የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲፪/፲፱፻፹፱ ዓ.ም. የፈጠራ፣ የአነስተኛ ፈጠራ እና የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲፪/፲፱፻፹፱ ዓ.ም. የፈጠራ፣ የአነስተኛ ፈጠራ እና የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲፪/፲፱፻፹፱
የፈጠራ፣ የአነስተኛ ፈጠራ እና የኢንዱስትሪያዊ
ንድፍ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር ፬/፲፱፻፹፯ አንቀጽ ፭ እና የፈጠራ፣ የአነስተኛ ፈጠራና የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ አዋጅ ቁጥር ፩፻፳፫/፲፱፻፹፯ በአንቀጽ ፶፫ (፩) መሠረት ይህን ደንብ አውጥቷል፡፡
ምዕራፍ አንድ
ጠቅላላ
፩. አጭር ርዕስ
ይህ ደንብ ‹‹የፈጠራ፣ የአነስተኛ ፈጠራ እና የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲፪/፲፱፻፹፱›› ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ትርጓሜ
የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም እንዲሰጠው ካላስፈለገ በስተቀር በዚህ ደንብ ውስጥ፤
፩. ‹‹ኮሚሽን›› ማለት የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ነው፤
፪. ‹‹መርማሪ›› ማለት ለፓተንት፣ ለግልጋሎት ሞዴል ሰርተፊኬት ወይም ለኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ምዝገባ ሰርተፊኬት የሚቀርብን ማመልከቻ እንዲመረምር በኮሚሽኑ የተሰየመ ባለሙያ ነው፤
፫. ‹‹ባለ ፓተንት›› ማለት የፓተንት ወይም የአስገቢ ፓተንት ባለቤት ነው፤
፬. ‹‹አዋጅ›› ማለት የፈጠራ፣ የአነስተኛ ፈጠራ እና የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ አዋጅ ቁጥር ፩፻፳፫/፲፱፻፹፯ ነው፡፡

፫. ክፍያዎች
በአዋጁ አንቀጽ ፶፫ (፪) መሰረት የሚፈጸሙ ክፍያዎች ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ I በተዘረዘረው መሠረት ይሆናል፡፡

፬. ቅጾች
፩. በዚህ ደንብ ውስጥ የተጠቀሱት ቅጾች ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሰንጠረዥ II ላይ የተመለከቱት ናቸው፡፡
፪. ኮሚሽኑ የታተሙ ቅጾችን ቅጅዎች ያለ ክፍያ ያቀርባል፡፡

፭. ሰነዶች ስለሚቀርቡበት ቋንቋና ትርጉም
፩. ማናቸውም ማመልከቻ በአማርኛ ወይም በእንግሊዝኛ ቋንቋ መቅረብ አለበት፡፡
፪. በአዋጁ ወይም በዚህ ደንብ መሠት ለኮሚሽኑ የሚቀርብ የማመልከቻ አካል የሆነ ወይም ሌላ ሰነድ በእንግሊዝኛ ወይም በአማርኛ ያልተዘጋጀ ከሆነ በአማርኛ ወይም በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ ከዋናው ሰነድ ጋር መቅረብ አለበት፡፡

፮. ስለስም፣ አድራሻ፣ ዜግነትና የመኖሪያ ቦታ ጥቆማ
፩. ከኢትዮጵያዊያን በስተቀር የአንድ ተፈጥሮአዊ ሰው ስም የቤተሰብን ስም በማስቀደም በቤተሰብና በመጀመሪያ ስም መገለፅ ያለበት ሲሆን ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው አካሎች ደግሞ ሙሉ ሕጋዊ መጠሪያ ስማቸው መመልከት ይኖርበታል፡፡
፪. ማናቸውም አድራሻ አመልካቹ የሚገኝበትን የተሟላ አድራሻ በተለይም የፖስታ ሳጥን፣ የቴሌግራፍ፣ የቴሌክስ፣ የስልክ ወይም የፋክስ ቁጥር ሊያመለክት ይገባል፡፡
፫. ዜግነት አንድ ሰው ዜጋ በሆነበት አገር ስም መገለጽ አለበት፡፡ የሕግ ሰውነት ያለው ድርጅት ከሆነ የተቋቋመበትን ሀገር ስም የሚገልጽ ሆኖ ዋናው መሥሪያ ቤት የተመዘገበበትን ዝርዝር መግለጫ የያዘ መሆን ይኖርበታል፡፡
፬. የመኖሪያ ቦታ አንድ ሰው የሚኖርበትን ሀገር ስም ጭምር የሚገልጽ መሆን ይኖርበታል፡፡

፯. በሽርካዎች፣ በኩባንያዎችና በማሕበራት ስለሚደረግ ፊርማ
፩. ማናቸውም ሰነድ በሽርካው ወይም በኩባንያው ወይም በማሕበር ስም የሚፈረመው ሥልጣን በተሰጣቸው ሰዎች ይሆናል፡፡
፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሰረት የሚፈረም ሰነድ ላይ የሽርካው፣ የኩባንያው ወይም የማሕበሩ ማሕተም ሊያርፍበት ይገባል፡፡

፰. ስለውክልና
የውክልና ሠነድ ከማመልከቻው ጋር ወይም ከምዝገባው ቀን አንስቶ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ውክልናው በአዋጁ አንቀጽ ፱(፯) እንዲሁም በዚህ ደንብ አንቀጽ ፵፰ በተደነገገው መሠረት ካልተፈጸመ ማመልከቻውን ከማስመዝገብ ውጭ በወኪሉ በየደረጃው የተከናወኑ ተግባራት እንዳልተፈፀሙ ይቆጠራሉ፡፡

ምዕራፍ ሁለት
ፓተንት
ክፍል አንድ
ስለማመልከቻ እና የፓተንት አሰጣጥ ስርዓት
፱. ስለፓተንት ምደባ
ከፓተንት አሰጣጥና ሕትመት ጋር ለተዛመዱ ጉዳዮች እንዲሁም የፍለጋ ፋይሎችን ለማኖር ኮሚሽኑ እ.ኤ.አ ማርች ፳፬/፲፱፻፸፩ ዓ.ም በስትራስበርግ ስምምነት የፀደቀውንና በተከትታይ ሕትመቶች የተሻሻለውን ዓለም አቀፍ የፓተንት ምደባ ስርዓት ይጠቀማል፡፡

፲. የፓተንት ይሰጠኝ ጥያቄ
፩. የፓተንት ይሰጠኝ ጥያቄ በቅፅ 1 ተሞልቶ እና በእያንዳንዱ አመልካች ተፈርሞ መቅረብ ይኖርበታል፡፡
፪. ጥያቄው የእያንዳንዱን አመልካች ስም፣ አድራሻ፣ ዜግነትና መኖሪያ ማመልከት ይኖርበታል፡፡
፫. አመልካቹ የፈጠራ ሠራተኛው ሲሆን ጥያቄው ይህንኑ የሚገልጽ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሆኖም አመልካቹ የፈጠራ ሰራተኛ ካልሆነ ጥያቄው የእያንዳንዱን የፈጠራ ሰራተኛ ስም እና አድራሻ እንዲሁም አመልካቹ በፓተንቱ ላይ ያለውን መብት የሚያስረዳ መግለጫ መያዝ ይኖርበታል፡፡
፬. አመልካቹ በወኪል ከተወከለ ጥያቄው ይህንኑ ማመልከትና የወኪሉን ስምና አድራሻ መግለፅ ይኖርበታል፡፡
፭. የፈጠራው ርዕስ አጠር ያለና ቢቻል ከሁለት እስከ ሰባት ባልበለጡ ቃላት ሊገለጽ የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡

፲፩. ስለ መግለጫ
፩. መግለጫው በቅድሚያ በመጠይቁ ላይ እንደመለከተው የፈጠራውን ርዕስ የሚገልጽ ሆኖ፤
ሀ) ከፈጠራው ጋር ግንኙነት ያለውን የቴክኒክ መስክ የሚያመለክት፣
ለ) በአመልካቹ እስከታወቀ ድረስ ፈጠራውን ለመረዳት፣ ለመፈለግ፣ እና ለመመርመር ጠቃሚ የሆኑ መነሻ ጥበቦችን በይበልጥም እነኝህኑ ጥበቦች የሚያመለክቱ ሰነዶችን የሚጠቁም፣
ሐ) ፈጠራው ያሟላል ተብሎ የታለመውን ተግባር የሚገልጽ፣
መ) በሙያው የሰለጠነ ሰው ፈጠራውን ተግባራዊ ሊያደርገው በሚችልበት አኳኋን በበቂና በተሟላ ሁኔታ የሚያብራራ እና ጠቃሚ ውጤት ካለው ከመነሻ ጥበቡ ጋር በማነፃፀር የሚገልጽ፣
ሠ) ከቀደምት ጥበብ ጋር ሲወዳደር ፈጠራው የሚኖረውን በጎ ጎን ወይም ውጤታማነት የሚገልጽ፣
ረ) ሥዕሎች ካሉ በሥዕሎቹ ውስጥ ያሉ ቁጥሮችን በአጭሩ የሚዘረዝር፣
ሰ) ፈጠራውን በሥራ ላይ ለማዋል በአመልካቹ ከተተለሙ መንገዶች ቢያንስ አንዱን የሚገልጽና እንደ አስፈላጊነቱ ምሳሌዎችን በመጠቀም እና ስዕሎች ካሉ ከሥዕሎች ጋር በማገናዘብ የሚያቀርብ፣
ሸ) ከፈጠራው መግለጫ ወይም ባህርይ ግልፅ ሊሆን ካልቻለ ፈጠራው በኢንዱስትሪ ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበትን እና ፈጠራው የሚሰራበትንና ግልጋሎት ላይ የሚውልበትን መንገድ ወይም አገልግሎት መስጠት ብቻ ከሆነም አገልግሎት ላይ የሚውልበትን መንገድ በግልጽ የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል፡፡
፪. በፈጠራው ባህሪ ምክንያት ፈጠራውን በተለየ መንገድ ወይም ቅደም ተከተል መግለጹ በተሻለ ሁኔታ ለመረዳትና በአጭሩ ለማቅረብ የሚያመች ሆኖ ካልተገኘ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) ላይ በተመለከተው መንገድ እና ቅደም ተከተል መግለጫው መቅረብ ይኖርበታል፡፡
፫. የፈጠራው መግለጫ የኬሚካል ወይም የሂሳብ ፎርሙላዎችን እንጅ የንግድ ማስታወቂያዎችን ሊይዝ አይችልም፡፡
፬. መግለጫው ፈጠራውን የበለጠ ለማብራራት የሚረዱ ነገሮችን ብቻ መያዝ የሚችል ሆኖ በአጠቃላይ ተቀባይነት ያላገኘ አዲስ ቃል ወይም ሙያ ነክ ቃልን የያዘ እንደሆነ ቃሉ መገለጽ ይኖርበታል፡፡

