ስለ መክሰር | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

ስለ መክሰር

አንቀጽ ፪
ስለ መክሠር
ምዕራፍ ፩
ስለ መክሠር የሚሰጡ ፍርዶች

ቊ ፱፻፸፬ ባለሥልጣን ስለሆነው ፍርድ ቤት፡፡

(፩) በመክሠር ረገድ የሚቀርቡትን ክሶች ለመወሰን ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት፤ የነጋዴው ሥራ በተቋቋመበት፤ ወይም ይህ ሰው ብዙ ንግዶች ያሉት እንደ ሆነ፤ ዋናው የንግዱ ሥራ ባለበት ቦታ ያለው ፍርድ ቤት ነው፡፡
(፪) ይህም የንግዱ ዋና መሥሪያ ቤት በውጭ አገር የሆነ እንደ ሆነ፤ የኢንተርናሲዮናል ስምምነቶች አፈጻጸም ሳይነካ መክሠሩ በውጭ አገር ፍርድ ቤቶች የተወሰነ ቢሆንም እንኳ መክሠሩ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ሊታይ ይቻላል፡፡

ቊ ፱፻፸፭ ነገሩን ለፍርድ ቤት ስለ ማቅረብ፡፡

የነጋዴው መክሠር ነገር በፍርድ ቤት የሚታየው፤
(ሀ) ባለዕዳ የሆነው ነጋዴ መክሠሩን ለማስታወቅ ማመልከቻ ሲያቀርብ ወይም፤
(ለ) አንድ ወይም ብዙ ከነጋዴው ላይ ገንዘብ የሚጠይቁ ሰዎች አቤቱታ ሲያቀርቡ ወይም፤
(ሐ) ሕግ አስከባሪው ሲጠይቅ ወይም፤
(መ) ፍርድ ቤት ራሱ ሲፈቅድ ነው፡፡

ቊ ፱፻፸፮ ስለ ቀዳሚ ምርመራ፡፡

(፩) ፍርድ ቤት ጠቃሚ መስሎ የታየው እንደ ሆነ፤ የባለዕዳውን ሁኔታና ተግባር የሚመረምር አንድ ዳኛ መርጦ ማዘዝ ይችላል፡፡
(፪) ይህን ትእዛዝ የተቀበለ ዳኛ ንብረት ጠባቂ እንዲረዳው መጠየቅ ይችላል፡፡
(፫) በምርመራ የተገኘውን ሁሉ ለፍርድ ቤት ማስታወቅ ይገባዋል፡፡

ቊ ፱፻፸፯ መክፈል የተቋረጠበትን ጊዜ ስለ መወሰን፡፡

(፩) በመጀመሪያ ነገሩ በሚሰማበት ጊዜ በቁጥር ፱፻፸፮ የተመለከተውን መግለጫ ከተቀበለ በኋላ ፍርድ ቤቱ፤
(ሀ) የመክፈሉን መቋረጥ የተረዳው እንደ ሆነ፤ መክፈል የተቋረጠበትን ቀን  ይወስናል፤
(ለ) የመጠበቂያ ስምምነትን የሚመለከቱ ወሳኔዎች ሳይነኩ፤ መክሠሩን ይወስናል፡፡
(፪) መክፈሉ የተቋረጠበት ጊዜ ያልተወሰነ እንደ ሆነ፤ በቁጥር ፱፻፸፰ የተደነገጉት ውሳኔዎች እንደ ተጠበቁ ሆነው፤ መክፈሉ የተቋረጠው የመክሠሩ ፍርድ በተሰጠበት ቀን እንደ ሆነ ይቆጠራል፡፡

ቊ ፱፻፸፰ መክፈሉ የተቋረጠበትን ጊዜ ስለ ማርዘም፡፡

(፩) ፍርድ ቤቱ፤
(ሀ) የከሠረው ሰው ንብረት ጠባቂ ወይም አግባብ ያለው ማናቸውም ወገን ሲጠይቅ፤ ወይም
(ለ) የሕግ አስከባሪው ሲጠይቅ፤ ወይም
(ሐ) ፍርድ ቤቱ ራሱ ሲፈቅድ፤ መክሠርን የሚያስታውቅ ፍርድ ከተሰጠ በኋላ በሚሰጥ ፍርድ፤ ወይም በሚሰጡ ፍርዶች በቁጥር ፱፻፸፯  በንኡስ ቁ ፪ የተወሰነውን የመክፈል መቋረጥን ጊዜ እልፍ ለማድረግ ይችላል፡፡
(፪) ስለሆነም በቁጥር ሺ፵፮ የተወሰነው ጊዜ ካለፈ በኋላ በንኡስ ቁ ፩ መሠረት የሚቀርበው ማመልከቻ መቀበል አይቻልም፡፡ እንዲሁም ይኸው ጊዜ ካለፈ በኋላ ስለ መክፈል መቋረጥ የተወሰነው ጊዜ ሊለወጥ አይቻልም፡፡
(፫) በማናቸውም አኳኋን ስለ መክፈሉ መቋረጥ የተወሰነው ጊዜ፤ መክሠርን ለማስታወቅ ከተሰጠው ፍርድ በፊት፤ ከሁለት ዓመት የበለጠ ጊዜ ሊሆን አይችልም፡፡

ቊ ፱፻፸፱ ንግዱ ከተቋረጠ በኋላ ስለሚደረግ መክሠር፡፡

(፩) ስሙ ከንግድ መዝገብ ከመሰረዙ አስቀድሞ ዕዳውን ከመክፈል ያቋረጠ ነጋዴ ሁሉ፤ ስሙ ከንግድ መዝገብ በተሰረዘ በሚከተለው ዓመት ውስጥ መክሠሩ ሊነገር ይቻላል፡፡
(፪) ነጋዴው ያልተመዘገበ የሆነ እንደ ሆነ፤ መክፈሉን ባቋረጠ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን፤ መክሠሩ ሊነገር ይቻላል፡፡

ቊ ፱፻፹ ከሞት በኋላ ስለሚደረግ መክሠር፡፡

(፩) አንድ ነጋዴ አከፋፈሉን በማቋረጥ ሁኔታ ላይ ሆኖ የሞተ እንደ ሆነ፤ ከሞተ በኋላ በሚከተለው ዓመት ውስጥ መክሠሩ ሊነገር ይቻላል፡፡
(፪) ፍርድ ቤቱም፤
(ሀ) በአንድ ገንዘብ ጠያቂ፤ ወይም
(ለ) በሕግ አስከባሪው አመልካችነት እንዲሁም፤
(ሐ) በራሱ ሥልጣን ነገሩን መመርመር ይችላል፡፡
(፫) ማንኛቸውም ወራሽ በውርስ የተላለፈለት ሀብት ከግል ሀብቱ ጋራ እንዳይደባለቅ ለማድረግ፤ የሞተው ሰው መክሠር እንዲነገር ለመጠየቅ ይችላል፡፡
(፬) ነጋዴው ከሞተ በኋላ የሚፈረደው የመክሠር ፍርድ፤ በፍትሐ ብሔር ድንጋጌዎች መሠረት ገንዘብ ጠያቂዎች አግኝተው የነበረውን የንብረት መለየት ጥቅም ውጤት ወዲያውኑ በደንብ ያስቀረዋል፡፡

ቊ ፱፻፹፩ ስለ መክሠር ፍርድ፡፡

መክሠርን ለማስታወቅ የሚሰጠው ፍርድ፤ የኪሣራውን ሥራ መርማሪ አንድ ዳኛና፤ አንድ ወይም ብዙ የከሠረውን ሰው ንብረት ጠባቂዎች መመረጥ ይኖርበታል፡፡

ቊ ፱፻፹፪ ስለ ፍርድ አፈጻጸም፡፡

 ስለ መክሠር ረገድ የተሰጡ ፍርዶችና ትአዛዞች ለጊዜው ተፈጻሚዎች ይሆናሉ፡፡

ቊ ፱፻፹፫ የፍርድ ማስታወቂያ፡፡

(፩) በቁጥር ፱፻፸፯፣ ፱፻፸፱ እና ፱፻፹ መሠረት የተሰጠ ፍርድ፤ ለዕዳ ከፋዩ፤ ለከሠረ ሰው ንብረት ጠባቂና አቤቱታ ላቀረበው ገንዘብ ጠያቂ ወይም ለወራሹ፤ ቢዘገይ ፍርድ በተሰጠበት ቀን ማግስት ቅጂው ይተላለፋል፡፡ ቅጂው የወገኖቹን ስም፤ የፍርዱን ውሳኔና የተፈረደበትን ቀን የያዘ መሆን አለበት፡፡
(፪) በዚሁ ጊዜ ውስጥ የፍርድ መዝገብ ቤት ሹም የፍርዱን ቅጂ በፍርድ ቤቱ የውጭ በር ለጥፎ እስከ ሦስት ወር ድረስ ማቆየት አለበት፡፡
(፫) የፍርድ የመዝገብ ቤቱ ሹም የፍርዱን ቅጂ ለሕግ አስከባሪው ይልካል፡፡
(፬) የንግድ መዝገብ ኅላፊ የሆነው ሠራተኛ መዝገቡን ማስተካከል ይችል ዘንድ የፍርድ ቤቱ የመዝገብ ቤት ሹም የፍርድን ቅጂ ሦስት ግልባጭ ይልክለታል፡፡ እንደዚሁ ያለው መስተካከል በአገሩ ክፍል የንግድ መዝገብ ውስጥ ከተደረገ በኋላ ለጠቅላላ መዝገብ ክፍል መታወቅና በዚህ ሕግ አንደኛ መጽሐፍ አንቀጽ ፬ መሠረት በንግድ ኦፊሲዮል ጋዜጣ መውጣት አለበት፡፡
(፭) ከዚህም በቀር የመክፈሉ መቋረጥ በተረጋገጠበት ቦታ ሕጋዊ ማስታወቂያዎችን ለመቀበል በተፈቀደለት ጋዜጣ ውስጥ ቅጂው በማስታወቂያ ይወጣል፡፡
(፮) እንዲሁም ማስታወቂያው የዕዳ ከፋዩ የንግድ መሥሪያ ቤቶች በሚገኙበት ቦታ መደረግ አለበት፡፡

ቊ ፱፻፹፬ ፍርድን ስለ መቃወም፡፡

(፩) በመክሠር ረገድ በተሰጠው ፍርድ መቃወሚያ ለማቅረብ የሚቻለው ከተፈረደበት ቀን አንሥቶ እስከ ስምንት ቀን ነው፡፡ በሚለጠፉ፤ ማስታወቂያዎችን ለመቀበል በተፈቀደላቸው ጋዜጣዎች ወይም በንግድ ኦፊሲዬል ጋዜጣ ውስጥ መግባት ላለባቸው ፍርዶች ግን፤ ይህ ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው የሚያስፈልገው ሥርዐት በመጨረሻው ከተደረገበት ቀን አንሥቶ ነው፡፡
(፪) የመክሠር ፍርድ እንዲፈረድ የጠየቀው ሰው፤ በተፈረደው በመክሠር ፍርድ ላይ መቃወሚያ ለማቅረብ አይችልም፡፡
(፫) ባለዕዳው የሚያቀርበው መቃወሚያ በማናቸውም ጊዜ ፍርድን የማገድ ውጤት አይኖረውም፡፡

ቊ ፱፻፹፭ በመቃወሚያው ላይ ስለ ተሰጠ ፍርድ

(፩) መቃወሚያውን ውድቅ የሚያደርገውን ፍርድ ተቃዋሚው እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡
(፪) የመክሠር ማስታወቂያን የሚሽረው ፍርድ የከሠረው ሰው ንብረት ጠባቂ የመክሠርን ፍርድ የጠየቀው ገንዘብ ጠያቂ መቃወሚያ አላቀረበ እንደ ሆነ ባለዕዳው እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ በዚህም ፍርድ ላይ በቁጥር ፱፻፹፫ የተደነገጉት ሥርዐቶች ተፈጻሚዎች ይሆናሉ፡፡

ቊ ፱፻፹፮ ስለ ፍርድ ይግባኝ፡፡

(፩) መክሠርን ለማስታወቅ በተሰጠው ፍርድ ላይ ይግባኝ ለማለት የተወሰነው ጊዜ፤ ፍርዱን እንዲያውቀው ከተደረገበት ቀን አንሥቶ እስከ ዐሥራ አምስት ቀን ነው፡፡
(፪) ይግባኙም በአጭር ሥነ ሥርዐት በሦስት ወር ውስጥ ይፈረዳል፡፡ ፍርዱም ወዲያውኑ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

ቊ ፱፻፹፯ መቃወሚያ ወይም ይግባኝ ሊቀርብበት ስለማይቻል ፍርድ፡፡

(፩) መቃወሚያ ወይም ይግባኝ ሊቀርብባቸው የማይቻሉ ፍርዶች እነዚህ ናቸው፡፡
(ሀ) የመክሠርን ሥራ መርማሪ ዳኛ ወይም ምትኩን ለመሾም፤ ንብረት ጠባቂዎችን ለመሾም ወይም ለመሻር የተሰጠ ፍርድ፤
(ለ) ነጻ ለመውጣት በሚደረጉ ጥያቄዎችና ለዕዳ  ከፋዩና ለቤተሰቡ ርዳታ ለማግኘት በሚደረጉ ጥያቄዎች ላይ የተሰጠ ፍርድ፤
(ሐ) በንብረቱ ውስጥ የሚገኙት ዕቃዎች ወይም ሸቀጦች እንዲሸጡ የሚፈቅድ ፍርድ፤
(መ) መርማሪ የሆነ ዳኛ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፤ በሰጠው ትእዛዝ ላይ ፍርድ ቤት በቀረበ አቤቱታ የተሰጠ ፍርድ፤
(ሠ) የንግዱ ሥራ እንዲቀጥል የሚፈቅድ ፍርድ፤
(፪) መርማሪ የሆነው ዳኛ በንኡስ ቁጥር ፩ (መ) በተመለከተው ጉዳይ ዳኝነት ውስጥ አይገባም፡፡

ቊ ፱፻፹፰ መክሠርን ለማስታወቅ፤ የተሰጠውን ፍርድ ስለ ማንሣት፡፡

(፩) ይህ ፍርድ ከተሰጠበት ቀንና በተቃዋሚነት ወይም በይግባኝ ላይ ውሳኔ በሚደረግበት ቀን መካከል ለገንዘብ ጠያቂዎች በመክፈል ወይም ከነርሱ ጋራ ስምምነት በማድረግ የከሠረው ሰው መክፈልን ከማቋረጥ ሁኔታ የወጣ እንደ ሆነ፤ መክሠሩን ለመግለጽ የተሰጠው ፍርድ መነሣት አለበት፡፡
(፪) በማናቸውም ሁኔታ የመክሠሩን ሥራ የሚያስፈጽሙት ሰዎች የፈጸሟቸው ሕጋዊ የሆኑ ሥራዎች ያስገኙዋቸው ውጤቶች እንዳሉ ይቆያሉ፡፡

ምዕራፍ ፪
የመክሠርን ሥራ የሚያስፈጽሙ ሰዎች
ክፍል ፩
ስለ ፍርድ ቤት

ቊ ፱፻፹፱ ስለ ፍርድ ቤቱ ሥልጣን፡፡

የመክሠርን ፍርድ የፈረደው ፍርድ ቤት ጠቅላላውን የመክሠር ሥነ ሥርዐት ይቆጣጠራል፡፡ ከመርማሪው ዳኛ ሥልጣን በላይ በሆኑት አስቸጋሪ ነገሮች ሁሉ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ መርማሪው ዳኛ በሚሰጣቸው ትዕዛዞች ሁሉ ይግባኙን ያያል፡፡

ቊ ፱፻፺ ስለ ፍርድ ቤቱ ሥልጣን፡፡

በፍርድ ቤት ደንቦች መሠረት፤ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት ከሚታዩት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ከሚመለከቱት ክሶች በቀር፤ የመክሠርን ፍርድ የፈረደው ፍርድ ቤት ከመክሠር ጉዳይ የተነሣ የሚቀርቡትን ክሶች ሁሉ ማየት ሥልጣን አለው፡፡

ቊ ፱፻፺፩ ስለ መርማሪው ዳኛ ሥልጣን፡፡

(፩) መርማሪው ዳኛ የመክሠር ሥራዎችን ለመጠበቅና ለማፋጠን በተለይ የተሾመ ነው፡፡
(፪) ከመክሠር አሠራር በሚነሡት በዚሁ ፍርድ ቤት ሥልጣን ውስጥ በሆኑት ክርክሮች ሁሉ ለፍርድ ቤት መግለጫ ማቅረብ አለበት፡፡ የዚሁ መግለጫ መኖር በፍርድ ቤቱ ውሳኔዎች ውስጥ መጠቀስ አለበት፡፡
(፫) መርማው ዳኛ ተገቢ የሆኑትን ባለሥልጣኖች በመጠየቅ ወይም በራሱ ሥልጣን፤ በመክሠር ውስጥ የሚገኘውን ንብረት ለመጠበቅ አስፈላጊ የሆኑትን ሥራዎች ሁሉ ይፈጽማል፡፡
(፬) በሕግ የታዘዘ ሲሆን ወይም አስፈላጊ መሆኑን የገመተ እንደ ሆነ፤ መርማሪው ዳኛ የገንዘብ ጠያቂዎች  ኮሚቴ ስብሰባ እንዲደረግ ጥሪ ያደርጋል፡፡
(፭) መርማሪው ዳኛ ራሱ እንዲሾም በሕግ ካልታዘዘ በቀር ርዳታቸው ለመክሠሩ አሠራር አስፈላጊ የሆኑትን ሰዎች የከሠረው ሰው ንብረት ጠባቂ እንዲሾማቸው መርማሪው ዳኛ ሊፈቅድለት ይችላል፡፡
(፮) በከሳሽነት ወይም በተከሳሽነት የከሠረው ሰው ንብረት ጠባቂ በፍርድ ቤት እንዲነጋገር መርማሪው ዳኛ ይፈቅድለታል፡፡

