የተወሰነ አላፊነት ስላላቸው የግል ማኅበሮች | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

የተወሰነ አላፊነት ስላላቸው የግል ማኅበሮች

አንቀጽ ፯
የተወሰነ አላፊነት ስላላቸው የግል ማኅበሮች

ምዕራፍ ፩ ጠቅላላ ድንጋጌዎችና የማኅበሩ አቋቋም

ቊ ፭፻፲ ትርጓሜ ጠባይ፡፡
(፩) የተወሰነ አላፊነት ያለው የግል ማኅበር ማለት ማናቸውም ማኅበረተኛ ካገባው መዋጮ በላይ አላፊ የማይሆንበት ማኅበር ማለት ነው፡፡
(፪) ይኸውም ማኅበር ከሁለት ማኅበረተኛ ያነሰ ከኅምሳ ማኅበረተኞች በላይ ያለበት ለመሆን አይችልም፡፡ የማኅበሩ ዓላማ ማንኛውም ዐይነት ቢሆን ሁል ጊዜ የንግድ ማኅበር ነው፡፡
(፫) ማኅበር በማናቸውም ፎርም ቢሆን የሚተላለፉ የንግድ ወረቀቶችን (ሰነዶች) ለማውጣት አይችልም፡፡
ቊ ፭፻፲፩ በሕግ ከተወሰነው አነስተኛ ቁጥር በታች የማኅበረተኛ ቁጥር ማነስ፡፡
የማኅበረተኞቹ ቁጥር ከሁለት በታች የወረደ እንደ ሆነ ወይም ለማኅበሩ ሥራ አስፈላጊ የሆኑት መሥሪያ ቤቶች መኖራቸው የቀረ እንደ ሆነ፤ ማኅበሩም በሚገባ ጊዜ ውስጥ ሕጋዊ ሁኔታዎችን እንደገና ያላቋቋመ እንደ ሆነ፤ አንድ ማኅበረተኛ ወይም አንድ ገንዘብ ጠያቂ በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት ፍርድ ቤቱ ማኅበሩ እንዲፈርስ ለመፍረድ ይችላል፡፡ እንዲሁም ክሱ በቀረበ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ለጊዜው ለመጠባበቂያ የሆኑ ውሳኔዎች ለማዘዝ ይችላል፡፡
ቊ ፭፻፲፪ የማኅበሩ ዋና ገንዘብ፡፡
(፩) የተወሰነ አላፊነት ያለው የግል ማኅበር ዋና ገንዘብ በዐሥራ አምስት ሺሕ የኢትዮጵያ ብር ያነሰ ለመሆን አይችልም፡፡
(፪) የያንዳንዱ አክሲዮን ዋጋ ከዐሥር የኢትዮጵያ ብር ያነሰ ለመሆን አይችልም፡፡
(፫) የአክሲዮኖቹ ዋጋ ሁሉ ትክክል መሆን አለበት፡፡ እያንዳንዱ ማኅበረተኛ ከአንድ አክሲዮን የበለጠ ለመግዛት ይችላል፡፡
ቊ ፭፻፲፫ የተከለከሉ ሥራዎች፡፡
የተወሰነ አላፊነት ያለው የግል ማኅበር፤ የባንክ የአሹራንስ እንደዚሁም እነዚህን የመሰለ ጠባይ ያላቸው ድርጅቶች ለማቆም የተከለከለ ነው፡፡
ቊ ፭፻፲፬ አጠራር፡፡
(፩) የተወሰነ አላፊነት ያለው የግል ማኅበር የሚጠራበት የማኅበሩን የሥራ ዓላማ የሚገልጽ የማኅበር ስም ሊኖረው ይችላል፡፡
(፪) ከማኅበሩ ስም ቀጥሎ ‹‹የተወሰነ አላፊነት ያለው የግል ማኅበር›› የሚሉ ቃላት በሙሉ ተጽፈው እንዲገኙበት ያስፈልጋል፡፡
ቊ ፭፻፲፭ በማኅበሩ ወረቀቶች ላይ የሚጻፍ መግለጫ ፡፡
