ስለ እንደራሴነት፡፡ | GOALGOOLE | Because you need Information for your goals !
7023 Bole Kifle Ketema, Addis Ababa, Ethiopia
0116616179/85 mcc@ethionet.et

ስለ እንደራሴነት፡፡

አንቀጽ ፲፬፡፡
ስለ እንደራሴነት፡፡
ምዕራፍ ፩፡፡
ጠቅላላ ድንጋጌዎች፡፡

ቊ ፪ሺ፻፸፱፡፡ የእንደራሴነት ምንጭ፡፡

የሌላ ሰው እንደራሴ በመሆን ሥራዎችን የመፈጸም ሥልጣን የሚገኘው ከሕግ ወይም ከውል ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፻፹፡፡ ስለ ሥልጣን ፎርም፡፡

ስለ ውሉ አፈጻጸም፤ ሕጉ አንድ ዐይነት ፎርም እንዲደረግ ያስገደደ እንደሆነ ውሉን የሚፈጽምበት ሥልጣን በዚሁ ዐይነት ፎርም ለወኪሉ መስጠት አለበት፡፡

ቊ ፪ሺ፻፹፩፡፡ ስለ ሥልጣን ወሰን፡፡

(፩) የእንደራሴነት ሥልጣን የተገኘው በውል መሠረት የሆነ እንደሆነ፤ ሥልጣኑ የሚወሰነው በተዋዋዮቹ ስምምነት ነው፡፡
(፪) እንደራሴው የተሰጠውን ሥልጣን ሦስተኛ ወገን ለሆነ ሰው አስታውቆ እንደሆነ፤ በሦስተኛው ሰው ላይ ሥልጣኑ የሚጸናው፤ ባስታወቀው ማስታወቂያ መሠረት ነው፡፡
(፫) የእንደራሴነት ሥልጣን የሚተረጐመው ሳይስፋፋ በጠባቡ ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፻፹፪፡፡ ስለ ሥልጣኑ መቅረት፡፡

(፩) ተቃራኒ የሆነ ውል ከሌለ በቀር፤ እንደራሴው ወይም ሿሚው መሞቱ ወይም የሌለ መሆኑ ወይም ችሎታ የሌለው መሆኑ ወይም ደግሞ መክሠሩ የተገለጸ እንደሆነ ከአንድ ጽሑፍ የተገኘው ሥልጣን ይቀራል፡፡
(፪) እንዲሁም የሰውነት መብት የተሰጠው ድርጅት መኖሩ ሲቀር ይህ ሥልጣን ይቀራል፡፡

ቊ ፪ሺ፻፹፫፡፡ ሥልጣንን ስለ መውሰድ፡፡

(፩) እንደራሴ ሿሚው በማንኛውም ጊዜ በእሱ ስም ሆኖ እንዲሠራ በሦስተኛ ወገን ሰዎች ፊት ለእንደራሴው የሰጠውን ሥልጣን ሊቀንስበት ወይም ጨርሶ ሊያስቀርበት ይችላል፡፡
(፪) ይህን መብት የሚያስቀር በውሉ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ ፈራሽ ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፻፹፬፡፡ እንደራሴነትን ስለ መመለስ፡፡

(፩) ሥልጣኑን የሚያረጋግጥ ጽሑፍ የተሰጠው እንደራሴ በተሰጠው ሥልጣን የሚሠራበት ጊዜ ሲፈጸም፤ ይህን የተሰጠውን የሥልጣን ጽሑፍ ለሿሚው መመለስ አለበት፡፡
(፪) እንደራሴው ሒሳቡ ሳይጣራና የሚገባኝን ሿሚው ሳይሰጠኝ የተሰጠኝን ሥልጣን ይዤ እቈያለሁ ለማለት አይፈቀድለትም፡፡

ቊ ፪ሺ፻፹፭፡፡ የእንደራሴነቱ ጽሑፍ ስለ መጥፋት፡፡

እንደራሴው የሹመቱ ወረቀት መጥፋቱን ያስታወቀ እንደሆነ ሿሚው በእንደራሴው ኪሣራ ከፍርድ ቤቱ የእንደራሴነቱን መሰረዝ የሚገልጽ ውሳኔ ለማግኘት ይችላል፡፡

ቊ ፪ሺ፻፹፮፡፡ ሥልጣንን ስለ ማረጋገጥ፡፡

ከአንድ እንደራሴ ጋራ ሕጋዊ ተግባር የፈጸመ የሦስተኛ ወገን ሁል ጊዜ እንደራሴው ሥልጣኑን  እንዲያረጋግጥለት ሊያስገድድና እንደዚሁም የእንደራሴነቱ ተግባር በጽሑፍ የተደረገ እንደሆነ፤ እንደራሴው ስለዚሁ ተግባር በሚገባ የፈረመበትን ግልባጭ እንዲሰጠው ለማስገደድ ይችላል፡፡

ቊ ፪ሺ፻፹፯፡፡ ተቃዋሚ ጥቅሞች፡፡

(፩) እንደራሴው በፈጸመው ውል ምክንያት የሿሚውና የእንደራሴው ጥቅሞች የሚቃወሙ የሆኑ እንደሆነ ይህን ውል የፈረመው 3ኛ ወገን ይህን ሁኔታ የወቀና ሊያውቀውም የሚገባ የሆነ እንደሆነ በሿሚው ጥያቄ መሠረት ይህ የተፈጸመው ውል ሊፈርስ ይችላል፡፡
(፪) ሿሚው የዚሁኑ አካባቢ ሁኔታ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ውሉን ለማፍረስ አሳቡን ማስታወቅ አለበት፡፡
(፫) አንደኛው ወገን ተዋዋይ ይህን ማስታወቂያ ከተቀበለ ወዲህ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ውሉን የመቀጠል አሳቡን ያልገለጠ እንደሆነ ውሉ ይፈርሳል፡፡

ቊ ፪ሺ፻፹፰፡፡ ከገዛ ራስ ጋራ ስለሚደረግ ውል፡፡

(፩) እንደራሴው ለራሱ ጒዳይ በመሥራትም ሆነ ወይም በሌላ ሰው ስም ለሌላ ሰው ጒዳይ በመሥራት ውሉን ከራሱ ጋራ ባደረገ ጊዜ ሿሚው ይህ ውል እንዲፈርስ ለመጠየቅ ይችላል፡፡
(፪) ከዚህ በላይ በተጻፈው ቊጥር በ2ና በ3 ንኡስ ቊጥሮች የተሰጡ ውሳኔዎች ለዚህም ተፈጻሚነት አላቸው፡፡
(፫) ስለ ኮሚሲዮኔሮች የተሠሩ ልዩ ድንጋጌዎች የተጠበቁ ናቸው፡፡ (ቊ)

ቊ ፪ሺ፻፹፱፡፡ ፍጹም ስለሆነ እንደራሴነት፡፡

(፩) እንደራሴው ከወኪልነቱ ሥልጣን ወሰን ሳያልፍ በሌላ ሰው ስም የመዋዋል ተግባሮችን የፈጸመ እንደሆነ፤ እነዚህ በርሱ የተፈጸሙት ተግባሮች በቀጥታ በሿሚው እንደተፈጸሙ ሆነው ይቈጠራሉ፡፡
(፪) ነገር ግን ውሉ በተደረገበት ጊዜ በእንደራሴው ፈቃድ ላይ የተፈጸሙትን ጒድለቶች ሿሚው ለራሱ ጥቅም ጠቅሶ ሊከራከርባቸው ይችላል፡፡
(፫) ከእንደራሴው ጋራ የውል ስምምነት ያደረገ ሰው እንደራሴው ባደረሰበት የማሳሳት ጉዳት ሿሚውን ሊከራከረው ይችላል፡፡

ቊ ፪ሺ፻፺፡፡ የሥልጣን ወሰን ስለ ማለፍ፤ ወይም ቀሪ ስለሆነ ሥልጣን፡፡

(፩) እንደራሴው የሥልጣኑን ወሰን በመተላለፍ በሌላ ሰው ስም የሠራ እንደሆነ፤ በስሙ የተሠራለት ሰው ራሱ እንደ ፈቀደ እንደራሴው የፈጸመውን ተግባር ለማጽደቅ ወይም ለማፍረስ ይችላል፡፡
(፪) እንደዚሁም እንደራሴው ቀሪ በሆነው ሥልጣን መሠረት በሌላ ሰው ስም በሠራ ጊዜ በስሙ የተሠራለት ሰው እንደ ፈቀደ በስሙ የተሠራውን ሥራ ለማጽደቅ ወይም ለመሻር ይችላል፡፡

ቊ ፪ሺ፻፺፩፡፡ ለሿሚ ስለ ተሰጠው ምርጫ፡፡

(፩) ከእንደራሴው ጋራ የተዋዋሉ ሦስተኛ ወገኖች ሿሚው በስሙ የተሠራለትን ሥራ ለማጽደቅ ወይም ለማፍረስ የቈረጠውን ውሳኔ በፍጥነት እንዲያስታውቃቸው ለማስገደድ ይችላሉ፡፡
(፪) ሿሚው የመቀበሉን ውሳኔ በፍጥነት ሳያስታውቃቸው የቀረ እንደሆነ፤ እንደራሴው የሠራውን ሥራ እንዳልተቀበለው ይቈጠራል፡፡

