ደንብ ቁጥር ፲/፲፱፻፹፱ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

ደንብ ቁጥር ፲/፲፱፻፹፱ ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲/፲፱፻፹፱
የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ለማቋቋም
የወጣ የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ

የሚኒስትሮች ምክት ቤት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈፈሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር ፬/፲፱፻፹፯ አንቀጽ ፭ እና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር ፳፭/፲፱፻፹፬ በአንቀጽ ፵፯/፩/ሀ/ መሠረት ይህን ደንብ አውጥቷል፡፡
፩. አጭር ርዕስ
ይህ ደንብ ‹‹የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፲/፲፱፻፹፱›› ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. መቋቋም
፩. የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን (ከዚህ በኋላ ‹‹ኮርፖሬሽኑ›› እየተባለ የሚጠራ) የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ በዚህ ደንብ ተቋቁሟል፡፡
፪. ኮርፖሬሽኑ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር ፳፭/፲፱፻፹፬ መሠረት ይተዳደራል፡፡

፫. ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን
በመንግሥት የሚሰየም አካል የኮርፖሬሽኑ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ይሆናል፡፡

፬. ዋና መሥሪያ ቤት
የኮርፖሬሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ ሆኖ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች እንደአስፈላጊነቱ በማናቸውም ሥፍራ ሊኖረው ይችላል፡፡
፭. ዓላማ
ኮርፖሬሽኑ የተቋቋመባቸው ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፤
፩. የመንግሥትን የልማት ፖሊሲና ቅድሚያ ትኩረት መሠረት በማድረግ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን ማቋቋም፣ ማካሄድ፣ መጠገንና ማስፋፋት፤
፪. የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የቴሌፎን፣ የቴሌክስ፣ የቴሌፋክስ እና ሌሎች የኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን መስጠት፤
፫. የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ተቀብሎ ማስተላለፍን ጨምሮ በተቀናጀ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሚሰጡ የኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን መስጠት፤
፬. የቴሌኮሙኒኬሽንና ተዛማጅ መሣሪያዎችን መጠገን፣ መገጣጠምና ማምረት፤
፭. ለቴሌኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የሥልጠና አገልግሎት መስጠት፤
፮. ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተዛማጅ የሆኑ ሥራዎችን ማካሄድ፡፡

፮. ካፒታል
ለኮርፖሬሽኑ የተፈቀደለት ካፒታል ብር ፩ ቢሊዮን ፬፻፸፫ ሚሊዮን ፱፻፹ ሺህ ፭፻፸፰ (አንድ ቢሊዮን አራት መቶ ሰባ ሦስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሺህ አምስት መቶ ሰባ ስምንት ብር) ሲሆን ከዚህ ውስጥ ብር ፬፻፹ ሚሊዮን ፬፻፶፱ ሺህ ፭፻፸፰ (አራት መቶ ሰማንያ ሚሊዮን አራት መቶ ሃምሣ ዘጠኝ ሺህ አምስት መቶ ሰባ ስምንት ብር) በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ተከፍሏል፡፡

፯. ኃላፊነት
ኮርፖሬሽኑ ካለው ጠቅላላ ንብረት በላይ በእዳ ተጠያቂ አይሆንም፡፡

፰. ኮርፖሬሽኑ የሚቆይበት ጊዜ
ኮርፖሬሽኑ ላልተወሰነ ጊዜ ይቆያል፡፡

፱. የመብትና ግዴታ መተላለፍ
በአዋጅ ቁጥር መሠረት ፩፻፴፩/፲፱፻፵ይተዳደር የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን መብትና ግዴታዎች በዚህ ደንብ ለኮርፖሬሽኑ ተላልፈዋል፡፡

፲. ደንቡ የሚጸናበት ጊዜ
ይህ ደንብ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡
አዲስ አበባ ኅዳር ፲፱ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ.ም.
መለስ ዜናዊ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ጠቅላይ ሚኒስትር