በማንኛቸውም ከማኅበሩ በሚወጡ ጽሑፎች የማስታወቂያ ጽሑፎች ወይም ሌሎች ሰነዶች ላይ በቊ ፭፻፲፬ በንኡስ ቊ ፪ በተመለከተው የማኅበሩ ስም ወይም አጠራር ሁል ጊዜም አላፊነቱ የተወሰነበት ማኅበር የሚሉ እንደሚታዩ ሆነው በሙሉ ፊደላት የተጻፉትን ቃላት ማስቀደም ወይም ማስከተል እንዲሁም የማኅበሩን ዋና ገንዘብ ልክ መግለጽ አለባቸው፡፡
ቊ ፭፻፲፮ ስለ ማኅበሩ አመሠራረት፡፡
ማኅበሩ የሚቋቋመው በማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ ዐይነት የተዘጋጀው ግልጽ በሆነ ጽሑፍ ላይ ማኅበረተኞች ሁሉ ራሳቸው ወይም ልዩ ሥልጣን የተሰጣቸው እንደራሴዎቻቸው የፈረሙበት ሲሆን ነው፡፡
ቊ ፭፻፲፯ በመመሥረቻው ጽሑፍ ላይ የሚጻፈው ቃል፡፡
በማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ ላይ ሊጻፉ የሚገባቸው ከዚህ ቀጥለው የተዘረዘሩት ናቸው፡፡
(ሀ) የማኅበረተኞች ስም፤ ዜግነት፤ አድራሻ፤
(ለ) የማኅበሩ ስም፤ ዋና መሥሪያ ቤቱ፤ እንዳሉም ቅርንጫፎቹ፤
(ሐ) የማኅበሩ የንግድ ዓላማ፤
(መ) የማኅበሩ ዋና ገንዘብ ልክ፤
(ሠ) እያንዳንዱ ማኅበረተኛ ያገበው የመዋጮ ገንዘብ ልክ፤
(ረ) በዐይነት ያገባው የመዋጮ ግምት፤
(ሰ) የማኅበሩ ዋና ገንዘብ በሙሉ መግባቱን የሚያስረዳ መግለጫ፤
(ሸ) የንግዱ ማኅበረተኛ የሚደርሰው የአክሲዮኑ ድልድል ልክ፤
(ቀ) የትርፉ ክፍያ አፈጻጸም ሥርዐት፤
(በ) የሥራ አስኪያጆች ቁጥር ሥልጣናቸው እንዳሉም የማኅበሩ ወኪሎች፤
(ተ) እንዳሉም የተቆጣጣሪዎች ብዛት፤
(ቸ) ማኅበሩ የሚቆይበት ጊዜ፤
ቊ ፭፻፲፰ የማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ፡፡
በቊጥር ፫፻፲፬ የተመለከቱት ድንጌዎች የተወሰነ አላፊነት ባለው የግል ማኅበር የመተዳደሪያ ደንብ ላይም ተፈጻሚዎች ይሆናሉ፡፡
ቊ ፭፻፲፱ በዐይነት የሚገባ መዋጮ፡፡
(፩) ከማኅበረተኞቹ አንዱ በዐይነት መዋጮ ያገባ እንደ ሆነ የዚህን መዋጮ ዐይነትና ግምት ሌሎቹ ማኅበረተኞች የተቀበሉትን ዋጋና ከማኅበሩ ዋና ገንዘብ ውስጥ ስለ መዋጮ ግምት የተሰጠውን ድርሻ ልክ የማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ ማመልከት አለበት፡፡
(፪) ግምቱም የሚደረገው ለማኅበረተኞቹ መልካም መስሎ በታያቸው በማናቸውም አሠራር ነው፡፡
(፫) በዐይነት የሚገቡት መዋጮች በገቡበት ጊዜ ለተደረገላቸው ግምት ማኅበረተኞቹ ሁሉ ለሦስተኛ ወገኖች በአንድነት ሳይከፋፈል አላፊዎች ናቸው፡፡
(፬) በዐይነት ላገባው መዋጮ የተደረገው ግምት ከዋጋው በላይ መደረጉ የተረጋገጠ እንደ ሆነ፤ መዋጮውን ያገባው ማኅበረተኛ ከግምት የጐደለውን ከማኅበሩ ዋና ገንዘብ ውስጥ በጥሬ ገንዘብ ማግባት አለበት፡፡
ለዚሁም ገንዘብ መከፈል ከዋናው በላይ መዋጮው መገመቱን ባያውቁትም እንኳ ማኅበረተኞቹ በዚህ ቁጥር ባንድነት ሳይከፈል አላፊዎች ይሆናሉ፡፡