፲፪. ስለመብት ወሰን ጥያቄ
፩. የመብት ወሰን ጥያቄ ጥበቃ እንዲረግለት የሚፈለግን ጉዳይ በፈጠራው ቴክኒካዊ ገጽታዎች አማካኝነት ግልጽ በሆነና አጠር ባለ መንገድ የሚገልጽና አንድን ምርት ወይም የምርት ሒደት የሚመለከት ይሆናል፡፡
፪. የመብት ወሰን ጥያቄዎች ብዛት የፈጠራውን ባህሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት አግባብነት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡ ብዙ የመብት ወሰን ጥያቄዎች በሚኖሩበት ጊዜ ተከታታይ የአረብኛ ቁጥር ይሰጣቸዋል፡፡
፫. በመብት ወሰን ጥያቄ ላይ የሚገለጽ የቴክኒክ ቃል በመግለጫው ከተገለጸው ጋር ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡ የመብት ወሰን ጥያቄዎች የኬሚካል ወይም የሂሳብ ፎርሙላዎችን እንጂ ሥዕሎችን አይዙም፡፡
፬. አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የመብት ወሰን ጥያቄ፣
ሀ) ፈጠራውን ለመግለጽ አስፈላጊና በጣምራ የቀደምት ጥበብ አካል የሆኑትን የፈጠራውን ቴክኒካዊ ባህርያት የሚያመለክት መግለጫ፤
ለ) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፬)(ሀ) ከተመለከቱት ባህርያት ጋር በመጣመር ጥበቃ ሊደረግለት የተፈለገውን ቴክኒካዊ ባህርይ በአጭሩ የሚገልጽ ‹‹የሚገለጸው›› ‹‹የሚለየው›› ‹‹ማሻሻያው የሚያካትትው›› በሚሉ ሐረጐች የሚጀመር የመለያ  ባህርይ ክፍል ሊይዝ ይገባል፡፡
፭. የግድ አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ በቀር የመብት ወሰን ጥያቄ የፈጠራውን ቴክኒካዊ ባህርያት አስመልክቶ መግለጫዎችን ወይም ስዕሎችን መሠረት ያደረጉ በተለይም ‹‹በመግለጫው     ክፍል እንደተለገጸው››፣ ወይም ‹‹በስዕሉ         ላይ እንደተመለከተው›› በሚሉ ተጠቃሾች ላይ አይወሰኑም፡፡
፮. ማመልከቻው ሥዕሎችን ያካተተ እንደሆነ በመብት ወሰን ጥያቄ ውስጥ የተገለጹት ቴክኒካዊ ባህርያት ጠቋሚ ምልክቶችን ቢያስከትሉና ምልክቶቹም በጥቅም ላይ በዋሉ ጊዜ በቅንፍ ውስጥ ቢቀመጡ ይመረጣል፡፡ ጠቋሚ ምልክቶቹ የመብት ወሰን ጥያቄውን በፍጥነት ለመገንዘብ የሚያገለግሉ ካልሆኑ መካተት የለባቸውም፡፡
፯. ከማመልከቻው የምዝገባ ቀን በኋላ የቀረበ በቀድሞ ማመልከቻ ውስጥ ከሚገኙት የመብት ወሰን ጥያቄዎች ጋር ያልተዛመደ የመብት ወሰን ጥያቄ በአመልካቹ ምርጫ እንደተሻሻለ ወይም እንደ አዲስ ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል፡፡
፰. በቀድሞ ማመልከቻ ላይ ሰፍሮ የነበረ ማናቸውም የመብት ወሰን ጥያቄ የተሰረዘ እንደሆነ የቀድሞውን የመብት ጥያቄ የመለያ ቁጥሩን በመጥቀስ ‹‹ተሠርዟል›› የሚል ቃለ ይደረግበታል፡፡

፲፫. ሥዕሎች
፩. ለፓተንት የቀረበ ማመልከቻ አካል የሆኑ ሥዕሎች የሚቀርቡበት ወረቀት ጥቅም ላይ የሚውለው ክፍል ስፋት ከ፳፮.፪ ሣ.ሜ በ፲፯ ሣ.ሜ መብለጥ የለበትም፡፡ በእነኝህ ወረቀቶች በጥቅም ላይ በሚውለው ወይም በዋለው ቦታ ዙሪያ ክፈፍ ሊኖር አይገባም፡፡ የአነስተኛ ህዳጎች መጠን፣
ከላይ ፪ ነጥብ ፭ ሣ.ሜ
ከግራ ጎን ፪ ነጥብ  ፭ ሣ.ሜ
ከቀኝ ጎን ፩ ነጥብ ፭ ሣ.ሜ
ከታች ፩ ነጥብ ዜሮ ሣ.ሜ ይሆናል፡፡
፪. ሥዕሎች
ሀ) አጥጋቢ የሆነ ቅጅ ለማውጣት እንዲቻል ቀለም አልባ በሆኑ በበቂ መጠን ደማቅና ጥቁር እንዲሁም ወጥ ስፋትና ግልፅነት ባላቸው መስመሮችና ጭረቶች ሊሰሩ ይገባል፤
ለ) የአንድ ሥዕል ክፍል እይታ የመሪ መስመሮችንና የአመልካች ምልክቶችን ተነባቢነት በማይከለክል አኳኋን ተጋዳሚና ተደጋጋሚ መስመሮችን በመጠቀም መታየት ይኖርበታል፤
ሐ) የሥዕሎች ስኬልና የግራፊክ አሰፋፈራቸው የግልጽነት ደረጃ ወደ ሁለት ሶስተኛ በተቀነሰ የፎቶ ግራፍ ቅጅአቸው ሁሉንም ዝርዝር ያለምንም ችግር በቀላሉ ለመለየት የሚረዳ መሆን አለበት፤ በተለየ ምክንያት ስኬሉ በሥዕሉ ላይ ተሰጥቶ ከሆነ በግራፍ መልክ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡
መ) በሥዕሉ ላይ የሚታዩት ቁጥሮች፣ ፊደላት እና ጠቋሚ ምልክቶች ቀላልና ግልጽ መሆን ያለባቸው ሲሆን ቅንፎች፣ ክቦች እና የጥቅስ ምልክቶች ከቁጥሮች እና ከፊደላት ጋር በተያያዘ መንገድ አገለግሎት ላይ መዋል አይኖርባቸውም፤
ሠ) ለሥዕሉ ጥራት ሲባል የመጠን ልዩነት ማድረግ አስፈላጊ እስካልሆነ ድረስ የአንድ ሥዕል አካሎች መጠን እርስ በእርሳቸው ተመጣጣኝ መሆን አለባቸው፤
ረ) የቁጥሮችና የፊደላት ከፍታ ከዜሮ ነጥብ ፴፪ ሣ.ሜ ማነስ የሌለበት ሲሆን ሥዕሎችን ለማመልከት የላቲን እና የተለመደም ሆኖ ሲገኝ የግሪክ ፊደላትን መጠቀም ይቻላል፤
ሰ) አንድ የሥዕል ወረቀት ብዙ ምስሎችን ሊይዝ ይችላል፡፡ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ወረቀቶች ላይ የተሣሉ ሥዕሎች አንድ ሙሉ ሥዕልን የሚመሠርቱ ከሆነ እነኝሁ ሥዕሎች የስእሉን ማናቸውም አካል ሳይደብቁ ሊቀናጁ በሚችሉበት መንገድ መዘጋጀት አለባቸው፡፡ የተለያዩት ሥዕሎች በግልጽ አንዱ ከሌላው የሚለዩ ሆነው ቦታ ሳይባክን ሊቀናጁ የሚችሉ መሆን አለባቸው፤ለየገፁ ከተሰጠው ቁጥር ጋር ሳይገናዘቡ ለተለያዩ ሥዕሎች ተከታታይነት ያለው የአረብ ቁጥር መሰጠት ይኖርበታል፤
ሸ) በመግለጫ ወይም በመብት ወሰን ጥያቄዎች ለይ ያልተገለጹ ጠቋሚ ምልክቶች በስዕሎች ላይ ወይም በሥዕሎች ላይ ያልተገለጹ ጠቋሚ ምልክቶች በመግለጫው ወይም በመብት ወሰን ጥያቄዎች ላይ መታየት የለባቸውም፡፡ አንድ ዓይነት ገጽታዎች በጠቋሚ ምልክቶች ከተገለጹ ይህ ሁኔታ በማመልከቻው ውስጥ ያለምንም ለውጥ ስራ ላይ መዋል ይኖርበታል፡፡
ቀ) ስዕሎችን ለመረዳት አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ በስተቀር ማብራሪያ ጽሑፍ ተያይዞ መቅረብ የለበትም፡፡ እንደ ‹‹ውሀ›› ‹‹እንፋሎት›› ‹‹ክፍት ነው›› ‹‹ዝግ ነው›› በክፍል ሀሀ›› ያለ ቃል ወይም ቃላት እንዲሁም በብሎክ ስኬማቲክ ወይም በፍሎው ሺት ዲያግራም ውስጥ አጭርና ገላጭ ቃላት መካተት አይኖርባቸውም፤
በ) ስዕሎች ያረፉባቸው ገጾች በዚህ ደንብ አንቀጽ ፲፮(፯) በተደነገገው መሠረት ቁጥር ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
፫. የፍሎው ሺት እና ዲያግራሞች ሥዕሎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

፲፬. የፈጠራ አጭር ይዘት
፩. የፈጠራው አጭር ይዘት በአንድ የተወሰነ ጥበብ ዘርፍ ቀልጣፋ ፍለጋ ለማድረግ የሚያገለግል መሳሪያ በመሆን መዘጋጀት ያለበት ሆኖ ተጠቃሚው ሙሉ ማመልከቻውን ለመመልከት አስፈላጊ መሆኑን እና አለመሆኑን ለመወሰን የሚያስችለው ሆኖ መዘጋጀት አለበት፡፡
፪. የፈጠራው አጭር ይዘት የሚከተሉትን መያዝ አለበት፤
ሀ) ከፈጠራው ጋር የሚዛመደውን የቴክኒክ መስክ የሚጠቁም እና ቴክኒካዊ ችግሩን፣ ፈጠራው ለችግሩ የሚሰጠውን ዋና መፍትሄ እና የፈጠራውን ዋና ጥቅም ወይም ጥቅሞች በግልጽ ለመረዳት እንዲያስችል ሆኖ የተዘጋጀ በመግለጫው በመብት ወሰን ጥያቄውና በስዕሎች የተካተቱ የፈጠራው ገዐድነት ማጠቃለያ፤
ለ) እንደአግባቡ በማመልከቻው ውስጥ ከተካተቱ የኬሚካል ፎርሙላዎች መካከል በተሻለ ሁኔታ ፈጠራውን የሚገልጽ የኬሚካል ፎርሙላ፡፡
፫. የፈጠራው ገሀድነት በሚፈቅደው መጠን የፈጠራው አጭር ይዘት አጠር ያለ ሆኖ በፈጠራው ይገኛል ተብሎ ስለሚጠበቅ በጎ ጎን ወይም ዋጋ ወይም ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ስለሚባልበት ሁኔታ መግለጫ መያዝ የለበትም፡፡
፬. በፈጠራው አጭር ይዘት የተገለፀና በማመልከቻው ውስጥ ባሉ ስዕሎች የተመለከተ እያንዳንዱ አብይ ቴክኒካዊ ባህርይ በቅንፍ ውስጥ የተቀመጡ ጠቋሚ ምልክቶችን ማስከተል አለበት፡፡
፭. የፈጠራው አጭር ይዘት በአመልካቹ ከቀረቡት ሥዕሎች መካከል በይበልጥ ገላጭ ከሆነው ሥዕል ጋር አብሮ መሆን አለበት፡፡