ቊ ፪ሺ፻፺፪፡፡ የመቀበሉ ውጤት፡፡

ሿሚው እንደራሴው የፈጸመውን ተግባር ያጸደቀ እንደሆነ፤ እንደራሴው የፈጸመውን ተግባር ከውክልናው ሥልጣን ሳያልፍ እንደ ፈጸመው ይቈጠራል፡፡

ቊ ፪ሺ፻፺፫፡፡ ያለመቀበል የሚያስከትለው ውጤት፡፡

(፩) እንደራሴው የሠራውን ሥራ ሿሚው ባልተቀበለው ጊዜ በዚህ ሕግ ስለ ውሎች በጠቅላላው በሚለው አንቀጽ በተለከተው መሠረት ስለ ውሎች መሰረዝና መፍረስ የተነገሩት ድንጋጌዎች ተፈጻሚዎች ይሆናሉ፡፡
(፪) ከእንደራሴው ጋራ የስምምነቱን ተግባር የፈጸመው ሦስተኛ ወገን የእንደራሴነትን ሥልጣን መኖሩን በቅን ልቡና በማመኑ ስለ ደረሰበት ጉዳት ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ቊጥሮች ድንጋጌ መሠረት ካሣ እንዲከፈለው ለመጠየቅ ይችላል፡፡

ቊ ፪ሺ፻፺፬፡፡ ስለሚደርሱት አላፊነቶች፡፡

(፩) ስለ ደረሰው ጉዳት ኪሣራ እንዲከፍል መጠየቅ የሚገባው እንደራሴው ነው፡፡
(፪) ስለሆነም፤ የእንደራሴነቱን ሥልጣን የሚያስቀረውን ምክንያት ባለማወቅ በቅን ልቡና ሠርቶት እንደሆነ፤ በአላፊነት አይጠየቅም፡፡
(፫) እንደዚህም በሆነ ጊዜ ስለ ደረሰው ጉዳት ኪሣራ እንዲከፍል የሚጠየቀው ሿሚው ነው፡፡

 ቊ ፪ሺ፻፺፭፡፡ (፩) ስለ ሿሚው አላፊነት፡፡

በሌላው በኩል በሚደርሰው ጉዳት ሁሉ ሿሚው ከእንደራሴው ጋራ በሙሉ አላፊ የሚሆነው፤
(ሀ) ሿሚው ለሌላ ሦስተኛ ወገን የእንደራሴነቱን ሥልጣን አስታውቆ ሳለ፤ የሰጠውን የእንደራሴነት ሥልጣን በሙሉ ወይም በከፊሉ መሰረዙን ለዚያው ለሦስተኛ ወገን ያላስታወቀ እንደሆነ፤
(ለ) ሿሚው ለእንደራሴው የሰውን የእንደራሴነት ሥልጣን ጽሑፍ እንዲመልስለት እንደራሴውን ከማስገደድ ችላ ያለ እንደሆነና እንዲሁም ይህ ሿሚው የሰጠው የእንደራሴነት ሥልጣን ጽሑፍ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሰረዝ ያላደረገ እንደሆነ፤
(ሐ) በማናቸውም ሌላ አኳኋን ሿሚው በሚሰጣቸው መግለጫዎች ወይም በሥራው ወይም በአመራሩ ወይም ሊያደርግ የሚገባውን ባማድረጉ ከእንደራሴው ጋራ ስምምነት የሚያደርጉት ሦስተኛ ወገኖች እንደራሴው ይህ ሥልጣን ያለው መስሎዋቸው ስሕተት ያደረሰባቸው እንደሆነ ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፻፺፮፡፡ ከአላፊነት ውጭ ስለ መሆን፡፡

(፩) ከእንደራሴው ጋራ የተዋዋለው ሌላ ሦስተኛ ወገን ከመዋዋሉ በፊት የእንደራሴነቱን ሥልጣን ጽሑፍ ዐውቆ የተዋዋለ ከሆነ፤ በነገሩ የማታለል ሥራ ከሌለበት በቀር ከሥልጣኑ አልፎ የሠራውን እንደራሴ ማንኛውንም ኪሣራ ሊጠይቀው አይችልም፡፡
(፪) እንዲሁም ሦስተኛው ወገን የሚዋዋለው ማንም ቢሆን ግድ የሌለው ከሆነና እንደራሴውም ለሌላ ሰው የተፈጸመውን ውል በራሱ ስም ለማድረግ የተቀበለ እንደሆነ ሦስተኛው ወገን ማንኛውንም ኪሣራ ለመጠየቅ አይችልም፡፡

ቊ ፪ሺ፻፺፯፡፡ እንደራሴው በራሱ ስም ስለሚፈጽመው ተግባር፡፡

(፩) እንደራሴው በራሱ ስም የተዋዋለ እንደሆነ፤ ሌሎች ሦስተኛ ወገኖች ከእንደራሴው ጋራ መዋዋላቸውን ቢያውቁትም እንኳ፤ ከነዚህ ጋራ የፈጸማቸው ተግባሮች ለሚያስከትሉዋቸው ግዴታዎችና መብቶች እሱ ራሱ ባለቤት ይሆናል፡፡
(፪) እንዲህ በሆነ ጊዜ የተባሉ ሦስተኛ ወገኖች ከሿሚው ጋራ አንዳችም ቀጥታ ግንኙነት የላቸውም፤ ነገር ግን በእንደራሴው ስም ሆነው የእንደራሴውን መብት ከሿሚው ለመጠየቅ ይችላሉ፡፡

ቊ ፪ሺ፻፺፰፡፡ ስለ ሿሚው መብቶች፡፡

(፩) ሌሎች ሦስተኛ ወገኖች በቅን ልቡና ያገኙዋቸው መብቶች እንደተጠበቁ ሆነው እንደራሴው ለሿሚው ሲል በራሱ ስም ያፈራቸውን ተንቀሳቃሽ ንብረቶች፤ ሿሚው ገንዘቦቼ ናቸው ብሎ ለመጠየቅ ይችላል፡፡
(፪) እንደዚሁም እንደራሴው ለሿሚው ሲል ያገኛቸውን የገንዘብ መብቶች ሿሚው በእንደራሴው ተተክቶ ሊጠይቅ ይችላል፡፡
(፫) ስለሆነም፤ ሿሚው በበኩሉ በእንደራሴው ዘንድ ያሉበትን ግዴታዎች ፈጽሞ ካልተገኘ በቀር እነዚህን መብቶች ለመጠየቅ አይችልም፡፡

ምዕራፍ ፪፡፡
ስለ ወኪልነት፡፡

ቊ ፪ሺ፻፺፱፡፡ ትርጓሜ፡፡

ውክልና ማለት ተወካይ የተባለ አንድ ሰው ወካይ ለተባለው ሰው እንደራሴ ሆኖ አንድ ወይም ብዙ ሕጋዊ ሥራዎች በወካዩ ስም ለማከናወን ግዴታ የሚገባበት ውል ማለት ነው፡፡

ክፍል ፩፡፡
የወኪልነት ሥልጣን አቋቋምና የሥራው ግብ፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፡፡ የውክልና ፎርም፡፡

(፩) ውክልና በግልጽ ወይም በዝምታ ሊሰጥ ይችላል፡፡
(፪) ቢሆንም ተወካዩ ሊፈጽመው የሚገባው የሥራ ተግባር፤ ስለ አፈጻጸሙ በአንዳንድ ሕጋዊ ፎርም ውስጥ እንዲገባ የሚያስፈልገው ሲሆን ውክልናው ለተወካዩ ሊሰጠው የሚገባው ይኸው ሕግ በሚያዝዘው ፎርም መሠረት ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፩፡፡ ውክልናን ስለ መቀበል፡፡

(፩) ውክልናን የመቀበል ጒዳይ በግልጽ ወይም በዝምታ ሊፈጸም ይችላል፡፡
(፪) ተወካዩ ወኪል የሚሆንበት ነገር ከሚያካሂደው ሥራ ጋራ ግንኙነት ያለው ጒዳይ መሆኑ በግልጽ የታወቀ ከሆነ፤ ወይም ከሞያ ሥራው አመራር ጋር የሚመሳሰል ጒዳይ ከሆነ፤ ወይም ይህንን የመሰለውን ጒዳይ ለመሥራት ፈቃደኛ ለመሆኑ በአደባባይ ገልጾ አሳብ በማቅረብ አስታውቆ እንደሆኘ፤ ውክልናውን የማይቀበል ለመሆኑ ወዲያውኑ ካልገለጸ በቀር እንደተቀበለ ይቈጠራል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፪፡፡ የውክልናው ወሰን፡፡

