የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲፫/፲፱፻፹፱ የፌዴራል መንግሥት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲፫/፲፱፻፹፱ የፌዴራል መንግሥት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲፫/፲፱፻፹፱
የፌዴራል መንግሥት
የንግድ ምዝገባና ፈቃድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር ፬/፲፱፻፹፯ አንቀጽ ፭ እና በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር ፷፯/፲፱፻፹፱ ዓ.ም. አንቀጽ ፵፯ መሠረት ይህን ደንብ አውጥቷል፡፡

ክፍል አንድ
ጠቅላላ

፩. አጭር ርዕስ
ይህ ደንብ ‹‹የፌዴራል መንግሥት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲፫/፲፱፻፹፱›› ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ትርጓሜ
በዚህ ደንብ ውስጥ
፩. ‹‹አዋጅ›› ማለት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር ፷፯/፲፱፻፹፱ ነው፤
፪. ‹‹የንግድ ሥራ ፈቃድ›› ማለት በአዋጁ አንቀጽ () መሠረት ከአዋጁ ጋር ተያይዞ በሚገኘው አባሪ ከተዘረዘሩት የንግድ ሥራዎች ውስጥ ለየትኛውም የሚሰጥ የነግድ ሥራ ፈቃድ ማለት ነው፤
፫. ‹‹የንግድ ሕግ››፣ ‹‹ነጋዴ››፣ ‹‹የንግድ ሥራ››፣ ‹‹አገልግሎት››፣ ‹‹የአገር ውስጥ ንግድ››፣ ‹‹የውጭ ንግድ››፣ ‹‹የንግድ ዕቃዎች››፣ ‹‹የንግድ እንደራሴ››፣ ‹‹የንግድ ስም››፣ ‹‹የፀና የንግድ ሥራ ፈቃድ››፣ ‹‹ኢንዱስትሪ››፣ ‹‹ሚኒስቴር››፣ ‹‹ክልል››፣ ‹‹የአጭር ቃል ምዝገባ›› የሚሉት በአዋጁ አንቀጽ የተሰጣቸውን ትርጓሜ ይይዛሉ፡፡

ክፍል ሁለት
ስለ ንግድ ምዝገባ
፫. በንግድ ምዝገባ ስለመመዝገብ
፩. ሚኒስቴሩ ፈቃድ በሚሰጥባቸው የንግድ ሥራዎች ላይ የሚሠማራ ማንኛውም ሰው በዚህ ደንብ በተመለከተው አኳኋን በሚኒስቴሩ መመዝገብ አለበት፡፡
፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ለሚደረግ ዋና ምዝገባ ማመልከቻ የሚቀርበው ከዚህ ደነብ ጋር ተያይዞ በሚገኘው ሠንጠረዥ ‹‹ለ›› የተመለከተውን አግባብ ያለው ቅጽ ሁለት ቅጅ በመሙላት ይሆናል፡፡

፬. በግለሰብ ነጋዴ ላይ ስለሚደረግ ዋና ምዝገባ
፩. አመልካቹ ግለሰብ ነጋዴ በሚሆንበት ጊዜ፣
ሀ) የቅርብ ጊዜ ጉርድ ፎቶግራፉን፣
ለ) አካለ መጠን ያላደረሰ ሲሆን አግባብ ባለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የተረጋገጠ የቤተዘመድ ጉባዔ ፈቃድ ወይም ማመልከቻው የቀረበው በሞግዚት ሲሆን ሞግዚትነቱ የተረጋገጠበት የፍርድ ቤት ውሣኔ፣
ሐ) ቀደም ሲል የተሰጠ የነግድና የሥራ ፈቃድ ካለ ፈቃዱን፣
መ) ማመልከቻው የተፈረመው በወኪል ከሆነ የውክልና ሥልጣን ማረጋገጫ፣
ከማመልከቻው ጋር አያይዞ በሁለት ቅጅ ማቅረብ አለበት፡፡
፪. አመልካቹ እንደ አገር ውስጥ ባለሀብት የሚቆጠር የውጭ አገር ዜጋ በሚሆንበት ጊዜ፤
ሀ) የቅርብ ጊዜ ጉርድ ፎቶ ግራፉን፤
ለ) ማንነቱን የሚገልፅና በሕጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የሚያመለክቱ የፓስፖርቱን ገጾች ፎቶ ኮፒ፤
ሐ) የኢንቨስትመንት ፈቃድ፤
መ) የመኖሪያ ፈቃደ ፎቶ ኮፒ፤
ከማመልከቻው ጋር አያይዞ በሁለት ቅጅ ማቅረብ አለበት፡፡
፫. አመልካቹ የውጭ አገር ባለሀብት በሚሆንበት ጊዜ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) (ሀ)፣ (ለ) እና (ሐ) የተመለከቱትን መረጃዎች ከማመልከቻው ጋር አያይዞ በሁለት ቅጅ ማቅረብ አለበት፡፡