ቊ ፱፻፺፪ ስለ መርማሪው ዳኛ ትእዛዞች

(፩) የመርማሪው ዳኛ ትእዛዞች ወደያውኑ በፍርድ መዝገብ ቤት ይቀመጣሉ፡፡ መቀመጣቸውም በረኮማንዴ ደብዳቤ ለባለጉዳዮቹ ይነገራቸዋል፡፡
(፪) መርማሪው ዳኛ በሰጣቸው ትእዛዞች ላይ ባለጉዳዮቹ መቃወሚያቸውን ለፍርድ ቤቱ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ የረኮማንዴው ደብዳቤ ከተላከበት ቀን አንሥቶ በዐሥር ቀን ውስጥ መቃሚያው ለፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡
(፫) ፍርድ ቤቱም በመጀመሪያው ቀጠሮ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

ቊ ፱፻፺፫ መርማሪውን ዳኛ ስለ መተካት፡፡

ፍርድ ቤቱ በራሱ አስተያየት በማናቸውም ጊዜ መርማሪውን ዳኛ ከአባሎቹ ባንድ መተካት ይችላል፡፡

ክፍል ፫
የከሠረው ሰው ንብረት ጠባቂዎች

ቊ ፱፻፺፬ ስለ ንብረት ጠባቂዎች መሾም፡፡

(፩) ንብረት ጠባቂዎቹ፤ በኢትዮጵያ ከሚኖሩ ባንድ ሊስት ላይ ከተጻፉ ከተከበሩና ከታወቁ ሰዎች ውስጥ ይመረጣሉ፡፡ ይኸንንም ሊስት በየዓመቱ መጀመሪያ የንግድ ሚኒስቴር ያዘጋጀል፡፡
(፪) የሚሾሙትም ንብረት ጠባቂዎች በልክ እጅግ ቢበዛ ሦስት ነው፡፡
(፫) ብዙ ንብረት ጠባቂዎች የተሾሙ እንደ ሆነ ባንድነት ይሠራሉ፡፡ መርማሪው ዳኛ ግን አስፈላጊ መሆኑን እያየ ከመካከላቸው ለአንዱ ወይም ለብዙዎቹ ለብቻ የመሥራት መብትን ማሳየት ይችላል፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ ይህን ሥልጣን የተቀበሉ ጠባቂዎች ብቻ አላፊዎች ናቸው፡፡
(፬) ለንብረት ጠባቂነት ለመሾም የማይችሉ ሰዎች፤
(ሀ) ከስሯል ተብሎ  ተፈርዶበት የነበረ ሰው፤ ወይም የተፈረደበት ሰው፤ ወይም
(ለ) የሕዝባዊ መብቱን፤ ለጊዜውም ቢሆን፤ የሚከለክል የቅጣት ፍርድ የተፈረበደት ሰው፤ ወይም
(ሐ) የባለዕደው፤ እስከ አራተኛ ደረጀ ድረስ፤ የሥጋ ወይም የጋብቻ ዘመድ የሆነ ሰው፤ ወይም
(መ) ከኪሣራው ላይ ገንዘብ ጠያቂ የሆነ ሰው ናቸው፡፡
(፭) ንብረት ጠባቂዎቹ የባለዕደውን ንብረት ለመግዛት አይችሉም፡፡

ቊ ፱፻፺፭ ስለ ንብረት ጠባቂዎች ሥልጣን

(፩) ንብረት ጠባቂው የከሠረውን ሰው ንብረት በመርማሪው ዳኛ ጥበቃ ሥር ሆኖ ማስተዳደር አለበት፡፡ ከሦስተኛ ወገኖች ጋራ ስላለው ጉዳይ በኅብረት ውስጥ ላሉት ገንዘብ ጠያቂዎች እንደራሴ ነው፡፡
(፪) ሥልጣኖቹ የማይተላፉ ናቸው፤ የሆነ ሆኖ መርማሪው ዳኛ ከፈቀደለት ለአንዳንድ ሥራ በተለየ ሥልጣኑን ለሌላ ሰው ለማሳለፍ ይችላል፡፡

ቊ ፱፻፺፮ ገንዘብ ስለ ማስቀመጥ፡፡

(፩) በመርማሪው ዳኛ ትእዛዝ የሚወሰኑት የዳኝነትና የአስተዳደር ወጪዎች ሁሉ ከተቀነሱ በኋላ፤ ንብረት ጠባቂው የሚቀበላቸው ገንዘቦች ሁሉ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ባንክ በከሠረው ንብረት ስም በሚከፈተው ልዩ ሒሳብ ውስጥ ወዲያውኑ ተቀማጭ መሆን አለባቸው፡፡ ይኸውም ገንዘብ፤ መርማሪው ዳኛ ፈርሞ በሚሰጠው የመክፈያ ትእዛዝ መሠረት ካልሆነ በቀር ለመውጣት አይችልም፡፡
(፪) ያሉም እንደ ሆነ፤ ለዚሁ ነገር በፍትሐ ብሔርና በወንጀል ሕግ የተደነገጉት ቅጣቶች እንደ ተጠበቁ ሆነው፤ በንኡስ ቁ ፩ የተመለከቱትን ትእዛዞች ያልፈጸመ የንብረት ጠባቂ መሻር አለበት፡፡

ቊ ፱፻፺፯ ንብረት ጠባቂዎች በሠሩት ሥራዎች አቤቱታን ስለ ማቅረብ፡፡

ንብረት ጠባቂዎት በሠሩት ሥራ ላይ የከሠረው ሰውና ማናቸውም ሌላ ባለጉዳይ ለመርማሪው ዳኛ አቤቱታ ለማቅረብ ይችላል፡፡ ዳኛውም በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ ውሳንኔ ይሰጣል፡፡

ቊ ፱፻፺፰ ንብረት ጠባቂዎችን ሰለ መሻር፡፡

(፩) መርማሪው ዳኛ በከሠረው ሰው ወይም በገንዘብ ጠያቂዎቹ ኩሚቴ ስብሰባ በቀረቡለት አቤቱታዎች መሠረት ወይም በራሱ ሥልጣን አንዱ ወይም ብዙዎቹ ንብረት ጠባቂዎች እንዲሻሩ ለፍርድ ቤቱ ሐሳብ ለማቅረብ ይችላል፡፡
(፪)  መርማሪው ዳኛ ለቀረቡለት አቤቱታዎች በአምስት ቀን ውስጥ ውሳኔ ያልሰጠ እንደ ሆነ፤ አቤት ባይዎቹ አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላሉ፡፡
(፫) ፍርድ ቤቱ የመርማሪውን ዳኛ መግለጫ፤ የንብረት ጠባቂዎቹን ማስረጃና የሕግ አስከባሪውን ሐሳብ በዝግ ችሎት ይሰማል፡፡ ፍርድ ግን በአደባባይ ይነገራል፡፡

ቊ ፱፻፺፱ ንብረት ጠባቂዎችን ስለ መተካት፡፡

አንድ ወይም ብዙ ንብረት ጠባቂዎች ለመጨመር ወይም ለመተካት አስፈላጊ የሆነ እንደ ሆነ መርማሪው ዳኛ ለፍርድ ቤቱ አስታውቆ ፍርድ ቤቱ አስፈላጊውን ይሾማል፡፡

ቊ ሺ፡፡ ስለ ንብረት ጠባቂዎች አላፊነት፡፡

(፩) ንብረት ጠባቂዎች ሥራቸውን በሚያከናውኑት ጊዜ ሁሉ እንደ መንግሥት ባለሥልጣን ይቆጠራሉ፡፡ የተሰጣቸውን ተግባር በትጋት መፈጸምና ክርክርም የተነሣ እንደ ሆነ፤ በዚህ ትእዛዝ መሠረት የፈጸሙ መሆናቸውን ማስረዳት አለባቸው፡፡
(፪) የፈጸሙትን የአስተዳደር ሥራ ሁሉ በየቀኑ የሚመዘግቡበት፤ አስቀድሞ በመርማሪው ዳኛ የተፈረመ፤ አንድ መዝገብ መያዝ አለባቸው፡፡
(፫) የኪሣራው ሥራ በሚከናወንበትም ጊዜ በተሻረው ጠባቂ ላይ የሚቀርበውን የአላፊነት ክስ ሁሉ አዲሱ ንብረት ጠባቂ አስቀድሞ ከመርማሪው ዳኛ ፈቃድ ተቀብሎ ያከናውናል፡፡
(፬) የኪሣራው ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ ቢሆን፤ ሥራውን የሚተው ንብረት ጠባቂ በቁጥር ሺ ፺ እንደ ተመለከተው ስለሥራው አመራር መግለጫ መስጠት አለበት፡፡

ቊ ሺ፩፡፡ የንብረት ጠባቂዎች የሥራ ዋጋ፡፡

(፩) የንብረት ጠባቂዎችን ወጪዎችና የሥራ ዋጋዎች የሚወስን መርማሪው ዳኛ ነው፡፡
(፪) የሥራ ዋጋዎች በቁጥር ሺ ፺ አንደ ተመለከተው የሥራ ማስተዳደሪያው መግለጫ ካልተሰጠ በቀር አይከፈሉም፡፡ የሆነ ሆኖ በቂ ምክንያት ከተገኘ መርማሪው ዳኛ ለንብረት ጠባቂዎች ከሚገባቸው ገንዘብ አስቀድመው እንዲከፈላቸው ለመፍቀድ ይችላል፡፡
(፫) የከሠረው ሰውና ገንዘብ ጠያቂዎቹ በንኡስ ቁ ፩ መሠረት ስለተወሰነው የሥራ ዋጋ በስምንት ቀን ውስጥ መቃወሚያዎችን ለማቅረብ ይችላሉ፡፡ ፍርድ ቤቱም በዝግ ችሎት ውሳኔ ይሰጣል፡፡
(፬) በዚህ ቁጥር ከተመለከቱት በቀር ለንብረት ጠባቂዎች ሌላ ገንዘብ ሊከፈላቸው አይቻልም፡፡ ያሉም እንደ ሆነ፤ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ቅጣቶች እንደ ተጠበቁ ሆነው፤ ይህን ክልከላ በመጣስ የተከፈሉ ገንዘቦች ሁሉ ተመላሽ መሆን አለባቸው፡፡

ክፍል ፬
የገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ

ቊ ሺ፪፡፡ ኮሚቴውን ስለ ማቋቋም፡፡

(፩) በቁጥር ሺ፵፬ እንደ ተመለከተው የገንዘብ ጠያቂዎች ሁኔታ የሚገልጽ ትእዛዝ በፍርድ መዝገብ ከተቀመጠበት ቀን አንሥቶ በሚከተሉት ዐሥር ቀኖች ውስጥ የባለገንዘቦች ኮሚቴ መቋቋም አለበት፡፡
(፪) መርማሪው ዳኛ ጠቃሚ መሆኑን የገመተ እንደ ሆነ ከሚቴው ለጊዜው፤ ከዚህ ጊዜ በፊት፤ እንዲቋቋም ለማድረግ የችላል፡፡
(፫) ከገንዘብ ጠያቂዎች ውስጥ ሦስት ወይም አምስት አባሎች መርጦ መርማሪው ዳኛ ኮሚቴውን ያቋቁማል፤ የኮሚቴውንም ፕሬዚዳንት ይመርጣል፡፡
(፬) ከኮሚቴው ውስጥ እንዲተኩ የጠየቁትን አባሎች መርማሪው ዳኛ በሌሎች አሎባች ሊተካቸው ይችላል፡፡ ዳኛው ባቀረበው ሐሳብ መሠረት በሚሰጥ የፍርድ ቤት ውሳኔ ካልሆነ በቀር ከሥራቸው ሊሻሩ አይችሉም፡፡
(፭) ማናቸውም ከባለዕዳው ጋራ እስከ አራት ብት ድረስ ጭምር የሥጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ያለው ሰው የገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ አባል ለመሆን አይችልም፡፡

ቊ ሺ፫፡፡ ስለ ኮሚቴው ሥራ፡፡

(፩) ኮሚቴው ሐሳቡን እንዲሰጥ ሕጉ የሚያስገድድበት ሁኔታ ሳይነካ፤ ፍርድ ቤቱ ወይም መርማሪው ዳኛ ጠቃሚ መሆኑን የገመተ እንደ ሆነ፤ ኮሚቴው ሐሳቡን እንድሰጥ ሊጠየቅ ይችላል፡፡
(፪) የኮሚቴው ሐሳብ እንዲታወቅ በተጠየቀ ጊዜ ወይም ስብሰባ እንዲደረግ ለፕሬዚዳንቱ አስፈላጊ መስሎ በታየው ጊዜ ሁሉ፤ ፕሬዚዳንቱ ኮሚቴውን ይሰበስባል፡፡
(፫) የኮሚቴው ውሳኔዎች በድምፅ ብልጫ ይሰጣሉ፡፡
(፬) ኮሚቴው ባለዕዳው ያቀረበውን ሒሳብና የሁኔታውን መግለጫ መመርመርና የንብረት ጠባቂዎቹን ሥራ በተለይ መጠባበቅ አለበት፡፡
(፭) ኮሚቴው በማናቸውም ጊዜ የመክሠሩን አሠራር ሁኔታ፤ ገቢ የሆኑትንና የተከፈሉትን ገንዘቦች ሒሳብ መግለጫ ለመጠየቅ መብት አለው፡፡ ንብረት ጠባቂዎቹም ለሚጀምሩት ወይም ለሚቀጥሎት ክቦች የኮሚቴውን ሐሳብ መቀበል አለባቸው፡፡
(፮) የገንዘብ ጠያቂዎች ኮማቴ አባሎች ለሚያደርጉት ከባድ ጥፋት ብቻ አላፊዎች ናቸው፡፡
(፯) ስለ ሥራቸው ዋጋ አይቀበሉም፤ ነገር ግን በመርማሪው ዳኛ ፊርማ ያደረጓቸው ወጪዎች እነዲመለሱላቸው መብት አላቸው፡፡

ምዕራፍ ፫
የአጠባበቅ ሥራዎች
ክፍል ፩
የአጠባበቅ ውሳኔዎች

ቊ ሺ፬፡፡ የባለዕዳውን መዝገብች ስለ መዝጋት፡፡

(፩) አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ በቁጥር ሺ፲፩ የተነገረው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ንብረት ጠባቂዎቹ፤ ባለዕዳው ባለበት፤ መዝገቦቹን ለመዝጋትና ሒሳቡን ለማቆም ባለዕዳውን ይጠሩታል፡፡
(፪) በዚሁ ጥሪ ባለዕዳው ያልቀረበ እንደ ሆነ፤ በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ እንዲቀርብና መዝገቦችንም እንዲያቀርብ ደረሰኝ ባለው ሬኮማንዴ ደብዳቤ ይጠራል፡፡
(፫) ለመቅረብ የማይችልበትን ምክንያቶች ያስረዳ እንደ ሆነና፤ መርማሪውም ዳኛ በቂ መሆናቸውን የተረዳ እንደ ሆነ፤ ባለዕዳው ስለእርሱ ሌላ ሰው ለመወከል ይችላል፡፡
(፬) ራሱ ለመቅረብ ወይም ወኪል ለመላክ እንቢ ያለ እንደ ሆነ፤ ወይም የሸሸ እንደ ሆነና የማይገኝ እንደ ሆነ አስፈላጊውን ነገር  እንዲያደርግ መርማሪው ዳኛ ለሕግ አስከባሪው ያስታውቃል፡፡

ቊ ሺ፭፡፡ የባለዕዳውን መብቶች ስለ መጠበቅ፡፡

(፩)  ንብረት ጠባቂዎቹ ሥራቸውን እንደ ጀመሩ፤ ለባለዕዳው በራሱ ባለዕዳዎች ላይ ያሉትን መብቶች ለመጠበቅ አስፈላጊውን ተግባር ማድረግ አለበቸው፡፡
(፪)  ባለዕዳው ያላስመዘገበውን፤ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያለውን የመያዣ መብት፤ ንብረት ጠባቂዎቹ ማስመዝገብ አለባቸው፡፡ ንብረት ጠባቂዎቹ ንብረት ጠባቂዎች መሆናቸውን አስረድተው፤ የመያዣውን መብት የሚያስመዘግቡት በኅብረቱ ስም ነው፡፡

ቊ ሺ፮፡፡ የባለዕዳው በሆኑት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ የመያዣ መብትን ስለ ማስመዝገብ፡፡

(፩) ንብረት ጠባቂዎቹ የባለዕዳው በሆኑትና ወደፊትም በሚያገኛቸው የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ በኅብረቱ ስም የመያዣ መብትን ማስመዝገብ አለባቸው፡፡
(፪) በስምምነት የመጨረሻውን ድርሻ ከከፈለ በኋላ ወይም ስምምነት ያልተደረገ እንደ ሆነ የሒሳቡ ማጣራት ሥራ በፍጹም ከተዘጋ በኋላ ባለዕዳው በሚያገኛቸው በማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ የመያዣ መብቶች አይመዘገቡም፡፡

ቊ ሺ፯፡፡ በንግዱ ላይ የመያዣ መብትን ስለ ማስመዝገብ፡፡

(፩) በዚህ ሕግ በሁለተኛው መጽሐፍ ቁጥር ፻፸፪ ንኡስ ቁ (፩) (ለ) በተመለከተው መሠረት ሕጋዊ የሆኑትን የመያዣ መብቶች በባለዕዳው ንግድ ወይም ንግዶች ላይ ንብረት ጠባቂዎቹ ማስመዝገብ አለባቸው፡፡
(፪) መመዝገብ የሚገባው፤
(ለ) የባለዕዳው ስምና አድራሻ፤
(ለ) ባለዕዳው የከሠረ መሆኑ የተወሰነበት ፍርድ የተሰጠበት ቀን፤
(ሐ) ባለዕዳው የከሠረ መሆኑን የወሰነው ፍርድ ቤት ስም፤
(መ) የንግዱ ዐይነትና አድራሻ፤
(ሠ) መያዣ ያደረጉት የንግዱ ክፍሎች፤
(ረ) ያለም እንደ ሆነ፤ መያዣ የሆነው ቅርንጫፍና ውክልና ነው፡፡
(፫) በዚህ ቁጥር መሠረት መያዣ ስለሚደረግ ነገር ሁሉ በዚህ ሕግ አንደኛ መጽሐፍ ከቁጥር ፻፸፱ እስከ ፻፺፫ ያሉት ድንግጌዎች ተፈጻሚዎች ይሆናሉ፡፡