ቊ ፭፻፲፭ ስለ መታወቅ፡፡
(፩) በዚህ መጽሐፍ ከቊጥር ፪፻፲፱ እስከ ፪፻፳፬ ባለው ድንጋጌ መሠረት ማኅበሩ ለሦስተኛ ወገኖች እንዲታወቅ ማስታወቂያ እንዲወጣ ያደርጋል፤ የማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍና ያለም እንደ ሆነ፤ የማኅበሩን መመሥረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ በንግድ መዝገብ መሥሪያ ቤት አግብቶ ማስቀመጥ ግዴታ ነው፡፡
(፪) የሚታተመው ማስታወቂያና በንግድ መዝገብ ለመመዝገቢያ የሚቀርበው ማመልከቻ በቊጥር ፭፻፲፯ (ሀ) እስከ (ሸ) አና (በ) እስከ (ቸ) የተዘረዘሩት ሐተታዎች እንዲኖሩት ያስፈልጋል፡፡
(፫) በቊጥር ፫፻፳፬ የተነገረው ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

ምዕራፍ ፪ ስለ ማኅበሩ አክሲዮኖች

ቊ ፭፻፳፩ የአክሲዮኖች ድርሻ መዝገብ፡፡
(፩) የማኅበሩ አክሲዮኖች ሁሉ በአንድ መዝገብ ላይ ይጻፋሉ፤ መዝገቡ፤
(ሀ) የማኅበረተኞቹን ስም፤
(ለ) እያንዳንዱ ማኅበረተኛ ማግባት ያለበትን የመዋጮዎቹን ግምት፤
(ሐ) ማናቸውንም የማኅበር አክሲዮኖች በስም መተላለፍ፤
(መ) ማንኛውንም ስለነዚህ ሐተታዎች የተደረገውን መሻሻል መግለጽ አለበት፡፡
(፪) ሥራ አስኪያጁ የመጨረሻው ሊስት ከተሰጠ ወዲህ የተለወጠ እንዳች ነገር የለም ብለው ካላስታወቁ በቀር በየዓመቱ መጀመሪያ በንኡስ ቊ ፩ በ(በ) እና በ(ለ) እንደተመለከተው የማኅበረተኞቹን ስም መግባት ያለበትን መዋጮ ግምት የሚያመለክት ሥራ አሰኪያጆቹ የፈረሙበት አንድ ሊስት ለንግድ ሚኒስቴር ይሰጣል፡፡
(፫) በማኅበሩ የአክሲዮን መዝገብና ሊስቶች ትክክል ባልሆነ አጻጻፍ ምክንያት ለሚደርሰው ጉዳት ሥራ አስኪያጆች እየራሳቸውና በአንድነት ሳይከፋፈል አላፊዎች ናቸው፡፡ የተሰጡትም ሊስቶች በግልጽ ማንም ሊያያቸው ይችላል፡፡
ቊ ፭፻፳፪ አክሲዮኖቹን ለሌላ ስለ ማስተላለፍ፡፡
የአክሲዮኖቹ መተላለፍ በጽሑፍ የተረጋገጠ መሆን አለበት፡፡ መተላለፉም በአክሲዮኖቹ መዝገብ ላይ ካልተጻፈ በቀር ማኅበሩንና ሦስተኛ ወገኖችን መቃወሚያ ሊሆን አይችልም፡፡
ቊ ፭፻፳፫ አክሲዮኑ የተላለፈለት ለማኅበሩ ባዕድ የሆነ ሰው፡፡
(፩) በመተዳደሪያ ደንብ ተቃራኒ የሚሆኑ ድንጋጌዎች ከሌሉ በቀር በማኅበረተኞቹ መካከል አክሲዮኖችን ለማስተላለፍ ይቻላል፡፡
(፪) የማኅበር አክሲዮኖች እጅግ ቢያንስ የዋናው ገንዘብ ሦስት ሩብ ያላቸው የማኅበረተኞቹ አብዛኛው ቁጥር ካልፈቀደ በቀር የማኅበሩ አክሲዮኖች ለማኅበሩ ባዕድ ለሆኑ ሦስተኛ ወገኖች ሊተላለፉ አይችሉም፡፡ ከዚህ የበዛ የድምፅ ብልጫ ወይም ማኅበረተኞቹ ሁሉ እንዲፈቅዱ ያስፈልጋል የሚል ቃል በመተዳደሪያ ደንብ ሊጻፍ ይቻላል፡፡