፲፭. መለኪያዎች፣ ቃላቶች እና ምልክቶች
፩. የክብደት እና የርዝመት መለኪያዎች በሜትሪክ ሲስተም መገለጽ አለባቸው፡፡
፪. የሙቀት መጠን በዲግሪ ሴንትግሬድ መገለጽ አለበት፡፡
፫. እፍጋት በሜትሪክ አሀድ መግለፅ ይኖርበታል፡፡
፬. ሙቀት፣ ኃይል፣ ብርሀን፣ ድምፅ እና መግነጢሳዊነት እንዲሁም የሂሳብ ፎርሙላዎችን እና የኤሌክትሪክ አሀዶችን ለማመልከት በጥቅም ላይ ያሉ አጠቃላይ ደንቦችን መከተል ያስፈልጋል፡፡ ስለኬሚካል ፎርሙላዎች በአጠቃላይ አገልግሎት ላይ የዋሉ ምልክቶችን የአቶም ክብደቶችን እና የሞሎኪዊል ፎርሙላዎችን መገልገል ያስፈልጋል፡፡
፭. በአንድ የጥበብ መስክ በአጠቃላይ ተቀባይነት ያገኙት የቴክኒክ ቃላትና ምልክቶች ብቻ በጥቅም ላይ መዋል አለባቸው፡፡
፮. በማመልከቻ ውስጥ የቃላትና ምልክቶች አጠቃቀም መዛባት የለበትም፡፡

፲፮. የቅጅዎች ብዛትና የአቀራረብ መልክ
፩. የዚህ ደንብ አንቀጽ ፳(፯) ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ማመልከቻዎችና ማናቸውም ተያይዘው የሚቀርቡ ማብራሪያዎች ወይም ሠነዶች በሦስት ቅጅ መቅረብ አለባቸው፡፡ ነገር ግን ኮሚሽኑ አመልካቹን ተጨማሪ ቅጂዎች እንዲያቀርብ ሊጠይቀው ይችላል፡፡
፪. ሁሉም የማመልከቻው ክፍሎች በፎቶግራፍ፣ በኤሌክትሮ ስታቲክ ሂደት፣ በፎቶ ኦፍ ሴትና በማይክሮ ፊልም በቀጥታ ሊባዙ በሚችሉበት መልክ መቅረብ አለባቸው፡፡
፫. በማመልከቻው ውስጥ ያለ የእያንዳንዱ ወረቀት አንዱ ገጽ ብቻ ጥቅም ላይ መዋል አለበት፡፡
፬. ሁሉም የማመልከቻው ክፍሎች ተጣጣፊ፣ ጠንካራ፣ ነጭ፣ ለስላሣ፣ የማያንፀባርቅ እና ረጅም እድሜ በሚቆይ ወረቀት ላይ ሠፍረው መቅረብ አለባቸው፡፡
፭. የወረቀቶች መጠን ኤ፬ (፳፱ ነጥብ ፯ ሣ.ሜ x ፳፩ ሣ.ሜ) መሆን አለበት፡፡
፮. የዚህ ደንብ አንቀጽ ፲፫(፩) ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ የወረቀቶቹ አነስተኛ ህዳጎች እንደሚከተለው መሆን አለባቸው፡፡
ሀ) ከመጀመሪያው ገፅ በስተቀር የሌሎቹ ገፆች በሙሉ የላይኛው ህዳግ ፳ ሚ.ሜ
ለ) የመጀመሪያው ገፅ የላይኛው ህዳግ ፴ ሚ.ሜ.
ሐ) ወረቀቱ በሚጠረዝበት በኩል ያለው የጎን ህዳግ ፳፭ ሚ.ሜ.
መ) ሌላኛው የጎን ህዳግ ፳ ሚ.ሜ.
ሠ) የታችኛው ህዳግ ፳ ሚ.ሜ.
፯. ሀ) የዓረባዊ ቁጥሮች በሁሉም ወረቆች አናት መሀከሉ ላይ በተከታታይ መፃፍ አለባቸው፡፡
ለ) ለወረቀቶች ተከታታይ ቁጥር ሲሰጥ የማመልከቻው ክፍሎች ጥያቄ፣ መግለጫ፣ የመብት ወሰን፣ አጭር መግለጫ እና ሥዕል በተራ ሊቀመጡ ይገባል፡፡
ሐ) ለወረቀቶቹ ተከታታይነት ያለው ቁጥር አሰጣጥ ሶስት የተለያዩ የቁጥር አሰጣጥ ተራዎችን በመጠቀም ሆኖ የመጀመሪያው ተራ ለጥያቄው ብቻ የሚያገለግልና ከጥያቄው የመጀመሪያው ገፅ የሚጀምር ነው፡፡ ሁለተኛው ተራ ከመግለጫው የመጀመሪያ ገጽ የሚጀምርና የጥበቃ ወሰንን አካትቶ እስከ አጭር ይዘቱ የመጨረሻ ገፅ የሚቀጥል ነው፡፡ ሦስተኛው ተራ ሥዕሎችን ለያዙ ገፆች ብቻ የሚያገለግልና ከስዕሎች የመጀመሪያ ገፅ የሚጀምር ነው፡፡
፰. የማመልከቻው ጽሑፍ መተየብ ያለበት ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ግራፊክ ምልክቶች የኬሚካል ወይም የሂሣብ ፎርሙላዎች እና የተወሰኑ ካራክተሮች በእጅ ሊፃፉ ወይም ሊሣሉ ይችላሉ፡፡
፱. ሥዕሎች ሲሣሉ ያለ ቀለም ዘላቂነት ባለው ጥቁር በበቂ መጠን ወፈር እና ደመቅ ባሉ አንድ ወጥ ስፋት እና በግልጽ በተቀመጡ መስመሮችና ጭረቶች መሆን አለበት፡፡

፲፯. የፈጠራ አሀዳዊነት
፩. የአዋጁ አንቀጽ ፱ (፪) ከሚከተሉት ሦስት አማራጮች በተለይ
ሀ) ለአንድ ምርት ከሚቀርብ ራሱን የቻለ የመብት ወሰን ጥያቄ በተጨማሪ በተለይ የተጠቀሰውን ምርት ለማምረት የሚረዳ የምርት ሂደት ራሱን የቻለ የመብት ወሰን ጥያቄ እንዲሁም የተጠቀሰውን ምርት የመጠቀም ራሱን የቻለ የመብት ወሰን ጥያቄ በአንድ ማመልከቻ ውስጥ ማካተትን፤ ወይም
ለ) ለአንድ የምርት ሂደት ከሚቀርብ ራሱን የቻለ የመብት ወሰን ጥያቄ በተጨማሪ ሂደቱን ተግባራዊ ለማድረግ በተለይ ለተዘጋጀ መሣሪያ ወይም ዘዴ ራሱን የቻለ የመብት ወሰን ጥያቄ በአንድ ማመልከቻ ውስጥ ማካተትን፤ ወይም
ሐ) ለአንድ ምርት ከሚቀርብ ራሱን የቻለ የመብት ወሰን ጥያቄ በተጨማሪ በተለይ የተጠቀሰውን ምርት ለማምረት የሚረዳ የምርት ሂደት ራሱን የቻለ የመብት ወሰን ጥያቄ እና ሂደቱን ተግባራዊ ለማድረግ ለማከናወን በተለይ ለተዘጋጀ መሣሪያ ወይም ዘዴ ራሱን የቻለ የመብት ወሰን ጥያቄ በአንድ ማመልከቻ ውስጥ ማካተትን የሚፈቅድ ሆኖ ሊተረጐም ይገባል፡፡
፪. የአዋጁ አንቀጽ ፱(፪) እንደተጠበቀ ሆኖ በአንድ ማመልከቻ ውስጥ በአንድ መደብ የሚፈረጁ ሆኖም በቀጥታ በአንድ አጠቃላይ የመብት ወሰን የማይካተቱ ሁለት ወይም ከዛ በላይ ራሳቸውን የቻሉ የመብት ወሰን ጥያቄዎችን ማቅረብ ይፈቀዳል፡፡
፫. የአዋጁ አንቀጽ ፱(፪) እንደተጠበቀ ሆኖ በአንድ ማመልከቻ ውስጥ ራሱን በቻለ የመብት ወሰን ጥያቄ ስር የተመለከቱት የተለያዩ የፈጠራውን መስኮች የሚመለከቱ ተገቢ ቁጥር ያላቸው ጥገኛ የመብት ወሰን ጥያቄዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡
፬. በአዋጁ አንቀጽ ፱(፪) መሠረት የፈጠራ አሀዳዊነት መመዘኛ ለማያሟላ ማመልከቻ ፓተንት መስጠት ለፓተንቱ መሰረዝ ምክንያት አይሆንም፡፡

፲፰. ማመልከቻን ስለማሻሻልና መከፋፈል
፩. ማሻሻያው በመጀመሪያው ማመልከቻ ከተገለፀው ውጪ የሆነ ነገር የማያስከትል ከሆነ አመልካቹ ፓተንት እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ ማመልከቻውን ማሻሻል ይችላል፡፡
፪. እያንዳንዱ ክፋይ ማመልከቻ በመጀመሪያው ማመልከቻ ላይ ከተገለጸው ውጪ የሆነ ነገር የማያስከትል ከሆነ ፓንተን እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ አመልካቹ ማመልከቻውን ወደ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ማመልከቻዎች ሊከፋፍል ይችላል፡፡
፫. እያንዳንዱ ክፋይ ማመልከቻ የመጀመሪያው ማመልከቻ የምዝገባ ቀንና እንደአግባቡ የመጀመሪያው ማመልከቻ የቀዳሚነት ቀን ይኖረዋል፡፡
፬. አንድ ክፋይ ማመልከቻ የመጀመሪያውን ማመልከቻ የሚጠቅስ ክፍል መያዝ አለበት፡፡
፭. አመልካቹ ክፋይ ማመልከቻው የመጀመሪያው ማመልከቻ ማናቸውም የቀዳሚት ጥያቄ ተጠቃሚ እንዲሆን ከፈለገ ክፋይ ማመልከቻው ይህንኑ የሚያመለክት ጥያቄ መያዝ አለበት፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የመጀመሪያው ማመልከቻ የቀዳሚነት መግለጫ እና በዚህ ደንብ አንቀጽ ፳ መሠረት የቀረቡ ሠነዶች ለከፋይ ማመልከቻው የሚያገለግሉ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
፮. ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ቀድመው የገቡ ማመልከቻዎች ቀዳሚነት ለመጀመሪያው ማመልከቻ የተጠየቀ እንደሆነ ክፋይ ማመልከቻው ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው አግባብ ካለው /ካላቸው የቀዳሚነት ጥያቄ/ ጥያቄዎች ነው፡፡

