን ወይም ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ሥልጠናው ወይም ትምህርቱ የወሰደውን ጊዜ እጥፍ የማገልገል ግዴታ አለበት፤ ሆኖም የዚህ ዓይነቱ የግዴታ አገልግሎት ከአንድ ዓመት ሊያንስ አይችልም፡፡”
፭. አንቀጽ ፴፫ ተሠርዞ በሚከተለው አዲስ አንቀጽ ፴፫ ተተክቷል፤
“፴፫. ስለምርመራና ክስ አመሠራረት
፩. አንድ ጉዳይ ወታደራዊ ፍ/ቤት ከመቅረቡ በፊት ጥልቅና ገለልተኛ የሆነ ምርመራ መካሄድ አለበት፡፡
፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት አንድ ጉዳይ ለምርመራ እንዳስፈላጊነቱ ለአንድ መርማሪ፣ በቡድን እንዲሠራ ለተመደቡ መርማሪዎች ወይም ለፖሊስ ሊመራ ይችላል፡፡
፫. የምርመራ ውጤቱ ክስ ለመመሥረት የሚያስችል ሆኖ ሲገኝ ጉዳዩ አግባብ ላለው ወታደራዊ ፍ/ቤት ይመራል፤ ክሱን የሚከታተል ዐቃቤ ሕግም ይመደባል፡፡”
፮. ከአንቀጽ ፴፮ ቀጥሎ የሚከተለው አዲስ ክፍል ስድስት ተጨምሯል፤

“ክፍል ስድስት
ሜዳይ፣ ሪባንና የምስክር ወረቀት የሚያስገኙ
ሁኔታዎችና የተሸላሚዎች ልዩ መብቶች
፴፯. ሜዳዮች ሪባንና የምስክር ወረቀት
፩. ለመከለከያ ሠራዊት አባላት የሚሰጡ ሜዳዮች፣ ሪባንና የምስክር ወረቀት የሚከተሉት ናቸው፤
ሀ. የአድዋ ድል ሜዳይ፤
ለ. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ አንደኛ ደረጃ፤
ሐ. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ ሁለተኛ ደረጃ፤
መ. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ ሦስተኛ ደረጃ፤
ሠ. የትግል ተሳትፎ ሜዳይ ባለዘንባባ፤
ረ. የትግል ተሳትፎ ሜዳይ ያለዘንባባ፤
ሰ. የላቀ የሥራ ውጤት ሜዳይ፤
ሸ. የውትድርና አገልግሎት ሜዳይ አንደኛ ደረጃ፤
ቀ. የውትድርና አገልግሎት ሜዳይ ሁለተኛ ደረጃ፤
በ. የውትድርና አገልግሎት ሜዳይ ሦስተኛ ደረጃ፤
ተ. ዓለምአቀፍ የሠላም ማስጠበቅ ሜዳይ፤
ቸ. የአውደ ውጊያ ቁስለኛ ሜዳይ፤
ኀ. የውትድርና አገልግሎት ሪባን፤
ነ. የውጊያ ተሳትፎ የምስክር ወረቀት፡፡

፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተመለከቱት ሜዳዮች፤ ሪባንና የምስክር ወረቀት መጠን፤ ቅርጽና ይዘት በሚኒስትሮች ምክር ቤት መመሪያ ይወሰናል፡፡

