ስለ ይግባኝ ተከሳሹ በሌለበት የተሰጠውን ፍርድ ለማሻር ስለሚቀርበው ማመልከቻ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

ስለ ይግባኝ ተከሳሹ በሌለበት የተሰጠውን ፍርድ ለማሻር ስለሚቀርበው ማመልከቻ

አምስተኛ መጽሐፍ
ስለ ይግባኝ ተከሳሹ በሌለበት የተሰጠውን ፍርድ ለማሻር
ስለሚቀርበው ማመልከቻ
፩ኛ አንቀጽ
ይግባኝ።

ቊ ፻፹፩። መሠረቱ።

(፩) የወንጀል ፍርድ ቤት በተከሳሹ  ላይ ጥፋተኛ መሆኑን በመፍረዱ ለጊዜው የመልቀቅ ወይም ነጻ የመለቀቁ ፍርድ በመሰጠቱ የሚቀርቡ ይግባኞች ሁሉ በዚህ መጽሐፍ በተመለከተው መሠረት ይፈጸማሊ።
(፪) ሁለተኛ ይግባኝ በቊ ፻፹፪ መሠረት ይቀርባል።

ቊ ፻፹፪። ይግባኝ ለማየት ሥልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች።

(፩) በሚሰጠው  ፍርድ ይግባኙ ከዚህ በሚቀጥው ደረጃ ይቀርባል።
(ሀ) ከወረዳው ፍርድ ቤት ወረዳው በሚገኝበት አውራጃ ግዛት ውስጥ ሥልጣኑ ለሆነው አውራጃ ፍርድ ቤት፤
(ለ) ከአውራጃ  ፍርድ ቤት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት፤
(ሐ) ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ለጠቅላይ ፤
(፪) በሚሰጠው ፍርድ  የሚቀርበው ሁለተኛው  ይግባኝ ለከፍተኛው ደረጃ ይቀርባል።
(ሀ) አውራጃ ፍርድ ቤት የሚቀርበው በይግባኝ ሰሚነት ያየው ይግባኝ ለጠቅላላ ንጉሠ ነገሥት ፍርድ ቤት።
(ለ) ከፍተኛው ፍርድ ቤት በይግባኝ ሰሚነት ያየው ይግባኝ ለጠላላ ንጉሠ ነገሥት ፍርድ ቤት።

ቊ ፻፹፫። ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ችሎት ስለሚቀርቡ ማመልከቻዎችን።

(፩) በቊ ፻፹፪ መሠረት የይግባኝ መብቱን የፈጸመ ባለጉዳይ ነገሩ  እንደገና እንዲታይለት ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ለማመልከት በቊ ፻፹፪ የተመለከተው አይከለክለውም።
(፩) ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ከሚቀርበው ማመልከቻ ጋራ
(ሀ) አመልካቹ ያልተስማማበትን ፍርድ ወይም ፍርዶችና
(ለ) አመልካች ነገሩ እንድ ገና እንዲታይለት የሚጠይቅበትን ምክንያት ባጭሩ የሚገልጽ የይግባኝ ማመልከቻ አያይዞ ማቅረብ አለበት።

ቊ ፻፹፬። የትእዛዝ ይግባኝ ስላለመኖሩ።

ከዚህ በታች ባሉት ሁኔታዎች ፍርድ ቤት በሚሰጠው ትእዛዝ ይግባኝ ለማለት አይቻልም።
(ሀ) በቊ ፺፬ መሠረት ቀጠሮ መስጠት ወይም አለመስጠት ወይም
(ለ) በቊ ፻፴፩ መሠረት ስለሚቀርብ መቃወሚያ ወይም
(መ) በቊ ፻፵፮ መሠረት ማስረጃን ስለ መቀበል ወይም ስላለመበል ነገር ግን የጥፋተኛነት ውሳኔ  በተሰጠበት ለጊዜው በመልቀቅ ወይም ነጻ በመልቀቅ ፍርድ ተሰጥቶ ይግባኝ በተባለበት ጊዜ እነዚህ የተሰጡት ትእዛዞቸ ይግባኝ ለማለት  ምክንያቶች ለመሆን ይችላሉ።