፲፱. አስቀድሞ ለህዝብ የተገለጸ ፈጠራ እንደቀደምት ጥበብ ስለማይቆርበት ሁኔታ
በአዋጁ አንቀጽ ፫(፫) መሠረት ቀደም ሲል የተከናወነ ፈጠራውን ገሀድ የማድረግ ተግባር እንደቀደምት ጥበብ እንዳይቆጠር ፍላጎት ያለው አመልካች ይህንኑ በማመልከቻው ላይ መግለጽ እና ከማመልከቻው ጋር ወይም ማመልከቻው በገባ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በጽሁፍ የገሀድነቱን ሙሉ መግለጫ ማቅረብ አለበት፡፡ ለገሀድነት የበቃው በኢግዚቢሽን ላይ ከሆነ አመልካቹ ከላይ በተገለጸው ጊዜ ውስጥ የኢግዚቢሽኑ ኃላፊ በሆነው አካል የተዘጋጀና የተፈረመ የኢግዚቢሽኑ ኃላፊ በሆነው አካል የተዘጋጀና የተፈረመ የኢግዚቢሽኑን ልዩ ባህርይ የሚገልጽና በእርግጥም ፈጠራው በኢግዚቢሽኑ መቅረቡን የሚያረጋግጥ ሰርተፊኬት ማቅረብ አለበት፡፡

፳. ቀዳሚነትን ስለማሳወቅና ስለቀዳሚ ማመልከቻ ትርጉም
፩. በአዋጁ አንቀጽ ፲፩(፪) የተገለጸው መግለጫ የሚከተሉትን ማመልከት አለበት፤
ሀ) የቀዳሚውን ማመልከቻ ቀን፤
ለ) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የቀዳሚውን ማመልከቻ ቁጥር፤
ሐ) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፫) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ቀዳሚ ማመልከቻው የተመደበበትን የዓለም አቀፍ ፓተንት ምደባ መለያ፤
መ) ቀዳሚ ማመልከቻው ቀርቦበት የነበረው ሀገር ወይም ቀዳሚ ማመልከቻው አህጉራዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ ማመልከቻ ከሆነ በማመልከቻው የተመለከቱትን ሀገሮች፤
ሠ) ቀዳሚ ማመልከቻው አህጉራዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ ከሆነ ማመልከቻው የቀረበበት ጽሕፈት ቤት፡፡
፪. በአዋጁ አንቀጽ ፲፩ (፪) መሠረት የተገለጸው መግለጫ በሚቀርብበት ወቅት የቀዳሚ ማመልከቻው ቁጥር የማይታወቅ ከሆነ መግለጫውን የያዘው ማመልከቻ ከገባበት ቀን ጀምሮ ባሉ ሶስት ወራት ውስጥ ቁጥሩ መገለጽ አለበት፡፡
፫. ቀዳሚ ማመልከቻው የዓለም አቀፍ የፓተንት ምደባ መለያ ያልተሰጠው ወይም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) ላይ የተገለጸው መግለጫ በቀረበበት ጊዜም መለያው ያልተሰጠው ከሆነ አመልካቹ በመግለጫው ላይ ይህንኑ መግለጽና መለያው እንደተሰጠ ወዲያውኑ ማሳወቅ አለበት፡፡
፬. አመልካቹ ፓተንት ከመሰጠቱ አስቀድሞ በማንኛውም ጊዜ በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ (፩) የተገለጸውን መግለጫ ይዘት ሊያሻሽል ይችላል፡፡
፭. በአዋጁ አንቀጽ ፲፩(፪) የተገለጸው የቀዳሚ ማመልከቻ የተረጋገጠ ቅጅ ማቅረቢያ ጊዜ ኮሚሽኑ ጥያቄ ካቀረበበት ቀን ጀምሮ ለሶስት ወራት ይሆናል፡፡ ቅጅው ለሌላ ማመልከቻ የተሰጠ ከሆነ አመልካቹ ይህንኑ በማመልከት ምላሽ መስጠት ይችላል፡፡
፮. ቀዳሚ ማመልከቻው የቀረበው ከእንግሊዝኛ ወይም ከአማርኛ በተለየ ቋንቋ ሲሆን አመልካቹ የቀዳሚ ማመልከቻውን የእንግሊዝኛ ወይም የአማርኛ ትርጉም በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (፭) የተገለፀው ጥያቄ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
፯. ኮሚሽኑ የተለየ ጥያቄ ካላቀረበ በስተቀር የቀዳሚነት ማመልከቻውና ማናቸውም የዚሁ ትርጉም በአንድ ቅጅ ብቻ ይቀርባል፡፡

፳፩. የውጪ አገር አመልካች
፩. በአዋጁ አንቀጽ ፲ (፪) እና በዚህ አንቀጽ መሠረት የቀረቡ ሰነዶች የሚያገለግሉት የፓተንት ማመልከቻ የቀረበበትን ፈጠራ አዲስነት እና ፈጠራዊ ብቃት ግምገማ ለማገዝ ብቻ ይሆናል፡፡
፪. የውጭ አገር አመልካች በዚህ አንቀጽ መሠረት ባቀረባቸው ሰነዶች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ሊያቀርብ ይችላል፡፡
፫. በኢትዮጵያ ውስጥ የመኖሪያ ቦታ ወይም የንግድ ጽሕፈት ቤት በሌለው የውጭ ዜጋ፤ የውጭ ኢንተርፕራይዝ ወይም ሌላ የውጪ ድርጅት ለፓተንት ማመልከቻ ሲቀርብና ኮሚሽኑ ጥርጣሬ ሲያድርበት አመልካቹ የሚከተሉትን ሰነዶች እንዲያቀርብ ሊጠይቅ ይችላል፤
ሀ) የአመልካቹን  ዜግነት የሚመለከት ሰርተፊኬት፤
ለ) የውጭ ኢንተርፕራይዙን ወይም ሌላ የውጭ ድርጅቱን ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ የሚመለከት ሠርተፊኬት፤
ሐ) የአንድ የውጭ ዜጋ፣ የውጭ ኢንተርፕራይዝ ወይም የሌላ የውጭ ሀገር ድርጅት ለዜጎቿ ተፈጻሚ በሚሆንበት መልክ የኢትዮጵያ ዜጎች ወይም ድርጅቶች በሀገሪቱ ፓተንት የማግኘት መብት እንዳላቸው እውቅና የምትሰጥ መሆኑን ማረጋገጫ፡፡

፳፪. ተዛማጅ የውጪ ማመልከቻ፣ ፓተንት እና ሌሎች የጥበቃ
አይነቶችን አስመልክቶ መረጃ ስለማቅረቢያ ጊዜ
፩. በአዋጁ አንቀጽ ፲ መሠረት የተጠየቀ መረጃን የማቅረቢያ ጊዜ ገደብ ጥያቄው ከረቀበበት ቀን ጀምሮ ከሁለት ወር ማነስ ወይም ከስድስት ወር መብለጥ የለበትም፡፡ ሆኖም በአመለካቹ አሳማኝ ጥያቄ ኮሚሽኑ የጊዜ ገደቡን ሊያራዝም ይችላል፡፡
፪. በአዋጁ አንቀጽ ፲ መሠረት የተጠየቁትን ሰነዶች አመልካቹ ሊያገኛቸው እንዳልቻለ መልስ ከሰጠ ኮሚሽኑ የማመልከቻውን ምርመራ ሂደት ሰነዶቹ እስከ ሚቀርቡበት ጊዜ ድረስ ሊያግደው ይችላል፡፡

፳፫. ማመልከቻን ስለመተው
፩. አንድ ማመልከቻ አመልካቹ በፈረመበትና ለኮሚሽኑ በቀረበ የጽሁፍ መግለጫ ይተዋል፡፡
፪. ማመልከቻው ቢተውም የማመልከቻ ክፍያው ተመላሽ አይሆንም፡፡

፳፬. ማመልከቻ ላይ ምልክት ስለማድረግ
፩. ማመልከቻው እንደደረሰ ኮሚሽኑ ማመልከቻው በሚያቅፈው እያንዳንዱ ሰነድ ላይ ማመልከቻው የደረሰበትን እርግጠኛ ቀንና ኢት የሚሉ ፊደሎች እዝባር ፓ በሚል ፊደል እዝባር የመጀመሪያ ወረቀት የደረሰበት ዓመት የመጨረሻ ሁለት ቁጥሮች እዝባርና ማመልከቻዎች ሲደርሱ የሚሰጡ ተከታታይነት ያላቸው ፭ ቁጥሮች የያዘ የማመልከቻ ቁጥር ማስፈር አለበት፡፡ እርማቶቹ ወይም ዘግይተው የገቡ ሰነዶች በሌላ ቀን ሲደርሱ ኮሚሽኑ የደረሱበትን እርግጠኛ ቀን አግባብ ባለው ቦታ የፓተንት ጥያቄ በቀረበበት ሰነድ (ቅጽ ቁጥር ዜሮ ፩) ላይ ያሰፍራል፡፡
፪. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (፩) መሠረት ለማመልከቻ የተሰጠ ቁጥር ማመልከቻውን አስመልክቶ በሚደረግ የደብዳቤ ልውውጥ ላይ መጠቀስ አለበት፡፡

፳፭. የምዝገባ ቀን መስጠት እና ማሳወቅ
፩. ኮሚሽኑ የምዝገባ ቀን ለመስጠት ማመልከቻው የአዋጁን አንቀጽ ፲፪(፩) መመዘኛዎች የሚያሟላ መሆኑን ይመረምራል፡፡
፪. በአዋጁ አንቀጽ ፲፪(፪) መሠረት የሚቀርብ ማናቸውም ማሻሻያ የማቅረብ ጥሪ በጽሁፍ መደረግ ያለበት ሲሆን ተፈላጊውን ማሻሻያ መግለጽና ማሻሻያው ጥሪው ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ባለው የሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ከተመደበው ክፍያ ጋር እንዲቀርብ መጠየቅ አለበት፡፡
፫. ኮሚሽኑ የምዝገባ ቀን ከሰጠ በኋላ ለአመልካቹ በጽሁፍ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ሆኖም በአዋጁ አንቀጽ ፲፪(፪) መሠረት ማመልከቻው እንዳልቀረበ የተቆጠረ እንደሆነ ኮሚሽኑ ለአመልካቹ ምክንያቶችን በመዘርዘር በጽሁፍ ያሳውቃል፡፡