፴፰. የአድዋ ድል ሜዳይ
፩. የአድዋ ድል ሜዳይ ወደር የሌለው ጀግንነት በአውደ ውጊያ ለፈጸመ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ወይም የሠራዊት አሀድ ወይም ቡድን የሚሰጥ የመጨረሻ ከፍተኛ የጀግና ሽልማት ነው፡፡
፪. የአድዋ ድል ሜዳይ የተሸለመ ሰው፤
ሀ. በሕይወት ያለ ከሆነ ብር ፳፭ ሺ የአንድ ጊዜ ክፍያ ይሰጠዋል፤ ከሞተም  በጡረታ ሕግ በተመለከተው መጠን መሠረት ለወራሾቹ ብር ፳፭ሺ ይከፈላል፡፡
ለ. በብሔራዊ በዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓት ወቅት ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች በሚዘጋጀው ቦታ ይቀመጣል፤
ሐ. በርዕሰ ብሔሩ የተፈረመ ልዩ የመታወቂያ ወረቀት ይሰጠዋል፤
መ. በትውልድ ሥፍራው ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መንገድ፣ አደባባይ ወይም ሌላ ተመሳሳይ መጠሪያ በስሙ ሊሰየምለት ይችላል፤
፫. የአድዋ ድል ሜዳይ ሁለት ጊዜ የተሸለመ ሰው በፌዴራሉ ዋና ከተማ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መንገድ፣ ድልድይ፣ አደባባይ ወይም ሌላ ተመሳሳይ መጠሪያ በስሙ ሊሰየምለት ይችላል፤ በተጨማሪም መታሰቢያ ሐውልት ሊቆምለት ይችላል፡፡
፬. የአድዋ ድል ሜዳይ ተሸላሚ ለሆነ የሠራዊት አሃድ ወይም ቡድን ብር ፻ ሺ እና በርዕሰ ብሔሩ የተፈረመ ልዩ የምስክር ወረቀት ይሰጠዋል፡፡
፭. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፪ (መ) እና (፫) ለሠራዊት አሃድና ቡድንም ተፈጻሚ ይሆናል፤ ስለሆነም በትውልድ ሥፍራ ምትክ ጀግንነቱ የተፈጸመበት ሥፍራ ይሆናል፡፡
፴፱. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ አንደኛ ደረጃ
፩. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ አንደኛ ደረጃ በተሰለፈበት አውደ ውጊያ የዘወትር ወታደራዊ ግዳጅ አፈጻጸም ከሚጠይቀው በላይ እጅግ በጣም የሚያኮራ ጀግንነት ለፈጸመ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ወይም የሠራዊት አሃድ ወይም ቡድን የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡
፪. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ አንደኛ ደረጃ የተሸለመ ሰው፤
ሀ. በሕይወት ያለ ከሆነ ብር ፲ ሺ የአንድ ጊዜ ክፍያ ይሰጠዋል፤ ከሞተም በጡረታ ሕግ በተመለከተው መጠን መሠረት ለወራሾቹ ብር ፲ ሺ ይከፈላል፤
ለ. በብሔራዊ በዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓት ወቅት ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች በሚዘጋጀው ቦታ ይቀመጣል፤
ሐ. በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የተፈረመ ልዩ የመታወቂያ ወረቀት ይሰጠዋል፡፡
፫. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ አንደኛ ደረጃ ሁለት ጊዜ የተሸለመ ሰው በትውልድ ሥፍራው ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መንገድ፣ አደባባይ ወይም ሌላ ተመሳሳይ መጠሪያ በስሙ ሊሰየምለት ይችላል፡፡
፬. የአውደ ወጊያ ጀግና ሜዳይ አንደኛ ደረጃ ሦስት ጊዜ የተሸለመ ወይም የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ አንደኛ ደረጃ እና የአድዋ ድል ሜዳይ የተሸለመ ሰው በፌዴራሉ ዋና ከተማ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መንገድ፣ አደባባይ ወይም ሌላ ተመሳሳይ መጠሪያ በስሙ ሊሰየምለት ይችላል፡፡
፭. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ አንደኛ ደረጃ ተሸላሚ ለሆነ የሠራዊት አሃድ ወይም ቡድን ብር ፹ ሺ እና በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የተፈረመ ልዩ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡
፮. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፫) እና (፬) ለሠራዊት አሃድና ቡድንም ተፈጻሚ ይሆናል፤ ስለሆነም በትውልድ ሥፍራ ምትክ ጀግንነቱ የተፈጸመበት ሥፍራ ይሆናል፡፡
፵. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ ሁለተኛ ደረጃ
፩. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ ሁለተኛ ደረጃ በተሰለፈበት አውደ ውጊያ የዘወትር ወታደራዊ ግደጅ አፈጻጸም ከሚጠይቀው በላይ በጣም የሚያኮራ ጀግንነት ለፈጸመ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ወይም የሠራዊት አሃድ ወይም ቡድን የማሰጥ ሽልማት ነው፡፡
፪. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ ሁለተኛ የተሸለመ ሰው፤
ሀ. በሕይወት ያለ ከሆነ ብር ፲፭ ሺ የአንድ ጊዜ ክፍያ ይሰጠዋል፤ ከሞተም በጡረታ ሕግ በተመለከተው መጠን መሠረት ለወራሾቹ ብር ፲፭ ሺ ይከፈላል፤
ለ. በብሔራዊ በዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓት ወቅት ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች በሚዘጋጀው ቦታ ይቀመጣል፡፡
ሐ. በጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የተፈረመ ልዩ የመታወቂያ ወረቀት ይሰጠዋል፡፡
፫. የአውደ ውጊያ ጀግና ሁለተኛ ደረጃ ተሸላሚ ለሆነ የሠራዊት አሃድ ወይም ቡድን ብር ፵ ሺ እና በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የተፈረመ ልዩ የምሰክር ወረቀት ይሰጣል፡፡