ቊ ፻፹፭። የጥፋተኛነት  ውሳኔ በተሰጠበት ወይም በቅጣቱ ይግባኝ ስለ ማለት፡፡

(፩) የተፈረደበት ሰው የጥፋተኛነት  ውሳኔ በተሰጠበትና በቅጣቱ ይግባኝ ማለት ይችላል።
ነገር ግን ተከሳሹ የተከሰሰበትን ወንጀል ያመነ ሆኖ በእምነቱ መሠረት ጥፋተኛነቱ ከተወሰነ በኋላ ስለ ቅጣቱ ልክ ወይም ቅጣቱ ሕጋዊ ላለመሆኑ ይግባኝ ማለት ይችላል እንጂ የጥፋተኛነት ውሳኔ በተሰጠበት ላይ ይግባኝ ማለት አይችልም።
(፪) ዐቃቤ ሕጉ ወይም የግል ከሳሹ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ለጊዜው በመልቀቅ ወይም ነጻ በመልቀቅ ፍርድ ላይ ወይም ቅጣቱ በቂ አይደለም በማለት ይግባኝ ማለት ይችላል።
(፫) አካለ መጠን ያለደረሰ ወጣት ወይም ችሎታ የሌለው ሰው ይግባኝ ሲል ይግባኙን የሚያቀርብለት እንደራሴው ነው።

ቊ ፻፹፮። ሰው ካሣ በሚጠይቅበት ነገር ይግባኝ ስለ ማለት።

(፩) በወንጀለኛው መቅጫ ሕግ ቊ ፻ መሠረት ፍርድ ቤቱ ካሣ ማግኘት አይገባውም ብሎ የፈረደ እንደ ሆነ፤ የተበደለው ወገን በውሳኔው ይግባኝ ለማለት ይችላል።
(፪) ፍርድ ቤቱ የተበደለው ሰው ካሣ መቀበል ይገባዋል ብሎ በፈረደ ጊዜ ተከሳሹ በውሳኔው ይግባኝ ማለት ይችላል።
(፫) በተፈረደው የካሣ ልክ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁ ፪ሺ ፻፶፫ መሠረት ይግባኝ ለማለት ይቻላል።
(፬) በዚህ ቁጥር መሠረት ይግባኝ ሲባል የጥፋተኛነት ውሳኔ በተሰጠበት ወይም በቅጣቱ ውሳኔ ይግባኝ ሲቀርብ ይግባኙን የሚሰማው የወንጀል ይግባኝ ፍርድ ቤት ነው፤ ነገር ግን የጥፋተኛ ውሳኔ  በተሰጠበት ወይም ስለ ቅጣቱ  ይግባኝ ባልተባለ ጊዜ ወይም ይግባኙ በተተወ ጊዜ የካሣውን ፍርድ ይግባኝ የፍትሐ ብሔር ይግባኝ ችሎት ይሰማል።