(፩) የውክልናው ወሰን በውሉ ላይ በግልጽ ተጠቅሶ ካልተመለከተ በቀር ለውክልናው የሚሰጠው ወሰን እንደ ጒዳዩ ዐይነት ነው፡፡
(፪) ውክልናው ለአንድ ልዩ ጒዳይ ወይም ለየአንዳንዱ ጒዳዮች ወይም ለወካዩ ጒዳዮች ሁሉ ጠቅላላ ውክልና ሊሆን ይችላል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፫፡፡ ጠቅላላ ውክልና፡፡

በጠቅላላ አነጋገር የተደረገ ውክልና ለተወካዩ የአስተዳደርን ሥራ እንዲፈጽም ከሚያደርገው በቀር ሌላ ሥልጣን አይሰጠውም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፬፡፡ የአስተዳደር ሥራ፡

(፩) የወካዩን ሀብት የማስቀመጥ የመጠበቅ ከሦስት ዓመት ለማያልፍ ዘመን የማከራየት፤ በብድር የተሰጠውን ሀብት የመሰብሰብ፤ ከሀብቱ የሚመጣውን ገቢ ተቀብሎ የማስቀመጥና ለተከፈሉ ዕዳዎች ደረሰኝ የመስጠት ሥራዎች ሁሉ እንደ አስተዳደር ሥራ ይቈጠራሉ፡፡
(፪) እንዲሁም የሰብልን መሸጥ፤ ለሽያጭ የተመደቡ የንግድ ዕቃዎችን ወይም ይበላሻሉ ተብለው የሚታሰቡ ነገሮችን የመሸጥ ሥራ እንደ አስተዳደር የሥራ አፈጻጸም የሚቈጠር ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፭፡፡ ልዩ ውክልና፡፡

(፩) ተወካዩ ከአስተዳደር ሥራ በቀር ሌላ ሥራ ለመሥራት የሚያስፈልግ ሲሆን ልዩ ውክልና እንዲኖረው አስፈላጊ ነው፡፡
(፪) ተወካዩ ልዩ የውክልና ሥልጣን ከሌለው በቀር፤ ይልቁንም የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን መሸጥ ወይም አሲዞ መበደር ካፒታሎችን በአንድ ማኀበር ዘንድ ለማግባት የለውጥ ግዴታን ውል መፈራረም መታረቅ ለመታረቅ ውል መግባት ስጦታ ማድረግና በአንድ ጒዳይ በፍርድ ቤት ቀርቦ መከራከር አይችልም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፮፡፡ ልዩ ውክልና የተሰጠው ሰው ሥልጣን፡፡

(፩) ልዩ ውክልናው በላዩ ተዘርዝረው የተመለከቱትን ጒዳዮችና የነዚሁ ተከታታይና ተመሳሳይ የሆነውን እንደ ጒዳዩ ዐይነትና እንደ ልማድ አሠራር አስፈላጊ የሆነውን ከማከናወን በቀር ለተወካዩ ሌላ ሥልጣን አይሰጠውም፡፡
(፪) ተወካዩ ከተሰጠው የውክልና ሥልጣን ውጭ አልፎ የፈጸመውን የሥራ ተግባር ወካዩ ካላጸደቀው ወይም በሥራ አመራር መሠረታዊ ደንብ ካልሆነ በቀር ወካዩን አስገድደውም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፯፡፡ የማጽደቅ ግዴታ፡፡

(፩) ተወካዩ በውክልናው ከተሰጠው ሥልጣንና ወካዩ ከሰጠው ትእዛዝ ውጭ በማለፍ ሠርቶ የተገኘ እንደሆነ ተወካዩ የሠራው በቅን ልቡና ሆኖ ሲገኝ ሥራውን ወካዩ እንዲያጸድቅለት ይገደዳል፡፡
(፪) ወካዩ የሥራውን አረማመድና መልካም አካሄድ ሁኔታ ቢረዳው ኖሮ ለተወካዩ የሥራውን የሥልጣን ወሰን ማስፋት የሚያስፈልግ መሆኑን መገመት ይችል ነበር ተብሎ በአእምሮ ግምት የሚታመን ሆኖ ሲገኝም አፈጻጸሙ በዚሁ ዐይነት ነው፡፡
(፫) ተወካዩ ያልተፈቀደለትን ሥራ በገዛ አሳቡ ከመፈጸሙ አስቀድሞ የሥልጣኑን ወሰን እንዲያሰፋለት ወካዩን ለመጠየቅ የሚያስችለው ምቹ መንገድ እያለው ፈቃድ ሳይጠይቅ ቸል ብሎ በራሱ አሳብ ሠርቶ እንደሆነ፤ ወይም አስፈላጊ ተግባሩን ከፈጸመ በኋላ ለወካዩ ሳያስታውቀው ቀርቶ እንደሆነ ያለ ፈቃድ የፈጸምኩትን አጽናልኝ ብሎ ወካዩን የመጠየቅ መብት አይኖረውም፡፡

ክፍል ፪፡፡
የተወካዩ ግዴታዎች፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፰፡፡ ጥብቅ የሆነ ቅን ልቡና፡፡

(፩) ተወካዩ ከወካዩ ጋራ በሚያስተሳስረው ግንኙነት ውስጥ ጥብቅ የሆነ ቅን ልቡና ሊኖረው ይገባል፡፡
(፪) የውክልናውን ሥልጣን የሚያስቀሩትን ምክንያቶችና ወይም የቃላቸውን አነጋገር ማሻሻል አስፈላጊ የሚሆንበትን ምክንያት ለወካዩ አሳብ ማቅረብና ማስታወቅ አለበት፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፱፡፡ አፈጻጸሙ፡፡

(፩) ተወካዩ ሥራውን የሚፈጽመው በተለይ ለወካዩ ጥቅም ሊሰጥ በሚችልበት መንገድ ብቻ ነው፤ ስለዚሁም በወኪልነቱ ምክንያት በሚሠራው ሥራ ወካዩ ሳያውቅ አንዳችም ጥቅም ለግሉ መውሰድ አይችልም፡፡
(፪) ተወካዩ በውክልናው ምክንያት ያገኛቸውን መረጃዎች፤ የወካዩን ጥቅም በሚጎዳ ሁኔታ ሊሠራባቸው አይችልም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፲፡፡ የውክልናው ሒሳብ አያያዝ፡፡

(፩) ተወካዩ በውክልና ሥራው ምክንያት ገቢ ላደረገው ገንዘብና በሥራውም ላገኘው ትርፍ ሁሉ ያገኘው ገንዘብ ሁሉ ለወካዩ የማይገባው እንኳ ቢሆን ስለ ሒሳብ አያያዝ ሥራ ለወካዩ አላፊ ይሆናል፡፡
(፪) ተወካዩ ለወካዩ ሊከፍል የሚገባውን ገንዘብ ለራሱ ጥቅም አውሎት እንደሆነ፤ ገንዘቡን ከወሰደበት ቀን አንሥቶ አንድም ማስጠንቀቂያ ሳያስፈልግ እስከ ወለዱ ለወካዩ ሊከፍለው ይገባል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፲፩፡፡ አስፈላጊ ትጋት፡፡

(፩) ተወካዩ በውክልና ሥራው ላይ በሚገኝባቸው ጊዜዎች ሁሉ በውክልናው የተሰጠውን አደራ፤ አንድ መልካም የቤተሰብ አባት ቤተሰቡን ለመጠበቅ እንደሚያደርገው ሁሉ በትጋትና በጥንቃቄ መጠበቅ አለበት፡፡
(፪) በአላፊነት የሚጠየቀው የማታለል በሠራው ሥራ ብቻ ሳይሆን በሥራው አመራር በሚያደርጋቸው ጥፋቶችም ጭምር ነው፡፡
(፫) የውክልናው ሥልጣን የተሰጠው በነፃ እንደሆነ የወካዩን ጒዳዮች እንደራሱ ጒዳይ አድርጎ ተጠንቅቆ ከሠራ በአላፊነት ሊያስጠይቀው አይችልም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፲፪፡፡ ዋቢነት የሌለው ጒዳይ፡፡

(፩) በውላቸው ውስጥ ተቃዋሚ የሆነ ስምምነት የሚገኝበት ካልሆነ በቀር፤ ተወካዩ በራሱ ስም ሆኖ ቢሠራም ከሌላው ጋራ ላደረገው ውል አፈጻጸም ጒዳይ በራሱ ስም አላፊነት ሊጠየቅ አይገባውም፡፡
(፪) ውሉን በፈጸመበት ጊዜ የተዋዋለው ሰው እንደ ውሉ ቃል ለመፈጸም የማይችልና በገባበት ግዴታ መሠረት ገንዘቡን የማይከፍል መሆኑን የሚያውቅ ወይም ማወቅ የሚገባው የሆነ እንደሆነ አፈጻጸሙ ከዚህ በላይ ከተጻፈው የተለየ ይሆናል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፲፫፡፡ የሒሳብ ማቅረብ ግዴታ ፡፡