ክፍል ፪
ስለማመልከቻ ምርመራ
፳፮. መርማሪ ከመሆን ስለመገለል
አንድ መርማሪ በራሱ ፍላጎት፣ ወይም በአመልካቹ ወይም በሌላ ማናቸውም ጉዳዩ በሚመለከተው ወገን በሚቀርብ ጥያቄ ከምርመራ ሥራው የሚገለለው፤
፩. ከአመልካቹ ወይም ከፓተንት ወኪሉ ጋር የቅርብ ዝምድና ያለው ሆኖ ሲገኝ፣
፪. በፓተንት ማመልከቻው ላይ ጥቅም ያለው ሲሆን፣
፫. ከአመልካቹ ወይም ከፓተንት ወኪሉ ጋር ያለው ማንኛውም ሌላ አይነት ግንኙነት አድሎአዊ ያልሆነ የማመልከቻ ምርመራ ላይ ተፅእኖ ሊያሳድር የሚችል ሆኖ ሲገኝ ይሆናል፡፡

፳፯. የፎርማሊቲ ምርመራ
፩. በአዋጁ አንቀጽ ፱(፫) ና (፬) (ሀ) እና ይህንኑ በተመለከተ በደንቡ ከተገለጹት መሟላት ከሚገባቸው ሁኔታዎች በተጨማሪ የአዋጁ አንቀጽ ፭፣፰፣፱(፯) እና (፰) እንዲሁም ፲ ለአዋጁ ዓላማ ፎርማሊቲን አስመልክቶ መሟላት የሚገባቸው ሁኔታዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
፪. በአዋጁ አንቀጽ ፲፫ (፪) እና በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት የተጠቀሱት ሁኔታዎች ተሟልተው ያልተገኙ እንደሆነ ኮሚሽኑ አመልካቹን በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን ማሻሻያ ከተመደበው ክፍያ ጋር እንዲያቀርብ በጽሁፍ ይጠራዋል፡፡
፫. አመልካቹ የተጓደለውን ለማሟላት በተደረገው ጥሪ መሰረት ምላሽ ያላቀረበ ሲሆን ወይም አመልካቹ ማሻሻያ ያቀረበ ቢሆንም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ(፩) የተገለጹት ሁኔታዎች ያልተሟሉ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ሲያምን ማመልከቻውን ውድቅ በማድረግ ለአመልካቹ ምክንያቱን ገልጾ በጽሁፍ ያሳውቃል፡፡
፬. የማመልከቻው ውድቅ መሆን የምዝገባውን ቀን ተቀባይነት አያሳጣውም፡፡

፳፰. የሥረ-ነገር ምርመራ
፩. በአዋጁ አንቀጽ ፲፫(፫) መሠረት ኮሚሽኑ በሚሰይማቸው ልምድ ባላቸው የቴክኒክና የህግ ኤክስፐርቶች አማካኝነት የሥረ-ነገር ምርመራ ይከናወናል፡፡
፪. የፍለጋና የምርመራ ክፍያ ከተፈጸመ በኋላ ኮሚሽኑ ማመልከቻውን አግባብ ካላቸው ሰነዶች ጋር በማያያዝ በአዋጁ አንቀጽ ፲፫(፫) መሠረት የሚከናወነውን የምርመራ ተግባር በተመለከተ ከኮሚሽኑ ጋር ስምምነት ላደረገ የምርመራ ባለሥልጣን መላክና የፍለጋና የምርመራ ዘገባ እንዲላክለት መጠየቅ ይችላል፡፡
፫. አንድ ማመልከቻ በአዋጁ አንቀጽ ፫፣፬፣፯፣፱(፪) (፬) (ለ) (ሐ) እና (፭) እና አግባብነት ባላቸው የዚህ ደንብ ድንጋጌዎች የተገለጹትን ሁኔታዎች የሚያሟላ መሆኑን ይመረመራል፡፡
፬. ኮሚሽኑ የፍለጋና ምርመራ ሪፖርት ውጤትን ግምት ውስጥ በማስገባት በአዋጁ እና በዚህ ደንብ የተገለፁት መመዘኛዎች ያልተሟሉ መሆናቸውን ሲያምን አመልካቹን በመጥራት (አስፈላጊ ከሆነ ጥሪው ተደጋጋሚ ሊሆን ይችላል) ማመልከቻውን በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ አሻሽሎ ወይም ከፋፍሎ እንዲያቀርብ በጽሁፍ ይጠይቀዋል፡፡ የጊዜ ገደቡ ለአመልካቹ ጥሪ ከሚደረግበት ቀን ጀምሮ ከሁለት ወር ያላነሰ ወይም ከስድስት ወር ያልበለጠ ይሆናል፡፡ ጥሪውም የሚከናወነው በቅጽ ፪ መሠረት ነው፡፡
፭. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፬) እና በዚህ ደንብ አንቀጽ ፲፰ መሠረት የሚደረግ ማናቸውም ማሻሻያ ከተወሰነለት ክፍያ ጋር መከናወን አለበት፡፡
፮. አመልካቹ በጥሪው መሠረት ተገቢውን ሳያደርግ ሲቀር ወይም አመልካቹ ያቀረበው ማንኛውም አስተያየት፣ ማሻሻያ ወይም ክፍፍል የምርመራና ፍለጋ ሪፖርቱን ውጤት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲታይ በአዋጁና በዚህ ደንብ የተዘረዘሩ ሁኔታዎችን የማያሟላ መሆኑ ሲታመን ኮሚሽኑ ማመልከቻውን ውድቅ ያደርጋል፡፡ ይህንኑም ለአመልካቹ በጽሁፍ ያሳውቃል፡፡

ክፍል ፫
ፓተንት ስለመስጠትና ስለፓተንት ይዘት
፳፱. ፓተንት የመሰጠት ወይም የመከልከል ውሳኔ
፩. ተመሳሳይ የምዝገባ ቀን ወይም እንደ አግባቡ ተመሳሳይ የቀዳሚነት ቀን ያላቸው አንድን ፈጠራ የሚመለከቱ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ማመልከቻዎች በአንድ አመልካች ሲቀርቡ ኮሚሽኑ በዚሁ ምክንያት ከአንድ በላይ ለሆኑ ማመልከቻዎች ፓተንት አልሰጥም ብሎ መከልከል ይችላል፡፡
፪. ኮሚሽን የፍለጋና ምርመራ ሪፖርት ውጤትን ግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ ደንብ አንቀጽ ፳፰ የተጠቀሰውን መሠረት በማድረግ የአዋጁ አንቀጽ ፲፫ (፫) ሁኔታዎች መሟላታቸውን ሲያምን ፓተንት ይሰጣል፡፡
፫. ኮሚሽኑ ፓተንት ለመስጠት ወይም ለመከልከል የሰጠውን ውሳኔ ለውሳኔው መሠረት ከሆነው የፍለጋና ምርመራ ሪፖርት ቅጅ ጋር በማያያዝ ለአመልካቹ በጽሁፍ ያሳውቃል፡፡ በተጨማሪም ውሳኔው የፓተንት መሰጠትን የማከለክል ሲሆን ዝርዝር ምክንያቶቹ መገለጽ አለባቸው፡፡ ውሳኔው ፓተንት ለመስጠት ሲሆን አመልካቹ ውሳኔውን ካወቀበት ቀን ጀምሮ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ የፓተንትና የህትመት ክፍያ እንዲፈጽም ይጠይቃል፡፡

፴. ፓተንት ስለመስጠት
፩. የፓተንትና የህትመት ክፍያ ፓተንት ለመስጠት መወሰኑ ከታወቀበት ቀን ጀምሮ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ የተከፈለ እንደሆነ በአዋጅ አንቀጽ ፲፬ (፩) እና በዚህ አንቀጽ ድንጋጌዎች መሰረት ኮሚሽኑ ፓተንት ይሰጣል፡፡
፪. ኮሚሽኑ ለእያንዳንዱ ለሚሰጠው ፓተንት እንደአሰጣጡ ቅደም ተከተል የፓተንት የህትመት ቁጥር ይሰጣል፡፡
፫. ፓተንቱ፣
ሀ) በቅጽ ቁጥር ፫ መሠረት የሚሰጥና በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (፪) ከተገለጸው መረጃ በተጨማሪ የፓተንቱን ህትመት ቀን፣ በቀደምት ጥበብ የተመለከቱ ሰነዶች ዋቢዎች፣ የፈጠራው መግለጫ፣ የመብት ወሰንና ካሉም ስዕሎችን ያካትታል፤
ለ) እንደተሰጠ የሚገመተው ኮሚሽኑ በአዋጁ አንቀጽ ፲፬(፪)(ሀ) ስለፓተንቱ መሰጠት ጠቅሶ በህትመት ባወጣበት ቀን ነው፡፡

፴፩. ፓተንት ስለመሰጠቱ ጠቅሶ ስለማተም
ፓተንት ስለመሰጠቱ ተጠቅሶ የሚወጣ ህትመት፤
፩. የፓተንቱን ቁጥር፤
፪. የፓተንት ባለቤቱን ስምና አድራሻ፤
፫. በፓተንቱ ውስጥ ስሙ እንዳይጠቀስ ካልጠየቀ በስተቀር የፈጠራ ሰራተኛውን ስምና አድራሻ፤
፬. በኖረ ጊዜ የወኪሉን ስምና አድራሻ፤
፭. የማመልከቻውን የምዝገባ ቀንና ቁጥር፤
፮. ቀዳሚነት ከተጠየቀና ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘ ቀዳሚነቱን የሚመለከት መግለጫ፣ የቀዳሚነት ቀንና ቀዳሚው ማመልከቻ የገባበትን ሀገር ወይም ሀገሮች ስም፤
፯. ፓተንት የተሰጠበትን ትክክለኛ ቀን፤
፰. የፈጠራውን ርዕስ፤
፱. የፈጠራውን አጭር ይዘት፤
፲. በኖረ ጊዜ ከስዕሎቹ መካከል በይበልጥ ገላጭ የሆነውን እንዲሁም፤
፲፩. የዓለም አቀፍ ፓተንት ምደባ ምልክትን ማካተት አለበት፡፡

፴፪. የፓተንት ሰርተፊኬት ስለመስጠት
የፓተንት መሰጠት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት በቅጽ ቁጥር 5 ላይ መዘጋጀት፣ በኮሚሽነሩ መፈረምና፤
፩. የፓተንቱን ቁጥር፤
፪. የፓተንት ባለቤቱን ስምና አድራሻ፣
፫. የምዝገባውን ቀንና እንደአግባቡ የማመልከቻውን የቀዳሚነት ቀን፣
፬. ፓተንት የተሰጠበትን ትክክለኛ ቀን እና፣
፭. የፈጠራውን ርዕስ ማካተት አለበት፡፡