፭. በንግድ ሽርክና ማኅበር እና በሕብረት ሥራ ማኅበር ላይ
ስለሚደረግ ዋና ምዝገባ
፩. አመልካቹ የንግድ ሽርክና ማኀበር በሚሆንበት ጊዜ፤
ሀ) በአዋጁ አንቀጽ በተመለከተው መሠረት በጋዜጣ ታትሞ የወጣ ማስታወቂያ፤
ለ) የማመልከቻው ቅጽ በወኪል የተፈረመ በሚሆንበት ጊዜ የውክልናው ሥልጣን ማረጋገጫ፤
ሐ) የማኅበሩ መመሥረቻ ጽሁፍ ወይም ውል፤
መ) ከማኅበርተኞች መካከል የውጭ አገር ባለሀብት ካለ በዚህ ደንብ አንቀጽ ፬(፫) የተመለከተው መረጃ፣
ከማመልከቻው ጋር ተያይዞ በሁት ቅጅ ይቀርባል፡፡
፪. አመልካቹ የሕብረት ሥራ ማኅበር ሲሆን በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) (ለ)፣ (ሐ) እና (መ) የተመለከቱትን መረጃዎች ከማመልከቻው ጋር አያይዞ ያቀርባል፡፡

፮. በአክስዮን ማኅበር ላይ ስለሚደረግ ዋና ምዝገባ
አመልካቹ የአክስዮን ማኅበር በሚሆንበት ጊዜ፣
፩. በዚህ ደንብ አንቀጽ ፭(፩) (ሀ)፣ (ለ) እና (መ) የተመለከቱት ዝርዝሮች፣
፪. በንግድ ሕግ ቁጥር ፫፻፲፪(፩)(ለ) መሠረት በባንክ እንዲቀመጥ የሚያስፈልገው ገንዘብ ተቀማጭ ስለመደረጉ የባነክ ማረጋገጫ ጽሁፍ፣
፫. ከእያንዳንዱ ዓይነት የአክስዮን ምስክር ወረቀት ናሙና፣
፬. በዓይነት የተደረገ መዋጮ ካለ በንግድ ህግ ቁጥር ፫፻፲፭ መሠረት የተዘጋጀ ሪፖርት፣
፭. በንግድ ሕግ ቁጥር ፫፻፳፫(፪) መሠረት ተፈላጊ የሆኑ ሠነዶች፣
ከማመልከቻው ጋር ተያይዘው በሁለት ቅጅ ይቀርባሉ፡፡

፯. ኃላፊነቱ በተወሰነ የግል ማኅበር ላይ ስለሚደረግ ዋና ምዝገባ
አመልካቹ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሚሆንበት ጊዜ፣
፩. የማኅበሩ መመሥረቻ ጽሁፍና የመተዳደሪያ ደንብ፤
፪. በዚህ ደንብ አንቀጽ ፭(፩) (ሀ)፣ (ለ) እና (መ) የተመለከቱት ዝርዝሮች፣
ከማመልከቻው ጋር ተያይዘው በሁለት ቅጅ ይቀርባሉ፡፡

፰. በውጭ አገር የንግድ ማኅበር ላይ ስለሚደረግ ዋና ምዝገባ
አመልካቹ የውጭ አገር የንግድ ማኅበር በሚሆንበት ጊዜ፣
፩. በተቋቋመበት አገር የተመዘገበና ሕጋዊ ሕልውና ያለው ስለመሆኑ ማስረጃ፣
፪. የማኅበሩ መመሥረቻ ጽሁፍና መተዳደሪያ ደንብ ወይመ ማህበሩ የተቋቋመበት ተመሳሳይ ሰነድ፣
፫. በኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ላይ እንዲውል የመደበውን ካፒታል የሚገልጽ የንግድ ማኅበሩ ሥልጣን ያለው አካል ውሣኔ ወይም መግለጫ፣
፬. በኢትዮጵያ ለተመደበው ቋሚ ወኪል ሥልጣን ባለው የድርጅቱ አካል ውክልና የተሰጠበትና አግባብ ባለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የተረጋገጠ ሰነድ፣
፭. በኢትዮጵያ ያለው ወኪል ወይም ወኪሎች ስምና የፊርማ ናሙና፣
፮. በንግድ ሕግ ቁጥር ፫፻፲፫(፪-፮) እና (፲-፲፪) መሠረት የሚፈለገውን መረጃ የያዘ የጋዜጣ ማስታወቂያ፣
፯. በኢትዮጵያ ውሰጥ በማዕድን መስክ የንግድ ሥራ ለመሥራት የሚፈልግ ከሆነ ይህንኑ ሥራ እንዲሠራ አግባብ ባለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የተፈቀደበት ማስረጃ፣
ከማመልከቻው ጋር በሁለት ቅጅ ተያይዘው ይቀርባሉ፡፡

፱. በመንግሥት የልማት ድርጅት ላይ ስለሚደረግ ዋና ምዝገባ
አመልካቹ በፌዴራል መንግሥት የተቋቋመ የመነግሥት የልማት ድርጅት በሚሆንበት ጊዜ፣
፩. የተቋቋመበት ህግ፣
፪. የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የምደባ ደብዳቤ፣
ከማመልከቻው ጋር ተያይዞ በሁለት ቅጅ መቅረብ አለበት፡፡

