ስለ ድርሰትና ስለ ኪነ ጥበብ ባለሀብትነት፡፡ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

ስለ ድርሰትና ስለ ኪነ ጥበብ ባለሀብትነት፡፡

አንቀጽ ዐሥራ አንድ፡፡
ስለ ድርሰትና ስለ ኪነ ጥበብ ባለሀብትነት፡፡
 

ቊ  ሺ፮፻፵፯፡፡ የመብቱ አሰጣጥ፡፡

(፩) አንድ ሰው በአእምሮው አስቦ አንድ ቀዋሚ ነገር ፈጥሮ ያወጣ እንደሆነ ፈጥሮ በማውጣቱ ምክንያት ብቻ ለዚያ ፈጥሮ ላወጣው ግዙፍነት የሌለውን የባለሀብትነትን መብት ያገኛል፡፡
(፪) ሥራው ማናቸውም የአገላለጽ ዐይነት መልክ ፎርም ማንኛውም ምስጋና ወይም ግብ ቢኖረው ይህ መብት ይኖራል፡፡
(፫) ሠሪው የሠራው ነገር በሥራ ወይም በሥራ ማከናወን ውል (በአንትሪፕሪዝ) ምክንያት እንኳን ቢሆን ለሠራው ሥራ ዐይነት ይህ መብት አለው፡፡

ቊ  ሺ፮፻፵፰፡፡ በአእምሮ ታስቦ የሚወጣ ሥራ፡፡

የአእምሮ ሥራዎች ናቸው የሚባሉት ቀጥለው ያሉት ናቸው፡፡
(ሀ) እንደ መጻሕፍት በጥራዝ እየሆኑ እንደሚወጡት ጽሑፎች እንደ መጽሔት ጽሑፎች (ረቪዮ) ወይም እንደ ጋዜጦች በጉባኤ እንደሚሰጡት ንግግሮች እንደ አጭር ንግግሮች እንደ ስብከቶች ወይም እንደ ቲያትሮችና ቲያትርን እንደ መሳሰሉ ሌሎች ሥራዎች ያሉት የዕውቀት ድርሰቶች፤
(ለ) በቃል ወይም ያለ ቃል በሙዚቃ እንዲሰሙ የተዘጋጁ ሥራዎች በሙዚቃ እንዲሰሙ የተዘጋጁ የቲያትር ሥራዎች በራዲዮ ድምፅ እንዲሰሙ ወይም በራዲዮቢዙየል እንዲታዩ የተዘጋጁ ሥራዎች ለቲያትር የተዘጋጁ የዳንስ ወይም የዜማ ስልቶች ሆነው አፈጻጸማቸውም በጽሑፍ ወይም በሌላ አደራረግ የተወሰነ ሲሆን፤
(ሐ) እንደ ሥዕል፤ እንደ ንድፍ ሥዕል፤ እንደ ቅርጽ ወይም እንደ ድንጋይ ማነጥ ያሉ ሥራዎች፤ እንዲሁም እንደ ፎቶግራፍ ወይም እንደ ሲኒማ ያሉት የሚታዩ ሥራዎች፤
(መ) የሥዕል መጽሔቶች የጂኦግራፊ ካርታዎች ፕላኖች የመጀመሪያ ንድፍ ሥራዎች ጂኦግራፊን የአገር መልክን (ቶፖግራፊ) የሕንጻ አሠራርን ኦርሺቴክቱር ኪነ ጥበብን ወይም ሌላ ዕውቀትን ሁሉ የሚመለከቱ እንደ እጅ ጥበብ ማንሻ ያሉ የሥዕል ሥራዎች፤
(ሠ) በሠሪያቸው አእምሮ የተፈጠሩና የዚሁኑ አሠራር ልዩነት የሚያሳዩ ሌሎችም ሥራዎች ሁሉ ናቸው፡፡

ቊ  ሺ፮፻፵፱፡፡ ትርጒምና ማስማማት ፡፡

የመጀመሪያው አዲስ ሥራ አውጪ መብት ሳይነካ የመጽሐፉን ትርጒም የሥራውን ማስማማት (ማሻሻል) የሙዚቃ ማስማማቱን እና የድርሰትን ወይም የኪነ ጥበብን ዐይነት መለወጥ እንደ መጀመሪያ ሥራ ሆነው ይጠበቃሉ፡፡