(፩) ተወካዩ ወካዩ በጠየቀው ጊዜ የሥራውን አካሄድ መግለጫና ሒሳብ በየጊዜው የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡
(፪) የተሰጠውን የውክልና ሥራ መፈጸሙን ያለመዘግየት ለወካዩ ማስታወቅ ይገባል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፲፬፡፡ የሥራውን አመራር ተግባር ስለ ማጽደቅ፡፡

(፩) ተወካዩ ያቀረበው የሥራ አካሄድ መግለጫ ለወካዩ ደርሶት የጒዳዩ ዐይነትና ልማዳዊው ደንብ ለመልስ መስጫ የሚበቃ ጊዜ እስከሚፈቅድለት ቀን ድረስ፤ (በቀረበለት መግለጫ መሠረት የሚፈቅድ ወይም የማይፈቅድ መሆኑን) መልስ ሳይሰጠው ከተወሰነው የበለጠ ጊዜ በዝምታ ያሳለፈው እንደሆነ ተወካዩ የያዘውን የሥራ አካሄድ ዘዴ ወካዩ ፈቅዶ እንደተቀበለው ያስቈጥረዋል፡፡
(፪) ተወካዩ ወካይ ከሰጠው ትእዛዝ አልፎ ሠርቶ እንደሆነና በውክልናው ከተሰጠው ሥልጣን በላይም ሠርቶ እንደሆነ፤ ለወካዩ ላቀረበው መግለጫ ተቃዋሚ ወይም አጽዳቂ መልስ ካልተሰጠው አፈጻጸሙ ከላይ በተመለከተው ዐይነት ይሆናል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፲፭፡፡ በተወካይ ስለ መተካት፡፡ (፩) የሚቻልበት ሁኔታ፡፡

(፩) ከውክልናው ሥልጣን ውጭ የሆነውን ሌላ ሰው በራሱ ምትክ አድርጎ እንዲያሠራ ወካዩ ካልፈቀደለት በቀር፤ ተወካዩ የተወከለበትን ሥራ እሱ ራሱ መፈጸም አለበት፡፡
(፪) የተወካዩ በሥራው ላይ መገኘት ወይም ሌላ ሰው መተካቱ እንደ ልማዳዊው ሕግ ለወካዩ እኩል ሆኖ የሚታየው ከሆነ ተወካዩ ሌላ ሰው ተተክቶ ሥራውን እንዲያሠራ እንደ ተፈቀደለት ያህል ይቈጠራል፡፡
(፫) ተወካዩ በውክልናው የተሰጠውን የሥራ ጒዳይ ራሱ እንዳያካሂደው ድንገተኛ መሰናክል የገጠመው እንደሆነና የወካዩም ሥራ መልካም አመራር ጒዳይ የሚያስገድደው ሆኖ የተገኘ እንደሆነ፤ ይህንንም ከማድረጉ በፊት ለወካዩ ለማስታወቅና ለማስፈቀድ ጊዜ የሚያጥረው የሆነ እንደሆነ ሌላ ሰው ተክቶ ሥራውን ማሠራት አለበት፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፲፮፡፡ (፪) የተወካዩ አላፊነት፡፡

(፩) ተወካዩ በማይገባ በሥራው ላይ ተክቶ ያሠራው ሰው በሚያደርገው ሥራ ሁሉ፤ እሱ ራሱ እንደ ሠራው ያህል ተቈጥሮ በአላፊነት ይጠየቃል፡፡
(፪) በሥራው ላይ ሌላ ሰው እንዲተካና እንዲያሠራ በሚገባ ተፈቅዶለት እንደሆነ ግን፤ በአላፊነት የሚጠየቀው ተተኪውን በመምረጥ ላይ ጥንቃቄ ባላደረገበት ጒዳይና ለተተኪውም የሰጠው የሥራ መሪ ትእዛዝ የሚያስከትለውን ጒድለት በሚመለከተው ነገር ብቻ ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፲፯፡፡ (፫) በወካዩና በተተኪው ተወካይ መካከል ያሉ ግንኙነቶች፡፡

(፩) በወካዩና ተተኪው ተወካይ መካከል ያሉት ግንኙነቶች የሚወሰኑት ተተኪው ወኪል ዋናው ወኪል በሌላ ሦስተኛ ሰው ለመተካት መብት ያለው እንደሆነ ያህል በሚገባ ያመነ ሲሆን ተተኪው ወኪል ይህን ሥልጣን ያገኘው በቀጥታ ከወካዩ ላይ እንደሆነ ያህል በመቊጠር ነው፡፡
(፪) እንዲህ ባልሆነ ጊዜ ግን ጒዳዩ የሚወሰነው ስለ ሥራ አመራር በተነገረው ድንጋጌ መሠረት ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፲፰፡፡ ስለ ብዙ ወኪሎች፡፡

(፩) ተቃራኒ የሆነ ስምምነት ከሌለ በቀር፤ በአንድ ዐይነት ውል ላይ ብዙ ሰዎች ተወክለው እንደሆነ፤ ይህን የውክልና ሥልጣን ሁሉም በአንድነት መቀበላቸው ካልተረጋገጠ በቀር ውክልናው እንደ ጸና አይቈጠርም፡፡
(፪) እንዲሁም ተቃራኒ የሆነ ስምምነት ከሌለ በቀር በአንድ ውል ብዙ ሰዎች ተወክለው እንደሆነ፤ የሠሩዋቸው ሥራዎች ወካዩን ሊያስገድዱት የሚችሉት ተወካዮቹ ሁሉ አብረው ሠርተው ሲገኙ ነው፡፡

ክፍል ፫፡፡
ስለ ወካዩ ግዴታዎች

ቊ ፪ሺ፪፻፲፱፡፡ በውል ስምምነት መሠረት ስለሚከፈል የድካም ዋጋ፡፡

(፩) ተወካዩ በውሉ ላይ ታስቦ የተመለከተውን የድካም ዋጋ የመቀበል መብት አለው፡፡
(፪) በውሉ ላይ የተመለከተው የድካም ዋጋ ከመጠን ያለፈ ሆኖ ያገኙት እንደሆነና ተወካዩም ከሰጠው የአገልግሎት ፍሬ የበለጠ ሆኖ የመገቱት እንደሆነ፤ ዳኞች በውሉ ላይ ከተመለከተው የድካም ዋጋ ላይ በመጠኑ ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፳፡፡ በውል ያልተወሰነ የድካም ዋጋ፡፡

(፩) ስለ ድካሙ ዋጋ ሊከፈለው የሚገባው ነገር በውል ላይ ያልተመለከተ እንደሆነ፤ የሥራውን ተግባር በውክልናው የፈጸመው በሞያ ሥራው ውስጥ በተመለከተ በግል ሥራው ካልሆነና እንደ ልማዳዊው ሕግ የድካም ዋጋ ማግኘት የሚገባው ካልሆነ በቀር ወኪሉ ዋጋ የመጠየቅ መብት አይኖረውም፡፡
(፪) በተዋዋዮቹ መካከል ስምምነት የሌለ ሲሆንና በእንደዚህ ያለው አጋጣሚ ሁኔታ ለሞያ ሥራ ሊከፈል በሚገባው በታወቀው የሥራ ዋጋ ልክ ማስታወቂያ ታሪፍና በልማዳዊው ሕግ መሠረት ለወኪሉ የሚከፈለውን የድካም ዋጋ ዳኞች ይወስናሉ፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፳፩፡፡ ተቀዳሚ ተከፋይና ወጪ፡፡

(፩) ለተወካዩ ስለ ውክልናው ሥራ ማስኬጃና ማከናወኛ የሚሆን ተቀዳሚ ተከፋይ ወጪ ሊሰጠው ይገባል፡፡
(፪) እንዲሁም ተወካዩ ስለ ውክልና ሥራው መልካም አካሄድ ያደረገውን ወጪ ሁሉ ወካዩ ሊከፍለው ይገባል፡፡
(፫) የዚህም የተቀዳሚ ተከፋይና የወጪ ገንዘብ ወለድ ወጪ ከሆነበት ቀን ጀምሮ አንዳችም ማስጠንቀቂያ ሳያስፈልግ መታሰብ አለበት፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፳፪፡፡ ግዴታና ኪሣራ፡፡

(፩) ተወካዩ ለወካዩ ጥቅምና ለውክልናው ሥራ መልካም አካሄድ ሲል በወኪልነቱ ከገባው የውል ግዴታ ወካይ ነፃ ሊያወጣው ይገባል፡፡
(፪) እንዲሁም ተወካዩ በራሱ ጥፋት ያመጣው ካልሆነ በቀር የውክልና ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ ስለደረሰበት አደጋ ወካዩ ኪሣራ ሊከፍለው ይገባዋል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፳፫፡፡ ለመቃወም የሚቻልበት ነገር፡፡