ቊ ሺ፰፡፡ ለመርማሪው ዳኛ የሚደረግ መግለጫ፡፡

(፩) ሥራቸውን በጀመሩ በወሩ ወስጥ ንብረት ጠባቂዎቹ የባለዕዳውን ጉዳይ ሁኔታና ለዚሁም ሁኔታ መነሻ የሆኑትን ምክንያቶች ጭምር የሚያስረዳ መግለጫ ለመርማሪው ዳኛ ይልካሉ፡፡
(፪) መርማሪውም ዳኛ ሐሳቡን ጨምሮ ይህን መግለጫ ወዲያውኑ ለሕግ አስከባሪው ያስተላልፋል፡፡ መግለጫውም በታዘዘው ጊዜ ውስጥ ያልተሰጠ እንደ ሆነ፤ የዘገየበትን ምክንያቶች አስረድቶ ለሕግ አስከባሪው ማስታወቅ አለበት፡፡

ክፍል ፪
ስለ ማሸግ

ቊ ሺ፱፡፡ እሽግን ስለ ማድረግ፡፡

(፩) የባለዕዳውን መክሠር የፈረደው ፍርድ ቤት መክሠሩን ለማስታወቅ በሚሰጠው ፍርድ እሽግ እንዲደረግ ለማዘዝ ይችላል፡፡ እሽጉም የሚደረገው በማጋዜኖቹ በመደርደሪያዎቹ፤ በሣጥኖቹ፤ በቦርሳዎቹ በመዝገቦቹ በሰነዶቹ በወረቀቶቹና የባለዕዳው በሆኑት የቤት ዕቃዎች የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ ነው፡፡
(፪) ነገር ግን ባለዕዳው የጠፋ ወይም ገንዘቡን በሙሉ ወይም በከፊል ያሸሸ እንደ ሆነ፤ ችሎታ ያላቸው ባለሥልጣኖች በፈቃዳቸው ወይም በአንድ ገንዘብ ጠያቂ አመልካችነት፤ የመክሠር ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት በንኡስ ቁ (፩) በተዘረዘሩት ዕቃዎች ላይ እሽግን ለማድረግ ይችላሉ፡፡

ቊ ሺ፲፡፡ ሊታሸግባቸው ስለማይቻሉ ዕቅዎች፡፡

(፩) በንብረት ጠባቂዎች ጠያቂነት፤ መርማሪው ዳኛ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ዕቃዎች እሽግ እንዳይደረግባቸው፤ ተደርጎባቸውም እንደ ሆነ፤ እንዲነሣላቸው፤ ለመፍቀድ ይችላል፡፡
(ሀ) በሚሰጠው ዝርዝር ላይ በሚገኙት ለባለዕዳውና ለቤተሰቡ አስፈላጊ በሆኑት ልብሶችና ዕቃዎች፤
(ለ) በሚበላሹ ወይም በሚያልቁ ዕቃዎች፤
(ሐ) ሥራው እንዲቀጥል የተፈቀደ እንደ ሆነ፤ ለንግዱ ወይም ለኢንዱስትሪው መካሄድ በሚያገለግሉት ዕቃዎች፡፡
(፪) የዕቃዎቹን ፕሮሴቬርባል የሚፈርመው ተገቢው ባሥልጣን ባለበት፤ ንብረት ጠባቂዎቹ በንኡስ ቁ (፩) የተመለከቱትን ዕቃዎች ዝርዝር ከነዋጋቸው ያሰናዳሉ፡፡

ቊ ሺ፲፩፡፡ ከእሽግ ውስጥ ስለሚወጡ ዕቃዎች፡፡

(፩) በቁ ፩ሺ፱ ንኡስ ቁ ፩ መሠረት የሒሳብ ሰነዶችና መዝገቦች ታሽገው እንደ ሆነ፤ ተገቢው ባለሥልጣን እሽጉን አንሥቶ ሰነዶቹንና መዝገቦቹን ከዘጋቸው በኋላ ለንብረት ጠባቂዎቹ ማስረከብ አለበት፡፡ ይኸውም ባለሥልጣን መዝገቦቹና ሰነዶቹ የሚገኙበትን ሁኔታ በፕሮሴቬርባል ውስጥ በአጭሩ ያመለክታል፡፡
(፪)  የመክፈያ ጊዜያቸው አጭር የሆኑትን፤ እሽታ ማግኘት ወይም የአጠባበቅ ተግባር የሚያስፈልጋቸውን፤ በቦርሰው ውስጥ የሚገኙትን የንግድ ወረቀቶች ተገቢው ባለሥልጣን ከእሽጉ ውጭ አድርጓቸው ዝርዝራቸውን ከጻፈ በኋላ ገንዘቡ ገቢ እንዲድረግ ወይም አስፈላጊው እንዲፈጸም ለንብረት ጠባቂዎቹ ይሰጣቸዋል፡፡ የወረቀቶቹንም ሁኔታ የሚያሳይ መግለጫ ለመርማሪው ዳኛ ይተላለፋል፡፡

ቊ ሺ፲፪፡፡ ለከሠረው ሰው ስለ ተላከው ደብዳቤ፡፡

ለከሠረው ሰው የሚላኩት ደብዳቤዎች ለንብረት ጠባቂዎች ይሰጣሉ፡፡ የከሠረው ሰው ደብዳቤው ሲከፈት ለማየት ይችላል፡፡

ቊ ሺ፲፫፡፡ እሽግን ስለ ማንሣት፡፡

ንብረት ጠባቂዎቹ በአምስት ቀን ውስጥ የዕቃቹን ዝርዝር ለመመዝገብ እሽጉ እንዲነሣ ይጠይቃሉ፡፡

ክፍል ፫
የዕቃ ዝርዝር መዝገብ

ቊ ሺ፲፬፡፡ የሒሳቡን ሚዛን ስለ ማሰናዳትና ስለ መስጠት፡፡

 የሒሳቡን ሚዛን ባለዕዳው ያልሰጠ እንደ ሆነ፤ በሚገኙት መዝገቦች የሒሳብ ሰነዶች፤ ወረቀቶችና መረጃዎች መሠረት ንብረት ጠባቂዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሒሳቡን ሚዛን አሰናድተው ለፍርድ ቤቱ መዝገብ ቤት ሹም ይሰጣሉ፡፡

ቊ ሺ፲፭፡፡ የባለዕዳውን ንብረቶች በዕቃ ዝርዝር መዝገብ ስለ ማስገባት፡

(፩) ባለዕዳው ባለበት ወይም ደረሰኝ ሬኮማንዴ ደብዳቤ በሚገባ ተጠርቶ ንብረቶቹ በዕቃ ዝርዝር መዝገብ ውስጥ ይገባሉ፡፡
(፪) በዚሁ ጊዜ በቁጥር ሺ፲ ንኡስ ቁ (፩) መሠረት እሽግ ሳይደረግባቸው ወይም ከእሽግ ውጭ ሆነው በዝርዝር መዝገብ ውስጥ የገቡትና የተገመቱት ዕቃዎች እንደገና ይመረመራሉ፡፡
(፫) ይኸው የዕቃ ዝርዝር መዝገብ በሁለት ዋና ይሠራል፡፡ ከነዚህም አንዱ ወደያውኑ በፍርድ መዝገብ ቤት ይቀመጣል፡፡ ሁተኛውም በንብረት ጠባቂዎች እጅ ይቀራል፡፡
(፬) ስለ ዕበው ዝርዝር መዝገብ አጻጻፍና ስለ ዕቃዎቹ ግምት፤ ንብረት ጠባቂዎቹ፤ በመርማሪው ዳኛ ፈቃድ፤ የሚገቡ መስለው የሚገምቷቸውን ሰዎች ርዳታ መጠየቅ ይችላሉ፡፡

ቊ ሺ፲፮፡፡ ከሞት በኁላ ስለሚደርስ መክሠር የዕቃ ዝርዘር መዝገብ አሠራር፡፡

መክሠሩ ከሞት በኋላ የተገለጸና የዕቃውም ዝርዝር መዝገብ ያልተሠራ እንደ ሆነ፤ ወይም የዕቃው ዝርዝር መዝገብ ከመዘጋጀቱ በፊት ባለዕዳው የሞተ እንደ ሆነ፤ ይህ የዕቃ ዝርዝር የሚዘጋጀው ወይም መዘጋጀቱን የሚቀጥለው ወራሾች ባሉበት ወይም በሚገባ ጥሪ ከተደረገላቸው በኋላ ነው፡፡

ቊ ሺ፲፯፡፡ የሕግ አስከባሪው መብቶች፡፡

ሕግ አስከባሪው የዕቃው ዝርዝር መዝገብ ሲደራጅ ለማየትና ለመገኘት ይችላል፡፡ ከዚህም በላይ በማናቸውም ጊዜ መክሠሩን የሚመለከቱ ውሎችን ሰነዶችን መዝገቦችን ወይም ወረቀቶችን ሁሉ ለማየት የመጠየቅ መብት አለው፡፡

ቊ ሺ፲፰፡፡ የባለዕዳው ንብረቶች ለንብረት ጠባቂዎቹ ስለ ማስረከብ ፡፡

 የዕቃው ዝርዝር መዝገብ ከተሰናዳ በኋላ የባለዕዳው ሸቀጦች ገንዘቦች ዋጋ ያላቸው ሰነዶች፤ መዝገቦች፤ ወረቀቶችና ሰነዶች፤ የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችና ዕቃዎች ለንብረት ጠባቂዎች ይሰጣሉ፡፡ እነርሱም መረከባቸውን በዚሁ የዕቃ ዝርዝር መዝገብ ሥር ያመለክታሉ፡፡

ምዕራፍ ፬
መክሠርን የሚያስታውቅ ፍርድ የሚያስከትላቸው ውጤቶች
ክፍል ፩
በባለዕዳው ላይ ያሉት ውጤቶች

ቊ ሺ፲፱፡፡ የከሠረውን ሰው ስለ ማሰር ፡፡

የከሠረው ሰው፤ መርማሪው ዳኛ ሳይፈቅድለት በማናቸውም ምክንያት ከመኖሪያ ቦታው ለመራቅ አይችልም፡፡ ይህን ቢተላለፍ በወንደለኛ መቅጫ በቁጥር ፬፻፴፫ መሠረት ፍርድ ቤቱ የከሠረውን ሰው ሊያስረው ይችላል፡፡

ቊ ሺ፳፡፡ ለከሠረው ሰውና ለቤተ ሰቡ ስለሚደረግ ርዳታ፡፡

ንብረት ጠባቂዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት፤ መርማሪው ዳኛ ለከሰረው ሰውና ለቤተ ሰቡ፤ ኪሣራ ላይ ከሚገኘው ንብረት ርዳታ እንዲደረግላቸው ሊያዝ ይችላል፡፡

ቊ ሺ፳፩፡፡ ንብረት  ጠባቂዎቹ የከሠረውን ሰው ስለ መቅጠራቸው፡፡

ሥራውን በቀና ለማከናወን፤ ንብረት ጠባቂዎቹ ባለዕዳውን፤ መርማሪው ዳኛ በሚወስነው አኳኋን፤ ቀጥረው ሊያሠሩት ይችላሉ፡፡

ቊ ሺ፳፪፡፡ በከሠረው ሰው ስለሚደርሱት ክልከላዎችና መብት ማጣት፡፡

በከሠረው ሰው ላይ በሕጉ ውስጥ የተመለከቱት ክልከላዎችና መብት ማጣት ሊፈጸሙበት ይችላሉ፡፡ ልዩ የሆኑ ሕጋዊ ውሳኔዎች ሳይነኩ፤ እነዚህ ክልከላዎች ወይም መብት ማጣት እንደገና መልሶ በመሰየም ካልሆነ በቀር አይቀሩም፡፡

ቊ ሺ፳፫፡፡ የከሠረው በው በንብረቱ ለማዘዝ ስላለመቻሉ፡፡

የመክሠር ማስታወቂያ ፍርድ ከተሰጠበት ቀን አንሥቶ የከሠረው ሰው የኪሣራው ሥራ ተጣርቶ ነጻ እስኪደረግ ድረስ በንብረቶቹ ላይ በማናቸውም አኳኋን የሚያገኛቸው እንኳ ቢሆኑ፤ የማስተዳደርንና የማዘዝን መብት ያጣል፡፡

ቊ ሺ፳፬፡፡ ስለ ክስ አቀራረብ፡፡

የመክሠር ማስታወቂያው ፍርድ ከተሰጠበት ቀን አንሥቶ ለመክሰስ ወይም ለመከሰስ የሚችሉት የንብረት ጠባቂዎች ብቻ ናቸው፡፡ የከሠረው ሰው በክሱ ጣልቃ እንዲገባ ፍርድ ቤቱ ሊፈቅድለት ይችላል፡፡

ቊ ሺ፳፭፡፡ ስለ ገንዘብ ጠያቂዎች ንብረት፡፡

(፩) ገንዘባቸው በልዩ ቀዳሚነት መብት ወይም በመያዣ ያልተጠበቀ ገንዘብ ጠያቂዎች ሁሉ የባለዕዳውን መክሠር የሚያረጋግጥ ፍርድ ከተሰጠበት ቀን አንሥቶ በኅብረት ሁሉም አንድነት ሆነው ከኪሣራው ላይ ገንዘብ ጠያቂዎች የሆናሉ፡፡
(፪)  ኅብረቱም በሕግ የሰው መብት የተሰጠው እንደ አንድ ሰው ተቆጥሮ ገንዘብ ጠያቂ ወይም ባለዕዳ ለመሆን ይችላል፡፡ እንደራሴውም ንብረት ጠባቂነት የተሾመው ሰው ነው፡፡

ቊ ሺ፳፮፡፡ ለየብቻ በግል የሚቀርቡትን ክሶች ስለ ማቋረጥ፡፡

ስለመክሠር የተሰጠው ፍርድ፤ ከኪሣራው ላይ በኅብረት ገንዘብ ጠያቂ የሆኑትን ሰዎች ለየብቻ ክስ ከማቅረብ ያግዳቸዋል፡፡ የመክሠር ፍርድ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ገንዘብ ጠያቂው የባለዕዳውን ተንቀሳቃሽ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመያዝ የሚያደርገው የማስፈጸም ሥራ ይታገዳል፡፡

ቊ ሺ፳፯፡፡ የመክፈያ ጊዜያቸው ያልደረሰ ዕዳዎችን እንዲከፈሉ ስለ ማስገደድ፡፡

(፩) የመክሠር ማስታወቂያው ፍርድ የመከፈያ ጊዜያቸው ያልደረሱትን ለከሠረው ሰው የሚከፈሉ ዕዳዎች ሁሉ፤ ወዲያውኑ ተከፋይ ያደርጋቸዋል፡፡
(፪) እነዚህ ዕዳዎች የመክፈሉ መቋረጥ ከተገለጸበት ቦታ ካለው ገንዘብ በሌላ ዐይነት ገንዘብ የተመለከቱ እንደ ሆነ፤ ፍርድ በተሰጠበት ቀን ሕጋዊ በሆነው ምንዛሪ በአገሩ ገንዘብ ይለወጣሉ፡፡

ቊ ሺ፳፰፡፡ ስለ ወለድ ሒሳብ መቋረጥ፡፡

የማይንቀሳቀስ ዋስትና ካላቸው ብድሮች በቀር ከከሠረው ሰው ከሚፈለጉት ብድሮች የሚታሰቡት ወለዶች ሁሉ፤ የማስታወቂያው ፍርድ ከተሰጠበት ጊዜ አንሥቶ በኅብረት ላይ ከመቆጠር ይቋረጣሉ፡፡ ዋስትና ያሏቸው የብድር ዋና ገንዘብ ወለዶች፤ ለዋስትናው ከተመደቡት ንብረቶች ከሚገኙት ገንዘቦች ላይ ካልሆነ በቀር ሊጠየቁ አይቻልም፡፡

ቊ ሺ፳፱፡፡ የማስታወቂያው ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት የተሠሩ ሥራዎች የማይጸኑ ስለመሆናቸው፡፡

መክፈሉ ከተቋረጠበት ቀን በፊት ባሉት ዐሥራ አምስት ቀኖችና የማስታቂያው ፍርድ  በተሰጠበት ቀን መካከል፤ ባለዕዳው ቀጥለው የተመለከቱትን ሥራዎች ሠርቶ እንደ ሆነ እነዚህ ሥራዎች የማይጸኑና በኅብረቱ ላይ መቃወሚያ ለመሆን የማይችሉ ይሆናሉ፡፡
(ሀ) በችሮታ የተደረጉ ስጦታዎች ሁሉ፤
(ለ) የመክፈያ ጊዜያቸው ሳይደርስ በጥሬ ገንዘብ በማስተላለፍ በመሸጥ በማቻቻል፤ ወይም በማናቸውም አኳኋን የተደረገ የዕዳ አከፋፈል ሁሉ፤
(ሐ) የመክፈያ ጊዜያቸው ከደረሰ በኋላ በጥሬ ገንዘብ ሳይሆን በንግድ ሰነዶች ወይም በባንክ በኩል በማስተላለፍ የተደረገ የዕዳ አከፋፈል ሁሉ፤
(መ) ዋስትናው ከመሰጠቱ በፊት ለነበሩት ዕዳዎች፤ በባለዕዳው ንብረቶች ለይ የተሰጡ ዋስትናዎች ሁሉ፡፡

ቊ ሺ፴፡፡ የማስታወቂያው ፍርድ ከመስጠቱ በፊት ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ በፈቃድ የሚሰረዙ ስለሚሆኑት ፡፡