፲. በንግድ እንደራሴ ላይ ስለሚደረግ ዋና ምዝገባ
አመልካቹ በውጭ አገር ያለ የንግድ ድርጅትን የሚወክል እንደራሴ በሆነ ጊዜ፣
፩. ወካዩ ድርጅት በተቋቋመበት አገር የተመዘገበና ሕጋዊ ሕልውና ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ፣
፪. ድርጅቱ የንግድ ማኅበር ከሆነ መመሥረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ ወይም ድርጅቱ የተቋቋመበት ተመሳሳይ ሰነድ፣
፫. በኢትዮጵያ ውስጥ ለጽ/ቤቱ የተመደበውን ወጪ የሚገልጽ አግባብ ባለው የድርጅቱ ባለሥልጣን የተፈረመ ማረጋገጫ፣ እና
፬. እንደራሴው በወካዩ ድርጅት በእንደራሴነት የተሾመበት አግባብ ባለው መ/ቤት የተረጋገጠ ማስረጃ፣ ከማመልከቻው ጋር ተያይዘው በሁለት ቅጅ መቅረብ አለባቸው፡፡

፲፩. በምዝገባ ማመልከቻ ላይ ውሣኔ ስለመስጠት
ሚኒስቴሩ የምዝገባ ማመልከቻ ሲቀርብለት፣
፩. ማመልከቻው የተሟላ ሆኖ ሲያገኘው ከዚህ ደንብ ጋር ተያይዞ በሚኘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተወሰነውን አግባብ ያለው ክፍያ በማስከፈል መዝግቦ በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ይሰጠዋል፡፡
፪. ማመልከቻው ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ሲያረጋግጥ ያልተቀበለበትን ምክንያት ለአመልካቹ በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ በጽሁፍ ይገልጻል፡፡

፲፪. ስለምዝገባ ለውጥና ተጨማሪ ምዝገባ
፩. ማንኛውም የተመዘገበ ነጋዴ በዚህ ደንብ መሠረት ያስመዘገበውን ዝርዝር የሚለውጥ ሁኔታ ወይም አድራጐት ሲደርስበት አድራጎቱ ከደረሰበት ቀን አንስቶ በስድሳ ቀናት ውስጥ ለውጡ እንዲመዘገብለት ለሚኒስቴሩ ማመልከት አለበት፡፡
፪. ለዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) አፈጻጸም አመልካቹ አግባብ ያለውን መረጃ በሁለት ቅጂ ያቀርባል፡፡
፫. ስለሚደረገው የምዝገባ ለውጥ ወይም ተጨማሪ ምዝገባ ነጋዴው በአጭር ቃል ለተመዘገበባቸው ቢሮዎች ሁሉ ዝርዝር መረጃ ያቀርባል፡፡
፬. በዚህ ደንብ አንቀጽ ፲፩ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ለምዝገባ ለውጥ ወይም ተጨማሪ ምዝገባ አፈጻጸምም ተፈፃሚት ይኖራቸዋል፡፡

፲፫. ምዝገባን ስለመሠረዝ
በመዝገብ የገባ ነጋዴ በአዋጁ አንቀጽ ፲(፩) እና (፪) መሠረት ከንግድ መዝገብ እንዲሠረዝ ሲወስንና ይህንኑ የሚያመለክት ማስረጃ እንዲሰጠው ሲያመለክት ከዚህ ደንብ ጋር ተያይዞ በሚገኘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተመለከተውን አግባብ ያለው ክፍያ በማስከፈል ሚኒስቴሩ የሥረዛ ማስረጃ ይሰጠዋል፡፡

፲፬. የመረጃ ቅጅ ስለመጠየቅ
፩. በንግድ መዝገብ ውስጥ የሰፈረው ዝርዝር ቅጅ ወይም የዝርዝሩ በአጨር የተውጣጣ ቅጅ ወይም ተፈላጊው ዝርዝር ያልተመዘገበ ሲሆን ይህንኑ የሚያረጋግጥ ምስክር ወረቀት እንዲሰጠው የሚጠይቅ ሰው ጥያቄውን ለሚኒስቴሩ በጽሁፍ ማቅረብ አለበት፡፡
፪. ሚኒስቴሩ ከዚህ ደንብ ጋር ተያይዞ በሚገኘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተወሰነውን አግባብ ያለው ክፍያ አስከፍሎ ቅጂውን ወይም የምስክር ወረቀቱን ለአመልካቹ በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ይሰጠዋል፡፡

፲፭. ምትክ የምዝገባ ምስክር ወረቀት ስለመጠየቅ
፩. የተሰጠው የምዝገባ የመስክር ወረቀት የተበላሸበት ወይም የጠፋበት ማንኛውም ሰው ምትክ እንዲሰጠው ሲጠይቅ የምስክር ወረቀቱ እንዴት እንደጠፋ ወይም እንደተበላሸ የሚልጽ በራሱ የተፈረመ ማመልከቻ ማቅረብ አለበት፡፡
፪. ሚኒስቴሩ መግለጫው ሲቀርብለት የተበላሸውን የምስክር ወረቀት እንዲመለስ ካደረገ በኋላ ከዚህ ደንብ ጋር ተያይዞ በሚገኘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተወሰነውን አግባብ ያለው ክፍያ አስከፍሎ ምትክ የምዝገባ ምስክር ወረቀት በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለአመልካቹ ይሰጣል፡፡