(፩) ወካዩ የሥራውን ጒዳይ መልካም ውጤት አላገኘም በማለት ምክንያት፤ ለወኪሉ ሊከፍለው የሚገባውን ገንዘብ አልከፍልም ለማለት አይችልም፡፡
(፪) ተወካዩ ሊከፍለው ከሚገባው በተለይም የውክልና ሥራውን ሲፈጽም ስላደረገው ጥፋት ከሚከፍለው ገንዘብ ጋራ ወካዩ ለተወካዩ የሚከፍለውን ገንዘብ ለማቻቻል ይችላል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፳፬፡፡ የመያዝ መብት፡፡

ወካዩ ሊከፍለው የሚገባውን ገንዘብ ጨርሶ እስኪከፍለው ድረስ ተወካዩ በውክልናው ሥልጣን መሠረት እንዲሠራበትና እንዲገለገልበት ከተረከበው ዕቃ ውስጥ ሊከፈለው በሚገባው ገንዘብ መጠን በእጁ ለማቈየት ይችላል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፳፭፡፡ ስለ ብዙ ወካዮች፡፡

ብዙ ወካዮች ሆነው ለአንድ ዐይነት የጋራ ጒዳይ የወከሉት እንደሆነ፤ ወካዮቹ ሁሉ ስለ ውክልናው ውል መልካም አፈጻጸም ጒዳይ እየአንዳንዳቸው ለተወካዩ በሙሉ አላፊዎች ይሆናሉ፡፡

ክፍል ፬፡፡
ስለ ውክልና መቅረት፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፳፮፡፡ ውክልናውን ስለ መሻር፡፡

(፩) ወካዩ አስፈላጊ መስሎ በታየው ጊዜ የውክልናውን ሥልጣን ለመሻርና አስፈላጊ ሆኖም ቢገኝ በወካዩ የውክልና ሥልጣኑን የተቀበለበትን የውል ጽሑፍ በፈቀደ ጊዜ እንዲመልስለት ሊያስገድደው ይችላል፡፡
(፪) ይህንንም ተቃራኒ የሆነ የውል ቃል ፈራሽ ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፳፯፡፡ የውክልናው ሥልጣን መሻር የሚያስከትለው ውጤት፡፡

(፩) በውክልናው የተሰጠው የሥልጣን ጊዜ ከማለቁ በፊት ወካዩ ወኪሉን ከሥልጣኑ ሽሮት እንደሆነ፤ ወይም የሽረቱ ጒዳይ በተወካዩ ላይ ጉዳት የሚያደርስበት ሆኖ የተገኘ እንደሆነ፤ ወካዩ ተወካዩን ከሥልጣኑ በሻረው ጊዜ በሚደርስበት ጉዳት ሁሉ ኪሣራ መክፈል አለበት፡፡
(፪) የውሉ መጽኛ ዘመን የተወሰነው ለራሱ ልዩ ጥቅም ብቻ እንደሆነና ወይም ተወካዩን ለመሻር በቂ የሆነ ምክንያት ካለው ወካዩ ማናቸውም አላፊነት የለበትም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፳፰፡፡ ስለ ብዙ ወካዮች፡፡

(፩) ብዙ ወካዮች ሁነው ለጋራ ጒዳያቸው የወከሉትን ተወካይ አንዱ ብቻ ሊሽረው አይችልም፡፡
(፪) ስለ ተወካዩ መሻር በቂ የሆነ ትክክለኛ ምክንያት ከሌለ በቀር ወካዮቹ በመላው ሳይስማሙበት አንዱ ወካይ ብቻውን ተወካዩን ሊሽረው አይችልም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፳፱፡፡ ወኪሉ የውክልና ሥልጣኑኑ ስለ መተው፡፡

(፩) ተወካዩ የውክልናውን ሥራ የሚተው መሆኑን ለወካዩ አስታውቆ ውክልናውን ለመተው ይችላል፡፡
(፪) ይህ የተወካዩ ሥራ መተው በወካዩ ላይ ጉዳት የሚያደርስበት ከሆነ፤ ተወካዩ በወካዩ ላይ የደረሰውን ኪሣራ መክፈል አለበት፡፡ ሆኖም ተወካዩ የውክልናውን ሥራ መቀጠሉ በራሱ ላይ ከፍ ያለ ግምት ያለው ጉዳት የሚያደርስበት መሆኑ ከታወቀና ሥራውንም ለመቀጠል በፍጹም የማያስችለው ምክንያት መኖሩ ከተረጋገጠለት ማንኛውንም የጉዳት ኪሣራ ለመክፈል አይገደድም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፴፡፡ የተወካዩ መሞት ወይም ሥራ ያለ መቻል፡፡

(፩) ተወካዩ የሞተ እንደሆነ፤ በስፍራው ያለመኖሩ የተረጋገጠ እንደሆነ፤ ለመሥራት ችሎታ ያጣ እንደሆነ፤ ወይም ኪሣራ ደርሶበት በንግድ ኪሣራ ላይ መውደቁ የተረጋገጠ እንደሆነ ስለዚህ ጒዳይ ታስቦ ተቃራኒ የሚሆን ውል ተመልክቶ ካልተገኘ በበር የውክልናው ሥልጣን ወዲያውኑ ይቀራል፡፡
(፪) የተወካዩ ወራሾች ወይም ሕጋዊ እንደራሴ የውክልና ሥልጣን መኖሩን ካወቁ፤ በተወካዩ ላይ ይህን የመሰለ ነገር እንደ ደረሰበት ወዲያውኑ ለወካዩ ማስታወቅ አለባቸው፡፡
(፫) እንዲሁም ዋናው ተወካይ ይህን የመሰለ ነገር ከደረሰበት በኋላ ወካዩ ነገሩን ዐውቆ አስፈላጊውን ድርጅት እስኪያደርግ ድረስ ለወካዩ ጥቅም የሚሆነውን አስፈላጊ ነገር ሁሉ መፈጸም አለባቸው፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፴፩፡፡ ስለ ብዙ ተወካዮች፡፡

(፩) ብዙዎች ተወካዮች አንድ ዐይነት ጒዳይ ለማከናወን ተወክለው እንደሆነና ከመካከላቸው አንደኛው በአንድ ምክንያት ሥራውን ለመቀጠል የማያስችለው ነገር ገጥሞት የውክልናውን ሥራ ለማቋረጥ የተገደደ እንደሆነ፤ ስለ እንደዚህ ያለው ጒዳይ ተቃራኒ የሆነ ቃል በውላቸው ውስጥ ተመልክቶ ካልተገኘ በቀር የአንዱ ሥራ ማቆም የሁሉንም ተወካዮች ሥራ ለማቆም ይችላል፡፡
(፪) ሌሎቹ ተወካዮች የውክልና ሥልጣናቸው የቆመበትን ምክንያት እንዳወቁ ወዲያውኑ ለወካዩ ማስታወቅ አለባቸው፡፡ ወካዩም አስፈላጊውን ነገር እስኪያዘጋጅ ድረስ የሥራው ሁኔታና የጊዜው አጋጣሚ የሚያስገድደውን ዋና ዋና ጒዳይ እያከናወኑ መቈየት ይገባቸዋል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፴፪፡፡ የወካዩ መሞት ወይም ሥራ ያለ መቻል፡፡

(፩) ወካዩ የሞተ እንደሆነ፤ በስፍራው አለመኖሩ የተረጋገጠ እንደሆነ ለመሥራት ችሎታ ያጣ እንደሆነ ወይም በንግድ የመውደቅ ኪሣራ የደረሰበት እንደሆነ ለጒዳዩ ተቃራኒ የሚሆን ውል ካልተገኘ በቀር የውክልናው ሥልጣን ወዲያውኑ ይቀራል፡፡
(፪) በእንደዚህ ያለው አጋጣሚ ሁኔታ ተወካዩ ሥራውን ቢያቋርጥ በጒዳዩ ላይ አደጋ የሚደርስበት እንደሆነና በውክልናው ሥልጣንም መሠረት ሥራውን ጀምሮ እንደሆነ የዋናው ወካይ ወራሾች ወይም ሕጋዊ እንደራሴዎች አስፈላጊውን ጒዳይ እስኪያደርጉና ራሳቸውም ሊያስቡበት እስኪችሉ ድረስ ሥራውን መቀጠል አለበት፡፡

ክፍል ፭፡፡
ለሦስተኛ ወገኖች የውክልናው ሥልጣን የሚያስከትለው ውጤት፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፴፫፡፡ ወደ እንደራሴነት ደንብ ስለ መምራት፡፡

በወካዩ በተወካዩና የሦስተኛ ወገን በሆኑ በሌሎች ሰዎች መካከል የሚደረገው የግንኙነት ጒዳይ በዚህ አንቀጽ በምዕራፍ 1 በተደነገገው ደንብ ላይ በተመለከተው ሕግ መሠረት ይከናወናል፡፡

ምዕራፍ ፫፡፡
ስለ ኮሚሲዮን፡፡
ክፍል ፩፡፡
ስለ ግዥ ወይም ስለ ሽያጭ ኮሚሲዮን፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፴፬፡፡ ትርጓሜ፡፡