አከፋፈሉ ከተቋረጠበት ጊዜ በኋላ የመክፈያ ጊዜያቸው ለደረሰ ዕዳዎች ባለዕዳው ያደረጋቸው ሌሎች አከፋፈሎችና በዋጋ ያደረጋቸው ውሎች በንብረት ጠባቂዎቹ ጥያቄ ሊሰረዙ የሚችሉት፤ ተከፋዮቹ ወይም ተዋዋዮቹ የአከፋፈሉን መቋረጥ ሁኔታ እያወቁ የሆነ እንደሆነ ነው፡፡

ቊ ሺ፴፩፡፡ የማስታቂያው ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት የተደረገው የመብት ማስመዝገብ በኅብረቱ ላይ መቃወሚያ ስላለመሆኑ፡፡

(፩) ከንብረት ዋስትናዎች የሚገኙ በደንብ የተቋቋሙ መብቶች የመክሠር ማስታወቂያው ፍርድ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ፤ ለመመዝገብ ይችላሉ፡፡
(፪)  መክፈሉ ከተቋረጠ በኋላ፤ ወይም መክፈሉ ከመቋረጡ በፊት በአንድ ወር ውስጥ የተደረገው የመብት ማስመዝገብ ሁሉ በኅብረቱ ላይ መቃወሚያ ሊሆን የማይችለው በማስመዝገቢያው ጊዜና ዋስትናው የተቋቋመበት ውል በተደረገበት ጊዜ መካከል ከአንድ ወር በላይ ያለፈ እንደ ሆነ ነው፡፡

ቊ ሺ፴፪፡፡ የመያዣ መብቱ በኅብረቱ ላይ መቃወሚያ ሊሆን አይችልም ከተባለው ሰው ቀጥሎ የመያዣ መብቱን ስለ አስመዘገበው ሰው ሁኔታ፡፡

የመያዣ መብቱ በኅብረቱ ላይ መቃወሚያ ሊሆን አይችልም ከተባለው ገንዘብ ጠያቂ ቀጥሎ የመያዣ መብቱን ያስመዘገበ ሰው፤ መያዣ የሆነው የማይንቀሳቀስ ንብረት ወይም የንግድ መደብር ዋጋ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ በሚከፋፈልበት ጊዜ መብቱ ሳይታወቅለት በቀረው ሰው ቦታና ስፍራ ተተክቶ ሊከፈለው ይችላል፡፡ ነገር ግን በአዲሱ ተራ መሠረት ከሚያገኘውና ከእርሱ በፊት ለነበረው ሰው መብቱ ጸንቶለት ቢሆን ኖሮ በድሮው ተራ መሠረት ያገኘው ከነበረው ገንዘብ መካከል ያለውን የገንዘብ ልዩነት ለኅብረቱ መመለስ አለበት፡፡

ቊ ሺ፴፫፡፡ አከፋፈሉ ከተቋረጠ በኋላ ስለ ተከፈሉ የንግድ ወረቀቶች፡፡

(፩) አከፋፈሉ በተቋረጠበትና የማስታወቂያ ፍርድ በተሰጠበት ጊዜ መካከል የሐዋላ ወረቀቶች ወይም ቼኮች ተከፍለው እንደ ሆነ፤ የተከፈለው ገንዘብ እንዲመለስ የሚቀርበው ክስ የንግዱን ወረቀት ገንዘብ በመጀመሪያ በፈረመው ሰው ላይ ነው፡፡
(፪) የተስፋ ሰነድ የሆነ እንደ ሆነ፤ ክሱ የሚቀርበው በሰነዱ ጀርባ በመጀመሪያ በፈረመው ሰው ላይ ነው፡፡
(፫) ክሱ የቀረበበት ሰው ሰነዱ በተከፈለበት ጊዜ የአከፋፈሉን መቋረጥ ያወቀ መሆኑን፤ በንኡስ ቁ (፩) እና (፪) መሠረት ክስ አቅራቢው ማስረዳት አለበት፡፡

ቊ ሺ፴፬፡፡ ስለ ይርጋ ዘመን፡፡

 በቁጥር ሺ፳፱ ሺ፴ ሺ፴፩ መሠረት የሚቀርቡ ክሶች ኪሣራ ማስታወቂያ ፍርድ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ በሁለት ዓመት ይርጋ ዘመን ይታገዳሉ፡፡

ክፍል ፪
የባለዕዳውን ንብረቶች ስለ ማስተዳደር

ቊ ሺ፴፭፡፡ ስለ ንብረት ጠባቂዎች ጠቅላላ ተግባር፡፡

(፩) ንብረት ጠባቂዎች፤ በመርማሪው ዳኛ ፈቃድ፤ በቅርብ ጊዜ የሚበላሹትን ወይም ወደፊት ዋጋቸው የሚረክሰውን ወይም ለማስቀመጥ ብዙ ወጪ የሚያስፈልጋቸውን ዕቃዎች ይሸጣሉ፡፡
(፪) የብድር ገንዘባችን ገቢ ያስደርጋሉ፤ መርማሪውም ዳኛ የፈቀደ እንደ ሆነ፤ ሥራ ያካሂዳሉ፡፡

ቊ ሺ፴፮፡፡ የንግድ ዕቃዎችን ስለ መሸጥ፡፡

(፩) መርማሪው ዳኛ የከሠረውን ሰው ሐሳብ ሰምቶ ወይም በረኮንዴ ደብዳቤ የከሠረውን ሰው በሚገባ ጠርቶ ሌሎች የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች ወይም የንግድ ዕቃዎች እንዲሸጡ ለንብረት ጠባቂዎቹ ሊፈቅድላቸው ይችላል፡፡
(፪) ዳኛው የሸያጩን ሁኔታዎች ይወስናል፡፡

ቊ ሺ፴፯፡፡ የንግድ መደበርን ስለ መሸጥ፡፡

የንግድ መደብር (መድበል) ሊሸጥ የሚቻለው በፍርድ ቤት ፈቃድና ፍርድ ቤቱ በወሰነው የአሻሻጥ ሁናቴ ነው፡፡

ቊ ሺ፴፰፡፡ ስለ ስምምነትና ግልግል፡፡

(፩) መርማሪው ዳኛ የገንዘብ ጠያቂዎቹን ኮሚቴ ሐሳብ ከተቀበለ በኋላ የከሠረውን ሰው ሐሳብ ሰምቶ ወይም በሬኮማንዴ ደብዳቤ በሚገባ ጠርቶት ንብረቱን በሚመለከት ጉዳይ ሁሉ ስምምነትና ግልግል እንዲያደርጉ ለንብረት ጠባቂዎቹ ሊፈቅድላቸው ይችላል፡፡
(፪) ስምምነት ወይም ግልግል እንዲያደርግበት የቀረበው ጉዳይ ዋጋው ያልተወሰነ እንደ ሆነ፤ ወይም ከንብረት ጠባቂዎቹ ሥልጣን በላይ የሆነ እንደ ሆነ ስምምነቱ ወይም ግልግሉ በፍርድ ቤት እንዲጸድቅ ይቀርባል፡፡
(፫) የማጽደቁ ተግባር በሚፈጸምበት ጊዜ የከሠረው ሰው ይጠራል፡፡ በማናቸውም ሁኔታ ስምምነቱንና ግልግሉን ለመቃወም ባለዕዳው ችሎታ አለው፡፡

ቊ ሺ፴፱፡፡ የንግድ ሥራን ስለ መቀጠል፡፡

(፩) ሕዝባዊ ጥቅም ወይም የገንዘብ ጠያቂዎቹ ጥቅም በፍጹም የሚያስገደድ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ በገንዘብ ጠያቂዎቹ ኰሚቴ ሐሳብም በመርማሪው ዳኛ መግለጫ መሠረት ፍርድ ቤቱ የፈቀደላቸው እንደ ሆነ፤ ንብረት ጠባቂዎቹ የንግዱን ወይም የኢንዱስትሪውን ሥራ ለመቀጠል ይችላሉ፡፡
(፪) የንግዱ ሥራ የቀጠለ እንደ ሆነ፤ በዚህ የንግዱ ሥራ መቀጠል ምክንያት ገንዘብ ጠያቂ የሆኑት ሰዎች ከኅብረቱ ለይ ገንዘብ ጠያቂዎች ይሆናሉ፡፡ የመክሠሩም ደንብ በነሱ ላይ አይፈጸምባቸውም፡፡ ገንዘባቸውም ከከሠረው ነጋዴ ሀብት ላይ በኅብረቱ ውስጥ ከሚገኙት ሌሎች ገንዘብ ጠያቂዎች አስቀድሞ ይከፈላቸዋል፡፡
(፫) የሚቀጥለውን የንግድ ሥራ ራሱ እንዳይሠራ ለማድረግ፤ ንብረት ጠባቂው የንግዱን ሥራ የሚሠራ ተቀባይ ለማድረግ እንዲችል መርማሪው ደኛ ሥልጣን ሊሰጠው ይችላል፡፡

ቊ ሺ፵፡፡ የኪራይን ውል ስለ መቀጠል፡፡

(፩) ለባለዕዳው ንግድ ወይም እንዲስትሪ የተመደቡትን የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ውስጥ ለራሱና ለቤተሰቡ መኖሪያ ሆነው የሚያገለግሉትን ቤቶች የሚመለከት የኪራይ ውል የነጋዴው መክሠር ብቻ እንዲፈርስ አያደርገውም፡፡
(፪) ንብረት ጠባቂዎቹ የኪራዩ ውል እንዲሰረዝ ወይም እንዲቀጥል ለመምረጥ ይችላሉ፡፡ ውሉ እንዲቀጥል ያደረጉ እንደ ሆነ የተከራዩን ግዴታዎች ሁሉ መፈጸም አለባቸው፡፡ በሁለቱም አኳኋን ቢሆን፤ በቁጥር ሺ፵ እንደ ተመለከተው የዕዳዎቹ ሁኔታ ዝርዝር በፍርድ መዝገብ ቤት ከተቀመጠበት ቀን አንሥቶ በዐሥራ አምስት ቀን ውስጥ ንብረት ጠባቂዎቹ አሳባቸውን ለአከራዩ ማስታወቅ አለባቸው፡፡
(፫) ይኸውም ማስታወቅ ሊደረግ የሚቻለው በመርማሪው ደኛ ፈቃድና በገንዘብ ጠያቂዎቹ ኮሚቴ አሳብ ብቻ ነው፡፡
(፬) ከዚህ በላይ በንኡስ ቁ (፪) የተመለከተው የዐሥራ አምስት ቀን ጊዜ አስኪያልፍ ድረስ፤ ለአከራዩ የአጠባበቅ ሥራዎችንና ቦታዎችን መልሶ እጁ ለማድረግ ያለው መብት እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ለንግዱ ወይም ለኢንዱስትሪው ሥራ በሚያገለግሉ የሚንቀሳቀሱ ዕቃዎች ላይ ፍርድ ለማስፈጸምና የኪራዩንም ውል ለማሰረዝ የሚቀርቡ ክሶች ሁሉ ታግደው ይቆያሉ፡፡ አከራዩ ቦታዎቹን መልሶ እጁ ያደርገ እንደ ሆነ የማስፈጸም ሥራ መታገድ ሁሉ በደንብ ቀሪ ይሆናል፡፡
(፭) ንብረት ጠባቂው የኪራዩን ውል ለመቀጠል አሳቡን ለአከራዩ አስታወቆት እንደ ሆነ፤ ማስታወቂያ በተደረገለት በዐሥራ አምስት ቀን ውስጥ አከራዩ የኪራዩ ውል እንዲሰረዝ ጥያቄውን ካላቀረበ ውሉ ይቀጥላል፡፡
(፮) መክሠር በደረሰ ጊዜ የኪራዩ ውል በደንብ ይሰረዛል የሚል የውል ቃል እንዳልተጻፈ ይቆጠራል፡፡
(፯) በቁጥር ሺ፷፩ እና ሺ፷፪ የተደነገጉት ውሳኔዎች እንደ ተጠበቁ ሆነው የዚህ ቁጥር ድንጋጌዎች ተፈጻሚዎች ይሆናሉ፡፡

ምዕራፍ ፭
የገንዘብ መጠየቂያ መብቶችን ስለ መመርመር
ክፍል ፩
ስለ ምርመራው አሠራር

ቊ ሺ፵፩፡፡ ገንዘብ ጠያቂዎቹ ማስረጆቻቸውን ስለ ማቅረብ ፡፡

(፩) የመክሠር ማስታወቂያ ፍርድ ከተሰጠበት ጊዜ አንሥቶ ገንዘብ ጠያቂዎች የሚጠይቁትን ገንዘብ ልክ ከማመልከት ጋራ የመብቶቻቸውን ማረጋገጫ ሰነዶች ለንብረት ጠባቂዎች ያቀርባሉ፡፡
(፪) ገንዘብ ጠያቂዎች ለተላኩላቸው ሰነዶች የደረሰኝ ወረቀት ይሰጣሉ፡፡ እነዚህንም ሰነዶች የኪሣራው ሒሳብ በመጨረሻ ከተዘጋ በኋላ ይመልሳሉ፤ ከዚህም ጊዜ አንስቶ እስከ አንድ ዓመት አላፊዎች ናቸው፡፡

ቊ ሺ፵፪፡፡ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ ስለሚላኩ ማስታወቂያዎች፡፡

(፩) በሒሳብ ሚዛን ውስጥ የተጻፉ ገንዘብ ጠያቂዎች የመክሠር ማስታወቂያው ፍርድ ከተሰጠበት ጊዜ አንሥቶ በዐሥራ አምስት ቀን ውስጥ ሰነዶቻቸውን ያላቀረቡ እንደ ሆነ፤ ይህ ጊዜ ሲያልቅ ገንዘብ ጠያቂዎቹ ሰነዶቻቸው እንደያቀርቡ ንብረት ጠባቂዎቹ ያስጠነቅቋቸዋል፡፡
(፪) ይህ ማስጠንቀቂያ የሚፈጸመው ሕጋዊ ማስታወቂያን ለመቀበል ከተፈቀደላቸው ጋዜጣዎች ውስጥ በአንዱ በመጻፍና በንግድ ኦፊሲዬል ጋዜጣ በአጭሩ በመጻፍ ነው፡፡ በንግድ ኦፊሲዬል ጋዜጣ የሚወጣው አጭር ጽሑፍ፤ በመጀመሪያ ጊዜ ማስጠንቀቂያው የተጻፈበትን ሕጋዊ ማስታወቂያ ለመቀበል የተፈቀደለትን ጋዜጣ ቁጥር ያመለክታል፡፡ ከዚህም በቀር ንብረት ጠባቂዎቹ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ ደብዳቤ ይልኩላቸዋል፡፡
(፫)  ማስጠንቀቂያው በንግድ ኦፊሲዬል ጋዜጣ በተጻፈ በ፲፭ ቀን ውስጥ ሰነዶቹ መቅረብ አለባቸው፡፡

ቊ ሺ፵፫፡፡ ዕዳዎችን ስለ መመርመር፡፡

(፩) ንብረት ጠባቂዎቹ ዕዳዎችን የሚመረምሩት፣ በከሠረው ሰው ፊት ወይም ደረሰኝ ባለው ሬኰማንዴ ደብዳቤ ከተጠራ በኋላ፤ ተቋቁሞም እንደ ሆነ፤ በገንዘብ ጠያቂዎች ክሚቴ ወይም በእንደራሴው ረዳትነት ነው፡፡
(፪) በተዘጋጀውም የዕዳዎች ዝርዝር፤ መርማሪው ዳኛ ይፈርምበታል፡፡
(፫) ንብረት ጠባቂዎቹ ስለ አንድ ዕዳ በሙሉ ወይም በከፊል ክርክር አንሥተው እንደ ሆነ፤ ንብረት ጠባቂዎቹ በረኮማንዴ ደብዳቤ ይህንኑ ለገንዘብ ጠያቂው ማስታወቅ አለባቸው፡፡ ገንዘብ ጠያቂውም በጽሑፍ ወይም በቃል መልሱን በስምንት ቀን ውስጥ ማቅረብ አለበት፡፡

ቊ ሺ፵፬፡፡ የዕዳዎችን ዝርዝር በፍርድ መዝገብ ቤት ስለ ማስቀመጥ፡፡

(፩) ምርመራው ወዲያው እንዳለቀ ንብረት ጠባቂዎቹ የዕዳዎችን ዝርዝር የተቀበሏቸውንና የተቃወሟቸውን አስረጆች አስመልክተው በፍርድ ቤቱ መዝገብ ቤት ያስቀምጣሉ፡፡
(፪) እንዲሁም ንብረት ጠባቂዎቹ በሚንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ ልዩ መብት አለን የሚሉትን የገንዘብ ጠያቂዎች ዝርዝር ለመርማሪው ዳኛ ያቀርባሉ፡፡

ቊ ሺ፵፭፡፡ የማስቀመጥ ማስታወቂያ፡፡

(፩) የፍርድ መዝገብ ቤት ሹም የዕዳዎችን ዝርዝር መቀመጥ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ ጊዜ ሳይወስድ በቁጥር ሺ፵፪ ንኡስ ቁ (፪) በተመለከተው ዐይነት ያስታውቃል፡፡
(፪) ክርክር የተደረገበትን ዕዳ፤ ለሚመለከተው ገንዘብ ጠያቂ በረኮማንዴ ደብዳቤ ያስታውቀዋል፡፡

ቊ ሺ፵፮፡፡ ስለ አቤቱታዎች፡፡

(፩) በሒሳብ ሚዛን ውስጥ የተጻፈ ወይም ሰነዱ የተመረመረ ገንዘብ ጠያቂ ሁሉ፤ በንግድ ኦፊሲዬል ጋዜጣ በአጭሩ ጽሑፍ ማስታወቂያው ከተደረገበት ቀን በሚከተሉት ስምንት ቀን ውስጥ ራሱ ወይም በወኪሉ ስለ ዝርዝሩ ጽሑፍ አቤቱታዎቹን ለፍርድ መዝገብ ቤት ለማስታወቅ መብት አለው፡፡
(፪) የከሠረው ሰው እንደዚሁ ያለ መብት አለው፡፡

