በመልካም ጠባይ እና በቤተዘመድ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

በመልካም ጠባይ እና በቤተዘመድ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች

ርዕስ አራት
በመልካም ጠባይ እና በቤተዘመድ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች
ምዕራፍ አንድ
በመልካም ጠባይ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች
ክፍል አንድ
በግብረ ሥጋ ነፃነትና ንፅህና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች

አንቀጽ ፮፻፳ አስገድዶ መድፈር

፩  ማንም ሰው የኃይል ድርጊት በመጠቀም ወይም በብርቱ ዛቻ ወይም ህሊናዋን እንድትስት ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ መከላከል እንዳትችል በማድረግ ከጋብቻ ውጭ አስገድዶ ከአንዲት ሴት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የፈጸመ እንደሆነ፤
ከአምስት ዓመት እስከ አሥራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡
፪  ወንጀሉ የተፈፀመው
ሀ/ ዕድሜዋ አሥራ ሦስት ዓመት ሆኖ አሥራ ስምንት ዓመት ባልሞላች ሴት ልጅ ላይ ሲሆን፤ ወይም
ለ/ በጥፋተኛው መሪነት፤ ቁጥጥር ወይም ሥልጣን ሥር በሆነ የመጦሪያ ቤት፣ የመማጠኛ ቦታ፣ የሕክምና፣ የትምህርት፣ የጠባይ ማረሚያ፣ የመታሠሪያ ወይም የተያዙ ሰዎች መቆያ ተቋማት ውስጥ በምትገኝ ወይም በተከሳሹ ጥበቃ ወይም ቁጥጥር ስር በምትገኝ ወይም የእሱ ጥገኛ በሆነች ሴት ላይ ሲሆን፤ ወይም
ሐ/ በዕድሜ መግፋት፣ በአካል ወይም በአእምሮ ሕመም፣ በመንፈስ ድክመት ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት የድርጊቱን ምንነት /ባህርይ/ ወይም ድርጊቱ የሚያስከትለውን ውጤት ለይታ ለማወቅ ወይም ለመከላከል በማትችል ሴት ላይ ሲሆን፤ ወይም
መ/ በጭካኔ ወይም በማሰቃየት፣ ወይም ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆኑ ወንዶች ህብረት ሲሆን፤
ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ ዓመት ለመድረስ የሚችል ፅኑ እሥራት ይሆናል፡፡
፫  አስገድዶ መድፈሩ ከባድ የአካል ወይም የእእምሮ ጉዳትን ወይም ሞትን ያስከተለ ሲሆን ቅጣቱ የዕድሜ ልክ እስራት ይሆናል፡፡
፬  ከአስገድዶ መድፈሩ ወንጀል ጋር ተያይዞ ተበዳዩዋን ከሕግ ውጭ ይዞ የማስቀመጥ ወይም የመጥለፍ ወንጀል የተደረገ ወይም ተበዳይዋ በወንጀሉ ምክንያት በሽታ የተላለፈባት ሲሆን፣ አግባብነት ያላቸው የዚህ ሕግ ድንጋጌዎች በተደራቢነት ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡

አንቀጽ ፮፻፳፩ አንድን ወንድ አስገድዶ የግብረ ስጋ ግንኙነት እንዲፈጽም ማድረግ

አንዲት ሴት አንድን ወንድ አስገድዳ ከእርሷ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲፈፅም ያደረገች እንደሆነ፤
ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ትቀጣለች፡፡

አንቀጽ ፮፻፳፪ በንፅህና ክብር ላይ የሚፈፀም የኃይል ድርጊት

ማንም ሰው ተቃራኒ ጾታ ያለውን ሰው በኃይል፣ በብርቱ ዛቻ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ መቃወም እንዳይችል ካደረገው በኋላ ግብረ ሥጋ ግንኙነት የመሰለን ተግባር ወይም ማናቸውንም ሌላ ዓይነት ለንጽሕና ክብር ተቃራኒ የሆነ ተግባር እንዲፈጽም ወይም ለመፈጸም እሺ እንዲል ያስገደደ እንደሆነ፤ ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ወይም ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡

አንቀጽ ፮፻፳፫ አእምሮአቸውን በሳቱ ወይም የአእምሮ ደካማ በሆኑ ወይም ለመቃወም በማይችሉ ሰዎች ላይ የሚፈፀም የክብር ንፅህና ድፍረት በደል