፲፮. ስለንግድ ስም ምዝገባ
፩. የንግድ ስም ምዝገባ ለማድረግ ማመልከቻ የሚቀርበው ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ለ›› የተመለከተውን አግባብ ያለውን ቅጽ በመሙላት ይሆናል፡፡
፪. ለንግድ ስም ምዝገባ፣ ለውጥና ሥረዛ ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተወሰነው አግባብ ያለው ክፍያ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

ክፍል ሦስት
ስለ ንግድ ሥራ ፈቃድ
፲፯. ፈቃድ የመስጠት ሥልጣን
፩. ሚኒስቴሩ በአዋጁ አንቀጽ ፳(፪) መሠረት ከአዋጁ ጋር በተያያዘው አባሪ በተዘረዘሩት የንግድ ሥራዎች የንግድ ሥራ ፈቃዶችን ይሰጣል፡፡
፪. ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ፈቃድ በሚሰጥበት ጊዜ፣ ፈቃዱ የላኪነት ወይም የአስመጪነት ከሆነ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የንግድ ዕቃዎች በተመለከተ የንግድ ዕቃው በግልጽ ካልተጠቀሰ በስተቀር ፈቃዱ ለነዚህ ዕቃዎች አስመጪነት ወይም ላኪነት የንግድ ሥራ አያገለግልም፤
ሀ) ቡና፣
ለ) የሰውና የእንስሳት መድኃኒት፣
ሐ) የሕከምና መገልገያ መሣሪያዎች፣
መ) የደን ውጤቶች፣
ሠ) የዱር እንስሳትና አዕዋፍ፣
ረ) የእርሻ፣ የኢንዱስትሪና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች፣ በመኪና ኃይል የሚሠሩ ዕቃዎችና ባለሞተር ተሽከርካሪዎች፣
ሰ) ማዕድናት፣
ሸ) ኬሚካሎች፣
ቀ) ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች፣ እና
በ) ሌሎች በሕዝብ ጤናና ደኅንነት እንዲሁም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ አግባብ ካለው መሥሪያ ቤት የብቃት ማረጋገጫ የሚያስፈልጋቸው የንግድ ዕቃዎች፡፡

፲፰. የንግድ ሥራ ፈቃድ ለማውጣት ስለሚቀርብ ማመልከቻ
፩. የንግድ ሥራ ፈቃድ ለማውጣት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሐ›› የተመለከተውን አግባብ ያለው ማመልከቻ ቅጽ በሁለት ቅጂ በመሙላት ለሚኒስቴሩ ያቀርባል፡፡
፪. አመልካቹ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ከሚያቀርበው ማመልከቻ ጋር፣
ሀ) የንግድ ምዝገባ ምሥክር ወረቀት፣
ለ) የቅርብ ጊዜ ጉርድ ፎቶግራፉን፣
ሐ) የውጭ አገር ዜጋ ሆኖ እንደ አገር ውስጥ ባለሀብት የሚቆጠር ከሆነ የኢንቨስትመንት ፈቃድና የመኖሪያ ፈቃዱን፣
በሁለት ቅጂ አያይዞ ያቀርባል፡፡
፫. አመልካቹ የውጭ አገር ባለሀብት ከሆነ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፪(ሀ) እና (ለ) ከተመለከቱት መረጃዎች በተጨማሪ የኢንቨስትመንት ፈቃድ በሁለት ቅጂ አያይዞ ያቀርባል፡፡
፬. አመልካቹ የንግድ ማኅበር ሆኖ የውጭ አገር ዜጎች የሆኑ አባላት ካሉት፣
ሀ) የንግድ ምዝገባ የምሥክር ወረቀት፣
ለ) የማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ ወይም ውል፣
ሐ) የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ የቅርብ ጊዜ ጉድር ፎቶግራፍ፣
ከማመልከቻው ጋር አያይዞ በሁለት ቅጅ ለሚኒስቴሩ ያቀርባል፡፡
፭. አመልካቹ በፌዴራል መንግሥት የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ድርጅት ከሆነ፣
ሀ) የምዝገባ የምሥክር ወረቀት፣
ለ) የተቋቋመበትን ሕግ፣
ሐ) የሥራ አስኪያጁን የምደባ ደብዳቤ፣
ከማመልከቻው ጋር አያይዞ በሁለት ቅጂ ያቀርባል፡፡