ቊ  ሺ፮፻፶፡፡ አንሲክሎፔዲና የቅኔ ጥርቅም፡፡

ነገሮቹን በማማረጥ ወይም በማዘጋጀት ከድርሰቶችና ከኪነ ጥበብ ሥራዎች ተለቅመው የአእምሮ ሥራ ፈጠራ እንደሚወጣቸው እንደ አንሲክሎፔዲና እንደ ቅኔ ያሉት የጥርቅም አስተዋጽኦችም በነዚህ በተዋጽኦ ውስጥ የሚገኙ በያንዳንድ ሥራዎች ላይ ያላቸው የመጀመሪያ አውጪዎች መብት ሳይነካ እንደ መጀመሪያ ሥራ ሆነው የሚጠበቁ ናቸው፡፡

ቊ  ሺ፮፻፶፩፡፡ ግልጽ የሆኑ የመንግሥት ጽሑፎች፡፡

(፩) የሕግ የአስተዳደር ወይም የዳኝነት ጠባይ ያላቸው ከመንግሥት ባለሥልጣኖች የሚነገሩት ጽሑፎች በዚህ ምዕራፍ የተነገረውን ጥበቃ አያገኙም፡፡
(፪) እንደ ተፈለገ በነጻ ሊባዙ ይቻላል፡፡

ቊ  ሺ፮፻፶፪፡፡ የወጣውን ሥራ የማስታወቅ መብት፡፡

(፩) ያወጣውን ሥራ የማስታወቅ መብት ያለው ሥራ አውጪው ብቻ ነው፡፡
(፪) እርሱ ከሞተ በኋላ በተባለው መብት የሚሠራ እርሱ የመረጠው ሰው ነው እርሱ የመረጠው የሌለ እንደሆነ የሥራው አውጪ ወራሾች ናቸው፡፡
(፫) የሥራ አውጪው ወራሾች ስለ ሥራው አወጣጥ ጊዜ ወይም ስለ ማስታወቁ ሁኔታዎች ያልተስማሙ እንደሆነ፤ ዳኞቹ ወራሾቹ እያንዳንዳቸው ያቀረቡትን የጥያቄ ቃል ያመዛዝናሉ፡፡

ቊ  ሺ፮፻፶፫፡፡ የወጣውን ሥራ ስለ ማሳየትና ማባዛት፡፡

(፩) ያወጣውን ሥራ በሕይወቱ ሳለ ለማሳየት መብት ያለው ሥራ አውጪው ብቻ ነው፡፡
(፪) እንደዚሁም ያወጣውን ሥራ በሕይወቱ ሳለ ለማባዛት መብት ያለው ያው ሥራ አውጪው ብቻ ነው፡፡

ቊ  ሺ፮፻፶፬፡፡ ሥራውን ስለ ማስማማት፡፡

(፩) ለቲያትር ለሲኒማ ለራዲዮ ቢዚዮን ወይም ለማንኛውም ዐይነት ሥራ የሠራው ሥራ እንዲስማማ ለመፍቀድ መብት ያለው ሥራ አውጪው ብቻ ነው፡፡
(፪) ለሌላ ሰው ሥራ ሆኖ አሠራሩን በማስማማት ወጣ የሚባለው አዲስ ሥራ የአሠራሩን ሁኔታዎች በማየት በፊት ከወጣው ሥራ ጋራ ግልጽ የመነጨ ለመሆኑ በግልጽ ሲታይ ነው፡፡
(፫) በሌላው ሰው ጽሑፍ ላይ ሐተታ መግለጽ ወይም በግጥም ላይ መግጠም ወይም በሚያሥቅ ዐይነት ሥዕሎችን ነድፎ የማውጣት የመጀመሪያውን ሥራ አስማምቶ እንደ ማውጣት አይቈጠርም፡፡

ቊ  ሺ፮፻፶፭፡፡ ትርጒም፡፡

(፩) ያውጣው ሥራ (መጽሐፍ) እንዳይተረጐም ደራሲው ለመቃወም አይችልም፡፡
(፪) ያለደራሲው ፈቃድ የተደረገው ትርጒም፤ የዚህን ሁኔታ በተተረጐመው መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ በግልጽ ማመልከት አለበት፡፡
(፫) ይህን ሳይገልጽ የቀረ እንደሆነ የደራሲውን መብት እንደነካ ይቈጠራል፡፡