ማንም ሰው የተበዳዩን ችሎታ ማጣት እያወቀ በኃይል ወይም በዛቻም ሳይሆን አእምሮውን ካጣ፣ የአእምሮ ደካማ ወይም ዘገምተኛ ከሆነ፣ ከእብድ ወይም የድርጊቱን ምንነት ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት የድርጊቱን ምንነት ወይም ድርጊቱ የሚያስከትለውን ውጤት ለይቶ ለማወቅ ከማይችል ሰው ጋር የግብር ሥጋ ግንኙነት የፈጸመ ወይም ይህን መሰል ወይም ሌላ ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ ተግባር የፈፀም እንደሆነ፤
እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት፣ ወይም ከአሥራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡

አንቀጽ ፮፻፳፬ ሆስፒታል ውስጥ በተኙ፣ በተጋዙ ወይም በታሰሩ ሰዎች ላይ የሚፈፀም የክብር ንፅህና ድፍረት በደል

ማንም ሰው ሹመቱን፣ ሥልጣኑን ወይም ማዕረጉን በመጠቀም በእርሱ መሪነት፣ ቁጥጥር ወይም ሥልጣን ስር በሚተዳደር ወይም ሆስፒታል፣ መጦሪያ ቤት ወይም ስደተኛ ሰፈር ወይም በማናቸውም የመልካም አስተዳደግ ትምህርት መስጫ፣ ጠባይ ማረሚያ ፣ የግዞት ወይም የእሥራት ተቋማት ወይም ቦታዎች ውስጥ ከሚገኝ ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የፈጸመ ወይም ይህን መሰል ወይም ሌላ ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ ተግባር የፈጸመ እንደሆነ፤
እንደነገሩ ሁኔታ ከአስራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ወይም ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡

አንቀጽ ፮፻፳፭ አንድ ሴት ያለባትን ከፍ ያለ ችግር ወይም ጥገኝነትዋን ምክንያት በማድረግ የሚፈፀም ድርጊት

ከዚህ በላይ ከተመለከቱት ሁኔታዎች ውጭ ማንም ሰው ባንዲት ሴት ላይ የደረሰውን ከፍ ያለ ቂሣዊ ችግር ወይም የኀሊና ኀዘን ምክንያት በማድረግ ወይም በጠባቂነት፣ በአስተማሪነት፣ በአሳዳሪነት፣ በአሠሪነት ወይም ያገኘውን ሥልጣን፣ ኃላፊነት ወይም ችሎታ በመጠቀም ከተባለችው ሴት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የፈፀም ወይም የግብረ ሥጋ ግንኙነትን የመሰለ ድርጊት ወይም ለንፅህና ክብር ተቃራኒ የሆነ ማናቸውንም ሌላ አይነት ድርጊት የፈፀመ እንደሆነ፤
የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡

አንቀጽ ፮፻፳፮ ዕድሜያቸው አስራ ሦስት ዓመት በሆነና አስራ ስምንት ዓመት ባልሞላቸው ልጆች ላይ የሚፈፀም የግብር ሥጋ ድፍረት በደል