ቊ ሺ፵፯፡፡ ዕዳን ማስጻፍ ስለሚቆምበት የመጨረሻ ቀን፡፡

(፩) ከዚህ በላይ ያለው ጊዜ ሲፈጸም ለፍርድ ቤቱ የሚቀርቡት አቤቱታዎች እንደ ተጠበቁ ሆነው፤ መርማሪው ዳኛ ዕዳዎችን ማስጻፍን ያቆማል፡፡
(፪) ይህን ውሳኔ በመፈጸም ንብረት ጠባቂዎቹ ክርክር ባልተደረገባቸው ዕዳዎች ዝርዘር ላይ ገንዘብ ጠያቂውን መቀበላቸውንና ያመኑለትንም የንዘብ ልክ ያመለክታሉ፡፡

ቊ ሺ፵፰፡፡ ክርክር ከተነሣባቸው ዕዳዎች ላይ ስለሚሰጥ ፍርድ፡፡

ክርክር የተነሣባቸው ዕዳዎች፤ በፍርድ መዝገብ ቤት ሹም አማካይነት በረኮማንዴ ደብዳቤ ከአምስት ቀን አስቀድሞ ለሁለቱ ወገኖች ማስተወቂያ ከተሰጠ በኋላ መርማሪው ዳኛ ባቀረበው መግለጫ ፍርድ ለመስጠት ለመጀመሪያው ችሎት ይላካሉ፡፡

ቊ ሺ፵፱፡፡ ገንዘብ ጠያቂን ለጊዜው ስለ መቀበል፡፡

(፩) ፍርድ ቤቱ በሚወስነው ገንዘብ ልክ፤ ገንዘብ ጠያቂው በመክሠሩ ሥርዐት ውስጥ ለጊዜው እንዲገባ ፍርድ ቤቱ ለመፍቀድ ይችላል፡፡
(፪) የፍርድ መዝገብ ቤት ሹም በረኮማንዴ ደብዳቤ በሦስት ቀን ውስጥ ስለነርሱ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ ለባለጉዳዮቹ ያስታወቃል፡፡

ቊ ሺ፶፡፡ የመክሠርን ሥርዐት ስለ ማቋረጥ ወይም መቃወሚያን ስለ ማለፍ፡፡

(፩) አንድ ዕዳ ጊዜ የሚፈጅ ክርክር ያነሣ እንደ ሆነ፤ ፍርድ ቤቱ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት መቃሚያው እስኪወሰን ድረስ፤ የመክሠሩ ሥርዐት እንዲቋረጥ ወይም መቃወሚያው እንዲታለፍ ይወስናል፡፡ እንዲታለፍ የወሰነ እንደ ሆነ በዚያው ጊዜ በቁጥ ሺ፵፱ መሠረት ለጊዜው መብቱን እንዲቀበሉት ለመፍቀድ ይችላሉ፡፡
(፪) ዕዳው የወንጀል ክስ የሚያስከትል የሆነ እንደ ሆነ፤ የመክሠሩን ጉዳይ የሚለከተው ፍርድ ቤት የመክሠር ሥርዐት እንዲቋረጥ ለማዘዝ ይችላል፡፡ ነገር ግን መቃወሚያው እንዲታለፍ የወሰነ እንደ ሆነ በወንጀሉ ክስ ፍርድ እስኪሰጥበት ድረስ ለጊዜው መብቱን እንዲቀበሉት ፍርድ ቤቱ ሊፈቅድ አይችልም፡፡ ገንዘብ ጠያቂውም በሚሠሩት ሥራዎች ተሳታፊ ለመሆን አይችልም፡፡

 ቊ ሺ፶፩፡፡ በዋስትናቸው ላይ ክርክር ስለተነሣሳባቸው ገንዘብ ጠያቂዎች፡፡

የንብረት ዋስትና ያለው ገንዘብ ጠያቂ በዋስትናው ብቻ ክርክር ያለበት አንደ ሆነ፤ እንደ ተራ ገንዘብ ጠያቂ በመክሠሩ ሥርዐት ውስጥ እንዲገባ ይፈቀድለታል፡፡

ቊ ሺ፶፪፡፡ በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ማስረጃቸውን ስላላቀረቡ ገንዘብ ጠያቂዎች፡፡

(፩) ማስረጃቸውን በተወሰኑት ጊዜዎች ውስጥ ያላቀረቡት ገንዘብ ጠያቂዎች በሚደረገው ክፍያ ውስጥ አይገቡም፡፡ የሆነ ሆኖ የመጨረሻው ክፍያ እሰኪደረግ ድረስ ለመቃወም የሚደረገውን ወጪ ችለው፤ መቃወሚያ ለማቅረብ ይችላሉ፡፡
(፪) የነርሱ መቃወም መርማሪው ዳኛ ያዘዛቸውን የክፍያዎች አፈጻጸም ሊያግደው አይችልም፡፡
(፫) ነገር ግን አዲስ ክፍያ የተደረገ እንደ ሆነ፤ ለጊዜው ፍርድ ቤቱ በሚወስነው ገንዘብ ልክ ተካፋይ ሆነው፤ በመቃወሚያውም ፍርድ እሰኪሰጥ ድረስ ድርሻቸው ተጠብቆ ይቀመጣል፡፡

ቊ ሺ፶፫፡፡ መብታቸው በኋላ ስለታወቀላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች፡፡

መብታቸው በኋላ የታወቀላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች መርማሪው ዳኛ ባዘዛቸው ክፍያዎች ላይ ምንም ለመጠየቅ አይችሉም፡፡ የሆነ ሆኖ ካልተከፋፈለው ንብረት መጀመሪያ በሚያደርጉት ክፍያዎች ውስጥ በመጀመሪያው ክፍያ ሊደርሳቸው ይገባ የነበረውን ድርሻ ለመውሰድ መብት አላቸው፡፡

ቊ ሺ፶፬፡፡ ለምርመራው ሥራ ስለ የተወሰነ ጊዜ፡፡

 የዕዳዎች ምርመራ ሥራ፤ የኪሣራ ማስታወቂያው ፍርድ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ ቢዘገይ በአምስት ወር ጊዜ ውስጥ መፈጸም አለበት፡፡ ልዩ የሆኑ ሁኔታዎች ባጋጠሙ ጊዜ፤ መርማሪው ዳኛ ከዚህ በላይ የተወነውን ጊዜ ለመለወጥ ይችላል፡፡

ክፍል ፪
ስለ ጋራ ተገዳጆችና ስለ ዋሶች

ቊ ሺ፶፭፡፡ ሳይከፋፈል ያንድነት አላፊነት የተጻፈባቸውን ሰነዶች ይዘው ስለሚቀርቡ ገንዘብ ጠያቂዎች፡፡

የከሠረው ሰውና መክፈላቸውን ያቋረጡ ሌሎች ሰዎች፤ ሳይከፋፈል ባንድነት ተገዳጆች በመሆን በጀርባው የፈረሙበትን ወይም አላፊ የሆኑባቸውን ሰነዶች የያዘ ገንዘብ ጠያቂ በሰነዱ ላይ በተጻፈው ዋጋ  ልክ በኅብረቶቹ ሁሉ ውስጥ ለመግባትና በሚደረጉትም ክፍያዎች ሁሉ በሙሉ ገንዘቡን እሰኪያገኝ ድረስ ተካፋይ ለመሆን ይችላል፡፡

ቊ ሺ፶፮፡፡ ስለ ተከፈሉት ድርሻዎች በከሠሩ ሰዎች መካከል አቤቱታ ስለማቅረብ ፡፡

 በጋራ ተገዳጅ ሆነው ከከሠሩት ሰዎች አንዱ ባንዱ ላይ በቁጥር ሺ፶፭ መሠረት በተከፈሉት ድርሻዎች ምክንያት አቤቱታ ለማቅረብ የሚችለው፤ ከከሠሩት ሰዎች ንብረት የተከፈሉት ድርሻዎች ድምር፤ ከሚከፈለው ዋና ገንዘብና ከተጨማሪዎቹ በላይ የሆነ አንደ ሆነ ብቻ ነው፡፡ እንደዚህም በሆነ ጊዜ አልፎ የተከፈለው ገንዘብ የሚሰጠው፤ ሌሎቹ ተገዳጆች ዋስ ለሆኑላቸው የጋራ ተገዳጆችና ግዴታ በገቡበት ተራ ነው፡፡

ቊ ሺ፶፯፡፡ መክፈሉ ከመቋረጡ በፊት ከዕዳው ላይ ከፊሉን ስለተቀበለ ገንዘብ ጠያቂ፡፡

(፩) በከሠረው ሰውና በሌሎች የጋራ ተገዳጆች መካከል ሳይከፋፈል የአንድነት ኅላፊነት ያለባቸውን ሰነዶች የያዘ ገንዘብ ጠያቂ ከሚጠይቀው ገንዘብ ከፊሉን፤ መክፈሉ ከመቋረጡ በፊት የተቀበለ እንደ ሆነ፤ በኅብረቱ ውስጥ ገብቶ የሚታሰብለት ገንዘብ ከሚገባው ገንዘብ ላይ በከፊል የተሰጠው ገንዘብ ተቀንሶ ነው፡፡ ለሚቀረውም ገንዘብ በጋራ ተገዳጆቹ ወይም በዋሶቹ ላይ ያለውን መብቶች አንደ ያዘ ይቆያል፡፡
(፪) በከፊል የከፈለ የጋራ ተገዳጅ ወይም ዋስ፤ ስለባለዕዳው በከፈለው ገንዘብ መጠን በዚሁ ኅብረት ውስጥ ይገባል፡፡

ከፍል ፫
ከንግድ መደብር ውስጥ ባልሆነ ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የመያዣ
ዋስትናዎች ያሏቸው  ገንዘብ ጠያቂዎች መብት

ቊ ሺ፶፰፡፡ የንብረት መያዣ ስላላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች፡፡

በደንብ የተቋቋመ የመያዣ መብት ያላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች ለማስታወሻ ያህል ብቻ በኅብረቱ ውስጥ ይጻፋሉ፡፡ ንብረት ጠባቂዎቹ በማናቸውም ጊዜ፤ በርማሪው ዳኛ ፈቃድ፤ ስለ ኅብረቱ ጥቅም በማለት ዕዳውን በመክፈል በመያዣ የተሰጠውን ነገር ለመውሰድ ይችላሉ፡፡

ቊ ሺ፶፱፡፡ ገንዘብ ጠያቂው መያዣውን ስለ መሸጡ፡፡

 በመያዣ የተሰጠውን ነገር ንብረት ጠባቂዎቹ ያልወሰዱት እንደ ሆነና፤ ገንዘብ ጠያቂውም ከሚገባው ገንዘብ በሚበልጥ ዋጋ የሸጠው እንደ ሆነ ትርፉን ንብረት ጠባቂዎቹ ይወስደሉ፡፡ የሸጠበት ዋጋ ከሚገባው ገንዘብ ያነሰ የሆነ እንደ ሆነ ግን ቀሪ ለሆነው ገንዘብ ክፍያ፤ መያዣ ያለው ገንዘብ ጠያቂ እንደ ተራ ገንዘብ ጠያቂ ሆኖ በኅብረቱ ውስጥ ይገባል፡፡

ቊ ሺ፷፡፡ ስለ አከራዩ ልዩ መብት ወሰን፡፡

(፩) በቁጥር ፩ሺ፵ መሠረት የኪራዩ ውል የፈረሰ እንደ ሆነ፤ የአከፋፈሉን መቋረጥ የሚያመለክተው ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት ላለፈው የሁለት ዓመት ኪራይ እና ለያዘው ዓመት፤ የኪራዩም አፈጻጸም ለሚመለከተው ሁሉና አጋጣሚ ለሚሆኑት የጉዳት ካሣዎች፤ ለአከራይ ልዩ መብት አለው፡፡
(፪) የኪራዩ ውል ያልፈረሰ እንደ ሆነ፤ ለአከራዩ ያለፈው ኪራይ ሁሉ አንድ ጊዜ ከተከፈለውና፤ ውሉ በተደረገበት ጊዜ የተሰጡት ዋስትናዎች የጸኑለት እንደ ሆነ፤ ወይም አከፋፈሉ ከተቋረጠ በኋላ የተሰጡት ዋስትናዎች በቂ መሆናቸው የተገመተ እንደ ሆነ በጊዜው ያለው ወይም ጊዜው ያልደረሰው ኪራይ እንዲከፈለው ሊያስገድድ አይችልም፡፡

ቊ ሺ፷፩፡፡ በተከራየው ቦታ ላይ ያሉትን የቤት ዕቃዎችን  መውሰድ፡፡

ከተከራየው ቦታ ላይ ያሉት የቤት ዕቃዎች የተወሰዱና የተሸጡ እንደ ሆነ፤ ሺ፷ ንኡስ ቁ (፩) ውል በሚፈርስበት ጊዜ እንደ ተመለከተውና ከዚህም በቀር የተያዘው ዓመት ከሚያልቅበት ጊዜ አንሥቶ ወደፊት ባለው አንድ ዓመት ኪራይ ላይ አከራዩ በልዩ መብቱ ሊሠራበት ይችላል፡፡

ቊ ሺ፷፪፡፡ ንብረት ጠባቂዎቹ ስለሚያደርጉት የውል መቀጠል ወይም ማስተላለፍ፡፡

ንብረት ጠባቂዎቹ ለውሉ ማለቂያ ለቀረው ጊዜ የኪራዩን ውል ለመቀጠል ወይም ለሌላ ሰው ለማስተላለፍ የሚችሉት፤ ንብረት ጠባቂዎቹ ወይም እነርሱ ያስተላለፉላቸው ሰዎች በተከራየው ቤት ውስጥ በቂ ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች የሚያስቀመጡ፤ ከሕጉ ወይም ከውሉ የሚገኙትን ግዴታዎች ጊዜያቸው ሲደርስ የሚፈጽሙ እና ቤቶቹም የሚያገለግሉበትን ሁኔታ ሳይለውጡ የሆነ እንደ ሆነ ነው፡፡

ቊ ሺ፷፫፡፡ ተንቀሳቃሽ ዕቃዎችን ስለሚሸጠው ሰው ሁኔታ፡፡

(፩) በቁጥር ሺ፸፭ እስከ ሺ፸፰ የተመለከተው ድንጋጌ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ተንቀሳቃሽ ዕቃዎችን ለሰጠው ሰው በፍትሐ ብሔር ሕግ የተሰጡት ዋስትናዎች በኪሣራው ላይ መቃወሚያ ሆነው ሊቀርቡ አይችሉም፡፡
(፪) በንኡስ ቁጥር (፩) የተደነገገውን የሚቃወም ስምምነት ሁሉ ፈራሽ ይሆናል፡፡

ቊ ሺ፷፬፡፡ በሚንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ የቀደምትነት መብት ያላቸውን ገንዘብ ጠያቂዎች ስለ መክፈል፡፡

(፩) በቁጥር ሺ፵፬ ንኡስ ቁ (፪) የተመለከተው ዝርዝር በቀረበ ጊዜ፤ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ለተመለከቱት ገንዘብ ጠያቂዎች ከጀመሪያው ገቢ ገንዘብ እንዲከፈላቸው መርማሪው ዳኛ ይፈቅደል፡፡
(፪) ስለ ቀደምትነቱ ክርክር የተነሣ እንደ ሆነ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

ክፍል ፬
በማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ የመያዣና ልዩ መብት ያላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች

ቊ ሺ፷፭፡፡ ከሚንቀሳቀሱ ዕቃዎች ሽያጭ ዋጋ በፊት ስለ ተከፋፈለ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሽያጭ ዋጋ፡፡
የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሽያጭ ዋጋ ከሚንቀሳቀሱ ዕቃዎች የሽያጭ ዋጋ በፊት፤ ወይም በአንድነት ክፍያው የተደረገ እንደ ሆነ፤ ከማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሸያጭ ዋጋ በሙሉ ዋጋቸውን ያልተቀበሉ፤ የመያዣ ወይም ልዩ መብት ያላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች፤ በቁጥር ሺ፵፩ እና በተከታዮቹ ውሳኔዎች መሠረት መብታቸው ተቀባይነት አግኝቶ እንደ ሆነ፤ ባልተከፈላቸው ገንዘብ መጠን ለኅብረቱ ከሚከፈለው ገንዘብ ውስጥ ከተራ ገንዘበ ጠያቂዎች ጋራ ተካፋይ ይሆናሉ፡፡

ቊ ሺ፷፮፡፡ ከማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ሽያጭ ዋጋ በፊት ስለ ተከፈለ የሚንቀሳቀሱ ዕቃዎች የሽያጭ ዋጋ፡፡

የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሽያጭ ዋጋ ከመከፋፈሉ በፊት፤ የሚንቀሳቀሱ ዕቃዎች የሽያጭ ዋጋ አንዴ ወይም ብዙ ጊዜ ክፍያዎች ተደርጎ እንደ ሆነ፤ በቁጥር ሺ፷፯ የተመለከቱት ልዩነቶች ካላጋጠሙ በቀር፤ በደንብ ተቀባይነት ያገኙ የመያዣና ልዩ መብት ያላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች በጠቅላላ መብታቸው መጠን በክፍያው ውስጥ ገብተው ይካፈላሉ፡፡

ቊ ሺ፷፯፡፡ ዋስትና ከሌለው ኅብረት ውስጥ የተቀበሉትን ገንዘብ ስለ መቀነስ፡፡

(፩) የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ከተሸጡና፤ መያዣና ልዩ መብት ባላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች መካከል ያለው ተራ ከተወሰነ በኋላ፤ ከነዚሁ መካከል ከማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ዋጋ ለጠቅላላው መብታቸው ተካፋይ ለመሆን የሚችሉት ከመያዣው የተነሣ ለማግኘት ከሚችሉት ገንዘብ ዋስትና ከሌለው ኅብረት ውስጥ ያገኙት ገንዘብ ተቀናሽ ሆኖ ነው፡፡
(፪) ተቀናሽ የሆነውም ገንዘብ መያዣ ባለው ንብረት ውስጥ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ዋስትና ለሌለው ኅብረት ተመላሽ ሆኖ ይቆያል፡፡