ቊ  ሺ፮፻፶፮፡፡ በግልና ያለ ዋጋ የሚደረግ ማሳየት፡፡

በተለይ በቤተ ዘመድ ክበብ ውስጥ ወይም በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ለብቻና ያለ ዋጋ የሚፈጽመውን የሥራውን ማሳየት ተግባር ሥራ አውጪው ለመከልከል አይችልም፡፡

ቊ  ሺ፮፻፶፯፡፡ የዘመኑ ሁኔታ ጽሑፎችና ወሬዎች፡፡

(፩) የዘመኑን ጠባይ የሚገልጹ ጋዜጣዎች ወይም በማኅተም መባዛታቸው በግልጽ ያልተጠበቀ እንደሆነ በማኅተም ወጥተው ወይም በራዲዮ ተገልጸው ለመታየት ይችላሉ፡፡
(፪) ቢሆንም የተገኙበት ምንጭ ሁል ጊዜ በግልጽ መነገር አለበት፡፡
(፫) የተራ ነገር ጠባይ ያላቸው የዕለት ወሬዎችና ልዩ ልዩ ሥራዎች በነጻ ታትመው ለመውጣት ይችላሉ፡፡

ቊ  ሺ፮፻፶፰፡፡ በአደባባይ የተደረጉ ንግግሮች፡፡

በፖለቲካ ጉባኤ በሕዝብ ስብሰባ ወይም በመንግሥት ሥነ በዓል ምክንያት በተሰበሰበው ሕዝብ ውስጥ የተደረጉትን ንግግሮች ከተነገሩበት ቀን አንሥቶ እስከ ዐሥራ አምስት ቀን ድረስ እየታተሙ ሊወጡና  በራዲዮ ሊነገሩ ይችላሉ፡፡

ቊ  ሺ፮፻፶፱፡፡ የንግግሮቹ ወይም የጋዜጦቹ መድበል፡፡

የራሱን ንግግሮችና ጽሑፎች በመጽሐፍ ዐይነት አድርጎ ለማውጣትና በአንድ ለማጠቃለል መብት ያለው ራሱ ደራሲው ብቻ ነው፡፡

ቊ  ሺ፮፻፷፡፡ ሥራውን ሌላ ሰው እንዳያበዛ የመከልከል መብት ወሰን፡፡

(፩) ጸሓፊው እርሱ ስለ ጻፈው ጒዳይ የሚደረገውን ማፍታታትና በጋዜጣ የሚወጡትን የመግለጫ (ጽሑፎች) ለመከልከል አይችልም፡፡
(፪) እንደዚሁም ለግል አገልግሎት ብቻ የሚሆን ከመጽሐፉ አንድ ቅጂ ወይም ግልባጭ ብቻ ለመውሰድ ይፈቀዳል፡፡

ቊ  ሺ፮፻፷፩፡፡ ጥቅሶች፡፡

የሚጠቀሱ ነገሮች ከአንድ የቅኔ መጽሐፍ ሲሆን ከአርባ መሥመሮች ከሌላ ዐይነት መጽሐፍ ሲሆን ከዐሥር ሺሕ ፊደላት የማያልፉ (ማይበልጡ) ከሆኑ ከወጣው መጽሐፍ ውስጥ እንዳይጠቀሱ ደራሲው ለመከልከል አይችልም፡፡

ቊ  ሺ፮፻፷፪፡፡ የፎቶግራፍ ሥራዎች፡፡

(፩) የፎቶግራፍ ሥራዎች የሚጠበቁት በአንድ የፎቶግራፍ ማጠራቀሚያ ውስጥ ተያይዘው የሚገኙ ወይም በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ታትመው የወጡ ሲሆኑ ነው፡፡
(፪) በሌላ ሁኔታዎች የፎቶግራፍ አንሺውን ወይም የወኪሉን ስምና አድራሻ የያዙ ካልሆኑ በቀር እንዳይባዙ የተጠበቁ አይሆኑም፡፡