፩  ማንም ሰው ተቃራኒ ጾታ ካላት፣ ዕድሜዋ ከአስራ ሦስት ዓመት በላይ ሆኖ አስራ ስምንት ዓመት ካልሞላት ልጅ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የፈፀመ ወይም ይህችው ልጅ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ከእርሱ ጋር እንድትፈጽም ያደረገ እንደሆነ፤
ከሦስት ዓመት እስከ አሥራ አምስት ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡
፪  አንዲት ሴት ዕድሜው አስራ ሦስት ዓመት ሆኖ አሥራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ልጅ ከእርስዋ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲፈጽም ያደረገች እንደሆነ፤
እስከ ሰባት ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እሥራት ትቀጣለች፡፡
፫  ማንም ሰው ከእርሱ ጋር ተቃራኒ ጾታ ባለውና ዕድሜው አስራ ሦስት ዓመት ሆኖ አሥራ ስምንት ዓመት ባልሞላው ልጅ ላይ የግብረ ሥጋ ግንኙነትን የመሰለ ድርጊት ወይም ለንፅህና ክብር ተቃራኒ የሆነውን ማናቸውንም ሌላ አይነት ድርጊት የፈጸመ ወይም ይኸው ልጅ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት እንዲፈጽም የገፋፋ ወይም አስቦ በዚሁ ልጅ ፊት እንደዚህ ዓይነቱን ድርጊት የፈጸመ እንደሆነ፤
ከሦስት ወር በማያንስ ቀላል እሥራት ወይም እስከ አምስት ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡
፬  ተበዳዩ የጥፋተኛው ተማሪ፣ የሙያ ማለማመጃ ትምህርት ተማሪ፣ የቤት ሠራተኛ፣ ወይም ጥፋተኛው በሞግዚትነት የሚያሳድገው ልጅ ወይም እንዲጠብቀው ወይም እንዲንከባከበው በአደራ የተሰጠው ልጅ፣ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ በቀጥታ በእርሱ ጥገኝነት ወይም ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ልጅ እንደሆነ፤
ሀ/ በንዑስ አንቀጽ (፩) የተገለፀውን ወንጀል በሚመለከት ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እሥራት ይሆናል፤
ለ/ በንዑስ አንቀጽ (፪) የተገለፀውን ወንጀል በተመለከተ ቅጣቱ ከሦስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እሥራት ይሆናል፡፡
ሐ/ በንዑስ አንቀጽ (፫) የተገለፀውን ወንጀል በተመለከተ፣ ቅጣቱ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይሆናል፡፡
፭  ወንጀሉ በተበዳይ ላይ ከባድ የአካል ወይም የአእምሮ ጉዳትን ወይም ሞትን አስከትሎ እንደሆነ፤ አግባብነት ያለው የዚህ ሕግ ድንጋጌ በተደራቢነት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

አንቀጽ ፮፻፳፯ በሕፃናት ልጆች ላይ የሚፈፀም የግብረ ሥጋ ድፍረት በደል

፩  ማንም ሰው ከእርሱ ጋር ተቃራኒ ጾታ ካላት፣ ዕድሜዋ አስራ ሦስት ዓመት ካልሞላት ልጅ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የፈፀም ወይም ይህችው ልጅ እንዲህ አይነቱን ድርጊት ከእርሱ ጋር እንድትፈጽም ያደረገ እንደሆነ፤
ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡
፪  አንዲት ሴት ዕድሜው አስራ ሦስት ዓመት ያልሞላው ልጅ ከእርስዋ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲፈጽም ያደረገች እንደሆነ፣
ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ትቀጣለች፡፡
፫  ማንም ሰው ከአርሱ ጋር ተቃራኒ ጾታ ባለውና ዕድሜው አስራ ሦስት ዓመት ባልሞላው ልጅ ላይ የግብርሥጋ ግንኙነትን የመሰለ ድርጊት ወይም ለንፅህና ክብር ተቃራኒ የሆነውን ማናቸውንም ሌላ አይነት ድርጊት የፈጸመ ወይም ይኸው ልጅ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት እንዲፈጽም የገፋፋ ወይም አስቦ በዚሁ ልጅ ፊት እንደዚህ ዓይነቱን ድርጊት የፈፀመ እንደሆነ፤
ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡
፬  ተበዳዩ የጥፋተኛው ተማሪ፣ የሙያ መለማመጃ ትምህርት ተማሪ፣ የቤት ሰራተኛ፣ ወይም ጥፋተኛው በሞግዚትነት የሚያሳድገው ልጅ ወይም እንዲጠብቀው ወይም እንዲንከባከበው በአደራ የተሰጠው ልጅ፣ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ በቀጥታ በእርሱ ጥገኝነት ወይም ቁጥጥር ሥራ የሚገኝ ልጅ እንደሆነ፤
ሀ/ በንዑስ አንቀጽ (፩) የተገለፀውን ወንጀል በሚመለከት፣ ወንጀሉ በሌላ ሰው ከሚፈፀምበት ጊዜ ይልቅ በዚህ ዓይነቱ ሰው ላይ ቅጣቱ ይከብዳል፡፡
ለ/ በንዑስ አንቀጽ (፪) የተገለፀውን ወንጀል በተመለከተ፣ ቅጣቱ ከሦስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እስራት ይሆናል፡፡
ሐ/ በንዑስ አንቀጽ (፫) የተገለፀውን ወንጀል በተመለከተ ቅጣቱ ከሦስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እስራት ይሆናል፡፡
፭  ድርጊቱ በተጐጂ ላይ ከባድ የአካል ወይም የአእምሮ ጉዳትን ወይም ሞትን ያስከተለ እንደሆነ፤ ቅጣቱ የዕድሜ ልክ ጽኑ እሥራት ይሆናል፡፡