፲፱. የንግድ ሥራ ፈቃድ ስለመስጠት
፩. ሚኒስቴሩ
ሀ) በዚህ ደንብ አንቀጽ ፲፰ መሠረት የቀረበለትን ማመልከቻ ከገመገመ በኋላ ጥያቄው የተሟላ ሆኖ ሲያገኘው፣
ለ) አመልካቹ ካሁን ቀደም ተመሳሳይ የንግድ ሥራ ፈቃድ በጥፋት የተሠረዘበት ከሆነ ከተሠረዘበት ቀን ጀምሮ አንድ ዓመት የሞላው መሆኑን ሲያረጋግጥ፣
ሐ) የተጠየቀው የንግድ ሥራ በሕግ ያልተከለከለ መሆኑን ሲያረጋግጥ፣
ከዚህ ደንብ ጋር ተያይዞ በሚገኘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› መሠረት አግባብ ያለውን ክፍያ አስከፍሎ የተጠየቀውን የንግድ ሥራ ፈቃድ በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ይሰጣል፡፡
፪. ሚኒስቴሩ ጥያቄውን ያልተቀበለው እንደሆነ ያልተቀበለበትን ምክንያትና ውሣኔውን በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለአመልካቹ በጽሑፍ ይገልፃል፡፡
፫. በአዋጁ አንቀጽ ፳፰ (፩) (ሠ) መሠረት ፈቃድ ከተሠረዘባቸው ነጋዴዎች በስተቀር በሌሎች ምክንያቶች ፈቃድ የተሠረዘባቸው እንደገና አዲስ ተመሣሣይ ፈቃድ የሚያወጡት ከዚህ ደንብ ጋር በሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተያያዘውን አግባብ ያለውን የፈቀድ ክፍያ እጥፍ በመክፈል ይሆናል፡፡

፳. ስለንግድ ሥራ ፈቃድ እድሣት
፩. የንግድ ሥራ ፈቃድ በአዋጁ አንቀጽ ፳፭ መሠረት መታደስ አለበት፡፡
፪. ባለፈቃዱ ለፈቃድ እድሣት በሚቀርብበት ጊዜ፣
ሀ) የገቢ ግብርና የማዘጋጃ ቤት ሕጋዊ የአገልግሎት ክፍያን በሚመለከት እንደአግባቡ ከአገር ውስጥ ገቢ ባሥልጣን ወይም ከሚመለከተው ፊይናንስ ቢሮ ፈቃዱ እንዲታደስ የተሰጠ መረጃ፣
ለ) ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሐ›› የተመለከተውን አግባብ ያለው የፈቃድ እድሣት ማመልከቻ ቅጽ፣
በሁለት ቅጂ ለሚኒስቴሩ ያቀርባል፡፡
፫. ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) መሠረት የቀረበለት ማመልከቻ የተሟላ ሆኖ ካገኘው ከዚህ ደንብ ጋር ተያይዞ በሚገኘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተመለከተውን አግባብ ያለውን ክፍያ በማስከፈል ፈቃዱን በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ አድሶ ለአመልካቹ ይሰጠዋል፡፡
፬. ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) መሠረት የቀረበውን ማመልከቻ ያልተቀበለ እንደሆነ ያልተቀበለበትን ምክንያት በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለአመልካቹ በጽሑፍ ይገልጽለታል፡፡

፳፩. የንግድ ሥራ ፈቃድ የተሰጠው ሰው መብትና ግዴታዎች
፩. ማንኛውም የንግድ ሥራ ፈቃድ የተሰጠው ሰው በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪)፣ (፫)፣ (፬)፣ (፭)፣ እና (፮) እንዲሁም በሌሎች ሕጎች የተደነገጉ ክልከላዎችንና ገደቦችን በማክበር ፈቃድ በተሰጠበት የሥራ መስክ ማናቸውንም የንግድ ሥራ መሥራት ይችላል፡፡
፪. ማንኛውም ነጋዴ የንግድ ሥራ ፈቃዱ በተሰጠበት የሥራ መስክ የተለያዩ ሥራዎችን በአንድ ሥፍራ ወይም ቤት ውስጥ አጣምሮ መሥራት በተጠቃሚው ሕዝብ ጤንነትና ደህንነት ወይም በንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ እነዚህን ሥራዎች በተለያዩ ሥፍራዎች ወይም ቤቶች በተናጠል ማካሄድ አለበት፡፡
፫. ማንኛውም ነጋዴ፤
ሀ) በተጠቃሚው ወይም በደንበኛው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ፣ ወይም
ለ) የጥቅም ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ፤
የተለያዩ ሥራዎችን አጣምሮ መሥራት የለበትም፡፡
፬. ማንኛውም ነጋዴ እንደአግባቡ የንግድ ዕቃዎቹንና የአገልግሎቶቹን የዋጋ ዝርዝር በንግድ ቤቱ በግልጽ ሥፍራ በሚታይ ቦታ ማመልከት ወይም በንግድ ዕቃዎቹ ላይ መለጠፍ አለበት፡፡
፭. ማንኛውም ነጋዴ በሕዝብ ማስታወቂያ በሚወሰነው መሠረት የሥራው ጠባይ የሚጠይቀውን ማሟላትና አገልግሎት መስጠት አለበት፡፡
፮. ማንኛውም ነጋዴ የንግድ ሥራ ፈቃዱን በንግድ ቤቱ ውስጥ በግልጽ በሚታይ ቦታ ማስቀመጥ አለበት፡፡