ቊ  ሺ፮፻፷፫፡፡ የወጣውን ሥራ ስለ ማስተላለፍ፡፡

(፩) አንድ ሰው አስቦ ያወጣውን (ግዙፍነት) የሌለው ሥራ ባለሀብትነት መጠበቅ ከሚገባው ከግዙፍ ዕቃ ባለሀብትነት የተለየ ነው፡፡
(፪) ይህን ዕቃ በመግዛት እጅ ያደረገ ሰው ይህን ዕቃ እጅ በማድረጉ ምክንያት በዚህ ምዕራፍ ከተነገሩት መብቶች አንዱም አይሰጠውም፡፡
(፫) ስለሆነም ሥራውን አስቦ ያወጣው ሰው በለቀቀው ዕቃ ላይ በመብቱ እንድሠራበት አድርግልኝ ሲል የተባለው ግዙፍ ዕቃ ባለቤት የሆነውን ሰው ለማስገደድ አይችልም፡፡

ቊ  ሺ፮፻፷፬፡፡ አሳትሞ ለማስወጣት ወደ ተጻፈው የውል ደንብ ስለ መምራት፡፡

ድርሰትን ወይም ኪነ ጥበብን ያወጣው ሰው የዚህን ያወጣውን ሥራ መብት ለሌላ ሰው የሚለቅባቸው ሁኔታዎች የአሳትሞ ማስወጣት ውል በሚል አንቀጽ ውስጥ በዚህ ሕግ ተወስነዋል፡፡

ቊ  ሺ፮፻፷፭፡፡ የወጣውን ሥራ ስለ መለዋወጥ፡፡

ማንኛቸውም ተቃራኒ የሆነ የውል ቃል ቢኖርም እንኳ ያወጣውን ሥራ ዐይነቱን ሌላ ሰው የለወጠበት እንደሆነ የተባለው ሥራ የዚያ የለወጠው ሰው ነው በመባል እንዳይቀጥል ሥራ አውጪው ለመቃወም ይችላል፡፡

ቊ  ሺ፮፻፷፮፡፡ ሥራ አውጪው ማን መሆኑን ስለ መወሰን፡፡

(፩) ተቃራኒ የሚሆን አስረጂ ከሌለ በቀር የሥራው አውጪ ነው የሚባለው ሥራው በስሙ መውጣቱ የታወቀለት ሰው ነው፡፡
(፪) ሥራ አውጪው ያወጣው ሥራ የፈጠራ ስምን በመስጠት እንኳ ቢሆን ስለ ስሙ ትክክለኛነት አንዳች ጥርጥር ከሌለ በዚህ ምዕራፍ በተወሰኑት መብቶች ሊጠቀምባቸው ይችላል፡፡

ቊ  ሺ፮፻፷፯፡፡ የአውጪው ስም የሌለባቸው ሥራዎች፡፡

የአውጪው (የደራሲው) ስም የሌለባቸው ሥራዎችና ከዚህ በላይ በተጻፈው ቊጥር ከተጠቀሱት በቀር በፈጠራ ስም የተጻፉ ሌሎች ሥራዎች ሲገኙ በወጣው ሥራ ላይ ስሙ የተመለከተው አሳትሞ ጽሑፍ አውጪው ሌላ ማስረጃ ሳያስፈልግ የሥራ አውጪው ወኪል እንደሆነ ይገመታል፡፡

ቊ  ሺ፮፻፷፰፡፡ በብዙ ሰዎች የወጣው ሥራ፤ (፩) የጋራ ሥራዎች መብት፡፡

(፩) በብዙ ሰዎች ሠሪነት ታስቦ የወጣው ሥራ የአውጪዎቹ የጋራ ሀብት ይሆናል፡፡
(፪) የሥራው አውጪነት መብት በመካከላቸው በሚደረግ በጋራ ስምምነት ሊሠራበት ይገባል፡፡
(፫) የጋራ ሠሪዎቹ የያንዳንዱ ድርሻ መሳተፍም የወጣበት ከልዩ ልዩ ዐይነት ነገር የሆነ እንደሆነ ተቃራኒ የሚሆን ስምምነት ከሌለ በቀር የጋራው ሥራ የሚሰጠው ጥቅም ሳይነካ እያንዳንዱ ለዚሁ ሥራ ባደረገው በራሱ ድርሻ ወጪ ገንዘብ ለብቻው መጠቀም ይችላል፡፡