አንቀጽ ፮፻፳፰ ወንጀሉን የሚያከብዱ ሌሎች ምክንያቶች

የአስገድዶ መድፈር ወይም የግብር ሥጋ በደልን የሚመለከት ማናቸውም ሌላ ወንጀል በሚፈጸምበት ጊዜ (አንቀጽ ፮፻፳‐፮፻፳፯) አግባብነት ያለው ድንጋጌ ከፍ ያለ ቅጣት ካላስቀመጠ በቀር ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት የሚያስቀጣው፡-
ሀ/ ተበዳይዋ ያረገዘች እንደሆነ፤ ወይም
ለ/ በአባላዘር በሽታ መያዙን እያወቀ ተበዳይዋን/ተበዳዩን በበሽታው ያስያዘ እንደሆነ፤ ወይም
ሐ/ ተበዳይዋ/ተበዳዩ ከደረሰባት/ከደረሰበት ከባድ ኅዘን ወይም ጭንቀት፣ ሀፍረት ወይም ተስፋ መቁረጥ የተነሳ ራሷን/ራሱን የገደለች/የገደለ እንደሆነ፤
ነው፡፡

ክፍል  ሁለት
ለተፈጥሮ ባሕርይ ተቃራኒ የሆኑ የግብረ ሥጋ ግንኙነቶች

አንቀጽ ፮፻፳፱ ግብረሰዶም እና ለንፅህና ክብር ተቃራኒ የሆኑ ሌሎች ድርጊቶች

ማንም ሰው ከእርሱ ጋር አንድ ዓይነት ፆታ ካለው ከሌላ ሰው ጋር ግብረሰዶም ወይም ለንፅህና ክብር የፈፀመ እንደሆነ፤
በቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡

አንቀጽ ፮፻፴ ወንጀሉን የሚያከብዱ ጠቅላላ ሁኔታዎች

፩  ጥፋተኛው፡-
ሀ/ የሌላውን ሰው የገንዘብ ችግር ወይም የኀሊና ኀዘን፤ ወይም የዚህ ሰው አሣዳሪ፣ ሞግዚት፣ ጠባቂ፣ አስተማሪ፣ አሠሪ፣ ወይም ቀጣሪ በመሆኑ ያገኘውን ሀላፊነት፣ ሥልጣን፣ ወይም ችሎታ፣ ወይም በመካከላቸው ያለውን ይህን የመሰለ ሌላ ግንኙነት ያለአግባብ በመጠቀም ከላይ በአንቀጽ ፮፻፳፱ የተመለከተውን ድርጊት የፈፀመበት ወይም ይኸው ሰው ከእርሱ ጋር የዚህ ዓይነቱን ድርጊት እንዲፈጽም ያደረገ እንደሆነ፤ ወይም
ለ/ በዚህ ሕግ /አንቀጽ ፺፪/ በተደነገገው መሠረት ድርጊቱን ሞያው አድርጐ የያዘ እንደሆነ፤
ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት ወይም ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥም ከአስር ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እሥራት ይቀጣል፡፡
፪  ቅጣቱ ከሦስት ዓመት እስከ አሥራ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እሥራት የሚሆነው፡-
ሀ/ ጥፋተኛው በኃይል፣ በዛቻ ወይም በማስገደድ፣ በተንኮል ወይም በማታለል የተጠቀመ ወይም የተጐጂውን መከላከል አለመቻል፣ አቅም ማጣት፣ ወይም የአእምሮ ድክመት/ዝግመት ወይም ሕሊና መሳት ያለአግባብ የተጠቀመ፤ ወይም
ለ/ ጥፋተኛው ተበዳዩን (ተቀዳይዋን) ያሰቃየው ወይም የጭካኔ ድርጊት የፈፀመበት (የፈፀመባት)፣ ወይም እንዳለበት የሚያውቀውን የአባላዘር በሽታ ያስተላለፈበት (ያስተላለፈባት) እንደሆነ፤ ወይም
ሐ/ ተጐጂው (ተጎጂዋን) ከጭንቀት፣ ከሀፍረት ወይም ተስፋ ከመቁረጥ የተነሳ ራሱን የገደለ እንደሆነ፤ ነው፡፡

አንቀጽ ፮፻፴፩ ለአካለ መጠን ባልደረሱ ልጆች ላይ የሚፈጸሙ የግበረሰዶም ጥቃትና ለክብር ንጽህና ተቃራኒ የሆነ ሌላ ድርጊት

፩  ማንም ሰው ከእርሱ ጋር አንድ ዓይነት ጾታ ባለውና ለአካለመጠን ባልደረሰ ልጅ ላይ የግብረሰዶም ጥቃት የፈፀመ እንደሆነ፤
ሀ/ የተበዳዩ ዕድሜ አስራ ሦስት ዓመት ሆኖ አስራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት፤
ለ/ የተበዳዩ ዕድሜ ከአስራ ሦስት ዓመት በታች ሲሆን፣ ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት፤
ይቀጣል፡፡
፪  አንዲት ሴት ለአካለ መጠን ባልደረሰች ልጅ ላይ የግብረሰዶም ጥቃት የፈፀመች እንደሆነ፤ ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ትቀጣለች፡፡
፫  ማንም ሰው ከእርሱ ጋር አንድ ዓይነት ጾታ ባለውና ለአካለ መጠን ባልደረሰ ልጅ ላይ ማናቸውንም ዓይነት ሌላ ለንፅህና ክብር ተቃራኒ የሆነ ድርጊት የፈፀመ እንደሆነ፤ በቀላል እስራት ይቀጣል፡፡
፬  ተበዳዩ የጥፋተኛው ተማሪ፣ የሙያ መለማመጃ ትምህርት ተማሪ፣ የቤት ሰራተኛ፣ ወይም ጥፋተኛው በሞግዚትነት የሚያሳድገው ልጅ ወይም እንዲጠብቀው ወይም እንዲንከባከበው የተሰጠው ልጅ፣ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ በቀጥታ በእርሱ ጥገኝነት ወይም ቁጥጥር ሥራ የሚገኝ ልጅ እንደሆነ፡-
ሀ/ የንዑስ አንቀጽ (፩) ድንጋጌን በተመለከተ ወንጀሉ በሌላ ሰው ከሚፈፀምበት ጊዜ ይልቅ በዚህ ዓይነቱ ሰው ላይ ቅጣቱ ይከብዳል፤
ለ/ የንዑስ አንቀጽ (፪) ድንጋጌን በተመለከተ ቅጣቱ ከሦስት ዓመት እስከ አስር ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እሥራት ይሆናል፤
ሐ/ የንዑስ አንቀጽ (፫) ድንጋጌን በተመለከተ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማያንስ ቀላል እስራት ይሆናል፡፡
፭  ድርጊቱ በተበዳዩ ልዩ ሞትን ወይም  ከባድ የአካል ወይም የአእምሮ ጉዳትን አስከትሎ እንደሆነ፣ ወይም ተበዳዩ (ተበዳዩዋ) ከጭንቀት፣ ከሀፍረት ወይም ተስፋ ከመቁረጥ የተነሳ ራሱን (ራስዋን) የገደለ (የገደለች) እንደሆነ፤ ቅጣቱ የዕድሜ ልክ ጽኑ እሥራት ይሆናል፡፡

አንቀጽ ፮፻፴፪ የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት ለአካለመጠን ባልደረሱ ልጆች የንጽሕና ክብር በሚፈጸም የድፍረት በደል ያለው ተካፋይነት

ለአካለመጠን ያልደረሱ ልጆችን ለማሳደግ፣ ለማስተማር፣ ለማሰልጠን ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ለመንከባከብ የተቋቋመ ድርጅት ሃላፊ፣ ሠራተኛ ወይም ማንኛውም ሌላ ሰው በዚህ ዓይነቱ ድርጅት ውስጥ በሚገኝ ልጅ ላይ፣ በዚህ ሕግ ከአንቀጽ ፮፻፳፮-፮፻፳፰ እና በአንቀጽ ፮፻፴፩ ከተመለከቱት ድርጊቶች አንዱን የፈፀመ ሲሆንና የድርጅቱ አሠራር ወይም አስተዳደር ለወንጀሉ አፈፃፀም ምቹ ሁኔታን በቂ ጥበቃ ባለማድረጉ እንደሆነ፤
እንደየወንጀሉ ዓይነትና ከባድነት በዚህ ሕግ አንቀጽ ፺ መሠረት ይቀጣል፡፡

አንቀጽ ፮፻፴፫ በእንስሳት ላይ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀም

ማንም ሰው በእንስሳት ላይ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የፈጸመ እንደሆነ፤
በቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡

ክፍል ሦስት
በሌሎች የሥነ-ምግባር ብልሹነት መጠቀም

አንቀጽ ፮፻፴፬ የሌላውን ሰው የዝሙት ድርጊት የዘወትር መጠቀሚያ ማድረግ

ማንም ሰው ጥቅም ለማግኘት ሲል የሌላውን ሰው የዝሙት ድርጊት የዘወትር መጠቀሚያው አድርጐ የያዘ፣ ሌላውን ሰው ለዝሙት ድርጊት ያቀረበ ወይም ያቃጠረ፣ ቤቱን በሙሉ ወይም በከፊል ለዚሁ ተግባር ያዋለ ወይም ያከራየ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ የሌላውን ሰው የዝሙት ድርጊት የዘወትር መጠቀሚያ አድርጐ የያዘ እንደሆነ፤
በቀላል እሥራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡

አንቀጽ ፮፻፴፭ ሴቶችንና ለአካለመጠን ያልደረሱ ልጆችን ለዝሙት አዳሪነት በማቃጠር መነገድ

ማንም ሰው ለጥቅም ሲል ወይም የሌላውን ሰው ፍትወተ ሥጋ ለማርካት፡-
ሀ/ በፈቃዳቸውም ቢሆን በዝሙት አዳሪነት እንዲሰማሩ በማነሳሳት፣ በማባበል፣ በማቅረብ ወይም በማናቸውም ዘዴ በመገፋፋት ሴቶችን ወይም ለአካለመጠን ያልደረሱ ልጆችን በማቃጠር የነገደ ወይም ከቦታ ቦታ ያዟዟረ፤ ወይም
ለ/ የተባለውን ሰው ለዝሙት ለማቅረብ በዝሙት አዳሪ ቤት ያስቀመጠ፤
እንደሆነ፤ በተለይ ከሕግ ውጭ በግድ ይዞ የማስቀመጥ ድርጊት አብሮ በተፈጸመ ጊዜ ከበድ ያሉ የቅጣት ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤
ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራትና ከአሥር ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡

አንቀጽ ፮፻፴፮ ወንጀሉን የሚያከብዱ ሁኔታዎች

ሞያ ተብሎ በተያዘ ሰዎችን ለዝሙት የማቅረብ ወይም ከቦታ ቦታ የማዟዟር ሥራ፡-
ሀ/ ተበዳዩ ለአካለ መጠን ያልደረሰ እንደሆነ፤ ወይም
ለ/ ተበዳዩ የወንጀለኛው ሚስት ወይም ወደታች የሚቆጠር ተወላጅ፣ የጉዲፈቻ ልጅ፣ የሚስቱ፣ የወንድሙ ወይም የእህቱ ልጅ፣ በሞግዚትነት የሚጠብቀው ልጅ ወይም በማናቸውም ምክንያት እንዲጠብቀው ወይም እንዲንከባከበው በአደራ የተሰጠው እንደሆነ፤ ወይም
ሐ/ ወንጀለኛው ድርጊቱን የፈፀመው የተበዳዩን የገንዘብ ችግር ወይም የኀሊና ኀዘን ወይም በዚህ ሰው ላይ የለውን የጠባቂነት፣ የአሠሪነት፣ የአስተማሪነት፣ የአከራይነት ወይም የአበዳሪነት ወይም ይህን የመሰለውን ሌላ ሥልጣኑን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ፤ ወይም
መ/ ወንጀለኛው በተንኮል፣ በማታለል፣ በኃይል፣ በዛቻ ወይም በማስገደድ ተጠቅሞ ወይም በተበዳዩ ላይ ያለውን ሥልጣን ያለአግባብ ተገልግሎ እንደሆነ፤ ወይም
ሠ/ ተበዳዩ ማቃጠርን የሙያ ሥራ አድርጐ ለያዘ ሰው ተላልፎ የተሰጠ እንደሆነ ወይም ወደ ውጭ አገር ተወስዶ ወይም ወሬው፣ አድራሻው ወይም መኖሪያ ቦታው ሊታወቅ ያልተቻለ እንደሆነ፤ ወይም
ረ/ ተበዳዩ ከኃፍረት፣ ከጭንቀት ወይም ተስፋ ከመቁረጥ የተነሳ ራሱን ለመግደል ተገፋፍቶ እንደሆነ፤
ቅጣቱ ከሦስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እሥራት እና ከሃያ ሺ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡

አንቀጽ ፮፻፴፯ ሴቶችንና ለአካለመጠን ያልደረሱ ልጆችን ለዝሙት ለማቅረብ የሚደረጉ ዝግጅቶች

ማንም ሰው ሴቶችን ወይም ለአካለመጠን ያልደረሱ ልጆችን ለዝሙት ሥራ እንዲውሉ ለማቅረብ ወይም ከቦታ ቦታ ለማዟዟር ዝግጅቶችን ያደረገ ወይም ሁኔታዎችን ያመቻቸ እንደሆነ፤
በቀላል እሥራት፣ ወይም እንደነገሩ ሁኔታ በተለይም ማቃጠርን የሙያ ሥራ አድርጐ የያዘ ሰው ተሳትፎ እንደሆነ ወይም ዝግጅቶቹ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁና በብዙ ተበዳዮች ላይ ሊፈጸሙ ታቅደው እንደሆነ፤ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት፣ እና ጥፋቱ ከባድ ሲሆን ከአምስት መቶ ብር በማያንስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

አንቀጽ ፮፻፴፰ የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት የወንጀል ተጠያቂነት

የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በዚህ ክፍል በተደነገጉት ወንጀሎች ተካፋይ እንደሆነ፣ እንደወንጀሉ ዓይነትና እንደነገሩ ሁኔታ በዚህ ሕግ በአንቀጽ ፺(፫) መሠረት ይቀጣል፡፡

ክፍል አራት
በመልካም ጠባይ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች

አንቀጽ ፮፻፴፱ ለመልካም ሥነ ምግባርና ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ ብልግናና አሣፋሪ ሥራን በአደባባይ መፈፀም

፩  ማንም ሰው አስቦ ሕዝብ በሚያዘወትርበት ቦታ ወይም በሕዝብ ፊት የግብረ ሥጋ ድርጊትን ወይም ለመልካም ጠባይ ወይም ለመልካም ሥነ ምግባር በብርቱ ተቃራኒ የሆነውን ማናቸውንም ሌላ ጸያፍ ድርጊት የፈጸመ ወይም በአኳኋን ያሳየ እንደሆነ፤
ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እሥራት፣ ወይም ከአንድ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
፪  ጥፋተኛው ለአካለመጠን ባልደረሰ ልጅ ፊት ድርጊቱን የፈፀም እንደሆነ፤ ቅጣቱ ከስድስት ወር እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እሥራት ይሆናል፡፡

አንቀጽ ፮፻፵ ፀያፍ ወይም የብልግና ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ለሕዝብ መግለፅ

፩  ማንም ሰው፡-
ሀ/ ጸያፍ ሰው ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ጽሁፎችን፣ ምስሎችን፣ ስዕላዊ መግለጫዎችን /ፖስተሮችን/፣ ፊልሞችን ወይም ሌሎች ነገሮችን ያዘጋጀ፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባ ወይም ወደ ውጭ አገር የላከ፣ ያጓጓዘ፣ የተቀበለ፣ የያዘ፣ ለህዝብ ያሳየ፣ ለሽያጭ ወይም ለኪራይ ያቀረበ፣ ያከፋፈለ፣ ያሰራጨ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ከቦታ ቦታ ያዟዟረ ወይም በነዚህ ነገሮች የነገደ፤ ወይም
ለ/ እነዚህ ነገሮች እንደምን ወይም ከማን ሊገኙ ወይም ሊዘዋወሩ፣ ሊሠራጩ እንደሚችሉ በማናቸውም ዘዴ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስታወቀ፣ ያመለከተ ወይም እንዲታወቅ ያደረገ፤
እንደሆነ፤ የተከሰሰባቸው ነገሮች መወረሳቸው ወይም እንዲጠፉ መደረጋቸው ሳይቀር ከስድስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት እና በመቀጮ ይቀጣል፡፡
፪  ወንጀለኛው፡-
ሀ/ ይህ ዓይነቱን ንግድ ሙያው አድርጐ የያዘው ወይም የተሠማራበት፤
ለ/ እንደዚህ ያሉትን ነገሮች ለአካለ መጠን ላልደረሱ ልጆች አስቦ ያሳየ፣ የሰጠ ወይም ያስረከበ እንደሆነ፤ ወይም
ሐ/ ለዚሁ ዓላማ ሲባል ለአካለመጠን ያልደረሱ ልጆች የግብረስጋ ግንኙነት የፈጸሙ በማስመሰል ያሳየ ወይም ሀፍረተሥጋቸው እንዲታይ ያደረገ እንደሆነ፤
ቅጣቱ ከአንድ ዓመት የማያንስ ቀላል እሥራት እና ከአስር ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡

አንቀጽ ፮፻፵፩ ፀያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ማሣየት

ማንም ሰው ጸያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑነገሮችን በትያትር፣ በሲኒማ፣ በተንቀሳቃሽ ፊልሞች፣ በሬዲዮ፣ በቪዲዮ፣ በቴሌቪዥን ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ እንዲተላለፍ ያደራጀ፣ ለሕዝብ ያሰማ ወይም እንዲታይ ያደረገ እንደሆነ፤
ከዚህ በላይ በተመለከተው አንቀጽ የተወሰኑት ቅጣቶች ይፈጸሙበታል፡፡

አንቀጽ ፮፻፵፪ የተፈቀዱ ሥራዎች

ወሲብን ወይም ፍትወተ ሥጋን ለመቀስቀስ ያልታሰቡ በባሕሪያቸው በሞላ ስነ ጥበባዊ፣ ስነ ጽሁፋዊ ወይም ሣይንሳዊ የሆኑ ሥራዎች እንደጸያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች እንደሆኑ ሊቆጠሩ አይችሉም፡፡

አንቀጽ ፮፻፵፫ ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ መግለጫዎችና ማስታወቂያዎች

፩  ማንም ሰው ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ ወይም ከግብረ ገብ ውጭ የሆኑ ነገሮችን፣ ምርቶችን ወይም ሥራዎችን ለሕዝብ እይታ ያቀረበ እንደሆነ፤
ከአንድ ወር በማያንስ ቀላል እሥራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡
፪  ማንም ሰው እነዚህኑ ነገሮች ወዳልጠየቁ ወይም በነዚሁ ላይ የሙያ ዝንባሌ ወደሌላቸው ሰዎች በማናቸውም ዘዴ የላከ እንደሆነ፤
የግል አቤቱታ ሲቀርብበት ከአምስት መቶ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም በቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡

አንቀጽ ፮፻፵፬ ለአካለመጠን ያልደረሱ ልጆችን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ሥራዎች መጠበቅ

ማንም ሰው ለጥቅም ወይም ስሜትን ለመቀስቀስ ሲል፡-
ሀ/ ለአካለመጠን ያልደረሱ ልጆችን የግብረ ሥጋ የተፈጥሮአዊ ዝንባሌ ከልክ በላይ ለመቀስቀስ፣ ለማበላሸት ወይም ለማሳሳት ወይም ለአካለመጠን ባልደረሱ ልጆች ላይ የጭካኔ ወይም የገዳይነት ዝንባሌን ወይም ፀረ ማኀበራዊ የሆኑ ወይም ለማነሳሳት፣ ለመቀስቀስ ወይም ለማሳደር የሚችሉ ጽሁፎችን፣ ምስሎችን ወይም ነገሮችን በንግድ ቤት መስኮት፣ በንግድ ዕቃ ማሳያ ቦታ ወይም ከውጭ ለሕዝብ ሊታይ በሚችል በማናቸውም ሌላ ስፍራ በማስቀመጥ በቪዲዮ ወይም በማናቸውም ሌላ ዘዴ እንዲታይ ያደረገ እንደሆነ፤ ወይም
ለ/ እንደዚህ ያሉ ነገሮችን፣ ምስሎችን ወይም ጽሁፎችን ለአካለ መጠን ላልደረሰ ልጅ እያወቀ ያቀረበ፣ ያዋሰ፣ የሰጠ ወይም የሸጠ እንደሆነ፤
አስፈላጊም ሲሆን የዕቃው መወረስ ሳይቀር ከስድስት ወር እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እሥራት እና በመቀጮ ይቀጣል፡፡

አንቀጽ ፮፻፵፭ የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት፣ የወንጀል ተጠያቂነት

የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በዚህ ክፍል በተደነገጉት ወንጀሎች ተካፋይ እንደሆነ፣ እንደወንጀል ዓይነትና እንደነገሩ ሁኔታ በዚህ ሕግ በአንቀጽ ፺(፫) መሠረት ይቀጣል፡፡