(፫)  ማኅበረተኞቹም የተስማሙበት ውሳኔ በንግድ መዝገብ ላይ እንዲመዘገብ ያስፈልጋል፡፡
(፬) ማኅበሩ በመጣራት ላይ ቢሆንም እንኳን በንኡስ ቁጥር (፪) የተመለከተው ውሳኔ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
(፭) ባንድ ማኅበረተኛ አክሲዮን ላይ በግድ የማስፈጸም ሥርዐት በሚደረግበት ጊዜ የሌሎቹን ማኅበረተኞች ፈቃድ ስለ ማግኘት ያለው ግዴታ አክሲዮኑን በሚገዛውም ሰው ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
ቊ ፭፻፳፬ በውርስ ስለሚገኙ አክሲዮኖች፡፡
(፩) በማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ የተነገሩ ተቃራኒ የሆኑ ድንጋጌዎች ከሌሉ በቀር የአንድ ማኅበረተኛ ወራሾች ለሟቹ አክሲዮኖች በደንብ ወራሾች ይሆናሉ፡፡
(፪) በማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ አንዱ ማኅበረተኛ ከወራሾቹ መካከል ላንዱ ብቻ ድርሻው እንዲደርሰው ለመምረጥ መብቱን የሚጠብቅበት የውል ቃል የሚጸና ነው፡፡

ምዕራፍ ፫ የማኅበሩ አደረጃጀት

 ቊ ፭፻፳፭ ስለ ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅነት፡፡
(፩) የተወሰነ አላፊነት ያለው የግል ማኅበር በአንድ ወይም በብዙ ሥራ አስኪያጆች መተዳደር አለበት፡፡
(፪) ከሓያ በላይ የሚሆኑ ማኅበረተኞች ባሉበት ማኅበር ውስጥ ውሳኔ የሚደረገው በማኅበረተኞቹ ጉባኤ ነው፡፡ ተቆጣጣሪዎችንም መምረጥ አለባቸው፡፡
(፫) ከሓያ ወይም ከሓያ በታች የሆኑ ማኅበረተኞች ባሉባቸው ማኅበሮች ውስጥ የጉባኤ መሰብሰብና የተቆጣጣሪዎችን መምረጥ ጉዳይ በንኡስ ቁ (፪) በተነገረው አይገደዱም፡፡
ቊ ፭፻፳፮ የሥራ አስኪያጆች መሾም፡፡
ሥራ አስኪያጆቹን ከማኅበረተኞች ውጭ ለመምረጥ ይቻላል፡፡ በማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ ወይም በመተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ወይም ወሰን ላልተደረገለት ጊዜ ሥራ አሰኪያጆቹን የሚሾሙ ማኅበረተኞች ናቸው፡፡
ቊ ፭፻፳፯ የሥራ አስኪያጆቹ መሻር፡፡
(፩) በማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ ውስጥ የተሾመውን ሥራ አስኪያጅ በቊጥር ፭፻፴፮ በተነገሩት ሁኔታዎች በተሰጠ ውሳኔ ካልሆነ በቀር ማኅበረተኞቹ ሊሽሩት አይችሉም፡፡
(፪) በማኅበረተኞች የተሾመ ሥራ አስኪያጅ በቊጥር ፭፻፴፭ በተነገሩት ሁኔታዎች በተሰጠው ውሳኔ መሠረት ይሻራል፡፡