ቊ ሺ፷፰፡፡ የመያዣ መብት ያላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች በከፊል ለመቀበል ተራ ስለ መጻፍ፡፡

ከማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሽያጭ ዋጋ በከፊል ለመከፈል ተራ የተጻፉ የመያዣ መብት ያላቸው ገንዘብ ጠያቂዎችን የሚመለከት ጉዳይ ከዚህ እንደሚቀጥለው ይሠራል፡-
(ሀ) ከማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ዋጋ ለመቀበል ተራ ከተጻፉ በኋላ በሚቀራቸው ገንዘብ መጠን ዋስትና በሌለው ንብረት ውስጥ ተካፋይ ይሆናሉ፡፡
(ለ) ባለፈው መከፋፈል ውስጥ ከዚሁ ድርሻ በላይ የተቀበሏቸው ገንዘቦች፤ ለመቀበል ተራ ከተጻፉበት መያዣ ካለው ክፍያቸው ላይ ተይዘው፤ ዋስትና ለሌለው ንብረት ተመላሽ ሆነው ይቆያሉ፡፡

ክፍል  ፭
በንግዱ መደብር ላይ መያዣ ያላቸው የገንዘብ ጠያቂዎች መብት፡፡

ቊ ሺ፷፱፡፡ ከሌሎች ከሚንቀሳቀሱ ዕቃዎች ሽያጭ ዋጋ በፊት ስለ ተከፋፈለው የንግድ መደብር ሸያጭ ዋጋ፡፡

የንግዱ መደብር ሽያጭ ዋጋ ከመከፋፈሉ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ሽያጭ ዋጋ በፊት፤ ወይም አብሮ ክፍያው ተደርጎ እንደ ሆነ፤ ከመደብሩ ሽያጭ ዋጋ በሙሉ ዋጋቸውን ያልተቀበሉ የመያዣ ወይም ልዩ መብት ያላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች፤ በቁጥር ሺ፵፩ እና በተከታዮቹ ውሳኔዎች መሠረት መብታቸው ተቀባይነት አግኝቶ እንደ ሆነ፤ ባልተከፈላቸው ገንዘብ መጠን ለኅብረቱ በሚከፈለው ገንዘብ ውስጥ ከተራ ገንዘብ ጠይቂዎች ጋራ ተካፋይ ይሆናል፡፡

ቊ ሺ፸፡፡ ከንግዱ መደብር ሽያጭ ዋጋ በፊት ስለ ተከፋፈለው የሌሎች ተንቀሳቃሽ ዕቃዎች ዋጋ፡፡

የንግዱ መደብር ሽያጭ ዋጋ ከመከፋፈሉ በፊት የሌሎች ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ሽያጭ ዋጋ ተከፋፍሎ እንደ ሆነ፤ መያዣ ያላቸውና፤ መብታቸውም በደንብ ተቀባይነት ያገኘው ገንዘብ ጠያቂዎች፤ ከዚሁ ከሚከፋፈለው ገንዘብ፤ በሙሉ በሚጠይቁት ገንዘብ መጠን ተካፋይ ይሆናሉ፡፡ ስለ ሆነም፤ በቁጥር ሺ፷፯ የተደነገገው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ነው፡፡

ቊ ሺ፸፩፡፡መያዣ ካልሆነው ንብረት የሽያጭ ዋጋ የተከፈለውን ስለ መቀነስ፡፡

(፩) የንግዱ መደብር ከተሸጠና የሽያጩም ገንዘብ የሚከፋፈለበት አኳኋን ከተወሰነ በኋላ በንግድ መደብሩ ላይ ለሞላ ገንዘባቸው መያዣ ያላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች ገንዘባቸውን ከንግዱ መደብር ሽያጭ ላይ የሚያገኙት፤ መያዣ ካልነበረው ንብረት የሽያጭ ዋጋ የተከፈላቸው ገንዘብ ተቀናሽ ሆኖ ነው፡፡
(፪) በንኡስ ቁጥር (፩) መሠረት የተቀነሰው ገንዘብ ከኪሣራው ላይ በኅብረት ገንዘብ ጠያቂ ለሆኑት ሰዎች ጥቅም መያዣ ወዳልሆነው ንብረት ተመላሽ ይሆናል፡፡

ቊ ሺ፸፪፡፡ በንግዱ መደብር  ላይ የመያዣ መብት ያላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች በከፊል ለመቀበል ተራ ስለ መጻፍ፡፡

ከንግድ መደብር ሽያጭ ዋጋ ላይ የመያዣ መብት ኑሮዋቸው በከፊል ብቻ የተከፈሉ ገንዘብ ጠይቂዎች ጉዳይ ከዚህ እንደሚቀጥለው ይሠራል፤
(ሀ) ዋስትና በሌለው ንብረት ውስጥ ያላቸው መብት  የሚወሰነው ከንግዱ መደብር  ዋጋ ከተቀበሉት ገንዘብ በኋላ በሚቀራቸው ገንዘብ መጠን ነው፡፡
(ለ) ባለፈው መከፋፈል ውስጥ ከዚሁ ድርሻ በላይ የተቀበሏቸው ገንዘቦች፤ ለመቀበል ተራ ከተጻፉበት መያዣ ካለው ክፍያቸው ላይ ተይዘው ዋስትና ለሌለው ንብረት ተመላሽ ሆነው ይቆያሉ፡፡

ክፍል ፮
በመፋለም የመጠየቅ መብት

ቊ ሺ፸፫፡፡ የንግድ ወረቀቶችን በመፋለም ስለ መጠየቅ ፡፡   

የመክሠር ማስታወቂያ ፍርድ በተሰጠበት ጊዜ፤ በከሠረው ሰው ንብረት ውስጥ በዐይነት የሚገኙትን የንግድ ወረቀቶች ወይም ሌሎች ያልተከፈለባቸው ሰነዶች መልሶ ለመውሰድ የሚቻለው ባለሀብቱ እነዚህን ወረቀቶች ወይም ሰነዶች ለባለዕዳው የሰጠው ዋጋቸውን ተቀብሎ እንዲያስቀምጥለት ብቻ የሆነ እንደ ሆነ ነው፡፡ እንዲሁም፤ ባለሀብቱ ለተወሰኑ አከፋፈሎች ባለዕዳው እንዲከፍልለት የሰጠው ገንዘብ እንዲመለስለት ለመጠየቅ ይችላል፡፡

ቊ ሺ፸፬፡፡በአደራ የተቀመጡ የንግድ ዓቃዎችን ወይም ላንድ ኮሚሴዮኔር የተሰጡትን ዕቃዎች ስለ መጠየቅ፡፡

 (፩) ለባለዕዳው በአደራ የተሰጡ የንግድ ዕቃዎች ወይም በባለሀብቱ ስም ለመሸጥ የተቀበላቸው ዕቃዎች በሙሉ ወይም በከፊል በዐይነት የሚገኙ ከሆነ ባለሀብቱ እንዲመለሱለት መጠየቅ ይችላል፡፡
(፪) የነዚሁ ዕቃዎች ዋጋ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲመለስ ለመጠየቅ የሚቻለው በጥሬ ገንዘብ ወይም ዋጋ ባለው ነገር ያልተከፈለ ወይም በባለዕዳውና በገዢው መካከል በተመላላሽ ሒሳብ ያልተቻቻለ የሆነ እንደ ሆነ ነው፡፡

ቊ ሺ፸፭፡፡ ከመክሠሩ በፊት ሽያጫቸው የፈረሰውን ዕቃዎች በመፋለም ስለ መጠየቅ፡፡

(፩) በፍርድ ውሳኔ ወይም በውሉ ቃል መሠረት፤ የመክሠር ማስታቂያው ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት ሽይጫቸው ፈራሽ የሆነውን ዕቃዎች በዐይነታቸው በሙሉ ወይም በከፊል ካሉ በመፋለም ለመጠየቅ ይቻላል፡፡
(፪) የሽያጩ መፍረስ በፍርድ ውሳኔ የታወቀው ወይም የተወሰነው፤ የመክሠር ማስታወቂያው ፍርድ ከተሰጠ በኋላ ቢሆንም እንኳ ገንዘቡ ያልተከፈለው ሻጭ ያቀረበው የመፋለም ጥያቄ ወይም ክስ የመክሠሩ ማስታወቂያ ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት ከሆነ የመፋለሙን ጥያቄ በከፊል ገንዘብ ላይም ቢሆን ለማቅረብ ይችላል፡፡

ቊ ሺ፸፮፡፡ ባለሀብትነታቸው እነደ ተጠበቀ ሆኖ የተሸጡ ተንቀሳቃሽ ዕቃዎችን ስለ ማስመለስ፡፡

ዋጋቸው እስኪከፈል ድረስ ባለሀብትነታቸው ሳይተላለፍ ለከሠረው ሰው የተሸጡትን የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች በመፋለም መልሶ ለመውሰድ የሚቻለው የሽያጩ ቃል፤ የመክሠር ማስታቂያው ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር ፪ሺ፴፻፹፯ መሠረት ተመዝግቦ እንደ ሆነ ነው፡፡

ቊ ሺ፸፯፡፡ ለባለዕዳው የተላኩትን ዕቃዎች በመፋለም ስለ መጠየቅ፡፡

(፩) ለባለዕዳው የተላኩ ዕቃዎች በራሱ መጋዘን ውስጥ ወይም ስለርሱ በሚሸጠው በኮሚሲዮኔሩ ማጋዘኖች ውስጥ ያልገቡ ከሆነ፤ በመፋለም ለመጠየቅ ይቻላሉ፡፡
(፪) የሆነ ሆኖ ላኪው በፈረመው ሰነድ መሠረት ቅን ልቡና ላለው ሁለተኛ ገዢ፤ ከመድረሳቸው በፊት ያለማታለል፤ ዕቃዎቹ የተሸጡ እንደ ሆነ የመፋለሙን ጥያቄ ለመቀበል አይቻልም፡፡

ቊ ሺ፸፰፡፡ ስለ መያዣ መብት፡፡

ለባለዕዳው ያልተሰጡትን ወይም ለርሱ ወይም ስለ እርሱ ሆኖ ለሚሠራ ሦስተኛ ወገን ገና ያልላካቸውን ዕቃዎች ሻጩ ለመያዝ ይችላል፡፡

ቊ ሺ፸፱፡፡ ዕቃዎች እንዲሰጡ ለማስገደድ ለንብረት ጠባቂዎች ስለ አላቸው ሥልጣን፡፡

(፩) በቁጥር ሺ፸፯ እና ሺ፸፰ ስለ ተመለከቱት ጉዳዮች ንብረት ጠባቂዎቹ በመርማሪው ዳኛ ፈቃድ የተስማሙበትን ዋጋ ለሻጩ በመክፈል ዕቃዎቹ እንዲሰጡዋቸው ለማስገደድ ሥልጣን አላቸው፡፡
(፪) በዚህ ሥልጣናቸው ያልሠሩበት እንደሆነ ሻጩ ከዕቃዎቹ ዋጋ የተቀበለውን እና ከከሰረው ሰው ለኪራይ ወይም ለመጫኛ ለኮሚሲዮን ለኢሹራንስ ወይም ለሌሎች ወጪዎች አስቀድሞ የወሰዳቸውንና እነዚህንም ለመሳሰሉ ምክንያቶች የሚከፈሉትን ገንዘቦች ለኅብረቱ መልሶ እነዚህንም ወጪዎች ራሱ እንዲከፍል ሻጩ ይገደዳል፡፡ የሆነ ሆኖ የውሉ አለመፈጸም ለሻጩ የጉዳት ኪሣራዎችን ሊያስገኙለት ይችላሉ፡፡

ቊ ሺ፹፡፡ የመፋለም ጥያቄዎችን ስለ መቀበል፡፡

የመፋለም ጥያቄዎችን፤ በመርማሪው ዳኛ ፈቃድ ንብረት ጠባቂዎቹ ለመቀበል ይችላሉ፡፡

ምዕራፍ ፮
ስለኪሣራው አሠራር የሚደረግ ዘዴ
ክፍል ፩
ስምምነት

ቊ ሺ፹፩፡፡ የስምምነት አሳብ ስለ ማቅረብ፡፡

(፩) በቁጥር ሺ፵፮ የተመለከተው ቀን ካለቀበት አንሥቶ በማናቸውም ጊዜ የከሠረው ነጋዴ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ አንድ የስምምነት አሳብ ለማቅረብ ይችላል፡፡ ይኸውም አሳብ የሚቀርበው በተለይ ለመርማሪው ዳኛ ነው፡፡
(፪) በሚቀርበው አሳብ ውስጥ ዋስትና ለሌላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች የሚሰጠው በመቶ ይህን ያህል የሚባለው ገንዘብና ባለዕዳው ለመክፈል እስከዚህ ቀን ይሁንልኝ ሲል የጠየቀው ግዜ ይጠቀሳል እከፍለለሁ ላለው ገንዘብና ለሥነ ሥርዐት ወጪና ለንብረት ጠባቂዎች ኪሣራ ማረጋገጫ እንዲሆን የሚሰጠውን ዋስትና መጥቀስ አለበት፡፡
(፫) ስለ ስምምነት የቀረበው አሳብ የሒሳብ ማጣራቱን ያግዳል፡፡

ቊ ሺ፹፪፡፡ የቀረበውን ስምምነት ስለ መመርመርና የተባለውን አሳብ ለገንዘብ ጠያቂዎች ስለ ማስታወቅ፡፡

(፩) የስምምነቱ አሳብ የቀረበለት መርማሪ ዳኛ የንብረት ጠባቂዎችንና የገንዘብ ጠያቂዎችን ኮሚቴ ሐሳብ ይቀበላል፡፡
(፪) የቀረበው አሳብ የሚገባ ነው ሲል የገመተ እንደ ሆነ፤ ዳኛው ገንዘብ ጠያቂዎቹ እንዲያውቁት በፍጥነት እንዲተላለፍላቸው ያዛል፡፡
(፫) ይህ ለገንዘብ ጠያቂዎች የሚላከው ማስታወቂያ በፍርድ ቤቱ መዝገብ ቤት ሹም በኩል ሆኖ ለያንዳንዱ ገንዘብ ጠያቂ በሚላከው በሬካማንዴ ደብዳቤ ይፈጸማል፡፡ ስለሆነም የገንዘብ ጠያቂዎቹ ብዛት ለያንዳንዱ ማስታወቂያ ለመላክ የማይፈቀድ በሚሆንበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ፤ የንብረት ጠባቂዎቹን እና የሕግ አስከባሪውን አሳብ ከሰማ በኋላ ለመርማሪው ዳኛ ስለ ስምምነቱ የቀረበው አሳብ የሕግ ማስታወቂያዎችን ለመቀበል በተፈቀደለት ጋዜጣና በንግድ ኦፊሲዬል ጋዜጣ እንዲወጣ ለማዘዝ ይፈቅድለታል፡፡
(፬) ማስታወቂያውም፤ የከሠረው ነጋዴ ካቀረበው አሳብ በላይ ንብረት ጠባቂዎቹና የገንዘብ ጠያቂዎቹ ኮሚቴ የሰጡትን አሳብ ያመለክታል፡፡ በመክሠር አሠራር ሁኔታ፤ በተፈጸሙት ሥርዐቶችና በተደረጉት ሥራዎች ላይ ንብረት ጠባቂዎቹ ያቀረቡት መግለጫ ከዚህ ማስታወቂያ ጋራ ይያያዛል፡፡
(፭) ስለስምምነቱ በተላለፈው ማስታወቂያ ውስጥ ከሓያ ቀን የማያንስ ከ፴ቀን የማይበልጥ ጊዜ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ ይወሰናል፡፡ በዚሁም ጊዜ ውስጥ በሐሳቡ ያልተስማሙት ገንዘብ ጠያቂዎች የከሠረው ሰው ያቀረባቸውን አሳቦች ያለመቀበላቸውን ለፍርድ ቤቱ መዝገብ ቤት ማስታወቅ አለባቸው፡፡

ቊ ሺ፹፫፡፡ ገንዘብ ጠያቂዎች ስለሚሰጡት ድምፅ፡፡

(፩) የሚሰጠው ድምፅ በፕሮሴቬርባል ተጽፎ መርማሪው ዳኛና የፍርድ መዝገብ ቤት ሹም ይፈርሙበታል፡፡
(፪) በውለታ ወይም ለጊዜው የተቀበሏቸው ቢሆንም፤ መብታቸው በአገባብ የታወቀላቸው ገንዘብ ጠይቂዎች ሁሉ የድምፅ መስጠት መብት አላቸው፡፡
(፫) ልዩ ማረጋገጫዎች ያሏቸው ገንዘብ ጠያቂዎች፤ የቀረበውን የስምምነት አሠራር በሚመለከተው ጉዳይ ስላላቸው መብት ድምፅ ለመስጠት የሚችሉት ማረጋገጫቸውን የለቀቁ እንደ ሆነ ነው፡፡ ስምምነቱ ሳይደራጅ ወይም ፍርድ ቤቱ ሳያጸድቀው የቀረ፤ ወይም የተሰረዘ ወይም የፈረሰ እንደ ሆነ፤ ማረጋገጫቸውን መልቀቃቸው ቀሪ ይሆናል፡፡
(፬) የከሠረው ሰው ባል ወይም ሚስት፤ እስከ አራት ቤት የሚቆጠሩ የሥጋ ወይም የጋብቻ ዘመዶች እና እንዲሁም የመክሠሩ ማስታወቂያ ከተነገረበት ጊዜ አስቀድሞ በአንድ ዓመት ውስጥ ከነዚሁ ሰዎች መብት የተላለፈላቸው ወይም የገዙ ሰዎች ድምፅ ለመስጠትና ከድምፅ ብልጫው ቁጥር ውስጥ ለመግባት አይችሉም፡፡
(፭)  የመክሠሩ ማስታወቂያ ፍርድ ከወጣ በኋላ የተደረጉት የገንዘብ ጠያቂዎችን መብት ማስተላለፍ የድምፅ መስጠትን መብት አይሰጡም፡፡