፳፪. ምትክ የንግድ ሥራ ፈቃድ ስለመጠየቅ
፩. የንግድ ሥራ ፈቃድ የተበላሸበት ወይም የጠፋበት ሰው እንዴት እንደበተላሸበት ወይም እንደጠፋበት የሚገልጽ ራሱ የፈረመውን መግለጫ በማቅረብ ምትክ ፈቃድ እንዲሰጠው ሊጠየቅ ይችላል፡፡
፪. ሚኒስቴሩ ባለፈቃዱ የተበላሸውን ፈቃድ እንዲመልስ ካደረገ በኋላ ከዚህ ደንብ ጋር ተያይዞ በሚገኘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተመለከተውን አግባብ ያለው ክፍያ በማስከፈል ምትክ ፈቃድ በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ይሰጠዋል፡፡
፫. ሚኒስቴሩ ፈቃዱ የጠፋበት ሁኔታ መግለጫ ከደረሰው በኋላ አመልካቹ ፈቃዱ የጠፋበትና ምትክ ፈቃድ እንዲሰጠው የጠየቀ መሆኑን የሚገልጽ የጋዜጣ ማስታወቂያ በአመልካቹ ወጪ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተቃዋሚ ካልቀረበ ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተመለከተውን አግባብ ያለውን ክፍያ በማስከፈል በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለአመልካቹ ምትክ ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡

፳፫. የንግድ ድርጅት ሲተላለፍ የንግድ ሥራ ፈቃድ ስለሚሰጥበት ሁኔታ
፩. የንግድ ድርጅት በማናቸውም ሕጋዊ መንገድ ለሌላ ሰው ሲተላለፍ አመልካቹ ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሐ›› አግባብ ያለውን የማመልከቻ ቅጽ በመሙላት ከማመልከቻው ጋር የቀድሞውን የንግድ ፈቃድና አግባብ ያለውን ሕጋዊ ሠነድ አያይዞ በሁለት ቅጂ ያቀርባል፡፡
፪. ሚኒስቴሩ የንግድ ድርጅቱ በሕጋዊ መንገድ መተላለፉን በማጣራት ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተመለከተውን አግባብ ያለውን ክፍያ አስከፍሎ ሌላ ተመሣሣይ ፈቃድ ድርጅቱ ለተላለፈለት ሰው በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ይሰጠዋል፡፡
፫. ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) የቀረበለት ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ሲያረጋግጥ ያልተቀበለበትን ምክንያት በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለአመልካቹ በጽሑፍ ያሳውቃል፡፡

፳፬. ጊዜያዊ ፈቃድ
፩. በአዋጁ አንቀፅ ፴፩(፩) ለተመለከቱት ዘርፎች ጊዜያዊ ፈቃድ እንዲሠጠው የሚጠይቅ ማንኛውም ሰው ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሐ›› የተለከተውን አግባብ ያለው የማመልከቻ ቅፅ በመሙላት ከማመልከቻው ጋር፣
ሀ) የንግድ ምዝገባ ምሥክር ወረቀት፣
ለ) የቅርብ ጊዜ ጉርድ ፎቶግራፉን፣
በሁለት ቅጂ አያይዞ ያቀርባል፡፡
፪. ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተመለከተውን ተሟልቶ መቅረቡን ሲያረጋግጥ ከዚህ ደንብ ጋር ተያይዞ በሚገኘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተመለከተውን አግባብ ያለው ክፍያ በማስከፈል የተጠየቀውን ጊዜያዊ ፈቃድ በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ይሰጣል፡፡
፫. ሚኒስቴሩ ጥያቄውን ያልተቀበለው እንደሆነ ያልተቀበለበትን ምክንያትና ውሳኔውን በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለአመልካቹ በጽሑፍ ያሳውቃል፡፡

፳፭. የማስፋፋትና የማሻሻል ፈቃድ
፩. በኢንዱስትሪ፣ በሆቴል፣ በጤና፣ በትምህርትና በግብርና ልማት የሥራ ዘርፎች የማስፋፋት ወይም የማሻሻል ሥራ ያጠናቀቀ የውጭ ባለሀብት ማምረት ወይም አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት በአዋጁ አንቀጽ ፳፪(፪) እና (፫) መሠረት አስፈላጊ መረጃዎችን በማያያዝ ለማምረት ወይም አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ እንዲሰጠው ማመልከቻ ማቅረብ አለበት፡፡
፪. ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተመለከቱት መረጃዎች ሲቀርቡለትና የማስፋፋቱ ወይም የማሻሻሉ ሥራ ለማምረት ወይም አገልግሎት ለመስጠት ብቁ መሆኑን ሲያረጋግጥ ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› አግባብ ያለውን ክፍያ በማስከፈል ፈቃዱን ለአመልካቹ በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ይሰጠዋል፡፡
፫. የማስፋፋቱ ወይም የማሻሻሉ ሥራ ቀደም ሲል ፈቃድ የተሰጠባቸውን ሁኔታዎች የማይቀይር ሆኖ ከተገኘ ፈቃድ ጠያቂው በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተመለከቱትን መረጃዎች በድጋሚ እንዲያቀርብ አይገደድም፡፡
፬. ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (፩) መሠረት የቀረበለትን ጥያቄ ያልተቀበለው እንደሆነ፣ ያልተቀበለበትን ምክንያትና ውሳኔውን በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለአመልካቹ በጽሑፍ ያሳውቃል፡፡