(፫) ፍርድ ቤት ሊቀበል በሚችለው ተገቢ ምክንያቶች ካልሆነ በቀር ሊሻር አይቻልም፡፡ የተሻረው ሥራ አስኪያጅ ከተሻረበት አንሥቶ ሥራውን ለመሥራት አይችልም፡፡ ፍርድ ቤቱም የተሻረበት በቂ ምክንያት ያለመሆኑን የተረዳው እንደ ሆነ የተሻረው ሥራ አስኪያጅ ኪሣራ እንዲያገኝ ለመወሰን ይችላል፡፡
(፬) ምንም እንኳ በንኡስ ቁ ፫ የተነገሩት ድንጋጌዎች ቢኖሩ ሥራ አስኪያጆቹ በማናቸውም ዐይነት ቢሾሙ በማኅበረተኞቹ ነጻ ፈቃድ ሊሻሩ የሚችሉ ለመሆናቸው በማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ሊጻፉ ይቻላል፡፡
(፭) በሚገባ ምክንያት ሥራ አሰኪያጅ እንዲሻር የሚቀርበው ክስ ማንኛውም ማኅበረተኛ በየራሱ ሊያቀርበው ይችላል፡፡
ቊ ፭፻፳፰ የሥራ አስኪያጆቹ ሥልጣን፡፡
(፩) ሥራ አስኪያጆቹ ከማኅበሩ ዓላማ ወሰን ሳያልፉ፤ በማንኛዎቹም ሁኔታዎች ሁሉ በማኅበሩ ስም ለመሥራት ሙሉ ሥልጣን አላቸው፡፡
(፪) ለሥራ አስኪያጆቹ ሥልጣን ወሰን በመስጠት በማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ ውስጥ የሚነገሩ የውል ቃሎች በማኅበረተኞቹና በሥራ አስኪያጆቹ መካከል ላሉት ግንኙነቶች ካልሆነ በቀር ውጤት የላቸውም፡፡ በደንብ ሆነው በማስታወቂያ ቢወጡም እንኳ በሦስተኛ ወገኖች ዘንድ ውጤት የላቸውም፡፡
ቊ ፭፻፳፱ ስለ ሥራ አስኪያጆቹ የሥራ ዋጋ፡፡
የሥራ አስኪያጆችን የሥራ ዋጋ የሚወስኑ ማኅበረተኞቹ ናቸው፡፡ ይህም የተባለው የሥራ ዋጋ የቁርጥ አደር ደመወዝ ወይም የትርፍ ተካፋይ ወይም ሁለቱንም በማግኘት እንዲሆን ለማድረግ ይቻላል፡፡
ቊ ፭፻፴ ስለ ሥራ አስኪያጆች አላፊነት፡፡
በፍትሐ ብሔር ሕግ መሠረት ሥራ አስኪያጆቹ በዚህ በንግድ ሕግ የተሰጡትን ድንጋጌዎች ወይም የማኅበሩን የመተዳደሪያ ደንብ በመጣስም ቢሆን በሥራ አስኪያጅነታቸው በሠሩዋቸው ጥፋቶችም ስሕተቶችም ቢሆን በማኅበሩና  በሦስተኛ ወገኖች ፊት በየራሳቸው ወይም በአንድነት ሳይከፋፈል እንደ ነገሩ ሁኔታ አላፊዎች ይሆናሉ፡፡
ቊ ፭፻፴፩ የማኅበሩ መክሠር፡፡
(፩)  የማኅበሩ መክሠር፤ የንብረቱን በቂ አለመሆኑን ያሳየ እንደ ሆነ የከሠረ ማኅበር ንብረት ጠባቂ (ሰንዴክ) በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት፤ በፍርድ ቤቱ እስከሚወሰነው ገንዘብ ልክ የማኅበሩን ዕዳዎች ሁሉምንም ወይም ጥቂቱን ሥራ አስኪያጆቹ፤ ማኅበረተኞቹ ወይም ሁለቱም ወይም ከሥራ አስኪያጆቹ አንዳንዶቹ ባንድነት ወይም በየራሳቸው የማኅበሩን ዕዳዎች ይችላሉ ብሎ ፍርድ ቤቱ ለመወሰን ይችላል፡፡
(፪) ለማኅበሩ ሥራ አስኪያጅነት ተካፋይ ሆነው ካልተገኙ በቀር በንኡስ ቊ ፩ የተመለከተው አላፊነት ማኅበረተኞቹን ሊያገኛቸው አይችልም፡፡ አላፊነቱ የሚመለከታቸው ሥራ አስኪያጂዎችና ማኅበረተኞች አላፊነታቸውን ለማስወገድ ለማኅበሩ ሥራ አመራር የሚያስፈልገውን ተገቢ ሥራና ትጋት የፈጸሙ መሆናቸውን ያስረዱ እንደ ሆነ በንኡስ ቁ (፩) የተነገረው ውሳኔ ተፈጻሚ አይሆንባቸውም፡፡