፴፫. ስለፓተንት መብት መራዘም
በአዋጁ አንቀጽ ፲፮ መሠረት የፓተንት መብት ጥበቃ ዘመን የማራዘም ጥያቄ በጽሁፍ ለኮሚሽኑ መቅረብና ፈጠራው በኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ላይ የዋለበትን ዝርዝር ሁኔታ ከሚገልጽ በፓተንት ባለቤቱ የተፈረመበት መግለጫ ጋር ተያይዞ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

ክፍል ፬
ፈቃድ በተሰጠው ሰው በፓተንት
የሚጠበቅን ፈጠራ ጥቅም ላይ ስለማዋል
፴፬. በፓተንት የሚጠበቅን ፈጠራ በመንግሥት ወይም
በመንግሥት ሥልጣን በተሰጣቸው ሦስተኛ ወገኖች ጥቅም ላይ
ስለማዋል
፩. ኮሚሽኑ በአዋጁ አንቀጽ ፳፭(፪) መሠረት ውሳኔ ከመስጠቱ አስቀድሞ ለባለፓተንቱ፣ ለግዴታ ፈቃድ ተጠቃሚዎች እና ለማንኛውም ተሳትፎው ጠቃሚ ይሆናል ብሎ ለሚገምተው ወገን ጉዳያቸው ከሚሰማበት ቀን በፊት ቢያንስ ሀያ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የጽሑፍ ማስታወቂያ መስጠት አለበት፡፡ ባለፓተንቱ ፓተንቱን በፈቃድ ለወሰዱ ወገኖች በሙሉ የጉዳዩን መሰማት አስመልክቶ የጽሑፍ ማስታወቂያ መስጠት ያለበት ሲሆን እነሱም በጉዳዩ የመሳተፍ መብት አላቸው፡፡
፪. ኮሚሽኑ ጉዳዩን ካየ በኋላ ለውሳኔው መሠረት ያደረጋቸውን ነጥቦች እና ፈጠራው በአዋጁ አንቀጽ ፳፭(፪) መሠረት አገለግሎት ላይ እንዲውል ከወሰነ ጥቅም ላይ የሚውልበትን ሁኔታ በጽሑፍ መግለጽ አለበት፡፡
፫. ኮሚሽኑ ውሳኔውን መመዝገብ፣ ማሳተም እንዲሁም ባለፓተንቱ እና ሌሎች በጉዳዩ የገቡ ወገኖች በጽሑፍ እንዲያውቁት ማድረግ አለበት፡፡
፬. ኮሚሽኑ የመጠቀሚያ ክፍያን በተመለከተ የሰጠው ውሳኔ ይግባኝ ከተጠየቀበት የፍርድ ቤቱ ሬጀስትራር የፍርድ ቤቱን የመጨረሻውን የይግባኝ ውሳኔ ለኮሚሽኑ ማሳወቅ አለበት፡፡ ኮሚሽኑም ውሳኔውን ይመዘግባል፣ በሕትመት ታትሞ እንዲወጣ ያደርጋል፡፡

፴፭. የግዴት ፈቃድ ጥያቄ
በአዋጁ አንቀጽ ፳፱ መሠረት ለኮሚሽኑ የሚቀርብ የግዴታ ፈቃድ ጥያቄ በቅፅ ቁጥር ፮ ተሞልቶ ከተመደበው ክፍያ ጋር እና፤
፩. ፈጠራው በሌላ ፓተንት በተሰጠው ፈጠራ ላይ ጥገኛ መሆኑንና ይህንኑ ፓተንት የተሰጠውን ፈጠራ ካልተጠቀመ ፈጠራውን ለመጠቀም እንደሚያስቸግር ከሚገልጽ ማስረጃ፤
፪. ባለፓተንቱ ከግዴታ ፈቃድ ጠያቂው የፈቃድ ውል ጥያቄ የደረሰው መሆኑንና የግዴታ ፈቃድ ጠያቂው ፈቃዱን በተገቢው ሁኔታና ጊዜ ውስጥ ሊያገኝ ያልቻለ መሆኑን ከሚገልጽ ማስረጃ፤
፫. የግዴታ ፈቃድ ጠያቂው ፓተንት የተሰጠውን ፈጠራ በስራ ላይ ለማዋል የታለመውን የስራ እቅድ ፈጠራውን በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ ለማዋል ብቃት እንዳለው ከሚገልጽ ማስረጃ ጋር ተያይዞ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

፴፮. የግዴታ ፈቃድ ጥያቄን ስለመቀበል ወይም አለመቀበል
፩. ኮሚሽኑ የግዴታ ፈቃድ እንዲሰጥ ጥያቄ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ባሉ ሦስት ወራት ውስጥ በአዋጁ አንቀጽ ፳፱ እና በዚህ ደንብ አንቀጽ ፴፭ የተገለጹት ሁኔታዎች ጠቅለል ባለ አኳኋን መሟላታቸውና አለመሟላታቸውን ይመረምራል፡፡
፪. ኮሚሽኑ በምርመራው ወቅት፤
ሀ) መሟላት የሚገባቸው ሁኔታዎች ያልተሟሉ ሆኖ ሲያገኝ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ የግዴታ ፈቃድ እንዲሰጠው ጥያቄ ላቀረበው ግለሰብ ውሳኔውን በጽሑፍ ያሳውቃል፤
ለ) መሟላት የሚገባቸው ሁኔታዎች ተሟልተው ሲያገኝ ወዲያውኑ ለባለፓተንቱ፣ ለግዴታ ፈቃድ ተጠቃሚዎች እና በአዋጁ አንቀጽ ፳፭(፪) መሠረት ፓተንት የተሰጠበትን ፈጠራ ጥቅም ላይ ላዋሉ ሰዎች የጥያቄውን ቅጅ መላክና ጥሪው ከተደረገበት ቀን ጀምሮ ባሉት ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ያላቸውን አስተያየት ለኮሚሽኑ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ መጋበዝ አለበት፡፡
፫. ባለፓተንቱ ወዲያውኑ ለሁሉም ፈቃድ ተቀባዮች ስለጥያቄው በጽሑፍ ማሳወቅ አለበት፡፡ ፈቃድ ተቀባዮቹ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) መሠረት ጥሪ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ ባሉት ሦስት ወራት ውስጥ ያላቸውን አስተያየት በጽሑፍ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡
፬. ኮሚሽኑ ለግዴታ ፈቃድ ጠያቂው ወዲያውኑ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) እና (፫) መሠረት የቀረቡትን አስተያየቶች ያሳውቃል፡፡
፭. ኮሚሽኑ ጉዳዩ የሚሰማበትን ቀን በመወሰን የግዴታ ፈቃድ የጠየቀውን ግለሰብ፣ ባፓተንቱን እና በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) እና (፫) መሠረት አስተያየታቸውን ያቀረቡ ግለሰቦች ይጠራል ይህንኑም ጉዳዩ የሚሰማበት ቀን ከመድረሱ ከአንድ ወር በፊት በጽሑፍ ያሳውቃል፡፡

፴፯. የግዴታ ፈቃድ የመስጠት ወይም የመከልከል ውሣኔ
፩. በዚህ ደንብ አንቀጽ ፴፮(፭) መሠረት ጉዳዩ ከተሰማ በኋላ ኮሚሽኑ የግዴታ ፈቃድ ለመስጠት የሚያበቁት ሁኔታዎች መሟላታቸውን ሲያረጋግጥ ፈቃዱን ይሰጣል፣ ካልሆነ ግን ይከለክላል፡፡
፪. የግዴታ ፈቃድ ለመስጠት ወይም ለመከልከል የተሰጠው ውሳኔ በጽሑፍ ሆኖ ለውሳኔው መሰረት የሆኑትን ምክንያቶች መያዝ ይኖርበታል ውሳኔው የግዴታ ፈቃድ ለመስጠት ሲሆን፤
ሀ) ፈቃድ የተሰጠበትን ጊዜ ገደብ፤
ለ) ፈቃዱ በአዋጁ አንቀጽ ፳፪(፩) ከተገለጹት ተግባራት የትኞቹን እንደሚሸፍን፤
ሐ) የግዴታ ፈቃድ ተጠቃሚው ፓተንት የተሰጠውን ፈጠራ ተግባራዊ ለማድረግ የሚጀመርበትን የጊዜ ገደብ፤ እንዲሁም
መ) የመጠቀሚያ ክፍያ አፈፃፀም ሁኔታዎችን መዘርዘር አለበት፡፡
፫. ኮሚሽኑ የግዴታ ፈቃድ ለመስጠት ወይም ለመከልከል የደረሰበትን ውሳኔ በመመዝገብ ታትሞ እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ የውሳኔውን ቅጅ የግዴታ ፈቃድ እንዲሰጠው ለጠየቀው ሰው፣ ለባለፓተንቱ በዚህ ደንብ አንቀጽ ፴፮(፪) እና (፫) መሠረት አስተያየታቸውን ላቀረቡ ሰዎች ይልካል፡፡

፴፰. ስለፓተንት መሰረዝ
፩. የአዋጁ አንቀጽ ፴፮(፩) ድንጋጌ ተፈፃሚነት በተወሰኑ የጥበቃ ወሰን ጥያቄዎች ላይ ብቻ ወይም በተወሰኑ የጥበቃ ወሰን ጥያቄ አካሎች ላይ ሲሆን እነኝህ የጥበቃ ወሰን ጥያቄዎች ወይም የጥበቃ ወሰን አካሎች ይሰረዛሉ፡፡
፪. ባለፓተንቱ የፓተንት መሰረዝን አስመልክቶ በፍርድ ቤት ስለተጀመረ ጉዳይ ለማንኛውም ፈቃድ ተቀባይ በፅሑፍ ማሳወቅ አለበት፡፡ የፓተንት ስረዛን ጥያቄ ያቀረበው ወገን በአዋጁ አንቀጽ ፴ መሠረት ለተሰጠ የግዴታ ፈቃድ ተጠቃሚዎች በጽሑፍ ማሳወቅ ያለበት ሲሆን ለፓተንቱ መሰረዝ የቀረበው ምክንያት ባለፓተንቱ ወይም የእርሱ ወራሽ የፈጠራው ሠራተኛ ወይም የሱ ሕጋዊ ወራሽ አይደለም በሚል ከሆነ በፓተንቱ ላይ መብት አለው ለሚባል ወገን በጽሑፍ ማሳወቅ አለበት፡፡