(፩) የግዥ ወይም የሽያጭ ኮሚሲዮን ሲባል ኮሚሲዮኔር ተብሎ የሚጠራው፤ ተወካይ ኮሚሲዮን ሰጭ ተብሎ ለሚጠራው ወካይ ተወካዩ በራሱ ስም ሆኖ ነገር ግን ለወካዩ ጥቅም የንግድ ዕቃዎችን ዋጋ ያላቸው ወረቀቶችን፤ ወይም ይህን የመሳሰሉትን ሌላ ነገሮች፤ ለመግዛት ወይም ለመሸጥ ግዴታ የሚገባበት ውክልና ማለት ነው፡፡
(፪) በዚህ ክፍል ውስጥ ከተመለከተው ግልጽ ድንጋጌና የማሻሻል ደንብ በመሠረቱ ልዩነት ከሚኖረው በቀር የውክልና ደንብ ለእንደዚህ ያለው ውል ጒዳይ ይጸናል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፴፭፡፡ የአጠባበቅ ጥንቃቄዎች፡፡

(፩) ኮሚሲዮኔሩ፤ በኮሚሲዮን ሰጪው ስም የተላኩለትን ዕቃዎች ለመጠበቅ የሚያስፈልገውን ጒዳይ ሁሉ መፈጸምና ዕቃዎችም የተበላሹ መስለው የታዩ እንደሆነ፤ ወይም ከተወሰነው ጊዜ በመዘግየት ደርሰው እንደሆነ በዕቃ ጫኚው ዘንድ እንደ ባለንብረት ሆኖ የኮሚሲዮን ሰጪውን መብት ይዞ መሥራት አለበት፡፡
(፪) ስለ እንደዚህ ያለውም ጒዳይ ዕቃዎቹ እንዳልደረሱ ያህል በሚያስቈጥር አጋጣሚ ሁኔታ፤ ኮሚሲዮኔሩ ለኮሚሲዮን ሰጪው ወዲያውኑ አሳቡን ማቅረብ ይገባዋል፡፡
(፫) አንድ ሰው የኮሚሲዩኑን አደራ ያልተቀበለም ቢሆን እንኳ የኮሚሲዮኑ ሥራ ጒዳይ የዚህን ሰው የሞያና የግል ሥራውን የሚመለከት ከሆነ ይህን የመሰሉ ግዴታዎችን መፈጸም ይገባዋል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፴፮፡፡ የንግድ ዕቃዎች መሸጥ፡፡

በኮሚሲዮን የተላኩትን የንግድ ዕቃዎች በቶሎ ይበላሻሉ ተብሎ የሚያሠጋ ነገር የተገኘ እንደሆነ፤ ኮሚሲዮኔሩ የንግድ ዕቃዎች በሚገኙበት አገር ባሉት ባለሥልጣኖች ፊት እንዲሸጣቸው መብት ይኖረዋል፤ እንዲያውም የኮሚሲዮን ሰጪው ጥቅም የሚያስገድደው ሆኖ ሲገኝ ይህንኑ የመፈጸም ግዴታ አለበት፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፴፯፡፡ አስቀድሞ ዋጋ ስለ መክፈል፡፡

ሻጭ ዕቃውን ከማስረከቡ በፊት ኮሚሲዮን ሰጪው ሳይፈቅድለት ኮሚሲዮኔሩ ላልተረከበው ዕቃ አስቀድሞ ዋጋ የከፈለ እንደሆነ ለሚመጣው ኪሣራና ጥፋት አላፊ የሚሆነው ራሱ ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፴፰፡፡ በዱቤ የመሸጥ ጒዳይ፡፡

(፩) የሽያጩ ጒዳይ በሚፈጸምበት ስፍራ ያለው የንግድ ልማድ የዚሁ ዐይነት እንደሆነና ኮሚሲዮን ሰጪውም ተቃዋሚ የሆነ ትእዛዝ ካልሰጠው በቀር ኮሚሲዮኔሩ ለዕቃ ገዢው ዕቃውን በዱቤ ሸጦ የዋጋውን መክፈያ ጊዜ ሊወስንለት ይችላል፡፡
(፪) ለዕቃ ገዢው የመክፈያ ቀን የፈቀደለት ኮሚሲዮኔር ገዢው ማን መሆኑንና ለዋጋ መክፈያ የፈቀደለት ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ለኮሚሲዮን ሰጪው ማስታወቅ አለበት፡፡
(፫) ኮሚሲዮኔሩ በራሱ ጥፋት ይህን ጒዳይ ለኮሚሲዮን ሰጪው ሳያስታውቅ የቀረ እንደሆነ፤ የዕቃው ዋጋ እጅ በእጅ እንደተከፈለ ከመቈጠሩም ይልቅ ከዚህ ቀጥሎ ባለው ቊጥር ውስጥ የተመለከተው ድንጋጌ የጸና ይሆናል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፴፱፡፡ ያለ ፈቃድ የተደረገ ዱቤ፡፡

(፩) ኮሚሲዮኔሩ ኮሚሲዮን ሰጪው የሰጠውን ትእዛዝ በመቃምና የአገሩንም ልማድ ተቃራኒ በሆነ ዐይነት የንግድ ዕቃውን በዱቤ ሸጦ ለዋጋው መክፈያ ጊዜ ሰጥቶ እንደሆነ፤ ባለንብረቱ የዕቃውን ዋጋ ወዲያውኑ እንዲከፍለው ኮሚሲዮኔሩን ለማስገደድ ይችላል፡፡
(፪) በእንደዚህ ያለው ጊዜ ኮሚሲዮኔሩ ለዕቃው ዋጋ አከፋፈል ጊዜ በመስጠት ያገኘውን ትርፍ ለግል ጥቅሙ ለማስቀረት ይችላል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፵፡፡ ኮሚሲዮኔሩ መስጠት ስለሚገባው ዋቢነት፡፡

(፩) ኮሚሲዮኔሩ፤ በኮሚሲዮን ሥራው የተሰጠው ሥልጣን ራሱ በሚያምነው ነገር ሁሉ እንዲሠራ እንደሆነ፤ በዚሁ ሥራው ከሌሎች ጋራ ለተዋዋለው ግዴታ መልካም አፈጻጸምና ስለ ዕቃውም ዋጋ አከፋፈል ጒዳይ ሁሉ ለኮሚሲዮን ሰጪው አላፊ ነው፡፡
(፪) ዋጋ ያላቸው ወረቀቶችን የመግዛትና የመሸጥ ኮሚሲዮን ሥልጣን የተሰጠው ኮሚሲዮኔር፤ ተቃራኒ የሆነ ስምምነት ከሌለ በቀር፤ በራሱ እምነት ሊሠራ የሚችል ኮሚሲዮኔር ተብሎ የሚጠራ ነው፡፡
(፫) የንግድ ዕቃዎችን ለመግዛት ወይም ለመሸጥ ሥልጣን የተሰጠው ኮሚሲዮኔር፤ የኮሚሲዮኑ ውል በተደረገበት አገር ያለው የንግድ ልማዳዊ ሕግ የዚሁ ዐይነት እንደሆነ ወይም ስለ ንግድ ለተዋዋላቸው ሰዎች አላፊ ዋስ ሆኗቸው እንደሆነ፤ በራሱ እምነት ሥልጣን የሚሠራ ኮሚሲዮኔር ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፵፩፡፡ በራሱ እምነት ስለሚሠራ ኮሚሲዮኔር፡፡

(፩) በራሱ እምነት የሚሠራ ኮሚሲዮኔር በኮሚሲዮኑ ጒዳይ ለሚዋዋለው ሰው ሙሉ አላፊ የሆነ ዋስ ነው፡፡
(፪) የውሉን ስምምነት ያለመፈጸም ጒዳይ ያስከተለው በኮሚሲዮን ሰጪው ጒድለት በተነሣ ምክንያት ካልሆነ በቀር ኮሚሲዮኔሩ ላደረገው ውል አፈጻጸምና ለማናቸውም አጋጣሚ ነገር ሁሉ ለኮሚሲዮን ሰጪው አላፊ ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፵፪፡፡ የአደጋ መጠባበቂያ ውል (ኢንሹራንስ)፡፡

ኮሚሲዮን ሰጪው ትእዛዝ ካልሰጠው በቀር ኮሚሲዮኔሩ የአደጋ መጠባበቂያ ውል (ኢንሹራንስ) እንዲያደርግ አይገደድም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፵፫፡፡ ለኮሚሲዮኔሩ የሚከፈል የድካም ዋጋ፡፡

