የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፸፬/፲፱፻፺፫ የባለሞተር ተሽከርካሪና የተሳቢ መለያ መመርመሪያና መመዝገቢያ ማሻሻያ ደንብ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፸፬/፲፱፻፺፫ የባለሞተር ተሽከርካሪና የተሳቢ መለያ መመርመሪያና መመዝገቢያ ማሻሻያ ደንብ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፸፬/፲፱፻፺፫
የባለሞተር ተሽከርካሪና የተሳቢ መለያ መመርመሪያና
መመዝገቢያ ማሻሻያ ደንብ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር ፬/ አንቀጽ ፲፱፻፹፯ አንቀጽ ፭ መሠረት ይህንን ደንብ አውጥቷል፡፡

፩. አጭር ርዕስ
ይህ ደንብ ‹‹የባለሞተር ተሽከርካሪና የተሣቢ መለያ፣ መመርመሪያና መመዝገቢያ (ማሻሻያ) ደንብ ቁጥር ፸፬/፲፱፻፺፫›› ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ማሻሻያ
የባለሞተር ተሽከርካሪና የተሣቢ መለያ፣ መመርመሪያና መመዝገቢያ ደንብ ቁጥር ፫፻፷/፲፱፻፷፩ (እንደተሻሻለ) እንደገና እንደሚከተለው ተሻሽሏል፤
፩. ‹‹ሚኒስቴር›› የሚለው ቃል ተሠርዞ ‹‹ባለሥልጣን›› በሚለው ተተክቷል፡፡
፪. የአንቀጽ ፫ ንዑስ አንቀጽ (፲፪) ተሰርዞ በሚከተለው ‹‹;; ‹‹የመከላከያ ኃይል ተሽከርካሪ›› ማለት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የአገር መከላከያ ኃይል ንብረት የሆነ ባለሞተር ተሽከርካሪ ወይም ተሳቢ ነው፡፡››
፫. የአንቀጽ ፮ ንዑስ አንቀጽ (፫) እና (፭) ተሰርዘዋል፡፡ ንዑስ አንቀጽ (፬) እና (፮) እንደቅደም ተከተላቸው ንዑስ አንቀጽ (፫) እና (፬) ሆነዋል፡፡
፬. የአንቀጽ ፲፫ ንዑስ አንቀጽ (፪) እና (፬) ተሰርዘዋል፡፡ ንዑስ አንቀጽ (፫) እና (፭) እንደቅደም ተከተላቸው ንዑስ አንቀጽ (፪) እና (፫) ሆነዋል፡፡
፭. የአንቀጽ ፳፰ ንዑስ አንቀጽ (፬) እና (፮) ተሰርዘዋል፡፡ ንዑስ አንቀጽ (፭) እና (፯) እንደቅደም ተከተላቸው ንዑስ አንቀጽ (፬) እና (፭) ሆነዋል፡፡
፮. ከአንቀጽ ፵፱ ቀጥሎ የሚከተሉት አዲስ አንቀጾች ፶ እና ፶፩ ተጨምረዋል፡፡ የደንቡ አንቀጽ ፶፣ ፶፩፣ እና ፶፪ እንደቅደም ተከተላቸው ፶፪፣ ፶፫፣ እና ፶፬ ሆነዋል፡፡
‹‹፶. በባለሥልጣኑ ስለሚመዘገቡ ተሽከርካሪዎች
ባለሥልጣኑ፤
፩. በአገር አቋራጭ የንግድ የመንገድ ማመላለሻ ሥራ ላይ ለሚሠማሩ፤
፪. ንብረታቸው የዲፕሎማቲክ ወይም የዓለም አቀፍና የተራድኦ ድርጅቶች እና
፫. ንብረትነታቸው የፌዴራል መንግሥት የሆኑ ባለሞተር ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ ምዝገባና የቴክኒክ ምርመራ ለማካሔድ፤
የአመቺ የሆነ አደረጃጀት ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
‹‹፶፩. ስለ መከላከያ ኃይል ተሽከርካሪ
፩. የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በዚህ ደንብ መሠረት ለአገር ለመከላከያ ኃይል ተሽከርካሪ የባለቤትነት መታወቂያ ደብተር፣ የመታወቂያ ሠሌዳ ቁጥር፣ እና የዓመታዊ ተለጣፊ ምልክት እንዲሰጥ በባለሥልጣኑ ሊወከል ይችላል፡፡
፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ለመከላከያ ኃይል ተሽከርካሪ የሚሰጠው የመታወቂያ ሠሌዳ በዚህ ደንብ ሠንጠረዥ ‹‹ለ›› ከተመለከተው የቀለም ኅብር፣ የፊደል ጣምራ ወይም ምልክቶች የተለየ መሆን አለበት፡፡››
፯. ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ተሰርዘው ከዚህ ደንብ ጋር ተያይዘው በሚገኙት አዲስ ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ተተክተዋል፡፡
፰. ‹‹የሠሌዳ ሥዕላዊ መልክ›› በሚል ርዕስ ከዚህ ደንብ ጋር የተያያዘው አዲስ ሠንጠረዥ ‹‹ሐ›› ተጨምሯል፡፡

፫. ደንቡ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ ደንብ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ሰኔ ፳፪ ቀን ፲፱፻፺፫ ዓ.ም
መለስ ዜናዊ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ጠቅላይ ሚኒስትር