ቊ ሺ፹፬፡፡ ስምምነቱን ስለማጽደቅ፡፡

(፩) ስምምነቱ ውድቅ እንዳይሆን፤ ከዕዳው ከሦስት ሁለት እጅ ባላቸው የንዘብ ጠያቂዎች ድምፅ ብልጫ እንዲጸድቅ ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ድምፅ በሚሰጥበት ጊዜ ያልነበሩት ሰዎች በድምፅና በገንዘብ ብልጫው አቆጣጠር ውስጥ አይገቡም፡፡
(፪) የከሠረው ሰው ያቀረበውን የስምምነት አሳብ አንቀበልም ሲሉ፤ በቁጥር ሺ፹፪ ንኡስ ቁ (፭) በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ያላስታወቁ ገንዘብ ጠያቂዎች ስምምነቱን እንደ ተቀበሉ ይቆጠራሉ፡፡
(፫) ይህ የተነገረው ጊዜ ካለፈ በኋላ ከሚሰጠው ውሳኔ የተነሣ መብታቸውን የተቀበሏቸው የንዘብ ጠያቂዎቹ ቁጥር ወይም የሚጠይቁት ገንዘብ ልክ ቢለዋወጥም የድምፅ ብልጫውን አቆጣጠር አይለውጠውም፡፡
(፬) የድምፅ መስጠትን ውጤት በቁጥር ሺ፹፫ ንኡስ ቁ (፩) በተመለከተው ፕሮሴቬርባል ላይ መርማሪው ዳኛ ያረጋግጠዋል፡፡

ቊ ሺ፹፭፡፡ ስምምነቱን ስለ መቃወም፡፡

(፩) በስምምነቱ ውስጥ ለመግባት መብት የነበራቸው ወይም ከዚያ ወዲህ መብታቸው የታወቀላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች ሁሉ በስምምነቱ ላይ መቃወሚያ ለማቅረብ ይችላሉ፡፡
(፪) ተቃዋሚነቱ ምክንያት ያለው መሆን አለበት፡፡ መቃወሚያው ምክንያት ካልተሰጠበትና ድምፅን በተሰጠበት በስምንት ቀኖች ውስጥ ለባለዕዳውና ለንብረት ጠባቂዎቹ ካልተላለፈላቸው ፈራሽ ይሆናል፡፡ ይኸውም መቃወሚያ በፍርድ ቤቱ መጀመሪያ ችሎት ለመቅረብ ጥሪ ይኖረዋል፡፡

ቊ ሺ፹፮፡፡ ስምምነቱን ስለ ማጽደቅ፡፡

ማናቸውም ጥቅም ያለው ወገን ፍርድ ቤቱ ስምምነቱን እንዲያጸድቀው ጥያቄ ለማቅረብ ይችላል፡፡ የሆነ ሆኖ ፍርድ ቤቱ በቁጥር ሺ፹፭ ከተወሰኑት ስምንት ቀኖች በፊት ለመወሰን አይችልም፡፡
(፪) በዚህ በተባለው ጊዜ ውስጥ መቃሚያዎች ቀርበው እንደ ሆነ ፍርድ ቤቱ ስለነዚህ መቃሚያዎችና እንዲጸድቅ ስለ ቀረበው ጥያቄ ባንድ ፍርድ ይወሰናል፡፡
(፫) ስለ ስምምነቱ መጽደቅ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ፍርድ ቤቱ የሚከተሉትን መመልከት አለበት፡-
(ሀ) መርማሪው ዳኛ ስለ መክሠሩ አሠራርና ስምምነቱ ሊፈቀድ የሚችል ስለ መሆኑ ለፍርድ ቤቱ የሚያቀርበውን መግለጫ እና፤
(ለ) ንብረት ጠባቂዎቹ በቁጥር ሺ ፹፪ ንኡስ ቁጥር (፬) መሠረት የሚያቀርቡትን መግለጫ እና፤
(ሐ) ያለም እንደ ሆነ ከከሠረው ሰው ጋራ በጋራ ተገዳጅ የሆኑት ሰዎች የሚያቀርቡትን ማስገንዘቢያ፡፡
(፬) መቃወሚያውንም ፍርድ ቤቱ የተቀበለው እንደ ሆነ፤ ስምምነቱ ባለጉዳዮች በሆኑት ሰዎች በኩል ሁሉ ፈራሽ መሆኑን ይወስናል፡፡

ቊ ሺ ፹፯፡፡ ስምምነቱን ለማጽደቅ ስላለመቀበል፡፡

ፍርድ ቤቱ ስምምነቱን የማያጸድቀው፤
(ሀ) ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ደንቦች ያልተፈጸሙ እንደ ሆነ፤ ወይም
(ለ) ስምምነቱን ማጽደቅ የሕዝብን ወይም የገንዘብ ጠያቂዎቹን ጥቅም የሚቃወም የሆነ እንደ ሆነ ነው፡፡

ቊ ሺ ፹፰፡፡ የስምምነቱን አፈጻጸም ስለ መጠባበቅ፡፡

(፩) ከስምምነቱ መጽደቅ በኋላ መርማሪው ዳኛ፤ ንብረት ጠባቂዎቹና የገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ስለ ስምምነቱ መጽደቅ በተሰጠው ፍርድ በተወሰኑት አደራረጎች መሠረት የስምምነቱን መፈጸም ይጠባበቃሉ፡፡
(፪) የስምምነቱ ውለታዎች ከተፈጸሙ በኋላ የገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ለኅብረቱ የተሰጠው የመያዣ መብት እንዲነሣ ለመፍቀድ ሥልጣን አለው፡፡

ቊ ሺ ፹፱፡፡ ስለ ስምምነቱ ውጤቶች፡፡

(፩) የንብረት መያዣ ካላቸውና መያዣቸውንም ካልለቀቁት ገንዘብ ጠያቂዎች፤ እንዲሁም መብታቸውን ያገኙት የመክሠሩ አሠራር በሚፈጸምበት ጊዜ ከሆኑት መያዣ ከሌላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች በቀር የስምምነት መጽደቅ ገንዘብ ጠያቂዎችን ሁሉ ያስገድዳል፡፡
(፪) በቁጥር ሺ፮ መሠረት በከሠረው ሰው የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይና፤ እንዲሁም በቁጥር ሺ፯ መሠረት በንግዱ ላይ ለገንዘብ ጠያቂዎቹ ያላቸው በኅብረቱ ስም የተመዘገበውን የመያዣ መብት፤ የስምምነቱ መጽደቅ አይለውጠውም፡፡ ስለዚህ፤ ንብረት ጠባቂዎቹ ስለ ስምምነቱ መጽደቅ የተሰጠውን ፍርድ ሥልጣን ባለው መሥሪያ ቤት ያስመዘግቡታል፡፡
(፫) ስምምነቱ ቢኖርም ቅሉ፤ ገንዘብ ጠያቂዎቹ ስለሚጠይቁት ሙሉ ገንዘብ በባዕዳው የጋራ ተገዳጆች ላይ ያላቸውን የክስ ማቅረብ መብት እንደ ያዙ ይቆያሉ፡፡

ቊ ሺ፺ ስለ መክሠሩ ሙጤቶች መቅረት፡፡

(፩) ስለ ስምምነቱ መጽደቅ የተሰጠው ፍርድ የመጨረሻ ፍርድ በሆነ ጊዜ፤ ወዲያው ስለ መብት እጦት በቁጥር ሺ፳፪ የተጻፈው ቃልና ለስምምነቱ እፈጻጸም በቁጥር ሺ፹፰ የተደነገጉት ድንጋጌዎች እንደ ተጠበቁ ሆነው፤ የመክሠሩ ውጤቶች ይቀራሉ፡፡
(፪) ንብረት ጠባቂዎቹ፤ በመርማሪው ዳኛና በገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ፊት፤ ለባለዕዳው የመጨረሻውን ሒሳብ ያስረክባሉ፡፡ በዚህም ሒሳብ ክርክር ከተደረገበት በኋላ ሒሳቡን ያቆማሉ፡፡ ለባለዕዳው፤ ንብረቶቹን፤ መዝገቦቹን፤ ወረቀቶቹንና ዕቃዎቹን በሙሉ ይመልሳሉ፡፡ ባለዕዳውም ደረሰኝ ይሰጣቸዋል፡፡ ባለዕዳው ሳይረከባቸው ቢቀር ንብረት ጠባቂዎቹ የመጨረሻውን ሒሳብ ካሰናዱበት ጊዜ አንሥቶ ለሁለት ዓመት ብቻ ኅላፊዎች ይሆናሉ፡፡
(፫) ለዚህ ሁሉ መርማሪው ዳኛ አንድ ፕሮሴቬርቫል ያዘጋጃል፡፡ ክርክር በሚነሣበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡

ቊ ሺ ፺፩፡፡ ከጸደቀ በኋላ ስለ ስምምነቱ መፍረስ፡፡

(፩) ከስምምነቱ መጽደቅ ወዲህ በተገለጸው ተንኰል ምክንያት ካልሆነና፤ ተንኰሉም የተገኘውን ሀብት ከመደበቅ ወይም ዕዳውን ከማጋነን የተፈጠረ ካለሆነ በቀር፤ ስምምነቱ ከጸደቀ በኋላ እንዲፈርስ የሚቀርበው ማናቸውም ክስ አይሰማም፡፡ ይኸንንም ክስ አንድ ገንዘብ ጠያቂ ራሱ ሊያቀርበው ይችላል፡፡ ነገር ግን ሊቀርብ የሚችለው፤ ተንኰሉ በተገለጸ በአምስት ዓመት ውስጥ ብቻ ነው፡፡
(፪) የከሠረው በተንኰል ነው የሚል ፍርድ የተሰጠ እንደ ሆነ፤ የተደረገው ስምምነት ፈራሽ ይሆናል፡፡ ይኸውም የስምምነቱ መፍረስ ለተንኰሉ ግብረ አበሮች ከሆኑት በቀር፤ ዋሶቹን ሁሉ በደንብ ነጻ ያወጣቸዋል፡፡

ቊ ሺ ፺፪፡፡ ከስምምነቱ መጽደቅ በኋላ፤ በተገለጸው ተንኰል ምክንያት ክስ በሚቀርብበት ጊዜ ስለሚደረጉ መጠባበቂያዎች፡፡

(፩) ከስምምነቱ መጽደቅ በኋላ፤ ባለዕዳው በተንኰል መክሠር ተከሶ የተቀጣ እንደ ሆነ፤ ፍርድ ቤቱ አስፈላጊ መስለው የታዩትን የመጠባበቂያ ሥራዎች ለማዘዝ ይችላል፡፡
(፪) እነዚሁ አስፈላጊ ሥራዎች የሚያስከስስ ነገር የለውም ከተባለበት ቀን ወይም የከሠረው ሰው በነጻ ከተለቀቀበት ጊዜ ጀምሮ በደንብ ይቀራሉ፡፡

ቊ ሺ ፺፫፡፡ ስምምነቱን ስለ መሰረዝ፡፡

(፩) ባለዕዳው የስምምነቱን ውለታዎች ያልፈጸመ እንደ ሆነ፤ ያሉም እንደ ሆነ፤ ዋሶች ባሉበት ወይም በሚገባ ከተጠሩ በኋላ፤ ስምምነቱ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤቱ ለማመልከት ይቻላል፡፡
(፪) ስምምነቱ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲፈጸመ ዋስ የሆኑትን ሰዎች የስምምነቱ መፍረስ ነጻ አያወጣቸውም፡፡

ቊ ሺ ፺፬፡፡ስምምነቱ ከተሰረዘ ወይም ከፈረሰ በኋላ የመክሠሩን አሠራር እንደገና ስለ መቀበል፡፡

(፩) ስምምነቱ የተሰረዘ ወይም የፈረሰ እንደ ሆነ፤ አስቀድሞ በተጻፈው የዕቃ ዝርዝር መዝገብ መሠረት፤ ንብረት ጠባቂዎቹ ሳይዘገዩ፤ እሽጎችም እንዳሉ ያሸገው ባለሥልጣን እየረዳቸው የተቆጠሩትን ባለዋጋ የሆኑትን ዕቃዎችና ወረቀቶችን ማረጋገጥ ይጀምራሉ፡፡ አስፈላጊ ሲሆኑም ተጨማሪ የዕቃ ዝርዝር መዝገብና የሒሳብ ሚዛን ያዘጋጃሉ፡፡
(፪) ወዲያውም በፍጥነት፤ ስለዚሁ የተፈረደውን ፍርድ ቅጅና፤ አዲስ ገንዘብ ጠያቂዎችም እንዳሉ፤ ገንዘብ የሚጠይቁባቸውን ሰነዶች፤ በቁጥር ሺ፵፫ በተመለከቱት ሁታዎች መሠረት ለምርመራ እንዲያቀርቡ በማሳሰብ ማስታወቂያ ያወጣሉ፡፡

ቊ ሺ ፺፭፡፡ የቀረቡትን አዲስ የንዘብ መጠየቂያ መብቶች ስለ መመርመር፡፡

(፩) በቁጥር ሺ፺፬ በተመለከተው መሠረት የቀረቡትን የገንዘብ መጠየቂያ ሰነዶች ንብረት ጠባቂዎች ይመረምራሉ፡፡
(፪) አስቀድሞ ተቀባይነት አግኝተው ስለነበሩት የገንዘብ መጠየቂያ መብቶች አዲስ ምርመራ አይደረግም፡፡ ይሁን እንጂ፤ ከዚያ ወዲህ በሙሉ ወይም በከፊል የተከፈሉትን ያለመቀበል ወይም የመቀነስ መብት ሳይነካ ነው፡፡

ቊ ሺ ፺፮፡፡ ስምምነቱ ከጸደቀ በኋላ ባለዕዳው ስላደረጋቸው ውሎች፡፡

ስምምነቱ በፍርድ ከመጽደቁ በኋላና ከስምምነቱ መሰረዝ ወይም መፍረስ በፊት ባለዕዳው ያደረጋቸው ውሎች፤ በገንዘብ ጠያቂዎች መብት ላይ ተንኰል በማድረግ ካልሆነ በቀር ፈራሽ አይሆንም፡፡

ቊ ሺ ፺፯፡፡ ከስምምነቱ አስቀድሞ ስላሉት የገንዘብ ጠያቂዎች መብት፡፡

ከስምምነቱ በት የነበሩት ገንዘብ ጠያቂዎች ባለዕዳውን ብቻ በሚመለከት ጉዳይ፤ ሙሉ መብታቸውን እንደገና መልሰው ይይዛሉ፤ ነገር ግን ከዚህ በታች በተመለከቱት መጠኖች ካልሆነ በቀር፤ ከኅብረቱ ውስጥ ለማግኘት አይችሉም፡፡ ይኸውም፤
(ሀ) እንዲከፈላቸው ከጠየቁት ገንዘብ ምንም ድርሻ ያልወሰዱ እንደ ሆነ ለሚጠይቁት ገንዘብ በሙሉ፤
(ለ) ገንዘብ ጠያቂዎች ከሚገባቸው ድርሻ በከፊል ተቀብለው እንደ ሆነ በሚቀራቸው ድርሻ ልክ ነው፡፡

ቊ ሺ ፺፰፡፡ ከስምምነቱ በኋላ አዲስ ለሆኑት ገንዘብ ጠያቂዎች ገንዘባቸው ባለመከፈሉ ምክንያት ሁለኛ ስለሚደረግ የመክሠር ማስታቂያ፡፡

  ስምመነቱ ሳየሰረዝ ወይም ሳይፈርስ ከስምምነቱ በኋላ አዲስ የመጡት ገንዘብ ጠያቂዎች ይከፈለን የሚሉት ገንዘብ ሳይከፈላቸው በመቅረቱ ምክንያት ሁለተኛ የኪሣራ ማስታወቂያ የሚያስፈልግ ሲሆን፤ በፊተኛው የኪሣራ ማስታወቅ ጊዜ የነበሩት ገንዘብ ጠያቂዎች ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ጠያቂነታቸው የተነሣ አዲሶቹን ጠያቂዎች በሚመለከት ነገር ምንም ብልጫ አለን ለማለት አይችሉም፤ በቁጥር ሺ፺፯ የተወሰኑትም ድንጋጌዎች ይፈጸሙባቸዋል፡፡

ቊ ሺ ፺፱፡፡ ንብረትን በመልቀቅ ስለሚደረግ ስምምነት፡፡

(፩) የከሠረው ሰው ያለውን ንብረት በሙሉ ወይም በከፊል በመልቀቀ ስምምነት ሊያግድ ይችላል፡፡ ይህ የባለው ስምምነት፤ ልክ ለመደበኛው ስምምነት የሚሰጡትን ደንቦች በመከተል ይፈጸማል፡፡ የሚሰጣቸውም ውጤቶች እንደነዚያው ያሉ ውጤቶች ናቸው፡፡ የማሰረዘውም የሚፈርሰውም መደበኛው ስምምነት በሚሰረዝባቸውና በሚፈርስባቸው ምክንያቶች ነው፡፡
(፪) የተለቀቀውንም ንብረት የማጣራት ሥራ በቁጥር ሺ)1 እና በተከታዮቹ በተጻፈው መሠረት ይፈጸማል፡፡
(፫) ያለውን ንብረት በመልቀቅ የሚደረገው ስምምነት፤ በተለቀቀው ንብረት ውስጥ ያልገቡትንና የከሠረው ሰው በኋላ የሚያገኛቸው ንብረቶች እንዳይያዙ ያደርጋል፡፡
(፬) ስምምነቱ ቢኖርም ቅሉ፤ ገንዘብ ጠያቁዎቹ ከባለዕዳው በጋራ ተገዳጅ በሆኑት ሰዎች ላይ ያላቸው መብታቸውን እንደ ያዙ ይቆያሉ፡፡

ቊ ሺ፻፡፡ በንግድ መዝገብ ስለ መግባት፡፡

ስምምነቱ የጸደቀበት ወይም የፈረሰበት ወይም የተሰረዘበት ፍርድ በቁጥር ፱፻፹፫ (፬) በተደነገገው መሠረት የፍርድ መዝገብ ቤቱ ሹም በንግድ መዝገብ መግባታቸውን ማረጋገጥ አለበት፡፡