(፩) ለኮሚሲዮኔሩ ሊከፈለው የሚገባው የድካም ዋጋ በውሉ ላይ ያልተወሰነ እንደሆነ፤ ኮሚሲዮኔሩ የኮሚሲዮኑን ውል በተዋዋለበት አገር ባለው ልማድ መሠረት እንዲከፈለው ይደረጋል፡፡
(፪) ልማድ የሌለ እንደሆነ፤ ኮሚሲዮኔሩ የፈጸመውን የሥራ ፍሬ መሠረት አድርጎ በመያዝና ሥራውንም ለማከናወን ያደገውን ወጪና የደረሰበትን ኪሣራና ድካም በመገመት ዳኞች በትክክለኛ ፍትሐዊ መንገድ ሊወስኑ ይችላሉ፡፡
(፫) ኮሚሲዮኔሩ በራሱ እምነት የሚሠራ እንደሆነ፤ በኮሚሲዮኑ ውል መሠረት የተወሰነለትን፤ በልማድ ወይም በትክክለኛ ሥርዐት መሠረት ልዩ የሆነ የድካም ዋጋ የማግኘት መብት አለው፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፵፬፡፡ የድካሙ ዋጋ የሚከፈልበት ጊዜ፡፡

(፩) ኮሚሲዮኔሩ እንዲፈጽም ለታዘዘው ሥራ የድካም ዋጋ የማግኘት መብት የሚኖረው የታዘዘውን ጒዳይ እግቡ በማድረስ፤ በሚገባ በፈጸመ ጊዜ ወይም ይህ ሥራ ሳይፈጸም የቀረው በኮሚሲዮን ሰጪው ጒድለት የተነሣ የሆነ እንደሆነ አፈጻጸሙ እግቡ ሊደርስ ሲችል በዚህ ምክንያት ተሰናክሎ በቀረ ጊዜ ነው፡፡
(፪) ሥራውን በሚያካሂድበት ስፍራ ላይ ተቃራኒ የሚሆን ልማድ ካልኖረ በቀር እንዲፈጽም የተሰጠው የሥራ ጒዳይ እግቡ ደርሶ ሳይፈጸም የቀረው በሌላ ምክንያት ከሆነ የድካም ዋጋ የመጠየቅ መብት አይኖረውም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፵፭፡፡ የድካም ዋጋ የማግኘት መብት ስለ ማጣት፡፡

(፩) ኮሚሲዮኔሩ በኮሚሲዮን ሰጪው ፊት እምነቱን በማጒደል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ፤ ማንኛውንም የድካም ዋጋ ለመጠየቅ መብት ይቀርበታል፡፡
(፪) እንዲሁም የገዛውን ዕቃ በእርግጥ ከገዛበት ዋጋ አብልጦ የገዛው ያስመሰለ እንደሆነ ወይም የሚሸጠውን ከሸጠበት ከእውነተኛው ዋጋ በታች አሳንሶ የሸጠ ያስመሰለ እንደሆነ የድካም ዋጋ መብት የማጣቱ ጒዳይ በዚሁ ዐይነት ይፈጸማል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፵፮፡፡ ልዩ ልዩ ወጪና ተቀዳሚ ተከፋይ፡፡

(፩) ኮሚሲዮኔሩ፤ ኮሚሲዮን ሰጪው ያዘዘውን የሥራ ጒዳይ ለማከናወን በቅን ልቡና ያደረገውን ወጪና በተቀዳሚነት የከፈለውን ሒሳብ ሁሉ ከነወለዱ እንዲከፍለው የመጠየቅ መብት አለው፡፡
(፪) ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በቀር ወጪ ያደረገበት ጒዳይ ፍጻሜ ያላገኘም ቢሆን እንኳ ሥራውን ለማከናወኛ የከፈለው ወጪ ሊመለስለት ይገባል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፵፯፡፡ የመያዝ መብት፡፡

(፩) ኮሚሲዮን ሰጪው ለኮሚሲዮኔሩ ሊከፍል የሚገባውን ገንዘብ እስኪከፍለው ድረስ ኮሚሲዮኔሩ አንድ ነገር በመያዣ ስም የማስቀረት መብት አለው፡፡
(፪) ይህንንም መብት ለኮሚሲዮን ሰጪው ሊገዛ ወይም ሊሸጥ ከመደባቸው ዕቃዎች ውስጥ በማናቸውም ዐይነት ዕቃ ላይ ሊፈጽም ይችላል፡፡
(፫) እንዲሁም በኮሚሲዮን ሰጪው ስም ከተቀበለው ከአንድ ዕቃ ዋጋ ላይ ይዞ ለማቈየት ይችላል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፵፰፡፡ የኮሚሲዮኔሩ የመግዛት መብት፡፡

(፩) እንዲገዛ ወይም እንዲሸጥ ትእዛዝ የተቀበለበት ዕቃ የንግድ ታሪፍ ተወስኖለት ወይም በገበያ ተወስኖ የታወቀ ዋጋ ያለው ሲሆን ኮሚሲዮኔሩ እንደ ሌላ ሰው ሆኖ ከራሱ ጋራ የውል ስምምነት ለመፈጸም ይችላል፡፡
(፪) በእንደዚህ ያለው ጊዜ፤ በስምምነቱ መሠረት ወይም እንደ ልማድ ሊከፈለው የሚገባውን መብት አይከለክልበትም፡፡
(፫) ከራሱ ጋራ የሚስማማበት ዋጋ፤ ኮሚሲዮን ሰጪው ከወሰነው ዋጋ በንግድ ታሪፍ ወይም በዕለት የገበያ ዋጋ ከተወሰነው በታች ሊሆን አይገባውም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፵፱፡፡ የይመስላል ግምት፡፡

ኮሚሲዮኔሩ ራሱ ገዥ ወይም ሻጭ ሆኖ በግዥው ወይም በሽያጩ ጒዳይ ከማን ጋራ እንደተዋዋለ ለኮሚሲዮን ሰጪው ሳይገልጽለት በውክልናው ሥልጣን የተሰጠው አደራ የተፈጸመ መሆኑን ብቻ ለኮሚሲዮን ሰጪው ያስታወቀ እንደሆነ የገዥነቱን ወይም የሻጭነቱን አላፊነት እሱ ራሱ እንደወሰደ ይቈጠራል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፶፡፡ ስለ ኮሚሲዮን መቅረት፡፡

ኮሚሲዮን ሰጪው፤ ወይም ኮሚሲዮኔሩ ቢሞቱ የመሥራት ችሎታ ቢያጡ፤ ወይም በአገር አለመኖራቸው ቢረጋገጥም እንኳ፤ የኮሚሲዮን ሰጪው ወይም የኮሚሲዮኔሩ ወራሾች ወይም እንደራሴዎቻቸው የነዚሁ ምትክ ሆነው የንግድ ሥራውን በማካሄድ ከቀጠሉ የኮሚሲዮኑ ሥራ እንደቀረ አይቈጠርም፡፡

ክፍል ፪፡፡
ስለ ማመላለሻ ኮሚሲዮን፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፶፩፡፡ የማመላለሻ ኮሚሲዮን፡፡

(፩) የማመላለሻ ኮሚሲዮን ሲባል ላኪ ኮሚሲዮኔር ወይም የትራንስፖር መልክተኛ ተብሎ የሚጠራ ተወካይ በራሱ ስም ሆኖ ነገር ግን ኮሚሲዮን ሰጪ ተብሎ ለተጠራው ወካይ ጥቅም ሲል የንግድ ዕቃዎች የማመላለሻ ስምምነት ከትራንስፖር ኮሚሲዮኔሮች ጋራ የመዋዋል ውክልና ማለት ነው፡፡
(፪) የግዥው ወይም የሽያጭ ኮሚሲዮን ደንቦች ለእንደዚህ ያለው ውልም የሚጸኑ ናቸው፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፶፪፡፡ የአደጋ መጠባበቂያ ውልና ኢንሹራንስ የዚሁ ለውጥ መብት፡፡

(፩) ዕቃ ላኪው ኮሚሲዮኔር ተቃራኒ የሆነ ስምምነት ከሌለ በቀር ለሚልካቸው የንግድ ዕቃዎች መጠባበቂያ ኢንሹራንስ እንዲያደርግ አይገደድም፡፡
(፪) የማመላለሱን (የትራንስፖርን) ጒዳይ እርሱ ራሱ ሊጠባበቀው ይችላል፡፡
(፫) በእንደዚህ ያለው ጊዜ ዕቃ ጫኙ የሚገባውን መብት ያገኛል፡፡ የሚደርስበትንም ግዴታ ይፈጽማል፡፡

ምዕራፍ ፬፡፡
ዳኞች ስለሚሰጡት ውክልና፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፶፫፡፡ መሠረቱ፡፡

አንድ የተወሰነ ሥራን ወይም የተመደቡ ሥራዎችን በሌላው ስም ሆኖ እንዲያከናውን ዳኞች ጠባቂ ባላደራ ለተባለው ለአንድ ሰው ውክልና ለመስጠት ይችላሉ፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፶፬፡፡ እንዲሾም ስለ መጠየቅ፡፡

(፩) እንደራሴ እንዲደረግበት ለሚያስፈልገው ሰው ባል ወይም ሚስት የሆኑ ወይም ዘመዶች የሆኑ ወኪል እንዲሾሙለት ለዳኞች ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ፡፡
(፪) ሌላ ሰው ግን ይህን ጥያቄ ማቅረብ አይችልም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፶፭፡፡ የዳኞች ውሳኔ፡፡