፵፩. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ ሦስተኛ ደረጃ
፩. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ ሦስተኛ ደረጀ በተሰለፈበት አውደ ውጊያ የዘወትር ወታደራዊ ግዳጅ አፈጻጸም ከሚጠይቀው በላይ የሚያኮራ ጀግንነት ለፈጸመ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ወይም የሠራዊት አሃድ ወይም ቡድን የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡
፪. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ ሦስተኛ ደረጃ የተሸለመ ሰው፤
ሀ. በሕይወት ያለ ከሆነ ብር ፲ ሺ የአንድ ጊዜ ክፍያ ይሰጠዋል፣ ከሞተም በጡረታ ሕግ በተመለከተው መጠን መሠረት ለወራሾቹ ብር ፲ ሺ ይከፈላል፡፡
ለ. በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የተፈረመ ልዩ የመታወቂያ ወረቀት ይሰጠዋል፡፡
፫. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ ሦስተኛ ደረጃ ሦስት ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ የተሸለመ ሰው በብሔራዊ በዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓት ወቅት በተለይ በሚወሰንለት የክብር ሥፍራ ይቀመጣል፡፡
፬. የአውደ ውጊያ ጀግና ሜዳይ ሦስተኛ ደረጃ ተሸላሚ ለሆነ የሠራዊት አሃድ ወይም ቡድን ብር ፵ ሺ እና በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የተፈረመ ልዩ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡

፵፪. የትግል ተሳትፎ ሜዳይ ባለዘንባባ
፩. የትግል ተሳትፎ ሜዳይ ባለዘንባባ በኢትዮጵያ ሠላምና ዲሞክራሲን  ለማስፈን ከደርግ ኢሠፓ መንግሥት ጋር ከ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. እስከ ግንቦት ፳ ቀን ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ድረስ በትጥቅ ትግሉ ከአሥር ዓመት ያላነሰ ተሳትፎ ላለው ታጋይ የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡
፪. የትግል ተሳትፎ ሜዳይ ባለዘንባባ የተሸለመ ሰው በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የተፈረመ ልዩ የመታወቂያ ወረቀት ይሰጠዋል፡፡

፵፫. የትግል ተሳትፎ ሜዳይ ያለዘንባባ
፩. የትግል ተሳትፎ ሜዳይ ያለዘንባባ በኢትዮጵያ ሠላምና ዲሞክራሲን ለማስፈን ከደርግ ኢሠፓ መንግሥት ጋር ከ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. እስከ ግንቦት ፳ ቀን ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ድረስ በትጥቅ ትግሉ ከአሥር ዓመት በታች ተሳትፎ ላለው ታጋይ የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡
፪. የላቀ የሥራ ውጤት ሜዳይ የተሸለመ ሰው በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የተፈረመ ልዩ የመታወቂያ ወረቀት ይሰጠዋል፤