ክፍል ፪
በግዴታ የሚሆን የንብረት ማጣራት

ቊ ሺ፻፩፡፡ ስምምነቱን ያለመቀበል ስለሚያስከትላቸው ውጤቶች፡፡

ስለ ስምምነቱየቀረበው አሳብ ቁጥር ሺ፹፬ የሚያስገድደውን ዕጥፍ የሆነውን የድምፅ ብልጫ ያላገኘ እንደ ሆነ፤ ንብረቱ በግድ እስኪሸጥና ገንዘብ ጠያቂዎቹም የሽያጩን ድርሻ ጨርሰው እስኪከፋፈሉ ድረስ የመክሠሩ ሥራዎች ሳያቋርጡ ይቀጥላሉ፡፡

ቊ ሺ፻፪፡፡ ለከሠረው ሰው ስለሚደረገው ዕርዳታ፡፡

ከሚከፋፈለው ንብረት ላይ ለከሠረው ሰው ወይም ለቤተሰቡ ርዳታ ለመስጠት ይቻል እንደ ሆነ፤ ለማወቅ መርማሪው ዳኛ የገንዘብ ጠያቂዎቹን ኮሚቴ ያማክራል፡፡ ኮሚቴው አሳቡን በመልካም የተቀበለው እንደ ሆነ፤ መርማሪው ዳኛ ንብረት ጠባቂዎቹ ባቀረቡት አሳብ መሠረት የተፈቀደውን ርዳታ ልክ ይወስናል፡፡

ቊ ሺ፻፫፡፡ ስለ ንብረቱ ማጣራት ሥራዎች፡፡

(፩) ንብረት ጠባቂዎቹ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዐት ሕግ መሠረት የባለዕዳውን የሚንቀሳቀሱትንና የማይንቀሳቀሱትን ንብረቶች ይሸጣሉ፡፡ ባለዕዳውም ለነዚህ ሥራዎች መጠራት የለበትም፡፡
(፪) ከሽያጩም የተገኘው ገንዘብ በቁጥር ፱፻፺፮ በተመለከተው መሠረት ይቀመጣል፡፡
(፫) ንብረት ጠባቂዎቹ ባለዕዳው ሳይጠራ፤ በቁጥር ሺ፴፰ እንደተመለከተው ስለማንኛውም ዐይነት፤ የባለዕዳውን መብቶች የሚመለከቱ ስምምነቶችንና ግልግሎችን ለማድረግ ይችላሉ፡፡

ቊ ሺ፻፬፡፡ የማይንቀሳቀሱትን ንብረቶች ስለ መሸጥ፡፡

ግደታ የሆነው ማጣራት ከመከፈቱ በፊት የተጀመረ የማይንቀሳቀሱትን ንብረቶች የማስለቀቅ ሥራ የሌለ እንደ ሆነ፤ የመሸጥን ሥራ ለመሥራት የሚችሉት ንብረት ጠባቂዎች ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱም በመርማሪው ዳኛ ፈቃድ በስምንት ቀን ውስጥ ሥራውን ለመጀመር ይገደዳሉ፡፡

ቊ ሺ፻፭፡፡ የንግድ መደብርን ስለ መሸጥ፡፡

የነጋዴው ንብረት በፍርድ ቤት እንዲጣራ ከመደረጉ በፊት የንግድ መደብሩ አንዲያዝ የታዘዘ ካልሆነ በቀር፤ የንግድ መደብሩ እንዲሸጥ የሚያስፈልገውን ለማድረግ የሚችሉት ንብረት ጠባቂዎች ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም በመርማሪው ዳኛ ፈቃድ፤ በቁጥር ሺ፩፻፮ የተመለከተው እንደ ተጠበቀ ሆኖ የንግዱን መደብር ለመሸጥ ይችላሉ፡፡

ቊ ሺ፻፮፡፡ በማጣራቱ ጊዜ ሥራውን ስለ መቀጠል፡፡

(፩) ዋስትና የሌላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች መክሠሩ በሚጠራበት ጊዜ ሥራውን እንዲቀጥሉ ለንብረት ጠባቂዎች ውክልናቸውን ሊሰጡ ይችላሉ፡፡
(፪) ስለዚህ ጉዳይ በገንዘብ ጠያቂዎቹ ኮሚቴ አሳሳቢነት፤ መርማሪው ዳኛ ገንዘብ ጠያቂዎቹ በሬኮማንዴ ደብዳቤ አሳባቸውን ይጠይቃቸዋል፡፡ ከብዛታቸው የተነሣ ለያንዳንዱ ገንዘብ ጠያቂ ማስታወቂያ ለመላክ ያልቻለ እንደ ሆነ በቁጥር ሺ፹፪ ንኡስ ቁ (፫) የተጻፉት ድንጋጌዎች ይፈጸማሉ፡፡
(፫)  ገንዘብ ጠያቂዎቹ ድምፃቸውን ለፍርድ መዝገብ ቤት በዐሥራ አምስት ቀን ውስጥ መስጠት እንዳለባቸው ይነግራቸዋል፡፡
(፬) ገንዘብ ጠያቂዎቹም የሥራው መቀጠል የሚቆይበትን ጊዜና የሥራውን ወሰን ይወስናሉ፡፡ እንዲሁም ለወጪዎችና ኪሣራዎች መክፈያ የሚሆን በንብረት ጠባቂዎች እጅ የሚቆየውን የገንዘብ ልክ ይወስናሉ፡፡ ውሳኔውም በቁጥርና በገንዘብ ሦስት ሩብ የሆነ አጠፌታ የድምፅ ብልጫ ያለው እንዲሆን ያስፈልገዋል፡፡ ይህንንም የሚያጸድቀው የመርማሪው ዳኛ ትእዛዝ ነው፡፡

 ቊ ሺ፻፯፡፡ ያለውን ጠቅላላ ሀብት በአንደዜ ስለ መሸጥ፡፡

(፩) ፍርድ ቤቱ፤ መርማሪው ዳኛ የሚለውን ሰምቶ ያለውን ንብረት በከፊል ወይም በሙሉ ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በቁጥር ዋጋ ባንደዜ እንዲሸጡዋቸው ለንብረት ጠባቂዎቹ ሊፈቀድላቸው ይችላል፡፡
(፪) የገንዘብ ጠያቂዎቹ ኮሚቴ ወይም ባለዕዳው በሚያቀርበው ጥያቄ ይህን ፈቃድ ለመስጠት ይቻላል፡፡
(፫) በሁለቱም ጊዜ ለሚቀርበው ጥያቄ በቁጥር ሺ፻፮ ንኡስ ቁ ፬ በተደነገጉት ሁናቴዎች መሠረት ገንዘብ ጠያቂዎች አሳባቸውን ይጠየቃሉ፤ የሰጡትም ድምፅ በቁ ሺ፻፮ ንኡስ ቁ ፬ መሠረት በቁጥርም ሆነ በገንዘብ ከአራት እጅ የሆነ አጠፌታ የድምፅ ብልጫ ያለው እንዲሆን ያስፈልጋዋል፡፡
(፬) የውሎን ዕቅድ ፍርድ ቤቱ እንዲያጸድቀው ያስፈልጋል፡፡
(፭) ውሉም የጸደቀ እንደ ሆነ፤ በኅብረቱ በኩል ባለዕዳውን ነጻ ያደርገዋል፡፡

ቊ ሺ፻፰፡፡ ከሚጣራው ንብረት ስለሚበልጡ ግዴታዎች፡፡

የንብረት ጠባቂዎች ሥራዎች በመጣራት ላይ ካለው ንብረት በላይ የሆኑት ግዴታዎች ያስከተሉ እንደ ሆነ፤ በድምር መስጠት ሥራዎቹን የፈቀዱት ገንዘብ ጠያቂዎች ብቻ በንብረቱ ውስጥ ከሚደርሳቸው ድርሻ በላይ ለሆነው ገንዘብ ራሳቸው አላፊዎች ናቸው፡፡ ይኸውም የሚሆነው በሰጡት ሥልጣን መጠን ነው፡፡ በሚገባቸውም ገንዘብ መጠን በግዴታዎቹ ተካፋይ ይሆናሉ፡፡

ቊ ሺ፻፱፡፡ ስለ አከፋፈሉ ድርጅት፡፡

(፩) በቁጥር ሺ፵፮ የተመለከተው ጊዜ ካለፈ አንሥቶ ንብረት ጠባቂዎቹ በየሁለቱ ወር የኪሣራውን ሁኔታ የሚያስረዳ መግለጫና በቁጥር ፱፻፺፮ መሠረት የተቀመጠውን ገንዘብ ዝርዝር ለመርማሪው ዳኛ ያስረክባሉ፡፡
(፪) የነዚህንም ገንዘቦች አከፋፈል ድርጅት ለዳኛው ያቀርባሉ፡፡
(፫) ዳኛውም የገንዘብ ጠያቂዎቹን ኮሚቴ ካማከረ በኋላ ጠቃሚ መስሎ የታየውን ማሻሻል በክፍያው ድርጅት ላይ አስፍሮ የተሻሻለው ድርጅት በፍርድ መዝገብ ቤት እንዲቀመጥ ያዛል፡፡ የድርጅቱንም መቀመጥ ገንዘብ ጠያቂዎቹ እንዲያውቁት ያደርጋል፡፡
(፬) ገንዘብ ጠያቂዎቹም ማስታቂያው ከተሰጣቸው በዐሥር ቀን ውስጥ ስለድርጅቱ አስተያየታቸውን ለማቅረብ ይችላሉ፡፡ ይህ የተባለው ጊዜ ሲያልፍ መርማሪው ዳኛ ማስገንዘቢያዎቹን ተመልክቶ ክፍያውን የሚወስን ትእዛዝ ይሰጣል፡፡

ቊ ሺ፻፲፡፡ ከማጣራቱ የተገኘውን ገንዘብ ስለ ማከፋፈል፡፡

  ከማጣራቱ ከተገኘው ገንዘብ፤
(ሀ) ለመክሠሩ አሠራር የወጣው ኪሣራና የተደረገው ወጪ ገንዘብ፤
(ለ) እንዳለም፤ ለባለዕዳውና ለቤተሰቡ የተደረገው ርዳታ፤
(ሐ) ልዩ መብት ላላቸው ገንዘብ ጠያቂዎች የተከፈለው ገንዘብ ከተቀነሰ በኋላ የሚቀረውን ገንዘብ በቁጥር ሺ፷፭– ሺ፷፮ እና ሺ፷፰ የተመለከተው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ገንዘብ ጠያቂዎቹ ሁሉ በተረጋገጠላቸውና ተቀባይነት ባገኘው መብታቸው መጠን ይከፋፈሉታል፡፡

ቊ ሺ፻፲፩፡፡ ክርክር ያለባቸውን የገንዘብ መብቶች ድርሻ ጠብቆ ስለ ማቆየት፡፡

 ተቀባይነት ስለ ማግኘታቸው ገና የመጨረሻ ውሳኔ ያልተሰጣቸው መብቶች ድርሻ ተጠብቆ ይቀመጣል፡፡

ቊ ሺ፻፲፪፡፡ ስለ አከፋፈሉ ሥርዐት፡፡

(፩) ንብረት ጠባቂዎቹ በቁጥር ፱፻፺፮ ድንጋጌዎች መሠረት በኪሣራው ስም ለመክፈሉ አሠራር ከተከፈተው ሒሳብ ላይ መብቱ ተቀባይነት ላገኘው ለያንዳንዱ ገንዘብ ጠያቂ ለሚደርሰው ክፍያ በስሙ የተጻፈ ቼክ ይልኩለታል፡፡
(፪) የተከፈለው ገንዘብ ገንዘብ ጠያቂው ባቀረበው ሰነድ ላይ ይጻፋል፡፡ ነገር ግን ሰነዱን ለማቅረብ በማይቻልበት ጊዜ መርማሪው ዳኛ የተቀመጠውን የዕዳ ሁኔታ የሚገልጸውን ፕሮሴቬርባል ተመልክቶ ክፍያውን ለመፍቀድ ይችላል፡፡

ምዕራፍ ፯
የመክሠሩ ሥራ መዘጋት

ቊ ሺ፻፲፫፡፡ የመክሠሩ ሥራ ስለሚዘጋባቸው ምክንያቶች፡፡

ስለ ስምምነቱ በቁጥር ሺ፹፩ እስከ ሺ፻ የተጻፉት ድንጋጌዎች እንደ ተጠበቁ ሆነው የመክሠሩ ሥነ ሥርዐት የሚዘጋው፤
(ሀ) ከግዴታ ማጣራት የተገኘውን ገንዘብ ጨርሶ በማከፋፈል፤
(ለ) የሚበቃ ንብረት የተገኘውን ገንዘብ ጨርሶ በማከፋፈል፤
(ሐ) ከንብረት የሚፈለግ ዕዳ ባለመኖሩ ነው፡፡

ቊ ሺ፻፲፬፡፡ የሚበቃ ንብረት ባለመኖሩ ስለሚሆን መዘጋት፡፡

(፩) የመክሠሩ ሥራዎች የሚበቃ ንብረት ባለመኖሩ ለመቀጠል ያልቻሉ እንደ ሆነ፤ ፍርድ ቤቱ መርማሪው ዳኛ ያቀረበውን መግለጫ መሠረት በማድረግ ሆነ ወይም በሥልጣኑ የሥራዎቹን መዘጋት ለመወሰን ይችላል፡፡
(፪) ይኸውም የተሰጠው ፍርድ ለያንዳንዱ ገንዘብ ጠያቂ በግል ክስ ለማቅረብ ያለውን መብት ይመልስለታል፡፡
(፫) የሆነ ሆኖ የከሠረው ሰው ንብረቶቹን የማስተዳደርን በንብረቶቹ የማዘዝን ሥልጣን እንደ ለቀቀ ይቆያል፡፡ እንዲሁም አዲስ የገባባቸው ዕዳዎች በኅብረቱ ላይ መቃወሚያ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ኅብረቱም ከአዲሶቹ ገንዘብ ጠያቂዎች ጋራ ተካፋይ መሆን የለበትም፡፡

ቊ ሺ፻፲፭፡፡ የሚበቃ ንብረት ባለመኖሩ ለተደረገው መዘጋጀት የተሰጠውን ፍርድ ስለማሻር፡፡

(፩) ባለዕዳው ወይም ማናቸውም ጥቅም ያለው ሰው በማናቸውም ጊዜ ቢሆን ለሥራዎቹ ወጪዎች አስፈላጊ የሆነው ገንዘብ መኖሩን በማስረዳት ወይም ለወጪዎቹ በቂ የሚሆነውን ገንዘብ በንብረት ጠባቂዎቹ እጅ በስቀመጥ ስለ ተደረገው መዘጋት የተሰጠው ፍርድ እንዲሻር ፍርድ ቤቱን መጠየቅ ይችላል፡፡
(፪) በማንኛዎቹም ሁኔታዎች በቁጥር ሺ፻፲፬ መሠረት ለተፈጸሙት የክስ ሥራዎች ወጪ የሆኑት ኪሣራዎች አስቀድሞ መከፈል አለባቸው፡፡

ቊ ሺ፻፲፮፡፡ ገንዘብ ጠያቂዎች ላልጠየቁዋቸው ሰነዶች በንብረት ጠባቂዎቹ ስላለባቸው አላፊነት፡፡

ገንዘብ ጠያቂዎቹ ላልጠየቁዋቸው ሰነዶች የመክሠር ማስታወቂያው ፍርድ ከተሰጠበት ቀን አንሥቶ እስከ አምስት ዓመት ድረስ ንብረት ጠባቂዎቹ ኅላፊ ይሆናሉ፡፡

ቊ ሺ፻፲፯፡፡ ከንብረቱ የሚፈለግ ዕዳ ባለመኖሩ ስለሚደረግ መዘጋት፡፡

(፩) በቁጥር ሺ፵፬ የተመለከቱት የገንዘብ መጠየቂያ ሰነዶች ዝርዝር ጽሑፍ ለፍርድ የመዝገብ ቤት ከተሰጠ በኋላ ባለዕዳው ማስረጃቸውን ላቀረቡ ገንዘብ ጠያቂዎቹ ሁሉ መክፈሉን ወይም ማስረጃ ላቀረቡት ገንዘብ ጠያቂዎች ሁሉ በደንብ ለማደላደል አስፈላጊውን ገንዘብ እንዲሁም እስከዚያን ጊዜ ድረስ ስለ መክሠሩ ሥነ ሥርዐት የወጡትን ወጪዎች የንብረት ጠባቂዎችንም ዋጋ ጭምር በንብረት ጠባቂዎች እጅ ማስቀመጡን ያስረዳ እንደ ሆነ፤ ባለዕዳው ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ፍርድ ቤቱ የመክሠሩ ሥነ ሥርዐት በሚፈጸምበት በማናቸውም ጊዜ የመክሠሩን መዘጋት ሊፈርድ ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን የሚሰጠው እነዚህ የተባሉትን ሁኔታዎች መፈጸም የሚያመለክተውን መርማሪው ዳኛ ያቀረበውን መግለጫ መሠረት በማድረግ ነው፡፡
(፪) ፍርዱ፤ ለባለዕዳው እንደገና መብቶቹን በመስጠትና መብቶቹን ካሳጡት ውሳኔዎች ነጻ በማድረግ በመክሠሩ የተከፈተውን ሥነ ሥርዐት ጨርሶ ይዘጋል፡፡

ቊ ሺ፻፲፰፡፡ በንግድ መዝገብ ስለ መመዝገብ፡፡

ያለው ሀብት የማይበቃ በመሆኑ ምክንያት ወይም ከንብረቱ ገንዘብ የመጠየቅ መብት ባለመኖሩ ምክንያት፤ ስለ መክሠር የቀረበው ክስ እንዲዘጋ የተወሰነውን ፍርድ በቁጥር ፱፻፹፫ ንኡስ ቁ (፬) መሠረት የፍርድ ቤቱ መዝገብ ቤት ሹም በንግድ መዝገብ ማስገባት አለበት፡፡