ቊ ፻፹፯። ይግባኝ ማለትን ስለ ማስታወቅና የይግባኝ ማመልከቻ

(፩) ይግባኝ ማለቱን ለማስታወቅ የሚጽፈውን ማመልከቻ ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው ይግባኝ የሚልበት ፍርድ በተሰጠ በአሥራ አምስት ቀን ውስጥ ማቅረብ አለበት።ይግባኝ ማለቱን ለማስታወቅ የጻፈው ማመልከቻ ለፍርድ ቤት መዝገብ ሹም (ለሬጂስትራሩ) ሲደርሰው ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ አስገልብጦ ለይግባኝ ባዩ ወይም ለጠበቃው ይሰጣል። ይግባኝ ባዩ በእስር ቤት ያለ እንደ ሆነ ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ ግልባጭ የፍርድ ቤት መዝገብ ሹም ለይግባኝ ባይ እንዲሰጥ ለወህኒ ቤቱ ሹም ይልካል። ፍርድ ተገልብጦ ያለቀበት ቀንና ኋላም ለይግባኝ ባዩ ወይም ለጠበቃው ወይም ለወህኒ ቤቱ ሹም የደረሰበትን ቀን የፍርድ ቤት መዝገብ ሹም በፊርማው ያረጋግጣል።
(፩) በ ቊ፻፹፱ መሠረት የሚቀርበው የይግባኝ ማመልከቻ የፍርድ ግልባጭ በደረሰው በሠላሳ ቀን ውስጥ ፍርድን ለሰጠው ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት መቅረብ አለበት።
(፫) ተከሳሹ በእስር ቤት የሆነ እንደ ሆነ የወህኒ ቤቱ ሹም ሳይዘገይ የይግባኙን ማመልከቻ ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ ለሰጠው ፍርድ ቤት መላክ አለበት።
(፬) የይግባኙ ማመልከቻ ግልባጭ ለመልስ ሰጪው እንዲደርሰው መደረግ አለበት።

ቊ ፻፹፰። ፍርድ እንዳይፈጸም ስለ ማገድ።

(፩) ጥፋተኛ ሆኖ የተፈረደበት ይግባኝ ባይ የይግባኝ ማስታወቂያ የሰጠ እንደ ሆነ ይግባኙ ሳይሰማ ወይም ይግባኙን ይግባኝ ባዩ ካልተወ በቀር የግርፋቱ ቅጣት አይፈጸምም፡፡
(፪) ተከሳሹ ይግባኙ እስኪወሰን ድረስ በዋስትና ወረቀት የተለቀቀ እንደ ሆነ፤ የእስራቱ ቅጣት የይግባኙ ፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ አይጀመርም፡፡
(፫) ይግባኝ የተባለበት ፍርድ ቤት እንዲፈጸሙ ለጥንቃቄ የሰጣቸው ትእዛዞች ይግባኝ የተባለባቸው ቢሆኑም መፈጸም አለባቸው፡፡
(፬) ስለ ካሣ ወይም ስለ ኪሣራ ወጪ የተሰጠ ፍርድ ከመፈጸም አይታገድም፡፡
(፭) ይግባኙ ከመሰማቱ በፊት በማንኛውም ጊዜ ወይም ይግባኙ በሚሰማበት በማንኛውም ጊዜ ፍርድ እንዲታገድ ለይግባኝ ፍርድ ቤት ማመልከት ይቻላል፡፡

ቍ ፻፹፱፡፡ በይግባኝ ማልከቻ ላይ ስለሚጻፈው፡፡

(፩) ይግባኝ ማመልከቻ ይግባኝ በተባለበት ፍርድ ላይ ያሉትን የመቃወሚያ ምክንያቶች ባጭሩ ለይቶ ዋና ዋናዎቹን ነገሮች በክርክር መልክ ሳይተቹ በተራ ቍጥር በዝርዝር መጻፍ አለባቸው፡፡ ከይግባኝ ማመልከቻው ጋራ ይግባኝ የተባለበት ፍርድ ግልባጭ መቅረብ አለበት፡፡ የይግባኙ ማመልከቻ ይግባኝ ባዩ እንዲወገድለት የሚጠየቀውን የፍርድ ልመናውን መግለጽ አለበት፡፡
(፪) የይግባኙን ማመልከቻ ይግባኝ ባዩ ራሱና ጠበቃ ያለው እንደ ሆነ፤ ጠበቃው ይፈርማሉ፡፡