(፩) እንደራሴ ይደረግለት የተባለው ሰው በመራቅ ወይም በሕመም ወይም በሌላ ምክንያት ወኪል ከማጣት ሁኔታ ውጭ ካልሆነ በቀር ዳኞች ወኪል እንዲሾሙለት የቀረበላቸውን ጥያቄ አይቀበሉትም፡፡
(፪) እነርሱም የሚሾሙት ጠባቂ ባላደራ አስቸኳይ የሆኑትን ጒዳዮች ብቻ እንዲያከናውን ይፈቅዱለታል፡፡
(፫) እንደራሴ የተደረገለት ሰው መብቶች በሙሉ የሚጠበቁበትንና እንደራሴ የተደረገለት ሰው ንብረት ጠባቂ ባላደራ በጥበቃ ሥራው ምክንያት በአላፊነት የሚፈረድበት ፍርድ እንዲፈጸም አስፈላጊ የሆኑትን ትእዛዞች ሁሉ ያደርጋሉ፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፶፮፡፡ ውጤቶች፡፡

(፩) ዳኞች የመረጡት ጠባቂ ባለአደራ እንደራሴው እንዲሆን ለተሾመለትሰው የርሱ ወኪል ሆኖ መሾሙን እንደተቻለ ወዲያው ያስታውቀዋል፡፡
(፪) ወኪልነቱን የሰጡት ዳኞች በሆኑ ጊዜ እንደራሴ የተደረገለት ሰውና የጠባቂው (ባለአደራው) የየራሳቸው መብቶችና ግዴታዎች በዚህ አንቀጽ በሁለተኛው ምዕራፍ ድንጋጌዎች መሠረት ይወሰናሉ፡፡

ምዕራፍ ፭፡፡
ስለ ሥራ አመራር፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፶፯፡፡ የአፈጻጸሙ ሥልጣን፡፡

አንድ ሰው የነገሩን ሁኔታ እየተገነዘበ ይህን እንዲፈጽም ሳይገደድ የወኪልነትም ሥልጣን ሳይሰጠው የሌላውን ሰው ጒዳይ በመምራት ሥራ ውስጥ ገብቶ ጒዳዩን ያካሄደ እንደሆነ የሥራ ጒዳይ አመራር እንዳለ ይቈጠራል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፶፰፡፡ ባለቤቱ ያልፈቀደውን ሥራ ስለ መምራት፡፡

(፩) አንድ ሰው የባለቤቱን ፈቃድ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የሥራውን ጒዳይ መምራት ያከናወነ እንደሆነ ያላገባብ ስለመበልጸግ የተወሰነው ድንጋጌ ተፈጻሚ ይሆናል፤ እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ከውል ውጭ የሚመጣ አላፊነትን ስለሚመለከተው ጒዳይ የተወሰነውን ድንጋጌ መፈጸም ይቻላል፡፡
(፪) ባለንብረቱ የሥራ አስኪያጅን ተግባር ያጸደቀለት እንደሆነ ግን በዚሁ ምዕራፍ ላይ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፶፱፡፡ ለባለንብረቱ ጥቅም በማይሰጥ ሁኔታ የተፈጸሙ የሥራ ጒዳይ አመራሮች፡፡

(፩) የሥራው አመራር ጒዳይ የተወሰነው ለባለንብረቱ ጥቅም ሳይሆን ሥራ መሪው ለራሱ ጥቅም ሲል በሌላው ሰው ጒዳይ ውስጥ ገብቶሥራውን ለመምራት ወጥኖ እንደሆነ፤ ያለአገባብ ስለ መበልጸግ ጒዳይ የተወሰነው ድንጋጌ ሊጸና ይችላል፡፡
(፪) እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ የተገመተ እንደሆነ ከውል ውጭ የሚመጣን አላፊነት ስለሚመለከተው ጒዳይ የተወሰነው ድንጋጌ የሚጸና ይሆናል፡፡
(፫) ይህ ሥራ መሪ ያካሄደው የሌላው ሰው ጒዳይ ከራሱ ሥራ ጋራ የተያያዘ ግንኙነት ያለው ሆኖ አንዱ ሥራ ካንደኛው ተለይቶ ብቻውን ሊካሄድ የማይችል በመሆኑ ምክንያት የሌላውን ሰው ሥራ ከራሱ ሥራ ጋራ ደርቦ መርቶት እንደሆነም ምን ጊዜም ቢሆን በዚህ ምዕራፍ ላይ የተመለከቱት ድንጋጌዎች መጽናታቸው አይቀርም፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፷፡፡ የሥራ መሪው ግዴታዎች፡፡

(፩) የሌላውን ሰው የሥራ ጒዳይ ለመምራት የወጠነው የሥራ መሪ፤ የወጠነውን የሥራ ጒዳይ በተቻለ መጠን ለባለንብረቱ የስታወቅ ግዴታ አለበት፡፡
(፪) የጉዳዩ ባለቤት የሥራውን ጒዳይ ራሱ ለማካሄድ እስኪችል ድረስ፤ ሥራ መሪው የወጠነውን የሌላውን ሰው ሥራ መቀጠል አለበት፡፡
(፫) የሥራውን ሁኔታ መግለጫ ስለ መስጠት ጒዳይ አንድ ተወካይ ሊፈጽመው የሚገባውን ጒዳይ የመፈጸም ግዴታ አለበት፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፷፩፡፡ ትጋትና አላፊነት፡፡

(፩) ሥራ መሪው ለማከናወን የወጠነውን ሥራ፤ እንደ መልካም የቤተ ዘመድ አባት ለቤተ ዘመዱ እንደሚያስብና እንደሚጠነቀቅ ያህል በጥንቃቄና በትጋት ማከናወን ይገባዋል፡፡
(፪) ምን ጊዜም ቢሆን፤ ዳኞች ከሥራ መሪው ጥፋት የተነሣ ለሚደርሰው ካሣና ኪሣራ አከፋፈል ጒዳይ ውሳኔ ለመስጠት ሲያስቡ ሥራ መሪው የሌላውን ሰው ሥራ ለማካሄድ ያነሳሱትን አጋጣሚ ምክንያቶች ገምቶ መሠረት በማድረግ የኪሣራውን ውሳኔ ከዚሁ ጋራ ማመዛዘን ይችላሉ፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፷፪፡፡ የመሪው ችሎታ ማጣት፡፡

ሥራ መሪው ይህን ሥራ ለመምራት በውል ግዴታ ለመግባት የማይችል ሆኖ ሲገኝ በመራው ሥራ አላፊ የሚሆነው በጥቅሙ በከበረበት መጠን ተመዛዛኝ ሊሆን በሚቻል ግምት ወይም በክፉ ልቡና በሥራው ካገኘው ትርፍ ባስቀረው ጥቅም ልክ ነው፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፷፫፡፡ ቅን ልቡና፡፡

(፩) የሥራ መሪው፤ ከባለንብረቱ ጋራ በሚያደርገው የሥራ ግንኙነት ጒዳይ ሁሉ የቅን ልቡናን ደንብ መከተል አለበት፡፡
(፪) እንደዚህ ላለው ነገር የውክልናን ሥልጣን ስለሚመለከቱት ጒዳዮች የተሰጠው ድንጋጌ ይጸናል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፷፬፡፡ የባለንብረቱ ግዴታዎች፡፡

(፩) የሥራው አመራር እንዲወጠንና በሥራ መሪው እንዲካሄድ የባለቤቱ ጥቅም የሚያስገድድ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ፤ ሥራ መሪው በስሙ የወጠነውን የሥራ ተግባር ባለንብረቱ ሊያጸድቅለት ይገባዋል፡፡
(፪) ሥራ መሪውም ይህን ሥራ ስለ መራለት ሥራውን ለማካሄድ ያወጣውን ወጪ መክፈል ለድካሙም የሚገባውን ዋጋ መስጠትና ለሥራውም መምራት ጒዳይ ያወጣውን ወጪ መተካት፤ በራሱ ጥፋት ሳይሆን በሥራው ጒዳይ ለደረሰበት አደጋ ኪሣራ መክፈል አለበት፡፡
(፫) ለሥራው ማካሄጃ በሥራ አስኪያጁ ሒሳብ ወጪ የሆነውን ገንዘብ አንዳችም ማስጠንቀቂያ አስፈላጊ ሳይሆን ወጪ ከሆነበት ቀን አንሥቶ ወለድ ይታሰብለታል፡፡

ቊ ፪ሺ፪፻፷፭፡፡ የሥራውን ማጽደቅ ጒዳይ የሚያስከትለው ውጤት፡፡

በሕጉ መሠረት ወይም በሥራው የጒዳዩ ባለቤት የሥራውን አመራር ተግባር ለሥራ መሪው የሚያጸድቅለት በሆነ ጊዜ ስለ ውክልና ጒዳይ የወጣው ደንብ ይጸናበታል፡፡