ቊ  ሺ፮፻፷፱፡፡ (፪) ሌሎች ሦስተኛ ወገኖችን ስለ መቃወም፡፡

(፩) አንድ የወጣ ሥራ በአንዱ አውጪ ስም ብቻ የወጣ እንደሆነ ሌሎቹ ሦስተኛ ወገኖች ይህ በሥራው አውጪነት ስሙ የተጠራው ሰው እርሱ ብቻ የሥራው አውጪ ነው ለማለት በቂ ምክንያት ይሆናቸዋል፡፡
(፪) የጋራ ሥራ አውጪዎቹ መብት እነዚህን ሦስተኛ ወገኖች መቃወሚያ ሊሆን አይችልም፡፡

ቊ  ሺ፮፻፸፡፡ የሥራ አውጪው ወራሾች፤ (፩) የገንዘብ መብት፡፡

(፩) አስቦ ሥራ ያወጣው ሰው ያወጣውን ሥራ የማሳየት የማባዛት ወይም የሥራውን ማስማማት የመፍቀድ መብቱ እርሱ ከሞተ በኋላ ወራሾቹ ሥራው በአደባባይ ወጥቶ ከታወቀበት አንሥቶ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ሊሠሩበት ይችላሉ፡፡
(፪) ወራሾቹ በነገሩ ሳይስማሙ በሚቀሩበት ጊዜ ዳኞቹ እያንዳንዱ ወራሽ ስለዚህ ጒዳይ ያቀረበውን ጥያቄ ለማመዛዘን ይችላል፡፡

ቊ  ሺ፮፻፸፩፡፡ (፪) የሕሊና መብት፡፡

የወጣውን ሥራ አንድ ሌላ ፫ኛ ወገን ዐይነቱን ሲለውጥ ይህ ዐይነቱ የተለወጠው ሥራ የአውጪው ነው ተብሎ እንዲቀጥል የማስደረጉ መብት በሕይወት ሳሉ ከባልና ከሚስት አንዳቸው የሥራ አውጪው ወላጆች ልጆቹና የልጅ ልጆቹ በየራሳቸው ሊሠሩበት ይችላሉ፡፡

ቊ  ሺ፮፻፸፪፡፡ ከሞት በኋላ የሚታወቅ ሥራ፡፡

ሥራውን ያወጣ ሰው ከሞተ በኋላ በግልጽ የታወቀ ሥራ ከታወቀበት ቀን አንሥቶ አምሳ ዓመት ድረስ የተጠበቀ ይሆናል፡፡

ቊ  ሺ፮፻፸፫፡፡ የሕዝብ ባለሥልጣኖች መብት፡፡

(፩) የወጣው ሥራ አውጪው ባለቤቱ ወይም ወራሾቹ በግልጽ አስታውቀውት ከታየ በኋላ ሠሪው ቢቃወምም ቅሉ ለጠቅላላ ጥቅም ከሆነ ይህ አስቦ ያወጣው ሥራ እንዲታይ ወይም መሰሉ እንዲባዛ ወይም ዐይነቱ የተስማማ በመሆን እንዲሻሻል የሕዝብ ባለሥልጣኖች ለመፍቀድ ይችላሉ፡፡
(፪) የዚህ የአፈቃቀድ ምክንያቶችና ፎርሞች ለሥራ አውጪው የሚገባ ትክክለኛ ኪሣራ እንዲሰጠው በሚናገረው ልዩ ሕግ ይወሰናሉ፡፡
(፫) የሕዝብ ባለሥልጣኖች በማናቸውም ምክንያት ቢሆን የሥራው ዐይነት እንዲለዋወጥ ለመፍቀድ አይችሉም፡፡

ቊ  ሺ፮፻፸፬፡፡ የድርሰት ወይም የኪነ ጥበብ ባለሀብትነት፡፡

(፩) የድርሰት ወይም የኪነ ጥበብ ባለ ሀብትነት መብቱ የተነካበት ሥራ አውጪ የተባለው መነካት እንዲቆም እና ሕግን በመተላለፍ (በመጣስ) የተደረጉት የሥራው ቅጂዎች ወይም የሥራው ማሻሻያዎች እንዲጠፉ ለማስገደድ ይችላል፡፡
(፪) ከዚህም በላይ በሕሊናም ሆነ በግዙፉ ረገድ ስለ ደረሰበት ጉዳት የገንዘብ ኪሣራ እንዲሰጠው ለመጠየቅ ይችላል፡፡
(፫) ይህን ለማድረግ የሚችልባቸው ሁኔታዎች ከውል ውጭ ስለሚደርስ ኀላፊነት በሚል አንቀጽ በዚህ ሕግ ተወስነዋል፡፡