ቍ ፻፺፡፡ ለይግባኝ ፍርድ ቤት ስለሚላኩ የይግባኝ ማመልከቻዎች መረጃዎችና (ኤግዚቢቶች) እና መዝገብ ፡፡

(፩) ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት የይግባኙ ማመልከቻ እንደ ደረሰው ካ፲፭ ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የመዝገቡን ግልባጭና የይግባኝ መዝገብ (ያለ እንደሆን) ይግባኝ እላለሁ ሲል ያስታወቀበትንም ከይግባኙ ማመልከቻ ጋራ መረጃዎችን ጭምር ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይልካል፡፡
(፪) መዝገቡን መገልበጥ የነገሩን በይግባኝ መታየት የሚያዘገየው ሲሆን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የመዝገቡ መገልበጥ እንዲቀርና ዋናው መዝገብ በትውስት እንዲቀርብለት ለማድረግ ይችላል፡፡

ቁ፡ ፻፺፩ የይግባኝ ጊዜ ካለፈ በኋላ ይግባኝ ለማቅረብ ፈቃድ ለማግኘት የሚቀርብ ማመልከቻ፡፡

(፩) ይግባኝ የተባለበትን ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት የይግባኙ ማስታወቂያ ወይም ማመልከቻ ጊዜው ካለፈ በኋላ የቀረበለት እንደ ሆነ፤ አልቀበልም ለማለት ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የይግባኙን ማስታወቂያ ወይም ማመልከቻ የሚያቀርበው ሰው የይግባኙ ጊዜ ካለፈ በኋላ ይግባኙን ለማቅረብ እንዲፈቀድለት ማመልከቻውን በጽሑፍ ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ያደርጋል፡፡
(፪) ማመልከቻውም የይግባኙ ጊዜ ካለፈ በኋላ ነገሩ ሊሰማ ይገባል የሚባልበትን ምክንያትና የዘገየበትን ምክንያት ገልጾ ማስረዳት አለበት፡፡
(፫) የይግባኝ ፍርድ ቤት የይግባኙ ጊዜ ያለፈው በአመልካቹ ጥፋት ባልሆነ ምክንያት ለመሆኑ ካልተረዳ በቀር ጊዜው ያለፈ ይግባኝ እንዲሰማ አይፈቀድም፡፡
(፬) ጊዜው ካለፈ በኋላ ይግባኙ እንዲሰማ የይግባኝ ፍርድ ቤት የወሰነ እንደ ሆነ፤ የይግባኙ ማመልከቻ የሚቀርብበትን ቀን ይወስናል፡፡

ቍ ፻፺፪፡፡ የነገሩ መሰማት፡፡

የይግባኙ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ ይግባኙ የሚሰማበትን ቀን ወስኖ ለነገረተኞቹ ይነገራቸዋል፡፡ ይግባኝ ባዩ ይግባኙን ማስረዳት ይጀምራል፤ መልስ ሰጪውም መልስ ይሰጣል፤ ይግባኝ ባዩ የመልስ መልስ የመስጠት መብት አለው፡፡

ቍ ፻፺፫፡፡ ከነገረተኞቹ አንዱ ወገን ይግባኙ በሚሰማበት ቀን ስላለመቅረቡ፡፡

(፩) ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው የይግባኙ ቀን ተነግሯቸው በተወሰነው ቀን ያልቀረቡ እንደ ሆነ፤ ይግባኙ ይሰረዛል፡፡ ነገር ግን ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ሳይቀርብ መቅረቱን ያረጋገጠ እንደ ሆነ ይግባኙ እንዲሰማ ማድረግ ይቻላል፡፡
(፪) መልስ ሰጪው ወይም ጠበቃው ያልቀረቡ እንደ ሆነ፤ በሌሉበት ነገሩ ይቀጥላል፡፡

ቍ ፻፺፬፡፡ ተጨማሪ ማስረጃ፡፡

(፩) የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይግባኝ በሚያይበት ጊዜ ተጨማሪ ማስረጃ የሚያስፈልግ መስሎ ከታየው አስፈላጊ መስሎ ሊታየው የቻለበትን ምክንያት በመዝገብ ጽፎ ማስረጃውን መቀበል ይችላል፡፡
(፪) በንኡስ ቍጥር (፩) መሠረት የሚቀርብ ማስረጃ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነገሩ በተሰማበት ጊዜ እንደ ቀረበ ዐይነት ሆኖ ይቆጠራል፡፡