ቊ ፭፻፴፪ ጉባኤዎች፡፡
(፩) ከሓያ በላይ የሆኑ ማኅበረተኞች ባሉባቸው ማኅበሮች ውስጥ ቢያንስ እንኳን በዓመት አንድ ጊዜ በማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ በተወሰነ ቀን አንድ ጠቅላላ ጉባኤ መደረግ አለበት፡፡
(፪) ሥራ አስኪያጅ ወይም ሥራ አስኪያጆቹ እነዚህም ባይኖሩ ያሉ እንደ ሆነ ተቆጣጣሪዎቹ፤ እነዚህም ባይኖሩ ከማኅበር ዋና ገንዘብ ከእኩሌታው በላይ ያላቸው ማኅበረተኞች በማናቸውም ጊዜ ሌሎቹ ጉባኤዎች እንዲደረጉ ጥሪ ለመላክ ይችላሉ፡፡
ቊ ፭፻፴፫ ጉባኤ ሳይደረግ የሚሰጡ ውሳኔዎች፡፡
ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሕጉ ወይም የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ በሚያስገድዱበት ጊዜ ሥራ አስኪያጆቹ ለእያንዳንዱ ማኅበረተኛ የቀረቡትን አሳቦች ወይም ውሳኔዎች የሚያመለክተውን ጽሑፍ ድምፁን በጽሑፍ እንዲሰጥ እያሳሰቡ መላክ አለባቸው፡፡
ቊ ፭፻፴፬ የማኅበረተኞቹ የድምፅ ብዛት፡፡
(፩) በማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ የተጻፈ ማናቸውም ተቃራኒ የውል ቃል ቢኖርም እንኳ ማንኛውም ማኅበረተኛ ውሳኔ ለመስጠት በሚደረገው ጉባኤ ውስጥ ተካፋይ ለመሆን ይችላል፡፡
(፪) እያንዳንዱ ማኅበረተኛ በማኅበሩ ውስጥ ባሉት አክሲዮኖች ልክ የድምፅ ብዛት አለው፡፡
ቊ ፭፻፴፭ የድምፅ ብልጫና ኮረም፡፡
(፩) ከማኅበሩ ዋና ገንዘብ እኩሌት በላይ ያላቸው በአብዛኛዎቹ ማኅበረተኞች የድምፅ ብልጫ ካልተቀበለው በቀር በቊጥር ፭፻፴፪ በንኡስ ቊ ፩ እና በቊጥር ፭፻፴፫ በተመለከቱት ሁለት ጉዳዮች ላይ ማንኛውንም ዋጋ ያለውን ውሳኔ ለማድረግ አይችልም፡፡
(፪) ይህ የተባለው የአብዛኛው የድምፅ ብልጫ በመጀመሪያው ስብሰባ ጊዜ ሊገኝ ያልቻለ እንደ ሆነ ማኅበረተኞቹ በሬኮማንዴ በሚላኩት ደብዳቤዎች ሁለተኛ ይጠራሉ፤ ከማኅበሩ ዋና ገንዘብ የሆነው ክፍል ምን ያህልም ቢሆን፤ ውሳኔው በአብዛኛው በሚሰጠው የድምፅ ብልጫ ይወሰናል፡፡
ቊ ፭፻፴፮ የማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ ስለ መለወጥ፡፡
(፩) ማኅበረተኞቹ በአንድ ቃል ካልተስማሙ በቀር የማኅበሩን ዜግነት ለመለወጥ አይችሉም፡፡
(፪) ስለሆነም ከማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ለሚደረጉት ማናቸውም አለዋወጥ ከማኅበሩ ዋና ገንዘብ ሦስት ሩብ ባላቸው በአብዛኛዎቹ ማኅበረተኞች ድምፅ ብልጫ መወሰን አለበት፡፡ ይህም የሚሆነው በመተዳደሪያው ደንብ ውስጥ ከዚህ የበለጠ የድምፅ ብልጫ ያልተወሰነ እንደሆነ ነው፡፡ ማኅበረተኛው ካልፈቀደ በቀር በማኅበሩ ውስጥ ባለው ድርሻ ላይ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲገባ ለማስገደድ አይችሉም፡፡
(፫) የሚደረጉት መለዋወጦች ሕጉ በሚያዘው መሠረት ለማስታወቂያ መውጣት አለባቸው፡፡
ቊ ፭፻፴፯ ሰነዶችን የማወቅ መብት፡፡
(፩) ቁጥራቸው ከሓያ የማይበልጥ ማኅበረተኞች ባሉባቸው ማኅበሮች ሁሉ ማናቸውም ማኅበረተኛ ከማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት በራሱ ወይም በወኪሉ፤ የንብረት ዝርዝር መዝገብ፤ የሒሳቡን ሚዛን እንዳለ የተቆጣጣሪዎች ራፖር ለማወቅ ወይም ቅጂ ለመውሰድ ይችላል፡፡
(፪) ቁጥራቸው ከሓያ በላይ የሆነ ማኅበረተኞች ባሉባቸው ማኅበሮች የሆነ አንደ ሆነ ጠቅላላው ጉባኤ ከመሰብሰቡ በፊት ዐሥራ አምስት ቀን አስቀድሞ ካልሆነ በቀር፤ በንኡስ ቁ 1 የተመለከተው የማወቅ መብት አይፈቀድም፡፡
ቊ ፭፻፴፰ ተቆጣጣሪዎች፡፡
(፩) ቁጥራቸው ከሓያ በላይ የሆነ ማኅበረተኞች ባሉበት ማኅበር ከሦስት የሚያንሱ ተቆጣጣሪዎች እንዲመረጡ ያስፈልጋል፡፡ ይህም የተባለው ምርጫ የሚደረገው በማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ ነው፡፡
(፪) እነዚህም ተቆጣጣሪዎች በማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ በተወሰኑት ጊዜዎችና ምክንያቶች እንደ ገና ለመመረጥ ይቀርባሉ፡፡
(፫) ተቆጣጣሪዎቹ የሚሻሩባቸውም ሁኔታዎች በማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ሊጻፉ ይችላል፡፡ ያልተጻፉ እንደ ሆነ በቁጥር ፭፻፴፭ በተመለከተው መሠረት ይፈጸማል፡፡
(፬) የተቆጣጣሪዎቹ ሥራና ሥልጣን በቁጥር ፫፻፸፬ አና በቁጥር ፫፻፸፰ የተመለከቱት ናቸው፡፡
(፭) ተቆጣጣሪዎቹ ሥራቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜ ራሳቸው በሚያደርጓቸው ጥፋቶች ወይም ቸልተኝነት በየራሳቸው ወይም በአንድነት ሳይከፋፈል ለማኅበሩና ለሦስተኛ ወገኖች አላፊዎች ናቸው፡፡
(፮) ነገሩን ዐውቀው ሳለ በራፖራቸው ውስጥ ለጉባኤው ሳይገልጹት በመቅረታቸው ካልሆነ በቀር ሥራ አስኪያጆቹ  ለሠሩት ወንጀል በፍትሐ ብሔር በኩል አላፊዎች አይደሉም፡፡

ምዕራፍ ፬ የማኀበሩ ሒሳቦች

ቊ ፭፻፴፱ ሕጋዊ የሆነ መጠባበቂያ ገንዘብ፡፡
በየዓመቱ መጠባበቂያ የሚሆነውን ገንዘብ ለማደራጀት ከትርፉ ላይ ቢያንስ ከሓያ አንድ እጅ አየተነሣ ይቀመጣል፡፡ ይኸውም የተባለው ገንዘብ መነሣት፤ መጠባበቂያው ከማኅበሩ ዋና ገንዘብ ከዐሥር አንድ እጅ ሲደርስ የግዴታ መሆኑ ያቋርጣል፡፡
ቊ ፭፻፵ ሐሰተኛ ትርፍ፡፡
(፩) ሐሰተኛ የሆኑትን የትርፎች ክፍያ የተቀበሉዋቸው ማኅበረተኞች እንዲመልሱ መጠየቅ ይቻላል፡፡
(፪) ትርፎቹን ለማካፈል ከተወሰነው ቀን አንሥቶ ከአምስት ዓመት በኋላ ስለ ተቀበለው ክፍያ መመለስ የሚቀርበውን ክስ ይርጋ ያግደዋል፡፡
ቊ ፭፻፵፩ የተወሰነ ወለድ፡፡
(፩) ማኅበሩ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎች ለሚከናወኑበት ጊዜ ብቻ ትርፍ ባይኖርም እንኳ ማኅበረተኞቹ ልኩ የተወሰነ ወለድ ለማግኘት መብት አላቸው የሚል የውል ቃል በማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ ውስጥ ለማግባት ይቻላል፡፡ የተባለውን የሚወስነው የማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ ነው፡፡
(፪) ይህም የተባለው የውል ቃል ፈራሽ እንዳይሆን በንግድ ኦፊሲዬል ጋዜጣ መውጣት አለበት፡፡
(፫) የመተዳደሪያ ደንብ በሚወስነው አሠራር እነዚህ የተከፈሉት ወለዶች ማኅበሩን ለማቋቋም ከሚደረጉት መጀመሪያ ወጪዎች ውስጥ ገብቶ ትርፍ በሚያሳዩት ዓመታት ላይ፤ ከነዚህ ወጪዎች ጋራ ይደላደላሉ፡፡

ምዕራፍ ፭ የማኅበሩ መፍረስ

ቊ ፭፻፵፪ የሚፈርሱበት ምክንያቶች፡፡
(፩) የተወሰነ አላፊነት ያለው የግል ማኅበር ለማኅበሮች ሁሉ መፍረሻ በሆኑት ምክንያቶች ማኅበሩ ላልተወሰነ ጊዜ የተቋቋመ የሆነ እንደሆነ ባንድ ማኅበረተኛ አቤቱታ ማቅረብ፤ እንዲሁም በቂ በሆኑ ምክንያቶች በፍርድ ቤት ውሳኔ ይፈርሳል፡፡
(፪) ለማኅበረተኛው ጥቅም በተወሰነ ዋጋ የማኅበረተኞችን አክሲዮኖች መልሶ የመግዛት ሥልጣን ለመስጠት በመተዳደሪያው ደንብ የማያመለክተው የውል ዋጋ ያለው ነው፡፡
(፫) ያንዱ ማኅበረተኛ መከልከል፤ መክሠር፤ ዕዳን መክፈል ያለመቻል ወይም ተቃራኒ የሚሆን የውል ቃል በመተዳደሪያ ደንብ ከሌለ በቀር የማኅበረተኛው መሞት፤ ማኅበሩን አያፈርሰውም፡፡
(፬)  ለሞተ ማኅበረተኛ ወራሾች በማኅበሩ ውስጥ የሚገባቸውን በመጨረሻው የንብረት መዝገብ ዝርዝር መሠረት የሚገባቸውን መልሶ ለመክፈል የምርጫ መብት በመተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ለመወሰን ይቻላል፡፡
ቊ ፭፻፵፫ ከማኅበሩ ዋና ገንዘብ ሦስት ሩብ ስለ መጥፋት፡፡
(፩) ከማኅበሩ ዋና ገንዘብ ሦስት ሩብ የጠፋ እንደ ሆነ የሥራ አስኪጆቹ የማኅበሩን መፍረስ ማስታወቅ የሚያስፈልግ መሆኑን ለማወቅና ለመወሰን ከማኅበረተኞቹ መመካከር አለባቸው፡፡
(፪) ሥራ አስኪያጆቹ ከማኅበረተኞቹ መመካከር ያላደረጉ እንደ ሆነ፤ ወይም በደንበኛ ውሳኔ ለማድረግ የማይችሉ እንደ ሆነ ማናቸውም ጥቅም ያለው ሰው ማኅበሩ እንዲፈርስ ፍርድ ቤትን ለመጠየቅ ይችላል፡፡