፵፬. የላቀ የሥራ ውጤት ሜዳይ
፩. የላቀ የሥራ ውጤት ሜዳይ በአእምሮ ሥራ ወይም በፈጠራ ወይም በማናቸውም መስክ ለመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ መሳካት የላቀና ወደር የሌለው ውጤት ላስገኘ ሰው ወይም የሠራዊት አሃድ ወይም ቡድን የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡
፪. የላቀ የሥራ ውጤት ሜዳይ የተሸለመ ሰው፤
ሀ. ብር ፲ ሺ የአንድ ጊዜ ክፍያ ይሰጠዋል፤
ለ. በብሔራዊ በዓል አከባበር ሥነ ሥርዓት ወቅት ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች በሚዘጋጀው ቦታ ይቀመጣል፤
ሐ. በሀገር መከላከያ ሚኒስትሩ የተፈረመ ልዩ የመታወቂያ ወረቀት ይሰጣል፡፡
፫. የላቀ የሥራ ውጤት ሜዳይ ለተሸለመ የሠራዊት አሃድ ወይም ቡድን ብር ፵ ሺ እና በመከላከያ ሚኒስትሩ የተፈረመ ልዩ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡

፵፭. የውትድርና አገልግሎት ሜዳይ አንደኛ ደረጃ
የውትድርና አገልግሎት ሜዳይ አንደኛ ደረጃ በሥነ ምግባሩና በወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት የጐላ እንከን የሌለበትና በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከሃያ አምስት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ ላገለገለ የሠራዊት አባል የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡

፵፮. ድርና አገልግሎት ሜዳይ ሁለተኛ ደረጃ
የውትድርና አገልግሎት ሜዳይ ሁለተኛ ደረጃ በሥነ ምግባሩና በወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት የጐላ እንከን የሌለበትና በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከአሥራ አምስት ዓመት ላላነሰ ጊዜ ላገለገለ የሠራዊት አባል የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡

፵፯. የውትድርና አገልግሎት ሜዳይ ሦስተኛ ደረጃ
የውትድርና አገልግሎት ሜዳይ ሦስተኛ ደረጃ በሥነ ምግባሩና በወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት የጐላ እንከን የሌለበትና በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከአሥር ዓመት ላላነሰ ጊዜ ላገለገለ የሠራዊት አባል የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡

፵፰. ዓለም አቀፍ የሰላም ማስጠበቅ ሜዳይ
፩. ዓለም አቀፍ የሠላም ማስጠበቅ ሜዳይ ከኢትዮጵያ ውጭ ከ፺ ቀናት ላላነሰ በዓለምአቀፍና አህጉራዊ የሠላም ማስጠበቅ ተግባር ለተሳተፈ ሰው የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡
፪. ዓለም አቀፍ የሠላም ማስጠበቅ ሜዳይ የተሸለመ ሰው በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የተፈረመ ልዩ የመታወቂያ ወረቀት ይሰጠዋል፡፡

፵፱. የአውደ ውጊያ ቁስለኛ ሜዳይ
፩. የአውደ ውጊያ ቁስለኛ ሜዳይ በአውደ ውጊያ ተሰልፎ የመቁሰል አደጋ ለደረሰበት ሰው የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡
፪. የአውደ ውጊያ ቁስለኛ ሜዳይ የተሸለመ ሰው በክፍለ ጦር ወይም በኮር አዛዥ ወይም በተመጣጣኝ ደረጃ የተፈረመ ልዩ የመታወቂያ ወረቀት ይሰጠዋል፡፡

፶. የውትድርና አገልግሎት ሪባን
የውትድርና አገልግሎት ሪባን ለሕገመንግሥቱ ታማኝ በመሆን በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ለተሰጠ ለእያንዳንዱ አምስት ዓመት አገልግሎት የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡

፶፩. የውጊያ ተሳትፎ የምስክር ወረቀት
የውጊያ ተሳትፎ የምስክር ወረቀት በመንግሥት በታወቀና በታወጀ ወታደራዊ ስምሪት (ዘመቻ) ለተሳተፈ ሰው ወይም የሠራዊት አሃድ ወይም ቡድን የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡

፶፪. የሜዳይ ተሸላሚ የሚያገኘው ተጨማሪ ልዩ መብት
በዚህ አዋጅ ሌሎች አንቀጾች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፴፯ (፩)(ሀ)-(ሰ)፣(ተ) ወይም (ቸ) የተመለከተውን ማንኛውም ሜዳይ የተሸለመ ሰው፤
፩. በመንግሥት ሆስፒታሎችና የሕክምና ተቋሞች ውስጥ ነፃ ሕክምና ያገኛል፤
፪. በመንግሥት የትምህርት ተቋሞች ውስጥ ለመማር ቅድሚያ ያገኛል፤
፫. በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፤ ድርጅቶችና ተቋሞች ውስጥ ችሎታው ለሥራ መደቡ ተስማሚ ሆኖ ሲገኝ የመቀጠር ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡

፶፫. ለሜዳይ ሽልማት የሚያበቃ ሥራ ሠርቶ ስለሞተ ሰው
፩. ለሜዳይ ሽልማት የሚያበቃ ሥራ ሠርቶ የሞተ ሰው አግባብ ያለው ሜዳይ በስሙ ይመዘገባል፡፡
፪. ሜዳዩ ለታላቅ ልጁ ይሰጣል፡፡ ልጅ ከሌለው ለባለቤቱ፤ ባለቤት ከሌለው አግባብ ባለው የውርስ ሕግ መሠረት ለውርስ ባለመበቱ ይሰጣል፡፡

፶፬. ከውጪ አገር ሜዳይ ወይም ሌላ ሽልማት ስለመቀበል
ማንኛውም የመከላከያ ሠራዊት አባል ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር ፈቃድ ሳያገኝ ከውጭ አገር ሜዳይ ወይም ሽልማት ሊቀበል አይችልም፡፡

፶፭. ሜዳይ፣ ሪባን ወይም የምስክር ወረቀት መልሶ ስለ መውሰድ
ተሸላሚው፤
፩. ሜዳዩ፣ ሪባኑ ወይም የምስክር ወረቀቱ የተሰጠው በተሳሳተ ማስረጃ መሆኑ ሲታወቅ፣ ወይም፤
፪. በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ከቁጥር ፪፻፶፱/፪፻፷፭ የተመለከቱትን ወንጀሎች መፈጸሙ በፍ/ቤት ውሣኔ ሲረጋገጥ፤
የተሰጠው ሜዳይ፣ ሪባን ወይም የምስክር ወረቀት ይወሰድበታል፡፡

፶፮. የሜዳዮች ደረጃ ቅደም ተከተል
የሜዳዮች ደረጃ ቅደም ተከተል በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፴፯(፩) በተመለከተው ዝርዝር ቅደም ተከተል መሠት ይሆናል፡፡

፶፯. የሜዳዮችና ሪባኖች አሰጣጥ ሥርዓትና አለባበስ
በዚህ አዋጅ የተመለከቱት ሜዳዮች ሪባኖች አሰጣጥ ሥርዓትና አለባበስ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መመሪያ ይወሰናል፡፡
፯. የአዋጁ የቀድሞው ክፍል ስድስት ክፍል ሰባት ሆኖ አንቀጽ ፴፯-፴፱ እንደ ቅደም ተከተላቸው አንቀጽ ፶፰-፷ ሆነዋል፡፡

፫. አዋጁ የሚጸናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ ከሰኔ ፳፫ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም. ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡
አዲስ አበባ ሰኔ ፳፫ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም.
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት