የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲፰/፲፱፻፹፱ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲፰/፲፱፻፹፱ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲፰/፲፱፻፹፱ ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን
ለማቋቋም የወጣ ደንብ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር ፬/፲፱፻፹፯  አንቀጽ ፭ እና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር ፳፭/፲፱፻፹፬ በአንቀጽ ፵፯/፮/ሀ መሠረት ይህን ደንብ አውጥቷል፡፡
፩. አጭር ርዕስ
ይህ ደንብ ‹‹የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲፰/፲፱፻፹፱›› ተብሎ ሊጠቀስ ይቻላል፡፡

፪. መቋቋም
፩. የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን (ከዚህ በኋላ ‹‹ኮርፖሬሽኑ›› እየተባለ የሚጠራ) የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ በዚህ ደንብ ተቋቁሟል፡፡
፪. ኮርፖሬሽኑ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር ፳፭/፲፱፻፹፬ መሠረት ይተዳደራል፡፡

፫. ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን
በመንግሥት የሚሰየም አካል የኮርፖሬሽኑ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ይሆናል፡፡

፬. ዋናው መሥሪያ ቤት
የኮርፖሬሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ ሆኖ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች እንደአስፈላጊነቱ በማናቸውም ሥፍራ ሊኖረው ይችላል፡፡

፭. ዓላማ
የኮርፖሬሽኑ ዓላማ (በመንግሥት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ የልማት ፖሊሲዎችና እቅዶች ላይ በመመርኮዝ) የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት፣ ማስተላለፍ፣ ማከፋፈል እና መሸጥ፣ በተጨማሪም ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተዛማጅ ሥራዎችን መሥራት ነው፡፡

፮. ካፒታል
ለኮርፖሬሽኑ የተፈቀደለት ካፒታል ብር ፮ ቢሊዮን ፩፻ ሚሊዮን  (ስድስት ቢሊዮን አንድ መቶ ሚሊዮን ብር) ሲሆን ከዚህ ውስጥ ብር ፪ ቢሊዮን ፮፻፸ ሚሊዮን (ሁለት ቢሊዮን ስድስት መቶ ሰባ ሚሊዮን ብር) በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ተከፍሏል፡፡

፯. ኃላፊነት
ኮርፖሬሽኑ ካለው ጠቅላላ ንብረት በላይ በዕዳ ተጠያቂ አይሆንም፡፡

፰. ኮርፖሬሽኑ የሚቆይበት ጊዜ
ኮርፖሬሽኑ ላልተወሰነ ጊዜ ይቆያል፡፡

፱. የመብትና ግዴታ መተላለፍ
በመንግሥት ማስታወቂያ ቁጥር ፪፻፲፫/፲፱፻፵፰ መሠረት ይተዳደር የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ባለሥልጣን መብትና ግዴታዎች በዚህ ደንብ ለኮርፖሬሽኑ ተላልፏል፡፡

፲. ደንቡ የሚጸናበት ጊዜ
ይህ ደንብ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ሰኔ ፴ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ.ም.
መለስ ዜናዊ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራራሲያዊ ሪፐብሊክ
ጠቅላይ ሚኒስትር