ክፍል አራት
ስለንግድ እንደራሴ
፳፮. የንግድ እንደራሴነት የምስክር ወረቀት
፩. በአዋጁ አንቀጽ ፴፮ መሠረት የነግድ እንደራሴነት የምስክር ወረቀት ለማውጣት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሐ›› የተመለከተውን አግባብ ያለውን ቅጽ በመሙላት፤
ሀ) በማዕከላዊ የንግድ መዝገብ የተመዘገበ ለመሆኑ የዋና ምዝገባ የምስክር ወረቀት፣
ለ) የንግድ እንደራሴው የሚያከናውናቸው ተግባራት መግለጫ፣
ሐ) ለደመወዝና ለሥራ ማስኬጃ በየዓመቱ ቢያነስ ፵ሺ የአሜሪካን ዶላር ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰነድ፣
መ) አመልካቹ የውጭ አገር ዜጋ ከሆነ የንግድ እንደራሴነት የምስክር ወረቀት እንደተሰጠው ወዲያውኑ አግባብ ካለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሥራ ፈቃድ አውጥቶ ለማቅረብ ግዴታ የገባበት ፅሁፍ፤ ከማመልከቻው ጋር በማያየዝ በሁለት ቅጅ ለሚኒስቴሩ ያቀርባል፡፡
፪. ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት የቀረቡት መረጃዎች መሟላታቸውን ካረጋገጠ በኋላ ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተመለከተውን አግባብ ያለውን ክፍያ በማስከፈል የንግድ እንደራሴነት የምስክር ወረቀት ለአመልካቹ በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ይሰጣል፡፡

፳፯. ለንግድ እንደራሴ የተፈቀዱ ሥራዎች
ለንግድ እደራሴ የተፈቀዱት ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፤
፩. የወካዩን ምርቶችና አገልግሎቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ማስተዋወቅ፣
፪. ወደፊት ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውሰጥ ኢንቨስት ማድረግ እንዲችል የሚረዱ ፕሮጀክቶችን ማጥናት፣
፫. የኢትዮጵያ ወጪ ምርቶችን ወካይ ድርጅቱ በሚገኝበት አገር ማስተዋወቅ፡፡

፳፰. የንግድ እንደራሴነት የምስክር ወረቀትን ስለማደስ
፩. ማንኛውም የንግድ እንደራሴነት የምስክር ወረቀት የያዘ ሰው ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተመለከተውን ገንዘብ በመክፈል የበጀት ዓመቱ በገባ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የንግድ እንደራሴነት የምስክር ወረቀቱን ማሳደስ አለበት፡፡
፪. የንግድ እንደራሴው በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) በተወሰነው ጊዜ ውስጥ የንግድ እንደራሴነት የምስክር ወረቀቱን ካላሳደሰ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ የማሳደሻ ክፍያውን ሃያ ከመቶ (፳ ፐርሰንት) በተጨማሪ ለእያንዳንዱ ወር በመክፈል ያሣድሳል፡፡
፫. ማንኛውም የንግድ እንደራሴ የምስክር ወረቀቱን ለማሳደስ ጥያቄ ሲያቀርብ ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሐ›› የተመለከተውን አግባብ ያለውን የማመልከቻ ቅጽ በመሙላት፤
ሀ) በዚህ ደንብ አንቀጽ ፳፮(፩) (ሐ) የተመለከተው ገንዘብ ገቢ ስለመደረጉ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጠ ማስረጃ፣
ለ) የንግድ እንደራሴው የውጭ አገር ዜጋ ከሆነ ለዘመኑ የታደሰ የሥራ ፈቃድና የመኖሪያ ፈቃድ፣ የምስክር ወረቀቱን ለማሳደስ ከሚያቀርበው ማመልከቻ ጋር አያይዞ በሁለት ቅጂ ያቀርባል፡፡
፬. ሚኒስቴሩ የቀረበለት ማመልከቻ የተሟላ ሆኖ ሲያገኘው ከዚህ ደነብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተመለከተውን አግባብ ያለውን ክፍያ በማስከፈል የንግድ እንደራሴነት የምስክር ወረቀቱን በአምስት የሥራ ቀን ውስጥ አድሶ ይሰጠዋል፡፡
፭. ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፬) መሠረት የቀረበውን ማመልከቻ ያልተቀበለው እንደሆነ ያልተቀበለበትን ምክንያት በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ በጽሑፍ ይገልጽለታል፡፡
የንግድ እንደራሴ የምስክር ወረቀት ስለሚሠረዝባቸው ሁኔታዎች
፩. ሚኒስቴሩ የንግድ እንደራሴነት የምስክር ወረቀት መሠዝ የሚችለው፣ የንግድ እንደራሴው፤
ሀ) ሚኒስቴሩ የሚጠይቀውን መረጃ ለማቅረብ ፈቃደኛ ካልሆነ፣
ለ) ለሚኒስቴሩ ያቀረበው መረጃ ሐሰት ሆኖ ከተገኘ፣
ሐ) የንግድ እንደራሴነቱን ሥራ የተወ እንደሆነ፣
መ) ከተፈቀደለት የሥራ መስክ ውጭ መሥራቱ ከተረጋገጠ፣ ወይም
ሠ) በተወሰነው ጊዜ ውስጥ የምስክር ወረቀቱን ሳያሳድስ ከቀረ ነው፡፡
፪. ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት የምስክር ወረቀቱ እንዲሰረዝ ውሣኔ ከመስጠቱ በፊት የንግድ እንደራሰው ሃሣቡን በፅሁፍ እንዲገልጽ የአንድ ወር ጊዜ ይሰጠዋል፡፡
፫. ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) በተወሰነው ጊዜ ውስጥ የንግድ እንደራሰው የሚያቀርበውን ማስረጃ መርምሮ ውሣኔ ይሰጣል፣ የንግድ እንደራሴው በዚህ ጊዜ ውስጥ ካልቀረበ ወይም የቀረበው መረጃ ብቁ ሆኖ ካልተገኘ የምስክር ወረቀቱን ይሠርዛል፡፡
ምትክ የንግድ እንደራሴነት የምስክር ወረቀት ስለመጠየቅ
የምስክር ወረቀቱ የጠፋበት ወይም የተበላሸበት የንግድ እንደራሴ ለሚኒስቴሩ በፅሁፍ ሲያመለክት ሚኒስቴሩ የተበላሸውን የምስክር ወረቀት በማስመለስና ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ‹‹ሀ›› የተመለከተውን አግባብ ያለውን ክፍያ በስከፈል ለንግድ እንደራሴው ምትክ የንግድ እንደራሴነት የምስክር ወረቀት በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ይሰጠዋል፡፡