ቍ ፻፺፭፡፡ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ሥልጣን፡፡

(፩) ይግባኙ በሚሰማበት ጊዜ በነገሩ ውስጥ ለመግባት በቂ ምክንያት የሌለ መስሎ ከታየው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይግባኙን ማሰናበት አለበት፡፡
(፪) በነገሩ ለመግባት በቂ ምክንያት ያለ በመሰለው ጊዜ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ከዚህ የሚቀጥሉትን ይፈጽማል፡፡
(ሀ) ተከሳሹን ነጻ በመልቀቅ ወይም ለጊዜው በመልቀቅ በተሰጠ ትእዛዝ ይግባኝ የተባለ ሲሆን፤ ትእዛዙን ሰርዞ ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት ነገሩን እንደ ገና እንዲያይ ማዘዝ ወይም ጥፋተኛ ነው ብሎ እንደ ሕጉ ፍርድ ቤት ሊፈርድበት ይችላል፤ ወይም
(ለ) ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔ በቅጣቱ ይግባኝ በተባለ ጊዜ
(፩) ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔና ቅጣቱን ሰርዞ ተከሳሹን በነጻ ለመልቀቅ ይችላል፤ ወይም
(፪) ፍርዱን ለውጦ ወይም ሳይለውጥ ቅጣቱን ያጸናል፤ ይጨምራል፤ ወይም ይቀንሳል፡፡
(ሐ) ጥፋተኛ ነው በተባለበት ውሳኔ ላይ ብቻ ይግባኝ በተባለ ጊዝ ፍርዱንና ቅጣቱን ሰርዞ ተከሳሹን በነጻ ለመልቀቅ ይችላል፡፡
(መ) በቅጣቱ ላይ ብቻ ይግባኝ በተባለ ጊዜ ቅጣቱን ያጸናል፤ ይጨምራል፤ ወይም ይቀንሳል፡፡
(፫) የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔ አጽንቶ ቅጣቱን የለወጠ እንደ ሆነ ወይም ቅጣቱን አጽንቶ ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔ የለወጠ እንደ ሆነ ጥፋተኛ ነው በተባለበት ወይም ቅጣቱ እንዲለወጥ በተወሰነው ላይ ብቻ ሁለተኛ ጊዜ ይግባኝ ለማለት ይቻላል፡፡

ቍ ፻፺፮፡፡ የተፈረባቸው ብዙ ሰዎች ሆነው አንዱ ብቻ ይግባኝ ሲያቀርብ፡፡

(፩) ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የቀረበው ይግባኝ ስለ ተፈረደባቸው ብዙ ሰዎች የሚመለከት ሆኖ ይግባኝ ያለው ግን የተፈረደበት አንድ ሰው ብቻ በሆነ ጊዜ፤ ከዚህ በታች እንደተመለከተው ሲሆን፤ የይግባኙ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ፍርድ ይግባኝ ላሉትም ሰዎች ይግባኝ እንዳሉ ተቆጥሮ ይፈጸምላቸዋል ለማለት የሚችለው፤
(ሀ) በይግባኝ የተሰጠው ፍርድ ለይግባኝ ባዩ የሚጠቅም በሆነ ጊዜና
(ለ) ተከሳሾቹ ይግባኝ ቢሉ ኖሮ በፍርዱ እነሱም ሊጠቀሙ ይችሉ ነበር የሚያሰኝ ሲሆን ነው፡፡
(፪) ፍርዱ በይግባኝ ባዩ ላይ ጉዳት የሚያመጣበት እንደ ሆነ ይግባኝ ባላሉ ሰዎች ላይ አይፈጸምም፡፡