ምዕራፍ ፫
ስለግልጋሎት ሞዴል ምስክር ወረቀት
፴፱. ከፓተንት ጋር ስለተዛመዱ ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት
፩. የአዋጁ አንቀፅ ፫(፩)፣ (፫) እና (፬) በግልጋሎት ሞዴል ምስክር ወረቀት ማመልከቻዎች ላይ ተፈፃሚነት አይኖራቸውም፡፡
፪. የአዋጁ አንቀጽ ፲፮ በግልጋሎት ሞዴል ምስክር ወረቀቶች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡
፫. አንድ ጉዳይ የአዋጁን አንቀፅ ፵፭ ከአንቀፅ ፴፮ ጋር በማጣመር በሚታይበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ በሚከተሉት ምክንያቶች የግልጋሎት ሞዴል ምስክር ወረቀትን ይሰርዛል፤
ሀ) የአዋጁ አንቀፅ ፴፱ እና ፵፭ ድንጋጌዎች ከአንቀፅ ፫(፭) ጋር በመጣመር ሲታዩ ጥበቃ እንዲረግለት የቀረበው ፈጠራ ለግልጋሎት ሞዴል ምስክር ወረቀት ብቁ ሳይሆን፤
ለ) የፈጠራው መግለጫና የመብት ወሰን ጥያቄዎች አንቀፅ ፵፭ ፣ አንቀጽ ፱(፬) (ለ) እና (ሐ) እና ከዚሁ ጋር በሚዛመዱ ደንቦች የተዘረዘሩትን ሁኔታዎች የማያሟሉ ሲሆን፤
ሐ) ፈጠራውን ለመረዳት አስፈላጊ የሆነ ማንኛውም ሥዕል ሳይቀርብ ሲቀር፤
መ) የግልጋሎት ሞዴል ምስክር ወረቀቱ ባለቤት የፈጠራ ሠራተኛው ወይም የሱ ሕጋዊ ወራሽ ሳይሆን፤
ሠ) በአዋጁ አንቀፅ ፵ መሠረት ጥበቃ እንዲደረግለት የቀረበው ፈጠራ ለጥበቃ ብቁ ያልነበረ ሲሆን፡፡
፬. ከዚህ በታች የተመለከቱት እንደተጠበቁ ሆነው በዚህ ደንብ ምዕራፍ ሁለት በተዘረዘሩት አንቀጾች የተገለፁት ድንጋጌዎች እንደአግባብነታቸው በግልጋሎት ሞዴል ምስክር ወረቀት ላይ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፤
ሀ) በደንቡ አንቀፅ ፳፬ ላይ የተገለጸው ፊደል ‹‹ፓ›› ‹‹ግልሞ›› ሆኖ እንዲነበብ፤
ለ) የዚህ ደንብ አንቀፅ ፳፰ ተፈፃሚነት አይኖረውም፣ እንዲሁም
ሐ) በደንቡ አንቀጽ ፴፰ የተጠቀሰው የአዋጁ አንቀጽ ፴፮(፩)፣ የአዋጁን አንቀጽ ፵፭ እና የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፫)ን የሚጠቅስ ሆኖ ይነበባል፡፡
፭. በአዋጁ አንቀጽ ፵፫ መሠረት የሚቀርብ የፓተንትና የግልጋሎት ሞዴል ምስክር ወረቀት ማመልከቻዎችን የማለዋወጥ ጥያቄ በአመልካቹ ተፈርሞ ከተመደበው ክፍያ ጋር አብሮ መቅረብ አለበት፡፡ ጥያቄው በቀረበ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ኮሚሽኑ ውሳኔውን በጽሑፍ ለአመልካቹ ማሳወቅ እና ጥያቄውን ካልተቀበለ ምክንያቱን መግለጽ አለበት፡፡

ምዕራፍ ፬
ስለኢንዱስትሪያዊ ንድፎች
፵. ከፓተንት ጋር ስለተዛመዱ ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት
የዚህ ደንብ አንቀጽ ፳ ፣ ፳፫ እና ፳፬ እንደአግባብነቱ በኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ላይ ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል፣ ለዚሁ ሲባል በዚሁ ደንብ አንቀጽ ፳፬(፩) የተገለጸው ፊደል ‹‹ፓ›› ‹‹ኢን›› ተብሎ ይነበባል፡፡

፵፩. ኢንዱስትሪያዊ ንድፍን ለማስመዝገብ የማቀርብ ማመልከቻ
፩. ኢንዱስትሪያዊ ንድፍን ለማስመዝገብ የሚቀርብ ማመልከቻ በቅጽ ቁጥር ፯ ተሞልቶ በእያንዳንዱ አመልካች መፈረም አለበት፡፡
፪. ማመልከቻው የእያንዳንዱን አመልካች ስም፣ አድራሻ፣ ዜግነትና መኖሪያ መያዝ ይኖርበታል፡፡
፫. አመልካቹ ኢንዱስትሪያዊ ንድፉን ያመነጨው ሰው ከሆነ ጥያቄው ይህንኑ የማያመለክት መገለጫ መያዝ አለበት፡፡ አመልካቹ ሌላ ሰው ከሆነ ጥያቄው የእያንዳንዱን የፈጠራ ሠራተኛ ስምና አድራሻ ማመልከትና አመልካቹ ኢንዱስትሪያዊ ንድፉን በስሙ ለማስመዝገብ ባለመብት መሆኑን የሚገልጽ ማረጋገጫ መያዝ ይኖርበታል፡፡
፬. አመልካቹ በወኪል የተወከለ ከሆነ ጥያቄው ይህንኑ ማመልከትና የወኪሉን ስምና አድራሻ መያዝ ይኖርበታል፡፡

፵፪. ስለመግለጫዎችና ስለናሙናዎች ብዛትና መጠን
፩. የሚከተሉት ከማመልከቻው ጋር መያያዝ አለባቸው፤
ሀ) ኢንዱስትሪያዊ ንድፉ ባለ ሁለት ገጽታ ከሆነ አራት ግራፊክ መግለጫዎች ወይም አራት ሥዕሎች፣ ወይም ንድፎች፣ ወይም
ለ) ኢንዱስትሪያዊ ንድፉ ባለሦስት ገጽታ ከሆነ የኢንዱሰትሪያዊ ንድፉ እያንዳንዱ የተለያዩ ጎኖች አራት ግራፊክ መግለጫዎች ወይም አራት ሥእሎች ወይም ንድፎች፣ እና
ሐ) የሕትመት መጠኑ በኮሚሽኑ ተገቢ ነው ተብሎ የሚወሰን የማተሚያ ቅርጽ ወይም የማተሚያ ቅርጾች፡፡
፪. የናሙና መጠን ከ፳ ሴ.ሜ x ፳ ሴ.ሜ x ፳ ሴ.ሜ መብለጥ የለበትም፡፡ ማንኛውም የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ የግራፊክ መግለጫ፣ ሥዕል ወይም ንድፍ ከ፲ ሴ.ሜ x ፳ ሴ.ሜ መብለጥ የለበትም፡፡ መግለጫዎቹ፣ ሥእሎቹ ወይም ንድፎቹ የኤ፬ መጠን ባላቸው ጠንካራና ረጅም እድሜ በሚቆዩ አራት ወረቀቶች ላይ መለጠፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ሥዕሎችና ንድፎች በጥቁር ቀለም መሠራት አለባቸው፡፡

፵፫. የምዝገባ ቀን ስለመስጠት፣ ስለማሳወቅ እና ምርመራ
፩. ኮሚሽኑ ማመልከቻውን በተቀበለበት ጊዜ ማመልከቻው ያመልካቹን ማንነት ለማረጋገጥ የሚረዳ ጥቆማ እና ተፈላጊውን ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ያካተተውን እቃ ግራፊክ መግለጫ የያዘ ሲሆን ማመልከቻውን የተቀበለበትን ቀን የምዝገባ ቀን አድርጎ ይወስደዋል፡፡ የአዋጁ አንቀጽ ፲፪(፪) እንደአግባቡ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡
፪. በአዋጁ አንቀጽ ፲፪(፪) እና ፶፩ እንዲሁም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት የሚቀርብ ማናቸውም የማሻሻያ ጥሪ በጽሑፍ ሆኖ ጥያቄው የሚፈለገውን ማሻሻያ ወይም ማሻሻያዎች ምንነት ይዞ ከተመደበው ክፍያ ጋር በሁለት ወር ውስጥ እንዲቀርብ የሚጠይቅ መሆን አለበት፡፡
፫. ኮሚሽኑ የምዝገባ ቀን ከሰጠ በኋላ ይህንኑ ለአመልካቹ በጽሑፍ ማሳወቅ አለበት፡፡ ማመልከቻው በአዋጁ አንቀጽ ፲፪(፪) እና አንቀጽ ፶፩ እንዲሁም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ከመጀመሪያ እንዳልቀረበ ከተቆጠረ ኮሚሽኑ ምክንያቶቹን በመዘርዘር ለአመልካቹ በጽሑፍ ማሳወቅ አለበት፡፡
፬. ኮሚሽኑ በአዋጁ አንቀጽ ፵፰(፩) እና በዚህ ደንብ አንቀጽ ፵፩ እና ፵፪ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች አለመሟላታቸውን ሲያረጋግጥ አመልካቹ ተፈላጊውን ማሻሻያ ከተመደበው ክፍያ ጋር ከጥሪው ቀን ጀምሮ ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ እንዲያቀርብ በጽሑፍ ይጠራዋል፡፡ አመልካቹ በተደረገለት ጥሪ መሠረት ጉድለቱን ሳያርም ሲቀር ወይም እርማቱ ቢቀርብም ኮሚሽኑ የተጠየቁት ሁኔታዎች አልተሟሉም የሚል እምነት ሲኖረው ማመልከቻውን ውድቅ በማድረግ ምክንያቶቹን በመዘርዘር በጽሑፍ ለአመልካቹ ያሳውቃል፡፡
፭. የማመልከቻው ውድቅ መሆን የምዝገባውን ቀን ተቀባይነት አያሳጣውም፡፡

፵፬. ማመልከቻን ስለመቀበል ወይም ስላለመቀበል ውሣኔ
ኮሚሽኑ ማመልከቻውን ለመቀበል ወይም ላለመቀበል መወሰኑን ለአመልካቹ በጽሑፍ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ኮሚሽኑ ማመልከቻውን ለመቀበል ከወሰነ ውሳኔውን ካሳወቀበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ወር ውስጥ አመልካቹ የምዝገባና የሕትመት ክፍያ እንዲፈጸም መጠየቅ ይኖርበታል፡፡