ክፍል አምስት
ንግድ እንዲስፋፋ ስለማስተባበር
፴፩. ስለንግድ ማስፋፋት
በአዋጁ አንቀጽ ፴፯ እና ፴፰ በተመለከተው መሠረት ሚኒስቴሩ የአገሪቱ የወጪ ንግድና የአገር ውስጥ የንግድ ሥራ እንዲስፋፋ ለማበረታታት የሚያስፈልገው ፈንድ የሚሰባሰብበትን፣ የሚተዳደርበትንና ሥራ ላይ የሚውልበትን ሁኔታ ያቅዳል፣ ያደራጃል፣ ያስተባብራል፣ አግባብ ባለው አካል ሲፈቀድም ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

፴፪. የንግድ ማስፋፊያ ፈንድ ስለማሰባሰብ
የንግድ ማስፋፊያ ፈንድ ማሰባሰቢያ ምንጮች ከዚህ የሚከተሉት ይሆናሉ፤
፩. ሚኒስቴሩ ከሚያደርገው የንግድ ምዝገባ፣ ከሚሰጠው ፈቃድ፣ ምስክር ወረቀትና የንግድ መረጃ የሚገኝ ገቢ፣
፪. በንግድ መስክ የሚቋቋሙ ማኅበራትና ነጋዴዎች በፈቃደኝነት ከሚያደርጉት መዋጮ ወይም ስጦታ የሚገኝ ገቢ፣
፫. ከሌሎች ምንጮች በዕርዳታ ወይም በስጦታ የሚገኝ ገቢ፡፡

፴፫. የማስፋፊያ ፈንድ በሥራ ላይ ስለማዋል
ሚኒስቴሩ ከዚህ በላይ በአንቀጽ ፴፪ መሠረት የሚሰበሰበውን ገቢ ለሚከተሉት ዓላማዎች ያውለዋል፤
፩. ወጪ ምርቶች በጥራትም ሆነ በመጠን ስለሚሻሻሉበትና የውጭ ምንዛሪ በብዛት ስለሚያስገኙበት መንገድ ለሚደረጉ ጥናቶች፣
፪. በውጭ ንግድ ሥራ፣ በውጭ ንግድ አስተዳደርና ማስፋፋት ተግባራት ለተሠማሩ ሠራተኞችና ድርጅቶች የሚዘጋጁ ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሽልማቶች ሥልጠናዎችና ሴሚናሮች ለማካሄድ፣
፫. የአገሪቱን ምርቶች በውጭ አገር ለማስተዋወቅና ተፈላጊነት እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ኤግዚቢሽኖችን ለማመቻቸትና ለማዘጋጀት፣
፬. በሌሎች አገሮች አማካይነት በሚዘጋጅ ኤግዚቢሽኖችና የንግድ ትምህርታዊ ጉብኝቶች ላይ ለሚሣተፉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለሚሰጥ ድጋፍ፣
፭. የገበያ ሁኔታ ለመከታተልና መረጃዎችን ለማሰባሰብ፣
፮. በክልሎች ውስጥና በክልሎች መካከል ንግድ ስለሚስፋፋበት ሁኔታ ለሚደረጉ ጥናቶች፣
፯. ወጪ ንግድ ስለሚስፋፋበትና ስለሚዳብርበት እንዲሁም የገቢ ንግድ በአግባቡ ስለሚካሄድበት ሁኔታ ለሚደረግ ጥናት፣

፴፬. ደንቡ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ ደንብ ከሐምሌ ፩ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ.ም ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ የካቲት ፳፱ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ.ም
መለስ ዜናዊ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ጠቅላይ ሚኒስትር