፵፭. ስለኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ምዝገባ፣ ሕትመትና ምስክር ወረቀት መሰጠት
፩. በዚህ ደንብ አንቀጽ ፵፬ በተገለጸው የጊዜ ገደብ ውስጥ የምዝገባና ሕትመት ክፍያ ከተፈጸመ ኮሚሽኑ በአዋጁ አንቀጽ ፵፰(፪) እና በዚህ አንቀጽ መሠረት የኢንዱስትሪያዊ ንድፉን ይመዘግባል፡፡
፪. ኮሚሽኑ ለሚመዘግበው ለእያንዳንዱ ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ በምዝገባ ቅደም ተከተል መሠረት ቁጥር ይሰጣል፡፡
፫. የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ምዝገባ የኢንዱስትሪያዊ ንድፉን መግለጫ፣ እና
ሀ) የኢንዱስትሪያዊ ንድፉን ቁጥር፣
ለ) የተመዘገበውን ባለቤት ስምና አድራሻ፣
ሐ) ወኪል ካለ የወኪሉን ስምና አድራሻ፣
መ) በምዝገባው ላይ ስሙ እንደይጠቀስ ካልጠየቀ በስተቀር ኢንዱስትሪያዊ ንድፉን ያመነጨው ሰው ስምና አድራሻ፣
ሠ) የቀዳሚነት ጥያቄ ከቀረበና ጥያቄውም ተቀባይነት ካገኘ የቀዳሚ ቀኑንና የመጀመሪያው ማመልከቻ የተመዘገበበት ሀገር/ሀገሮች ወይም የመጀመሪያው ማመልከቻ ምዝገባ እንዲሸፍን የተጠየቀ/ቁ ሀገር/ሀገሮች፣
ረ) ኢንዱስትሪያዊ ንድፉ ጥቅም ላይ የሚውልባቸውን ዕቃዎች ዓይነት መያዝ ይኖርበታል፡፡
፬. በአዋጁ አንቀጽ ፲፬(፪) (ሀ) እና አንቀጽ ፶፩ የሚከናወን የኢንዱሰትሪያዊ ንድፍ ምዝገባ ሕትመት በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፫) የተዘረዘሩትን መያዝ ይኖርበታል፡፡
፭. የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ምዝገባ ምስክር ወረቀት በቅጽ ቁጥር ፰ ተሞልቶ ይሰጣል፡፡

፵፮. ስለምዝገባ እድሳት
፩. በአዋጁ አንቀጽ ፶(፪) መሠረት የሚፈጸም የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ምዝገባ እድሳት በተመዘገበው ባለቤት ወይም በወኪሉ አማካይነት በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይችላል፡፡ የዚህ ደንብ አንቀጽ ፴፫ እንደአግባቡ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡
፪. እድሳቱ ተገቢውን የእሳቱን ክፍያ በመፈጸም በአዋጁ አንቀጽ ፶(፪) በተገለጸው ጊዜ ውስጥ ወይም ከተጨማሪ ክፍያ ጋር በአዋጁ አንቀጽ ፲፯(፩) እና በአንቀጽ ፶፪ በተፈቀደው የችሮታ ጊዜ ሊፈጸም ይችላል፡፡
፫. የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ምዝገባ እድሳት በመዝገቡ ላይ መስፈርና መታተም አለበት፤
፬. ኮሚሽኑ ለተመዘገበው ባለቤት፤
ሀ) የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ የምዝገባ ቁጥር፣
ለ) የእድሳት ቀንና የጥበቃ ዘመኑ የሚያበቃበትን ቀን፣
ሐ) የተመዘገበውን ባለቤት ስምና አድራሻ፣ እና
መ) ኢንዱስትሪያዊ ንድፉ ጥቅም ላይ ሊውልባቸው የተመዘገቡትን የምርት ዓይነቶች ጥቆማ የያዘ የእድሳት የምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡

ምዕራፍ ፭
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

፵፯. ስለባለቤትነት ለውጥ
፩. ማንኛውም የፓተንት፣ የግልጋሎት ሞዴል ምስክር ወረቀት ወይም የእንዱስትሪያዊ ንድፍ ምዝገባ ምስክር ወረቀት ወይም ለዚሁ የቀረበ ማመልከቻ ባለቤትነት ለውጥ በጽሑፍ መሆን ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም በጉዳዩ ላይ ፍላጎት ያለው ወገን ለኮሚሽኑ በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት ለውጡ መመዝገብና ከማመልከቻ ባለቤትነት ለውጥ በስተቀር በኮሚሽኑ መታተም አለበት፡፡ የሚደረገው ለውጥ ከመመዝገቡ በፊት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ውጤት አይኖረውም፡፡
፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት የሚቀርብ የመብት ባለቤትነት ለውጥ ወይም ለዚሁ የቀረበ ማመልከቻ ባለቤትነት ለውጥ ጥያቄ በቅጽ ቁጥር 9 ተሞልቶ የተመደበው ክፍያ ከተፈፀመ በኋላ ለኮሚሽኑ መቅረብ አለበት፡፡
፫. የባለቤትነት ለውጥ ሕትመት፣
ሀ) አግባብነት ያለውን የጥበቃ ዓይነት፣
ለ) የምዝገባ ቀን፣ በኖረ ጊዜ ቀዳሚ ቀን እና የምዝገባ ወይም መብት የተሰጠበትን ቀን፤
ሐ) ባለቤቱንና አዲሱን ባለቤት፣ እና
መ) የባለቤትነት ለውጥ፣ ባህርይን፣ መግለጽ ይኖርበታል፡፡

፵፰. ስለወኪል መሰየምና የግንኙነት አድራሻ
የወኪል ስያሜ በአመልካቹ ወይም ከአንድ በላይ አመልካቾች ካሉ በእያንዳንዱ አመልካች በተፈረመ ህጋዊ የውክልና ሰነድ መሆን አለበት፡፡ ከአዋጁ ወይም ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ወኪል ከሰየመው ሰው/ሰዎች ጋር የሚደረግ ግንኙነት በወኪሉ አድራሻ ይሆናል፡፡

፵፱. ስለ ማይቆጠሩ ቀናት
ማንኛውንም ተግባር ለማከናወን ወይም ሁኔታዎችን ለመፈጸም የተሰጠው የመጨረሻ ቀን የሚውለው የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ለሥራ ለሕዝብ ክፍት በማይሆንበት ቀን ከሆነ ተግባሩን ወይም ሁኔታውን የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ክፍት በሚሆንበት በቀጣዩ ቀን መፈጸም ሕጋዊነት ይኖረዋል፡፡

፶. ስለመዝገቦችና ኦፊሴላዊ ጋዜጣ
፩. ኮሚሽኑ ለፓተንት፣ ለግልጋሎት ሞዴል ምስክር ወረቀትና ለኢንዱሰትሪያዊ ንድፍ ምዝገባ ምስክር ወረቀት የተለያዩ መዝገቦች ይኖሩታል፡፡ በአዋጁና በዚህ ደንብ ውስጥ የተመለከቱቱ ምዝገባዎች በሙሉ በነዚሁ መዝገቦች ላይ ይፈጸማሉ፡፡
፪. በአዋጁና በዚህ ደንብ መሠረት የተገለጹ ሕትመቶችን ኮሚሽኑ በኦፊሴላዊ ጋዜጣ ላይ ያወጣል፡፡

፶፩. መዝገቦችን ስለማየት፣ ከመዝገቦቹ የተመረጡ ክፍሎች እና
የሰነዶች ቅጂዎችን ስለመጠየቅ
፩. ማንኛውም ሰው የተወሰነውን ክፍያ በመፈጸም መዝገቦችን ማየትና ከመዝገቦቹም ላይ ቅጂዎችን መውሰድ ይችላል፡፡
፪. ከመዝገቦች ላይ የሚወሰዱ የተመረጡ ክፍሎችን፣ የተረጋገጡ ቅጂዎች ወይም የሰነዶችን ቅጂዎች የማግኘት ጥያቄ በጽሁፍ ሆኖ ለኮሚሽኑ መቅረብ አለበት፡፡

፶፪. ስለግድፈቶች እርማት
፩. ኮሚሽኑ በቀረበለት ማመልከቻ ወይም ሰነድ ወይም በአዋጁና በዚህ ደንብ መሠረት በተፈጸሙ ምዝገባዎች ላይ ያለን ማንኛውንም የትርጉም ግድፈት፣ የአጻጻፍ ግድፈት ወይም ስህተት ሊያርም ይችላል፡፡
፪. ኮሚሽኑ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት የሚያከናውነው የግድፈቶች እርማት በጽሑፍ በሚቀርብለት ጥያቄ መሰረት ወይም በራሱ አነሳሽነት ሊፈጸም ይችላል፡፡ ኮሚሽኑ ከጉዳዩ ጋር አግባብ ላላቸው ሰዎች እርማቶችን በጽሑፍ ማሳወቅ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ማተም አለበት፡፡

፶፫. ስለጉዳዩ ማሰማት
፩. ኮሚሽኑ በአዋጁ ወይም በዚህ ደንብ የተሰጠውን ሥልጣን የማንኛውም ሰው ጥቅም በሚነካ ጉዳይ ላይ ከመጠቀሙና ከመወሰኑ አስቀድሞ ለሚመለከተው ሰው ጉዳዩን ለማሰማት ዕድል እንዳለው በመግለጽ ጉዳዩን የማሰማት ጥያቄ ማቅረብ የሚችልበት ከአንድ ወር ያላነሰ የጊዜ ገደብ ሰጥቶ በጽሑፍ ያሳውቃል፡፡
፪. ጉዳይን የማሰማት ጥያቄ የሚርበው በጽሑፍ ይሆናል፡፡
፫. ኮሚሽኑ ጥያቄው ሲደርሰው ጉዳዩ የሚሰማበትን ቀንና ሰዓት ለአመልካቹና ሌሎች ከጉዳዩ ጋር አግባብ ላላቸው ሰዎች ቢያንስ ሁለት ሳምንት አስቀድሞ በጽሑፍ ያሳውቃል፡፡

፶፬. በፖስታ መልዕክት የሚደረግ ግንኙነት
፩. ማንኛውም በፖስታ አማካኝነት ለኮሚሽኑ የሚላክ ማስታወቂያ፣ ማመልከቻ ወይም ሌላ ሰነድ ለኮሚሽኑ እንደተሰጠ ወይም እንደቀረበ የሚቆጠረው በተለመደው የፖስታ ሥርጭት ሂደት መሰረት ለኮሚሽኑ ሲደርስ ነው፡፡ መልዕክቱ ለመላኩ ማረጋገጫ ማስታወቂያውን፣ ማመልከቻውን ወይም ሌላ ሰነድ የያዘውን ደብዳቤ በትክክለኛው አድራሻና በአደራ መላኩን ማረጋገጥ ብቻ በቂ ነው፡፡
፪. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የምዝገባ ቀን መስጠትን አስመልክቶ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡

፶፭. ቅጾች
ከዚህ ደንብ ጋር በአባሪነት የተያያዙት ቅጾች ለተዘጋጁባቸው የተለያዩ ጉዳዮች መዋል ያለባቸው ሆኖ ኮሚሽኑ በሚሰጠው መመሪየ ለሌሎች ጉዳዮች እንዲውሉ ሊሻሻሉ ይችላሉ፡፡

፶፮. ደንቡ የሚጸናበት ጊዜ
ይህ ደንብ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ የካቲት ፳፯ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ.ም.

መለስ ዜናዊ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ጠቅላይ ሚኒስትር